Thursday, September 26, 2013

ከሰማይ ወረደ በተባለው መስቀል ላይ ሳይንሳዊ ምርመራ ማድረግ ክልክል ነው ተባለ

ነገሩ “በሃይማኖት ጉዳይ ሳይንስ ጣልቃ አይገባም” የሚል ቃና ያለው ይመስላል

ከሰሞኑ ከሰማይ ወረደ ስለተባለው መስቀል ከዘገቡት የፕሬስ ውጤቶች መካከል አንዱ የሆነው አዲስ አድማስ ጋዜጣ በመስከረም 11/2006 ዓ.ም. እትሙ ላይ “ከሰማይ ወረደ ለተባለው መስቀል የሳይንስ ምርመራ አይፈቀድም ተባለ” የሚል ርእስ ይዞ በድጋሚ ወጣ፡፡ ጋዜጣው እንደ ዘገበው መስቀሉ ከሰማይ ወርዷል ለሚለው የብዙዎች ጥርጣሬ ማረጋገጫ መስጠት እንዲቻል “ወረደ” በተባለው መስቀል ሳይ ሳይንሳዊ ምርመራ ይደረግ ዘንድ ስለመጠየቁ ሐሳብ ቀርቦ እንደሆን የተጠይቁት፣ መልስ የሠጡትና የዚህ “ተአምር ብቸኛ የዓይን ምስክር የሆኑት” መጋቤ ሐዲስ ፍስሃ እስካሁን “ከሰማይ የወረደውን መስቀል” አድናቂዎች እንጂ ምርምር እናካሂድ የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ምሁራን አለመኖራቸውን ጠቅሰው ጥያቄውን የሚያቀርቡ ቢኖሩ ግን “የማይሞከር ነው” ሲሉ ተከላክለዋል፡፡


ይህ “ተአምር” ለሳይንሳዊ ምርምር ክፍት እንዳይሆን መከልከሉ ሰዎች በጉዳዩ ላይ ከፊት ይልቅ እንዲጠራጠሩ ሰፊ በር የሚከፍት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ “ያደረገችውን ታስታውቅ ከወደ ደረቷ ትታጠቅ” እንዲሉ መጋቤ ሐዲስ ፍስሀ ያደረጉትንና የሆነውን ስለሚያውቁ “የማይሞከር ነው” በሚል “በሃይማኖት ጉዳይ ሳይንስ ጣልቃ አይገባም” አይነት መከራከሪያ አቅርበው ለምርምር በሩ ዝግ መሆኑን ፈርጠም ብለው ተናግረዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ “ወረደ” የተባለውን መስቀል ሳይንስ ቢያረጋግጠው ከሰማይ የወረደ እስከሆነ ድረስ ምንም የሚያስፈራ ነገር አይኖርም ነበር፡፡ ነገር ግን አስቀድመን በእርግጠኛነት እንደተናገርነው መስቀሉ ከምድር የተገኘ ስለሆነ “ከቶም አይሞከርም” ብለው “የነገርኳችሁን ማመን እንጂ መመርመር አትችሉም” የሚል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