Thursday, August 30, 2012

ታሪክ የማይረሳው ብቸኛው ፓትርያርክ


Cllick Here to read in PDF: Abune pawlos history
                                                                    በመምህር መላኩ
አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፤ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ፤ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንትና የዓለም ለሰላም አምባሳደር ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለዩ!
በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን የልዩ ልዩ እምነት ተከታይ መሪዎችና እንዲሁም የሮማ ቤተክርስቲያን መሪ የሆኑትን ፖፕ ፔነዲክ 16ኝን ጨምሮ የዓለም የሃይማኖት መሪዎችና ዓለም አቀፉ ሕብረተ ሰብ የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን በአካልና በልዩ ልዩ የዜና ማሰራጫዎች በመግለጥ ላይ ይገኛል ። 

Tuesday, August 28, 2012

የሲኖዶሱ የሰሞኑ ሁኔታ


Click here to read in PDF: Sinodos
  • “ሚዲያ ጥሩ እና ሌላ አቃቤ መንበር ሹሙ።” አቡነ ናትናኤል
(ዐውደ ምሕረት፤ ማክሰኞ፤ ነሐሴ 22 ቀን 2004 ዓ.ም. /awdemihret.blogspot.com// awdemihret.wordpress.com)ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የቅዱስነታቸው የቀብር ሥነ ስርዓት ከተፈጸመ በኃላ በነጋታው ሲኖዶሱ ወደ መደበኛ ሥራው ተመልሷል። ከተመለከታቸው ጉዳዩች አንዱም የእርቁ ሁኔታ ነበር። የቅዱስነታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ቀን ማታ አቡነ መልከጻዲቅ ቅዱስነታቸው ተወግዘው ነው የሞቱት ብለው መናገራቸው የእርቁን ሀሳብ አደጋ ላይ ጥሎታል።
አርብ ዕለት በነበረው ስብሰባ የእርቁ ሀሳብ ሲነሳ በርካታ ጳጳሳት የአቡነ መልከጻዲቅን ንግግር ማዘናቸውን ገልጸዋል። በተለይም የአቡነ እስጢፋኖስ አቋም ጠንካራ እና የሁሉንም ልብ ማሸነፍ የቻለ ነበር። ብጹዕነታቸው ሲናገሩ “ቀብቶ የሾመን ተወግዞ ሞተ ከተባለ እኛም የተወገዝን ነን ማለት ነው። ስለዚህ የምን እርቅ ነው የሚደረገው? እኛ የእርቅን ሀሳብ መነጋገር ከጀመርን ጀምሮ ከቅዱስነታቸው ጀምሮ ሁላችንም ስለ እነርሱ መወገዝ አንስተን አናውቅም። ምክንያቱም እርቅ የሚመጣው ያሉበትን አቋም ትቶ ነው እንጂ የወሰድኩት አቋም አይለወጥም ብሎ አይደለም። ስለዚህ ቅዱስነታቸው ሲያርፉ መነሳት የሌለበትን ርዕስ አቡነ መልከጻዲቅ ሰላነሱ በአደባባይ የተናገሩትን ንግግራቸውን በአደባባይ እስካላስተባበሉ ድረስ የእርቅ ሀሳብ አይኖርም” በማለት በአጽንኦት ተናግረዋል። ይህንንም ሀሳብ አብዛኛዎቹ ጳጳሳት ተቀብለውታል።

