Monday, December 31, 2012

ካህናቶቻችሁን አትበድሉ: ካህን ማለት የእድር ዕቃ ማለት አይደለምና!

Read in PDF: kahematocacehun
በዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
መግቢያ:
የተራበ እንጅ የጠገበ ሰው ባያሳዝንም የሀገሬ ሰው "ከተራበ ይልቅ የጠገበ …" እንዲል ሰው ሲባል ሆዱ ሞልቶ/በልቶ ካደረ መጀመሪያ ጸብ የሚጀምረው ከፈጠሪው ጋር ለመሆኑ ስለሚበላና ስለሚጠጣ ጨርሶ ሃሳብ ለሌለው/የማይገባው ሰው ነገሩን ማውሳት በራሱ ቀባሪን የማርዳት ያክል ነው የሚሆነው። አንድ ሰው ስለሚላው፣ ስለሚጠጣውና ስለሚያርፍበት መጠሊያ ስፍራም የሚያሳስበው ነገር ከሌለ ባለቤት ከሌለው ከሜዳ አህያ የሚለየው በተፈጥሮ ብቻ ይሆናል። አንድ እውነት አለ ይኸውም: አንድ ከድህነት ወለል በታች ይኖር የነበረ ሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀድሞ በነበረው ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ይኖር ሳለ ያላየውን ሀብትና ንብረት ማፍራት ሲጀምር የቀድሞ ህይወቱን የዘነጋ እንደሆነ በቀላሉ የነበረውን ታላቅህን የማክበር ባህሪ፣ በሰዎች መካከል የነበረውን ፍቅርንና ይታይበት የነበረውን ትህትና በአጠቃላይ ፈሪሐ እግዚአብሔርን አጥቶ ሣር ቅጠሉ ሁላ "ምን አልክ አንተ? ..." እያለ ግዑዙን አካል ሳይቀር እያገላመጠ ከራሱ ጥላ እስከመጣላት ድረስ መሄዱ የማይቀር ነው።
ለመንደርደሪያ ያህል ይህን ካልኩ ዘንዳ በዛሬው ዕለት ላካፍላችሁ ወደ ወደድኩት ወደ ቅድመ ፍሬ ነገሬ/መልዕክት ሳልፍ ለጽሑፌ መነሻ የሆነኝን ነጥብ እንደሚከተለው በአጭሩ ላስቀምጥ። በዕረፍት እንዲሁም በአንዳንድ ጉዳዮች ምክንያት በአሜሪካ ጥቂት የማይባሉ ክፍለ ግዛቶች ለመዘዋወር ዕድሉ ገጥሞኝ በማደርጋቸው ጉብኝቶች ሁሉ በሄድኩበት ክፍለ ግዛት እናት ቤተ ክርስቲያኔን ጎራ ሳልል የተመለስኩበት ዕለት የለም። በጉብኝቴ ወቅትም በርካታ መጠሪያ ያላቸው አብያተ ክርስትያናት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት አገልጋዮችና ደቀ መዛሙርት እንዲሁም የምእመናን የልብ ትርታ ለማዳመጥ ችያለሁ። ታድያ በእነዚህ ሁሉ ቀናት ለመታዘብ እንደቻልኩ በሀገር ቤት የምትገኘውን "ቤተ ክርስትያን" የራሱ መልክና ገጽታ ያለው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተዘፍቃ እንደምትገኝ ሁሉ በውጭው ዓለም በተለይ በሰሜን አሜሪካ የምትገኘው "ጉባኤም" እንዲሁ ራሱ በቻለ ሌላ ገጽታ ያለው በቀላሉ የማይታለፍና ምናልባትም አሉ በማለት ልንዘረዝራቸው የምንችላቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ችግሮች ሁሉ እንደ ምንጭ ሊወሰድ የሚችል ትርጉሙ የጠፋበት "የቤተ ክርስቲያን" ምስረታ፣ በአገልጋዮች ካህናትና በምእመናን መካከል ያለውን መራራ ግኑኝነት እንደው ካህን እንደ ምጻተኛ፣ የእድር ዕቃ ያክልም ክብር የሌለውና በአንጻሩ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶች በገንዘባቸው ብዛት፣ በቀድሞ መንግሥት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በቀድሞ መጠሪያቸውና ማዕረጋቸው፣ በአስኳላው ሚዛን የሚደፉ ግለሰቦችም እንዲሁ ነን/አለን በሚሉት ሁሉ ፍጥጥ ባለ መልኩ እንደፈለጉ የሚሆኑበትን አሳዛኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁኔታ አንስተን በአጭሩ እንወያያለን።  

