Thursday, September 26, 2013

ከሰማይ ወረደ በተባለው መስቀል ላይ ሳይንሳዊ ምርመራ ማድረግ ክልክል ነው ተባለ

ነገሩ “በሃይማኖት ጉዳይ ሳይንስ ጣልቃ አይገባም” የሚል ቃና ያለው ይመስላል

ከሰሞኑ ከሰማይ ወረደ ስለተባለው መስቀል ከዘገቡት የፕሬስ ውጤቶች መካከል አንዱ የሆነው አዲስ አድማስ ጋዜጣ በመስከረም 11/2006 ዓ.ም. እትሙ ላይ “ከሰማይ ወረደ ለተባለው መስቀል የሳይንስ ምርመራ አይፈቀድም ተባለ” የሚል ርእስ ይዞ በድጋሚ ወጣ፡፡ ጋዜጣው እንደ ዘገበው መስቀሉ ከሰማይ ወርዷል ለሚለው የብዙዎች ጥርጣሬ ማረጋገጫ መስጠት እንዲቻል “ወረደ” በተባለው መስቀል ሳይ ሳይንሳዊ ምርመራ ይደረግ ዘንድ ስለመጠየቁ ሐሳብ ቀርቦ እንደሆን የተጠይቁት፣ መልስ የሠጡትና የዚህ “ተአምር ብቸኛ የዓይን ምስክር የሆኑት” መጋቤ ሐዲስ ፍስሃ እስካሁን “ከሰማይ የወረደውን መስቀል” አድናቂዎች እንጂ ምርምር እናካሂድ የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ምሁራን አለመኖራቸውን ጠቅሰው ጥያቄውን የሚያቀርቡ ቢኖሩ ግን “የማይሞከር ነው” ሲሉ ተከላክለዋል፡፡


ይህ “ተአምር” ለሳይንሳዊ ምርምር ክፍት እንዳይሆን መከልከሉ ሰዎች በጉዳዩ ላይ ከፊት ይልቅ እንዲጠራጠሩ ሰፊ በር የሚከፍት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ “ያደረገችውን ታስታውቅ ከወደ ደረቷ ትታጠቅ” እንዲሉ መጋቤ ሐዲስ ፍስሀ ያደረጉትንና የሆነውን ስለሚያውቁ “የማይሞከር ነው” በሚል “በሃይማኖት ጉዳይ ሳይንስ ጣልቃ አይገባም” አይነት መከራከሪያ አቅርበው ለምርምር በሩ ዝግ መሆኑን ፈርጠም ብለው ተናግረዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ “ወረደ” የተባለውን መስቀል ሳይንስ ቢያረጋግጠው ከሰማይ የወረደ እስከሆነ ድረስ ምንም የሚያስፈራ ነገር አይኖርም ነበር፡፡ ነገር ግን አስቀድመን በእርግጠኛነት እንደተናገርነው መስቀሉ ከምድር የተገኘ ስለሆነ “ከቶም አይሞከርም” ብለው “የነገርኳችሁን ማመን እንጂ መመርመር አትችሉም” የሚል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡

ይህ አሰራር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቦታ እንደሌለው ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ጥያቄ ለቀረበባቸው የፈጠራ ታሪኮች በተሰጡ ምላሾች ግልጽ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ፦ የብሉይ ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢትዮጵያ ሳይመጣ መጥቷል ተብሎ የሚተረከውን አፈታሪክ ለማረጋገጥ ብዙዎች ጥረት አድርገዋል፡፡ ስፍራው ድረስ በመገኘት ታቦቱን ለማየት ጥያቄ ያቀረቡ ሁሉ ግን “የሃይማኖታችን ቀኖና ይህ እንዲሆን አይፈቅድም” ተብለው አፍረው ተመልሰዋል፡፡ ይህም ምላሽ ታቦቱ ባይመጣ ነው የሚለውን የብዙዎችን ጥርጣሬ አጉልቶታል፡፡  