Monday, August 27, 2012

የክብረ መንግስት ከተማ የማኅበረ ቅዱሳን ወኪሎች ቅብጠትና የመንግስት ምላሽ


 Click here to read inPDF: kebbremenegeste kidanemihret
(አውደ ምህረት፤ ሰኞ ነሐሴ 21 2004 ዓ.ም. /awdemihret.blogspot.com// awdemihret.wordpress.com) ቅዱስነታቸው ካረፉ በኃላ ጊዜው የኛ ነው በማለት የሚሆኑትን ያጡት የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች በማን አለብኝነት ስሜት ያለ ሊቀጳጳስ ትዕዛዝ በየካቲት ወር እንጂ በነሐሴ 16 ቀን ነግሳ የማታውቀዎን የክብረ መንግስት ኪዳነምህረትን በማንገሳቸው እና ሀገሪቱ ብሔራዊ ሀዘን አውጃ ሳለ ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረጋቸው ከመንግስት ኃላፊዎች ጋር መጋጨታቸው ተሰማ።
በአካባቢው በተሰራው ደንብ እና የገጠር አብያተ ክርስቲያናትም የንግስ በዓል እንዲያከብሩ በተደረገው መሰረት የነሐሴ ፍልሰታ ንግስ የጨንቢ ኪዳነምህረት ተራ መሆኑን እያወቁ እና ከክብረ መንግስት ካህናት ካልሄዱም በቀር ማንገስ እንደማይቻል እየተረዱ የጨንቢ ኪዳነ ምህረትን ንግስ ወደጎን ብለው የክብረ መንግስት ኪዳነ ምህረትን አንግሰዋል:: በንግሱ ዕለትም ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ባለስልጣናትም የጉዳዩ ዋና ተዋናይ የነበሩትን እና የየካቲት ኪዳነ ምህረት ዕለት ተከስቶ በነበረው ብጥብጥ ታስረው የነበሩትን እነ ሊቀስዩማን ልሳነወርቅ ሁንዴን ጠርተው እንዲጠየቁ ያደረጉ ሲሆን ያለ ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ በቤተክርስቲያኒቱ ንግስ እንዲነግስ ያደረጉበትን ምክንያት እና ባንዲራ ከፍ አድርገው ያወለበለቡበትን የደስታቸውን ምንጭ በአግባቡ ማስረዳት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ በከባድ ማስጠቀቂያ መታለፋቸውን ምንጮቻችን አስታውቀዋል።
ይህ ሁኔታ ያስደነገጣቸው ሊቀስዩማን ልሳነ ወርቅ ሁንዴ በጠቀላ ሚኒስቴሩ ሞት ምክንያት በትናንትናው ዕለት በነበረው የአደባባይ ሀዘን ሰንበት ተማሪ አሰልፈው የወጡ ሲሆን ንግግር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ሳይፈቀድላቸው ቀርቷል፡፡ የእሳቸው ሁኔታ ተጣርቶ እስኪታወቅም በማንኛወም ሁኔታ ላይ ቤተክርስቲያንን ወክለው ንግግር ማድረግ እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል፡፡ ለቀስዩማኑ ከነበራቸው ሀላፊነት በህጋዊ መንገድ የተነሱ ሲሆን ማህተም አላስረከብም በማለት ማቅን ተተግነው በህገ ወጥ መንገድ እየሰሩ መሆናቸውነ ከዚህ በፊት የዘገብን መሆኑ ይታወሳል፡፡

Sunday, August 26, 2012

የፓርትርያርክ የምርጫ ግርግር ለማኅበረ ቅዱሳንና ለወዳጅ ጳጳሳት ጥቅም እንዳይውል ያስፈራል!