የጽሑፉ ውሱንነት:
ከፍ ሲል በጽሑፉ መግቢያ እንደተገለጸ የጽሑፉ ሙሉ ይዘት የሚያጠነጥነው በሰሜን አሜሪካ የሚገኙትን "አብያተ ክርስትያናት" በዋናነት እየታመሱበት ያለውን ችግር አንዱ ክፍል የሆነውን የሚያሳይና መፍትሔ ጠቋሚ ጽሑፍ ሲሆን በይዘቱ "የቦርድ" አባላት ተብለው ስለሚታወቁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የሌለው አንጃ የሚያትተውን ክፍል በተመለከተ ስለ አብላጫውን ተጻፈ እንጅ አንድስንኳ ለመልካም ነገር የሚበቃ ግለሰብ (ጡረተኛ) የለም የሚል አንድምታ የለውም። በተመሳሳይ ፀሐፊው በአገላለጻቸው ከሺሕ አንድ ልብ አውልቅ፣ አፈ ጮሌ፣ ወረበላ፣ መጋቢ መሳይ መንዳቢ ጠምጣሚም የለም የሚል እምነት የላቸውም። ካህን በሚለው ቃል ዙሪያ ላይ የሰፈረውን ሙሉ ሐተታም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ሥርዓተ ትምህርትና ትውፊት በጠበቀ መልኩ የተዘጋጀ ነው። በተረፈ ጽሑፉ ጥናት ላይ የተመረኮዘ ሚዛናዊ ሥራ እንደመሆኑ መጠን አንባቢ ሚዛንዎን ጠብቀው ያነቡ ዘንድም ይመከራል።
የጽሑፉ ዓላማ:
የጽሑፉ ዓላማ አንድና አንድ ነው ይኸውም: በቤተ ክርስትያን አከባቢ ለሚሆነው ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴና አሰራር ቅድሳት መጻሕፍት እንደሚያስተምሩት መንፈሳዊት በሆነችው ቤት መሆን ያለበትንና የሚገባውን አሰራር ለማስተዋወቅ ሲሆን በተጨማሪም በሺሕ ዘመናት የቤተ ክርስቲያን ዕድሜ በየትኛውም ዘመን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ምእመናን በካህናት ጫንቃ ላይ ወጥተው ካህናትን የማጎሳቀልና የማሳደድ ሰይጣናዊ ድርጊት አግባብ አለመሆኑን ለማሳወቅ ለትምህርትና ለተግሳጽ ተፃፈ።  
ሐተታ:
እንደ አለቃ ወልደ ኪዳኔ ፍቼ ካህን የሚለውን ቃል ተክህነ = አገለገለ ከሚለው ግሥ የተገኘ ሲሆን ካህን ማለት አገልጋይ ማለት ነው። በዋናነት የካህን አገልግሎት ለሰው ልጆች ሲሆን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር የሰጡና የቀደሱ ቅዱሳንን ማገልገል ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ ካህንን የእግዚአብሔር ባሪያ/አገልጋይ ተብሎ የሚገለጸው አንድ ሀብታም ሰው በገንዘቡ ሠራተኛ ቀጥሮ በተቀመጠበት የቀጠረውን ሰው (ሰራተኛውን) እባክህና አመሰግናለሁ በሌለበት በደረቁ እየተጣራ ወይንም ቃጭል እየጨቆነ "እስቲ የሚጠጣ ውኃ አቀብለኝ፣ ይህን ዕቃ ወደ መኪናዬን ጫንልኝ፣ ያንን አቀብለኝ፣ ይህን ደግሞ ከአጠገቤ አርቅልኝ …" ዓይነቱ ሳይሆን አንድ ካህን የእግዚአብሔር ባሪያ/አገልጋይ ተብሎ የሚገለጸው የእግዚአብሔር ሃሳብ/ፈቃድ የሚያስፈጽምና የሚደርግ ማለት እንጅ እግዚአብሔር እጁ አጥሮበት ውሃ የሚያቀብለው ሞግዚት ማለት እንዳይደለ ማወቁ መሰረታዊው የቃሉ ትርጓሜ እንዳንስተው ይረዳናል።