በሌላው ዓለም ግን ጥርጥርን ለማስወገድ ሳይንስ ሊመረምራቸው ለሚችሉ ሃይማኖታዊ ነገሮች በር ይከፈታል እንጂ አይዘጋም፡፡ ከዚህ ቀደም የክርስቶስን ምስል የያዘ የተባለ የከፈን ጨርቅ ተገኘ ተብሎ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ተነግሮ ነበር፡፡ በትክክል እርሱ የተገነዘበት ጨርቅ መሆኑ በሳይንሳዊ መንገድ መጣራት ነበረበትና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥ የሆነ ዕውቀት ያላቸው የበርካታ ሳይንቲስቶች ቡድን ተቋቁሞ ሰፊ ጥናትና ምርምር አድርጎ ነበር፡፡ በመጨረሻም ጨርቁ ጌታ የተገነዘበት መሆኑን በሳይንቲስቶቹ ጥናት ተረጋገጠ፡፡ ይህን ዘገባ በወቅቱ ናሽናል ጂኦግራፊ መጽሔት ቅጽ 157 ቁጥር 6 ሰኔ 1980 ላይ እንዲሁም ኒውስ ዊክ የተሰኘ ሳምንታዊ መጽሔት በመስከረም 18/1978 እ.ኤ.አ እትሙ ላይ አውጥተውት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ድርጅት ያሳትመው በነበረው ትንሣኤ መጽሔት ላይ ተተርጉመው ዘገባዎቹ ለንባብ በቅተው ነበር (ትንሣኤ መጽሔት ሐምሌ 1972 እና ሚያዝያ 1973 እትሞችን መመልከት ይቻላል)፡፡ በተለይም የሐምሌ 1972 ዘገባ “በጌታ መግነዝ ላይ የተደረገው ሳይንሳዊ ምርመራ የብዙ ሳይንቲስቶችን ጥርጣሬ አስወገደ” በሚል ርእስ ነበር የቀረበው፡፡ 

ዛሬም እነመጋቤ ሀዲስ ፍስሀ ከሰማይ ወረደ ያሉት መስቀል በርግጥ ከሰማይ ወርዶ ከሆነ ተጠራጣሪዎች ያምኑ ዘንድ ለምርምር ክፍት ማድረግ አለባቸው እንጂ “ከቶ አይሞከርም” በሚል በሩን መዝጋት አልነበረባቸውም፡፡ መስቀሉ ከሰማይ የወረደ እስከ ሆነ ድረስ ሳይንስ መርምሮ አስገራሚነቱን ቢያረጋግጠው በጉዳዩ ላይ ልበሙሉ ሆኖ ለመናገር ያግዛል እንጂ የሚያስከትለው ጉዳት የለም፡፡ ነገር ግን “ከፊተኛው ስህተት ይልቅ የኋለኛው ጥፋት ይብሳል” ብለው ነው መሰል “አይሞከርም” ብለዋል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ክርስቲያን በማንኛውም ሁኔታ በብርሃን መመላለስ አለበት፡፡ ብርሃንን የሚሸሽና በጨለማ የሚኖር ከሆነ ግን ችግር አለበት፡፡ ቃሉም እንዲህ ይለናል “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።” (ዮሐ. 3፥20-21)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከኃጢአትና ከቀድሞው እግዚአብሔርን ያለማወቅ ሕይወት ጋር አያይዞ የተናገረው ተመሳሳይ መልእክት አለው፡፡ “ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ፥ እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና፤ ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና።” ስለዚህ መጋቤ ሐዲስ በእርግጥ መስቀሉ የወረደው ከሰማይ ከሆነ ጉዳዩን ወደ ብርሃን ማምጣት አለባቸው እንጂ “አይሞከርም” በሚለው ጨለማ ውስጥ መደበቅ የለባቸውም፡፡ እንዲያውም ተጠራጣሪዎችን ሁሉ ለማሳመን ትልቅ እድል ይፈጥራልና የነገሩ እውነትነት ይረጋገጥ ለማለት ግንባር ቀደም መሆን አለባቸው፡፡ ነገር ግን የዚህ “ተአምር” ደራሲ መጋቤ ሀዲስ ፍስሀ ሲጀመርም አላማቸው ሌላ ስለሆነና መስቀሉም ከሰማይ ስላልወረደ ለሳይንስ ምርመራ በራቸውን ጠርቅመዋል፡፡ መስቀሉ ከሰማይ ነው የወረደው የሚለውን ለሚጠራጠሩ ሰዎች “ወርዷል ማለት ወርዷል ነው ዝም ብላችሁ በእምነት ተቀበሉ” ማለት በእምነት ስም የሚደረግ ማጭበርበር ነው እንጂ ሃይማኖትን ለአደጋ የሚያጋልጥ ጥያቄ ሊሆን አይችልም፡፡ አሊያ ዐይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ አይነት ጨዋታ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ጥርጣሬውን ለማስወገድ በሩን ለምርመር ክፍት ማድረግ ይገባል፡፡