Click here to read in PDF: mercha 
ምንጭ፡- ደጀ ብርሃን
ቅዱስ ፓትርያርኩ ቢቻል ከስልጣናቸው በሆነ መንገድ ቢነሱ፤ ባይቻል እንኳን ባሉበት ተሽመድምደው መስራት የማይችሉበት ገጠመኝ ቢከሰት ብዙ የደከመው ማኅበር፤ ማኅበረ ቅዱሳን እንደነበረ ይታወቃል። በየሲኖዶስ ጉባዔያት ፓትርያርኩም ይሁኑ ጽነት የሞላባቸው ጳጳሳት የየራሳቸውን ዓላማ የማስጠበቅ ህልም ለማሳካት ሲሉ ጥቅምትና ግንቦትን በቤተክርስቲያን አካባቢ የውጥረት ወራት አድርገው እንደሚያሳልፉ የምንረሳው አይደለም። ማኅበሩም ለውጥረቱ መባባስ አንዱ ምክንያት ሆኖ ለመቆየቱ ማሳያዎቹ፤ የሲኖዶስ ነደ እሳትና ጀግና እየተባሉ በስም የሚደገፉት ጳጳሳት ብዙ ጊዜ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር እሳትና ጭድ ሆነው በጉባዔው ላይ ውጥረት ፈጣሪዎች በመሆናቸው ነበር። ውጥረት ፈጣሪዎቹን ጳጳሳት ስንመለከት በእርግጥ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር እሳትና ጭድ ሆነው ጥቅምትና ግንቦትን የሚያጨሱት ለቤተክርስቲያን የሚቆረቆርና የሚመሰከርላቸው ሃይማኖታዊ፤ ሞራላዊና  ክርስቲያናዊ ማንነት ስላላቸው አልነበረም።  ስለምናውቀው ማንነታቸው፤ የኅሊና ጸጸት ስላላቸው ሳይሆን፤ ይልቁንም በውጥረቱ ውስጥ ብርቱ አሳቢና የቤተክርስቲያን ታጋይ ሆነው በመታየት የራሳቸውን ስብእና ለመገንባትና የስልጣን ጫናቸውን ለማሳረፍ ሲሆን በሌላ መልኩም ማንነታቸውን እንደመጽሐፍ የሚያነባቸውን ማኅበር ዓላማዎች በማስጠበቅ ውጪያዊ ስእላቸውን ለማሳመር ብቻ እንደነበር እንረዳለን።  አሁንስ?  አሁን እንግዲህ በማኅበሩም ሆነ በውጥረት ፈጣሪ ጳጳሳት ዘንድ የሚጠሉት ፓትርያርክ ጥሩም ሰሩ መጥፎ፤ ፍርዱን ለታሪክና ለትውልድ ትተው ላይመለሱ ሄደዋል። የቀሩት እነዚህ ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ገጾች ብቻ ናቸው።

Thursday, August 23, 2012

የቅዱስነታቸው ቀብር በደማቅ ሁኔታ ተፈጸመ


በ76 ዓመታቸው ያረፉት የብጹዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የአለም የአብያተክርስትያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፤ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ፤ የዓለም ሰላም አምባሳደር ስርዓተ ቀብር ዛሬ ነሐሴ 17 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡30 ላይ በደማቅ ሁኔታ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

የቅዱስነታቸው ስርዓተ ቀብር ላይ ቁጥሩ እጅግ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ የተገኘ ሲሆን ጊዚያዊ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የእህት አብያተ ክርስቲያናት አባቶች የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ ፤ የህዝብ ተወካች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አባ ዱላ ገመዳ ፤ ምክትል አፈጉባዬ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ፤ አምባሳደሮች፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበትና በአክሱም ካሕናት እምቢልታ የታጀበ የቀብር ስነ ስርዓት ተደርጎላቸዋል። 

Wednesday, August 22, 2012

ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሥርዓተ ቀብር ሐሙስ ይፈጸማል፤ መጪው ዘመንስ ምን ይመስል ይሆን?

source:www.dejebirhan.blogspot.com
ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ እነሆ አንድ ሳምንት ሊሆናቸው ነው። የሚወዷቸው አዝነዋል፤ የሚጠሏቸውም ደስ ተሰኝተዋል። አንዳንዶች ቢጠሏቸውም እንኳን ሞት የጋራ ርስት መሆኑን በማመን እግዚአብሔር እረፍቱን ይሰጣቸው ዘንድ ከልባቸው ተመኝተዋል።
አብዛኛው ሕዝብ ደግሞ መጪው ዘመን ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለሀገሪቱ ምን ይመጣ ይሆን? በሚል ሃሳብ ረጅሙን ጊዜ በማስላት ይጨነቃል። በእርግጥም ሟቾች ጥፋትም ይስሩ ልማት ላይመለሱ ሄደዋል። የነበሩበት ቦታ ትልቅ የመንፈሳዊና የሥጋዊ ሥልጣን ደረጃ በመሆኑ ቤተክርስቲያኒቱን በመንፈሳዊ አባትነት ሊመራ የሚችልን ሰው በማግኘት አንጻር ቢያሳስበን አይገርምም። በስጋዊ ሥልጣን ደረጃም እንደዚሁ በሀገር መሪነት ደረጃ የሚመጣው ሰው የነበሩ ድክመቶችን በማስተካከል፤ የታዩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል ስለመቻሉ ቢያሳስበን እንደዜጋ ከተገቢነቱ የወጣ አስተሳሰብ አይደለም።
 ቀና ቀናውን አስበን፤ መጪውን ጊዜ ብንፈራ ሰው ነንና ተገቢ ነው።

ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስና ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ምን እንማራለን?


