Friday, May 11, 2012

ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ሊያሳካቸው የሚፈልጋቸው ተጨማሪ ግቦች ምን ምን ናቸው?

click here to read in PDF
በክፍል አንዱ ጽሁፋችን ማኅበረ ቅዱሳን  በቅዱስ ሲኖዱሱ ስብሰባ ሊያሳካቸው ከሚፈልጋቸው ጉዳዮች አንዱ አቡነ ፋኑኤልንን ከአሜሪካ አህጉረ ስብከት ማስነሳት መሆኑንን በበቂ ማስረጃ አስደግፈን አቅርበናል።
አሁን ደግሞ ቀጣይ አጀንዳዎቹን እናቀርባለን።
1.    አቡነ አብርሃምን ወደ ሐዋሳ ሀገረ ስብከት ማዛወር
ብጹዕነታቸው አቡነ አብርሃም የማኅበረ ቅዱሳን ታዛዥ እንዲሆኑ የሚያደርጓቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ገልጠን ነበር። አቡነ አብርሃም በሙሉ ልባቸው ራሳቸውን ለማኅበረ ቅዱሳን ሀሳብ ስላስገዙና ማኅበሩ የሚለውን ሀሳብ መነሻና መድረሻ ሳይመረምሩ ለማስፈጸም ስለሚተጉ ለማኅበረ ቅዱሳን ከፍተኛ ችግር በሆነውና ከ5000 በላይ ምዕመን ተሰዶ በሚገኝበት በሐዋሳ ከተማ ቢመደቡ ችግሩን በፈለጉት መንገድ ልፈታ እችላለሁ ብሎ በማሰቡ፣ እንደልቡ ሊሆኑለት ያልቻሉትን አቡነ ገብርኤልን ለማስነሳት ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደነበር ይታወቃል። አሁን ደግሞ ማን ይመደብ ብሎ ማንያዘዋል የያዘው አስለፍልፍ ገፋፍቶት በታክሲ ውስጥ እንደነገረን በጓዳ ሲኖዶስ ተመክሮበት ያበቃለትን የአቡነ አብርሃምን ሹመት ለማስፈጸም ቆርጦ ተነስቷል።

2.   በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሃላፊ ላይ የተወሰደውን እርምጃ ማስቀልበስ
ከዚህ በፊት በጓዳው ሲኖዶስ በማቅ ጽ/ቤትና በአቡነ አብርሃም ቤት ከተመከረባቸው ጉዳዮች ውጭ ሆኖ ለማቅ አመራሮች ዱብ ዕዳና ከፍተኛ ስጋት ከሆነባቸው ነገሮች አንዱ የእበላ ባዩ አባ ኅሩይ ከስልጣን መነሳት ነው። ማኅበሩ አባ ኅሩይ በተነሱበት ዕለት የሳቸውን መሻርና የመምህር ዕንቆ ባሕርይን ሹመት ተቃውሞ መግለጫ አውጥቷል። እንዲያውም የመምህሩ ሹመት “ሕገ ወጥ ነው” ሲል ሕገ ወጥነቱን የሚያሳይ ሕግ ሳይጠቅስ መግለጫ አውጥቷል። መምህር ዕንቆ ባሕርይ ካለፉት 10 አመታት ጀምሮ በምክትል ኃለፊነት በሰሩበት ቦታ ላይ መሾማቸው ተገቢ እንጂ ሕገ ወጥ የሚያደርገው ምን እንደሆነ ባይገባንም ማኅበሩ የፈጠራቸውን ክፍተቶች ለመሙላትና ማኅበሩን ወደ ሕጋዊ አሰራር ለመመለስ ያላቸውን ቁርጠኝነት ስለሚያውቅ በጥፍሩም በጥርሱም ቧጦ ይህን ሹመት ለማሻር የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ የተባሉትንና የማኅበሩ ጉዳይ ሲነሳ ብቻ መኖራቸው የሚታወቀውና የማኅበሩ አባል መሆናቸውን በኩራት የሚናገሩትን አቡነ ቀሌምንጦስን ተቃመሙልኝ ብሎ እንዲቃመሙ ወሳኝ ያለውን ተልእኮ ሰጥቷቸዋል።