በአገራችን ከዚህ ቀደም በአንዳንድ ገዳማትና አድባራት መስቀልን ጨምሮ ከሰማይ ወረዱ የሚባሉ ንዋተ ቅድሳት መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ጣና ቂርቆስ ገዳም ወረደ የተባለ ጽዋ አለ፡፡ በዚያ ገዳም የመቀደስ እድል የገጠመው አንድ ዲያቆን በአንድ ወቅት እንደመሰከረው “ከሰማይ ወረደ በሚባለው ጽዋ ነበር የቀደስኩት፡፡ ነገር ግን ከቅዳሴ በኋላ ወደላይ ከፍ አድርጌ ከጽዋው ሥር የሰፈረውን ጽሑፍ ሳነብ ‘made in Italy’ ይላል፡፡ ከዚያም እንዴት አድርገው አጃጅለውናል ጃል! አልኩኝ ለራሴ” ብሏል፡፡ ማን ያውቃል ይህም ሰማያዊ የተባለ መስቀል ሳይንሳዊ ምርመራ ቢደረግበት ምድራዊ መሆኑ አይቀርም፡፡ ለዚህም ነው እነመጋቤ ሀዲስ “አይሞከርም” ያሉት፡፡

አዲስ አድማስ እንደጻፈው መጋቤ ሀዲስ ፍስሀ ተጠራጣሪዎች ቢኖሩ “እውነቱን የሚያውቀው እግዚአብሔር ነው” ሲሉ የሚሰነዘርባቸውን መስቀለልኛ ጥያቄ “ውርድ ከራሴ” ብለዋል፡፡ አክለውም “በምድራችን የተሰራ የሚመስል መስቀል ከሰማይ ሊወርድ አይችልም የምንል ከሆነ በምድራችን የምናረባው አይነት በግ ለአብርሃም ከሰማይ ወርዶለታል የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መጠራጠር ይሆናል ብለዋል፡፡” ይሁን እንጂ ጥያቄውን በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ የጠቀሱት ይህ ቃል ስህተታቸውን ለመሸፈን ከመሞከር አይዘልም፡፡ በቅድሚያ ግን መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃም በይስሐቅ ፈንታ የሠዋው በግ የወረደው ከሰማይ ነው ይላል ወይ? ነው ጥያቄው፡፡ በፍጹም!!!!!!!! መጽሐፍ ቅዱስ ለአብርሃም በግ ከሰማይ ወረደለት አይልም፡፡ “አብርሃምም ዓይኑን አነሣ፥ በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ አብርሃምም ሄደ በጉንም ወሰደው፥ በልጁም ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው።” (ዘፍ. 22፥13) ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ ይህ ጥቅስ በምንም መንገድ በሐሰት ከሰማይ ወረደ ለተባለው የጥበበ እድ ውጤት መስቀል መከራከሪያ ሊሆን አይችልም፡፡ አብርሃም በዱር ውስጥ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ ያገኘውንና በይስሐቅ ፈንታ የሰዋውን በግ ማንም የሚጠራጠር የለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብሏልና፡፡

