Friday, October 18, 2013

ይድረስ ለአቶ ተመስገን ደሳለኝ፡ ፋክት ወይስ ፕሮፖጋንዳ?

በቅድምያ “ቀጣዩ የኢሕአዴግ ዒላማ ማኅበረ ቅዱሳን ይኾን?” [ፋክት መጽሔት፤ ቁጥር 14 መስከረም 2006 ዓ.ም] ሲሉ ባልዋሉበት አልያም በሽፍጥነት የሐሰት ምስክርነታቸውን ለሰጡ/ለጻፉ ግለሰብ ራሴን ላስተዋውቅ። ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል እባላለሁ። ከልጅነት እስከ እውቀት ያደግኩት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነው። ራሱን “ማኅበረ ቅዱሳን” እያለ የሚጠራ መንፈሳዊ መልክ ያለው መሰሪ – ጸረ ሀገር፣ ጸረ ትውልድና ጸረ ቤተ ክርስቲያን ቡድን ተገንዞ ከተቀበረበት መቃብር ቀስቅሰው ሊነግሩን እንደቃጣዎት ዓይነት ሳይሆን “ማህበረ ቅዱሳን” ማለት ሰይጣን ራሱ በቁሙ የሚመለክበት፣ የሚዘከርበትና የሚታሰብበት የሲዖል ተረፈ ምርት ለመሆኑ በህይወቴ የማውቀው ሰው ነኝ። ሕገ መንግሥታዊ የመማር መብቴ ተጥሶ ለዓመታት ከለፋሁበት የትምህርት ገበታዬ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ያለ ስሜ ስም ተለጥፎብኝ እንድባረር የተደረግኩ፣ ከአንድም ሁለቴ በአንድ የክስ መዝገብ ለከፍተኛ እንግልትና ለእስር የተዳረግኩ፣ በሞትና በህይወት መካከል የተገረፍኩና በመጨረሻም አገሬን ለቅቄ በስደት ምድር በኬንያ ለሁለት ዓመት ከአምስት ወር ያለ ምንም የህይወት ዋስትንና እርዳታ የተንገላታሁ የሰው ሚስት ሳማግጥ ተገኝቼ ይመስሎታል? ከነተረቱ “ያልተነካ ግልግል ያውቃል” ነው የሚባለው። ለመሆኑ እርስዎ ስለ “ማኅበረ ቅዱሳን” ያልሆነውን ነው! በማለት ይህን ያህል ለማለት የደፈሩ እንደ አንድ የማኅበሩ አባል በጋዜጠኝነት ስም የአባልነት ግዴታዎ መወጣትዎ ነው ወይስ ነኝ እንደሚሉት “በጋዜጠኝነትዎ” ነው? ቁምነገሩ ያለው ወዲህ ነው። “ቀጣዩ የኢሕአዴግ ዒላማ ማኅበረ ቅዱሳን ይኾን?” ሲሉ በጻፉት ጽሑፍ በጋዜጠኝነትዎ እንዳልነቅፎት፥ በኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ሰርተው ያለ ተጠያቂነት ለመኖር ይሻሉ? 
እንግዲያውስ በጋዜጠኝነት የሥራ መስክ ይሰማሩ።

Thursday, October 17, 2013

ማኅበረ ቅዱሳን በአጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ በደረሰበት ተቃውሞ ተወካዮቹ ስብሰባ ረግጠው ወጡ

ምንጭ- አባ ሰላማ
32ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ፓትርያርኩን ጨምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከየሀገረ ስብከቱ የተወከሉ የአህጉረ ስብከቶች ሥራ አስኪያጆች፣ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎችም በተገኙበት ጥቅምት 3/2006 ዓ.ም ተጀምሯል፡፡ በስብሰባው ላይ ከየአህጉረ ስብከቶች በመጡ ሥራ አስኪያጆች የሥራ ሪፖርት እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን ውይይትም እየተደረገ ነው፡፡

 በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን በጠቅላይ ቤተ ክህነት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ካህናት ኃይለ ስላሴ ዘማርያም ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን ምን ያህል አስጊ ኃይል እንደ ሆነና ከተለያዩ የንግድ ተቋማቱ የሚሰበስበውንና በቤተክርስቲያን ስም ከአገር ውስጥና ከውጭ የሚሰበስበውን ገንዘብም ኦዲት እንደማይደረግ የገለጹ ሲሆን፣ በዚህም ማቅ ኪራይ ሰብሳቢ ድርጅት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 በትናንትናው ዕለት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት መልአከ ገነት አባ አፈወርቅ ዮሐንስ በሀገረ ስብከታቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በዓመቱ ከገጠሟት ችግሮች መካከል ዋና አድርገው የጠቀሱት ማኅበረ ቅዱሳንን ሲሆን፣ ማኅበሩ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ ቤተ ክርስቲያኗ የራሷ መተዳደሪያ ቃለ አዋዲ እያላት ቃለ ዐዋዲውን አሻሽሎ ሌላ መተዳደሪያ በማውጣትና የቤተክርስቲያንን መዋቅር በማዳከምሕዝበ ክርስቲያኑ ፐርሰንት እንዳይከፍሉና ሕዝቡ ለማኅበሩ በአባልነት ተመዝግቦ ለማኅበሩ እንዲከፍል በመቀስቀስ በቤተ ክርስቲያን ላይ ደባ መፈጸሙን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም የሀገረ ስብከቱ የሆነውን ሱቅ እንደማንኛውም ምእመን ተከራይተው ኪራይ አንከፍልም በማለት ማመጻቸውንና ሕዝብን ማነሳሳታቸውን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ማኅበሩ እንደ ትልቅ ስልት የያዘው የሕዝብ ተመራጭ በመምሰል በሰበካ ጉባኤ፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች በልማትኮሚቴና በስብከተወንጌል ኮሚቴነት በመግባት የበላይ መመሪያን አለመቀበልንና መዋቅር ማዳከምን ነው ብለዋል፡፡ ለማሳያነትም በወንጪ፣ በወሊሶ፣ በሰበታ አዋስ ወረዳ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሕዝብን የመከፋፈልና የማሳመፅ ድርጊት በመፈጸም ላይ መሆናቸውን በማስረጃ አስደግፈው አጋልጠዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በ11ዱ ወረዳዎች ኔትዎርክ በመዘርጋት የራሳቸውን ሥራ በመተው በሀገረ ስብከቱ ላይ ሰዎችን በማደራጀት ላይ እንደሚገኙ በማስረዳት ቅዱስ ሲኖዶስ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