በተጨማሪም ማን እንደወከላቸውና እንዴት እንደተመረጡ የማይታወቁትና ሙሉ በሙሉ የማቅ አባለት የሆኑት ህገ ወጦቹን የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤት ኅብረት ተብዬዎችም የመምህር ዕንቆ ባሕርይን ሹመት መቃወማቸውን አንድ አድርገን አስነብቦናል። አንድ አድርገን ዜናውን ሲነግረን የስብስቡን ሕገ ወጥነት በማያሻማ ቃል በማስቀመጥ ነው።
“የሰንበት /ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሃላፊነት ሹመት ህገወጥ የአዲስ አበባ ሰንበት /ቤቶች ህብረትም የተቃወመው ሲሆን…” በማለት የህብረቱን ሕገ ወጥነት አንድ አድርገን ስላገጋገጠልን እያመሰገንን ህገ ወጦች በህጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ እስካልጀመሩና በስነ ሥርዓት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካዮቻቸውን ልከው ሕጋዊ የሆነ ምርጫ እስካልተካሔደ ድረስ ሕገ ወጦች በህብረት ስም ተሰባስበው ጩኸት ቢያሰሙ ተቀባይነት ሊኖራቸው አይችልም አንላለን።

እንግዲህ ማቅ ድንገት የወደቀበትንና እንደ እግር እሳት እየለበለበው የሚገኘው አባ ኅሩይ ተነስተው መምህር ዕንቆ ባህርይ መሾማቸውን ለማስቀልበስ በሁለም አቅጣጫ እየተሯሯጠ ይገኛል። በእውነቱ ማቅ እዚህ ላይ እያደረገ ያለው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ሳይሆን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው የሚመስለው። ቤተ ክህነቱ የበላይ አካል እንደመሆኑ ይሰራልኛል ብቁ ነው ያለው መሾም አልሰራልኝ ብቁ አይደለም ያለውን ማውረድ ለእርሱ የሚተው እንጂ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ፈቃድ ላይ የሚመሰረት መሆን የለበትም። ማህበሩ በትክክል እስከ ሄደ ድረስ ማንም ይሹም ማን ምን አስፈራው? ያው ብዙ ጣጣ ስላለበት ነውጂ።