“ከሰማይ መስቀል ወረደ” የተባለው ለምንድነው? በእርግጥ መስቀሉ ከሰማይ ስለወረደ ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት ይኖረው ይሆን? ብለን ዛሬም መጠየቃችንን እንቀጥላለን፡፡  እነመጋቤ ሀዲስ ፍስሀ እንዲህ አይነት ነገር ውስጥ የገቡት ነገሩ ስለተከሰተ ሳይሆን ደብራቸው ታዋቂ እንዲሆንና ከፍተኛ ገቢ ለማግኘትም ነው፡፡ እንደተባለውም በአሁኑ ጊዜ በየቀኑ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ቦታውን እየጎበኙ እንደሆነና መስቀሉ ባረፈበት ሳር ላይና ወደ መቅደስ ከገባ በኋላ የተነሳቸው ፎቶዎችን የያዘ ካርድ ተዘጋጅቶ በ10 ብር እየተቸበቸበ መሆኑን የአዲስ አድማስ ዘገባ ያስረዳል፡፡ በየዕለቱ ከሚጐበኘው ሕዝብ “ለበረከት” እየተባለ ግማሽ ያህሉ እንኳን ካርዱን ቢገዛ የደብሩ ዕለታዊ ገቢ በቀን ከካርድ ሽያጭ ብቻ ቢያንስ 15 ሺህ ብር ይሆናል ማለትም አይደል? ታዲያ ከዚህ በላይ በሃይማኖት ሽፋን የሚሠራ ምን ቢዝነስ አለ!

ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ባወጣው ዘገባ ላይ የተነሳበትን ጥያቄ በገደምዳሜ ለመመለስና ማቅ የሰጠውን ተልእኮ ለመወጣት በሚል ነው መሰል “ዓለምን ያስደመሙ ተአምራት” በሚል ርእስ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች “ተአምር” የተባሉ ልዩ ልዩ የማርያም የመላእክት የስዕላት ግልጠቶችን ጠቅሶ አንድ ጽሁፍ አስነብቧል፡፡ ይህም ሰሞኑን ቃሊቲ ላይ ከሰማይ ወረደ የተባለው መስቀል የዚያው ክትያ ነው ለማለት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መታወቅ ያለበት ተአምር ከእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን ከሰይጣንም በኩል ሊደረግ እንደሚችል ነው፡፡ ቁም ነገሩ ከሰይጣን የሚሆነውን ተአምር በእግዚአብሔር ጣት ከሆነው ተአምር በምን እንለየዋለን? የሚለው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ እንደምንረዳው ከእግዚአብሔር የሚደረግ ተአምር የእግዚአብሔርን ታላቅነት ብቻ የሚገልጥ ሲሆን፣ ክብርን ወደሌላ የሚወስድ ሳይሆን ጠቅልሎ ወደ እግዚአብሔር ብቻ የሚያመጣ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ያልሆነው ተአምር ግን ፍጡራንን ከፍ ከፍ የሚያደርግና እነርሱኑ የሚያከብር ሆኖ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን ወረደ በተባለው መስቀል አማካይነት ሲወደስ የሰነበተው ማነው? የማንስ ታላቅነት ነው የተወራው? በሰዉ ሕይወት ውስጥስ ምን ለውጥ አመጣ? ምላሹን በትክክል የመለሰ ሰው ካለ፣ መስቀሉ ከሰማይ ሳይሆን ከምድር የተገኘ፣ የሐሳቡ ፈጣሪም ስጋና ደም (መጋቤ ሀዲስ ፍስሐ) ምናልባትም መስቀልን በማስመለክ ሕዝቡን ከአምልኮተ እግዚአብሔር ወደአምልኮተ መስቀል ያሸፈተው ያው ሰይጣን ነው የሚሆነው፡፡  ስለዚህ እናስተውል!!!

1 comment:

  1. Amazing Discovery !!!

    I am so confused, who we should have to believe? Many history that the church has is being disproved.

    I have seen shocking video about the discovery of the ark of the covenant(የቃል ክዳን ታቦት) which GOD had gave to mosses. I believe till today that the ark is taken from Jerusalem to Ethiopia, and so still it is in Ethiopia. But what I have seen disproves this history. It says the ark is discovered there in Jerusalem by archeologists deep in cave directly under the position where the cross of the Jesus Christ is stood. It is very long video. If you want to watch, You find it on YouTube via(http://www.youtube.com/watch?v=bYIwjYN4JVo and http://www.youtube.com/watch?v=cwBX66OuI7g ). Amazing Discovery!!!

    what is going on??!!!!

    ReplyDelete