ምንጭ፡- አባ ሰላማ

በዚያን ጊዜም ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች አወሩለት።
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን?
እላችኋለሁ፥ አይደለም፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ።
ወይስ በሰሌሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፥ እላችኋለሁ፤
ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።
(ሉቃ. 13፥1-5)
2004 ዓ.ም. አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ታላላቅ ሰዎችን በሞት የተነጠቀችበት ዓመት ነው፡፡ የቤተክርስቲያናችንና የአገራችን መሪዎች ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዲህ በአንድነት በሞት የተጠሩበት አጋጣሚም ያለ አይመስለንም፡፡ የመሪዎቻችን በአንድ ሰሞን በሞት መጠራትና የነገሮቹ ግጥምጥሞሾች በኢትዮጵያውያን ላይ ልዩ ልዩ ስሜት ፈጥሯል፡፡ ሁለቱንም መሪዎች የሚጠሏቸው ብዙዎቹ ሳይቀሩ አዝነዋል፡፡ ሌሎቹ የሚጠሏቸው ደግሞ ጸሎታቸው እንደተሰማ ቆጥረው ደስ ብሏቸው ይሆናል፡፡ እንዲህ የምንለው አቡነ ጳውሎስ በሕይወት እያሉ በአቡነ ጳውሎስ ላይ ሲያሟርቱ የነበሩና የዘንድሮው በዓለ ሲመታቸው የመጨረሻቸው ነው ብለው የጻፉ ብሎጎች ስለነበሩ ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ታመው በሕክምና ላይ እያሉ ሞታቸውን ብቻ ሲያቀነቅኑ የነበሩ ሚዲያዎችም ስለነበሩ ነው፡፡

Tuesday, August 21, 2012

ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ አረፉ


ኢትዮጵያን ለ21 ዓመታት የመሩት ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ አረፉ፡፡ ላለፉት ከ28 ዓመታት በመሪነት ቦታ ላይ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ህይወታቸው ዕረፍት አልባ እንደነበር እና በቀንም ሁለት ሰዓት ቢበዛ ሶስት ሰዓት ብቻ በእንቅልፍ ያሳልፉ እንደነበር ይነገራል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሞት  ለሀገራችን ኢትዮጵያ ከባድ ሸክም ነው፡፡ ለብዙ የሀገሪቱ እቅዶች ባለራዕይ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የለወጡ እና አለማቀፍ ተቀባይነትዋን የጨመሩ ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡
አገራችን ታላቅ መሪዋን አትጣለች፡፡ ለህዝቦችዋ ሁሉ መጽናናት ይሁንላቸው፡፡ አውደ ምህረትም የተሰማትን ጥለቅ ሀዘን ትገልጻለች፡፡

Monday, August 20, 2012

ሰበር ዜና፡ አቡነ ናትናኤል በአቃቤ መንበርነት ተሾሙ

Click Here to read in PDF: aba natenael 2
·          “ምን አስቸኮላችሁ? አፈር እስኪቀምሱ እንኳ ብትታገሱ ምን ነበረበት?”
                                                                            የአቡነ ጳውሎስ ታናሽ እህት
ለማኅበረ ቅዱሳን ፍላጎቶች ራሱን እያስገዛ የመጣው ሲኖዶስ ብጹዕ አቡነ ናትናኤልን በአቃቤ መንበርነት ሾመ፡፡
ብጹዕ አቡነ ናትናኤል በእድሜ የገፉ ስለሆነ እና የጤናም ችግር አለባቸው በሚል በስራቸው ቋሚ ሲኖዶሱን ጨምሮ 14 አባለት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መርጧል፡፡ በዚህ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ የማኅበረ ቅዱሳን የልብ ወዳጅ የሆኑት አቡነ ሉቃስ አቡነ አብርሃም አቡነ ጢሞቴዎስና አቡነ ሳሙኤል አቡነ ገብርኤል እና አቡነ እስጢፋኖስ ይገኙበታል፡፡
ሥራዎች በአጠቃላይ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በኩል የሚሰሩ ሲሆን የአቡነ ናትናኤል ስራም ስራ አስፋጻሚ ያጸደቀውን ላይ መፈረም ይሆናል፡፡