3.   ባለፈው ሲኖዶስ ይወገዝልኝ ብሎ ያልተሳኩለትትንን ወገኖች ሁሉ ማስወገዝ
በጥቅምቱ ሲኖዶስ በሁለት ሰነድ በአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ህብረት ስምና በራሱ ስም ያለምንም አይነት ሕጋዊ ማህተም ተጠያቂነትን እንዳያስከትልበት በሁለት ሰነድ ባስገባቸው የክስ ፋይሎቹ ከሕያዋኑም ከሙታኑም፣ ከጨዋውም ከሊቁም፣ ከመንፈሳዊውም ከፖለቲከኛውም ከሁሉም አይቅርብኝ በማለትና የጻፈ ያስጻፈ ያነበበ የተረጎመ በእጁ የተገኘ አስተያየት የሰጠ በሚል አስቂኝ ምክንያቶች ክስ ማቅረቡና ማቅ በሙት ላይ እንኳን ቂም እንደሚይዝ ያረገገጠበትን የጅምላ ይወገዙልኝ ጥያቄ ተፈጻሚ ማድረጉ ሌላው ማህበሩ የሚፈልገው አጀንዳ ነው።
በሀገራችን ሙት ወቃሽ ድንጋይ ነካሽ የሚል የቆየና እውነታን ያገናዘበ ምሳሌ ቢኖርም ሙትንም ወቅሼ ድንጋይም ነክሼ ፍላጎቴን አሳካለሁ ብሎ ተነስቶ እነ ብላቴን ጌታ ኅሩይን፣ ነጋድራስ ገብረህይወትን፣ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌን፣ አለቃ ተክለ ጽዮንን፣ አለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስንና ሌሎችንም ለሀገርም ለቤተክርስቲያንም ቅርስ የሆኑ አባቶችን ይወገዙልኝ ብሎ መጠየቁ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው። ከፖለቲኞችም ውስጥ እነ ፕሮፌሰር መስፍንን አስተያየት ስለሰጡ ይወገዙልን ማለት እነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ታሪክ ተቀብሮ እንዳይቀር በማሰብ መጽሀፍ ስለተረጎሙ እንዲወገዙ መጠየቁ ማኅበሩ አዲስ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን በራሱ ጊዜ መቅረጹንና ሰውን መናፍቅ ለማለት ቤተክርስቲያን የምታልፍበትን መንገድ ጨርሶ የማያውቅ ጎጋ እንኳ ሊያነሳቸው የማይችላቸውን ነጥቦች በማንሳት የጅምላ ውግዘት ጥያቄ ማቅረቡ ማኅበሩ የደረሰበትንን የዝቅጠት ደረጃና የቤተክርስቲያንን ዕውቀትን በፖለቲካው አይን ለመተርጎም ያለውን ፍላጎት ፍንትው አድርጎ ያሳየ ተግባር ሆኖ አልፏል። ለጥያቄው በሚሰጠው ምላሽ ውስጥ የተሰየመው አካል እንዲህ በማሰቡ ማኅበሩን ሊጠየቅና ተግሳጽ ሊሰጠው እንደሚገባ እናምናለን።
እነዚህ በጥቅምቱ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ እንቅልፍ አጥቶ ደጋፊ ጳጳሳቱን ኣነሳሳ፤ ካላወገዝን አንለያይም አሰኝቶዋቸው የነበረው ጉዳይ በእግዚአብሔር ቸርነት ከከሸፈ በኋላ አሁን ደግሞ ሰፊ ዝግጅት በማድረግ ለማስወገዝ ታጥቆ ተነስቷል።
4.   የስብከተ ወንጌል መምሪያውን ስልጣን መልሶ መረከብ
የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊነት ሥልጣን ከእጃቸው ስለወጣና አስቦ አሰላስሎ በሚሰራ ሊቅ እጅ ስለወደቀ ኣሻንጉሊቶች አስቀምጠን የምንመራውን ቦታ እንዴት እናጣለን? በሚል ስሜት አጀንዳውን የሚያስፈጽሙበት ጣራና ግድግዳ ባይታያቸውም፣ ከተሳካ እንሞክር በሚል ስሜት ለመውተርተር እየሞከሩ ይገኛሉ። ይልቁንም «አጉራ ዘለል» ሰባክያን በማለት ቤተክርስቲያን በኮሌጆችዋ አስተምራ እንዲያገለግሉ ያሰማራቻቸውን አገልጋዮች «አጉራ ዘለል ናቸው» ብለው በመፈረጅ ለሌላው ያወጡት ስም፣ የት እንደተማሩ የማይታወቁትንና የማቅ አባለት የሆኑትን ገና ጌታችንና መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱን ያልሰሙትን የተረትና የፍረጃ ጉዳዮች «ሊቃውንት» «አገልጋዮቻቸውን» መፈናፈኛ ስላሳጣና በአጉራ ዘለልነት ስላስፈረጃቸው፣ የማቅ አባል መሆን አጉራ ዘለል ላለመሆን ልዩ መታወቂያ ነው የሚሉትን የማቅ አመራሮች አበሳጭቶ ቦታውን እንደገና በአሻንጉሊቶቻቸው ለመተካት መሞከራቸው የሚጠበቅ ነው።

5.   የዋልድባና የዝቋላን ጉዳይ
ዋልድባንና ዝቋላን በተመለከተ ማቅ የሚፈልገው በሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ አባቶች በሁለቱም ጉዳዮች መንግስትን እንዲያወግዙና በዋልድባ ላይም የሚጠበቀውን የማቅ ዘገባ አጠይሞ ለማቅረብ ነው። ማቅ በዋልድባ ጉዳይ ሁለት ዘገባዎችን ያዘጋጀ ሲሆን የመጀመሪያው ዘገባ ገና ለጥናት ወደ ዋልድባ ከመሄዳቸው በፊት ያዘጋጁት ነው። እርሱም ዋልድባ ላይ ምንም ችግር የለም የሚል ነው። ይህንን ዘገባ ለማቅረብ ከቤተ ክህነት ሰው አብሮዋቸው እንዲሄድና ያም ሰው ዘገባውን እንዲያቀርብ አቅደው ነበር። ሲቀሰቅሱት የነበረው ህዝብ ምንም ችግር የለም የሚለውን ዘገባ ሲሰማ እንዴት? ብሎ ጥያቄ ከጠየቀ እኛ ያዘጋጀነው ሌላ ነበር ቤተ ክህነት አስገድዳን ነው ይህንን ያቀረብነው ለማለት ነበር። ቤተ ክህነት ግን እኔ የራሴን ጥናት አቅርቤ ውጤቱን ስለአሳወኩ የራሳችሁን ጥናት አቅርቡ በማለትዋ የመጀመሪያው እቅዳቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

ሁለተኛው እቅዳቸው ደግሞ በሲኖዶሱ ውሳኔ ላይ አባቶች በጉዳዩ ላይ ተቃውሞ እንዲያቀርቡ አድርጎ እነርሱም ከአልጫውም ከመረቁም የሆነና ከአባቶች ተቃውሞ አነስ ብሎ ከመንግስትም ከቀሰቀሱት ህዝብም ተቃውሞ ሳይገጥማቸው በዘዴ የሚያልፉበትን መንገድ መፍጠር ነው። ስለዚህ በሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ አባቶችንን ገፋፍቶ የተቃውሞ ድምጽ እንዲያሰሙ ማድረግ በዚያ ተከልሎ ማምለጥ የማህበሩ እስትራቴጂ ነው።

እውነታው ግን ምንድን ነው? በሀገራችን በኢትዮጵያ የበልግ ዝናብ በዘገየ ቁጥር ደኑ ከልክ በላይ ስለሚደርቅ በከሰል አክሳዮች በማር ቆራጮችና በልዩ ልዩ ምክንያት እሳት በሚያነዱ ሰዎች ምክንያት የደን ቃጠሎ በተደጋጋሚ ሲደርስ ቆይቷል። አሁን አሁን የተፈጥሮውንም ሰብአዊውንም ችግር ሁሉ እየወሰዱ መንግስት ላይ መላከክ ልማዳቸው የሆነው የማቅ አመራሮች ሀሳባቸውን በስውር በሚገልጹባቸው ብሎጎቻቸው አመካይነት ህዝቡን በመንግስት ላይ እንዲነሳሳ መቀስቀስ አላማቸው አድርገው ይዘውታል። ለዚህም የዝቋላ ደን መቃጠልንና የዋልድባን ገዳም በሚመለከት ሲያራግቡት የነበረው ዘገባ በቂ ማስረጃ ነው።

በዚህ አጋጣሚ የዚህ ብሎግ አዘጋጆች የዝቋላ ገዳም ደን ቃጠሎ እጅግ ያሳዘናቸው መሆኑንና እሳቱንም ለማጥፋት ወጣቶቹ ያደረጉትን ተጋድሎ በእጅጉ የሚያደንቁ መሆናቸውን ይገልጣሉ።  
የሆነው ሆኖ ግን በወቅቱ የማቅ ብሎጎች ጉዳዩን ከመንግስት ጋር አያይዘው ያቀርቡት የነበረውን ዘገባ ግን አንቀበለውም። መንግስተ በጥፋተኛነት ሊወቀስበት የሚገቡ ጉዳዮች ቢኖሩም ለሰው ሰራሹም ለተፈጥሮውም አደጋ ግን ጣትን ወደ መንግስት መቀሰር ከህፃናት መዋያ ፖለቲካ የዘለለ ትርጉም አይኖረውም።

ከዝቋላው በተለየ መልኩ የዋልድባውን ጉዳይ በተመለከተ ማኅበረ ቅዱሳን ያለው አቋም እጅግ የበዛ ፖለቲካዊ ፍላጎቱን ያሳየበት ነው። ዋልድባን በተመለከተ ከፍተኛ የሆነ ጸረ መንግስት ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩትና እያደረጉ ያሉት የማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች አንድአድርገንና ደጀ ሰላም ናቸው። ለረዥም ጊዜ አንቀላፍታ የነበረችው ገብርሄር እንኳ በዋልድባ ጉዳይ ከእንቅልፏ ባንናና አይኗን ጠራርጋ አለሁ ብላለች። ሁኔታውን ችግሩን በጥልቀት ሳያሳዩ ተደፈረ ተቆፈረ በሚል ሰበብ እኛስ ሞተናል እያሉና የሬሳ ሳጥን እያሳዩ ተነስ ታጠቅ ዝመት በማለት ቅስቀሳ በማድረግና ዘመቱ ተመሙ በማለት ህዝቡን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ በመምራት ከመንፈሳዊ ሥነ ምግባር የራቀ ድርጊት ማድረግ ጉዳቱ ትልቅ ነው።
በዚህ ወቅት ዋልድባን በተመለከተ በአሜሪካ የሚደረጉትን ተቃውሞዎች በፖለቲከኞች ጉያ ተጠልሎ የራሱን ፖለቲካዊ አላማ ለማስፈጸም  እያስተባበረ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን ነው።
         
6.  አቡነ ጳውሎስን ማንሳት
 ይህ እንግዲህ ትልቁና የመጨረሻው ግባቸው ነው። ቅዱስ ፓትርያርኩን ለማንሳት በ2001 ዓ.ም. ያልተሳካ ከፍተኛ ጥረት አድርገው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ እሳቸውን አንስተን እንደፈለግን በቤተክርስቲያኒቷ እንፋንን የሚለው እቅዳቸውን እንደ አማራጭ ማስቀመጣቸው ታውቋል። ይህም የሚፈልጉዋቸውን ውሳኔዎች በፈለጉት መጠን ማግኘት ካልቻሉ በእሳቸው ላይ አመጽ ማስነሳትን እንደ መጨረሻ አማራጭ ይዘውታል።

ማህበረ ቅዱሳን በቤተክርስቲያን ላይ በቅርብ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተከስቶ የማያውቅ ትልቅ ፈተና ሆኖባታል። በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ አባቶች ከማንም የውጭ ሰው ጋር ሳይገናኙ በቀረቡ አጀንዳዎች ሁሉ ላይ የመንፈስ ቅዱስን ውሳኔ እያከበሩ ይለያዩ የነበረበት ጊዜ ተለውጦ  ዛሬ ማኅበረ ቅዱሳን አጀንዳውን ለማስፈጸም የሚሯሯጥበትና አባቶችን ሙሉ ሌሊት በስብሰባ እያሽጨነቁ ለቀጣዩ ቀን አጀንዳ እያስያዙ የሚልኩበት አሰራር በእጅጉ አሳዛኝ ነው። አንዳንድ አባቶችን በገንዘብ በመደለል፣ የተደበቀ አሳፋሪ ስራችሁን እናጋልጣለን በማለት በማስፈራራትና በልዩ ልዩ ስልት በማሳሳት የራሱ ተላላኪዎች እያደረጋቸው መሆኑ ለቤተክርስቲያናችን ትልቅ ውርደት ነው። ስለሆነም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አንድን ቤተክርስቲያን ሊወክል የማይችልና የራሱን ኑሮ እየኖረ ያለን ማኅበር ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ደግፎ ከጎኑ መቆም በታሪክ ተወቃሽ እንደሚያደርጋቸው፣ ቤተክርስቲያንንም በእጅጉ እንደሚጎዳ ከግምት በማስገባት፣ በማኅበሩ መመራታቸውን ማቆምና ማኅበሩን ወደትክክለኛ አቅጣጫ ሊያመጡት ይገባል። ጥበበኛ ሰለሞን “ብዙ ጊዜ ተመክሮ አንገቱን ያደነደነ ይሰበራል። ፈውስም የለውም ብሎ” የተናገረው ቃል በማቅ ላይ ተፈጻሚ መሆኑ እንደማይቀር ታዛቢዎች እየተናገሩ ይገኛሉ።

2 comments:

  1. u gays made mk shut its mouth. really good. we love you. and we always interested in your articles

    ReplyDelete
  2. ሌላኛውን ድምጽ መስማት ጀምረናል ጥሩ ነው። ለማመዛዘንም ይረዳናል።

    ReplyDelete