ችግር አይኖርም ማለት አይደለም ችግሮች ይኖራሉ። ነገር በመቆስቀስ ችግር መፍጠርና ሆነ ተብለው በስሌት የሚፈጠሩ/የተፈጠሩ ችግሮችም ሌላ መልክ እንዲይዙ በማድረግ ችግርን ማባባስ፣ ካህንን ማንሳፈፍና መውጫ መግቢያ ማሳጣት ግን ለበረከት አይሆንም። ካህናትን እንደ የእድር ዕቃ እየተቀባበልክ ማጎሳቀልና ማመሰቃቀል ምን አመጣው? ለምንስ ተፈለገ? የእድር ዕቃ እንኳን ክብር አለው። ምንም እንደ ራሳችን ንብረት ባንቆጥረውም የራሳችን ለሆነ ንብረት ያለን ጥንቃቄና እንክብካቤ ባናደርግለትም ፈርመን በተረከብንበት ሁኔታ ተጠቅመን በአግባቡ መመለስ ካልተቻለን አንድም ገዝተንም ሆነ የራሳችን ተክተን መመልስ ካልሆነ ደግሞ የእድሩ ሊቀ መንበር እስኪነግረን ድረስ የማይጠበቅብንን የገንዘብ ቅጣት ለመክፈል ራሳችንን አዘጋጅተን መሄድ እንደሚገባን እንዴት ዘነጋነው? አገር ስለ ቀየርን ብቻ ያደግንበትንና ያሳደገንን ባህል መርሳት ካላብን አገር መቀየር ሳያስፈልገን እዛው በሀገራችን ሳለን ለምንም የማይጠቅም ብዙ መርሳት የሚገቡን ነገሮች አሉ።
ሌላው በምዕራቡ ዓለም የምትገኘው "ቤተ ክርስቲያን" ትልቁ ፈተና መሄጃ ያጣ ደጃ አዝማች፣ በጡረታ የተገለለ ዶክተር፣ በወንጀል የሚፈለግ ጀኔራልና የቀድሞ መንግሥት የጦር መኮንኖች ቦርድ በሚሉት ፈሊጥ ስም መሸሸጊያ ዋሻ መሆንዋን ነው። በእርግጥ ይህን ዓይነቱ ችግር በሰሜን አሜሪካ ያለችውን "ቤተ ክርስቲያን" ብቻ ሳይሆን በሀገር ቤት የምትገኘውን "ቤተ ክርስቲያን" ጭምር ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል አንዱ ነው። የሚፈጥሩት ችግርና የሚያደርሱት የግፉም መጠን ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ። ያም ሆነ ይህ ግን እነዚህ የተጠቀሱት ዓይነት ሰዎች በቀድሞ ስማቸውና የሥራ ድርሻ ማዕረጋቸው እንዲሁም ካላቸው ሀብት የተነሳ "በምርጫም" ሆነ በሌላም መንገድ የሚቆናጠጡት በቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ጡረተኞች በወንበር ላይ ተቀምጠው አንተ እለፍ፣ አንተ ደግሞ አዝግም እያሉ "ትርፍ" ቀናቶቻቸው በካህን ዕንባና ሐዘን እየተዝናኑ እርጅናቸውን የሚረሱባትና ከቤት ወጥተው የሚገቡባት መዝናኛ ቤተ- አረጋውያን አይደለችም። አንድ ሰው በዕድሜው ገፍቶ ሲያበቃ ነገር ግን የነገር ፋይል ማገለባበጥ ያልጠገበና ያልወጣለት እንደሆነም ባይሆን ቤተ ክርስትያን አራራውን የሚወጣባት ቤት ሳትሆን ራሱን ለእግዚአብሔር በመስጠትና ለካህኑም መንፈሳዊ ሥልጣን በማስገዛት ከተጸናወተው/ከያዘው አጥፍቶ ጠፊ የሆነ ትልቅ በሽታ የሚፈወስባት ቤት ነበረች/ናት።
ኧረ ግፍ ነው! በካህናት ላይ እየሆነና እየተደረገ ያለው ግፍ ጽዋው መልቶ መፍሰሱ ነው። በቦርድ ስም ምእመናን በወንበር ላይ ተቀምጠው ካህናት ቁሞው የሚብጠለጠሉበት አሰራር ትክክል አይደለም። ያጠፋ በጥፋቱ አይጠየቅ እያልኩ አይደልም። የምንልህን ካልሰማህና ካላደረግ ተብሎ ነገር እየተፈለገባቸው ካህናትን የማሸማቀቅ እኩይ ተግባር ግን ከግፍም ሁሉ በላይ ግፍ ነው። ባይሆን:
         ካህን በረከታችሁ ነው፣
         ካህን የህይወት መሪያችሁ ነው፣
         ካህን መጋቢያችሁ ነው፣
         ካህን ሚስቱንና ልጆችሁን ጥሎ ከወደቃችሁበት ሥፍራ ድረስ ተገኝቶ እግዚአብሔር ይማርህ! ብሎ በህይወታችሁ ላይ የበረከት ቃል በመናገር የሚያጽናና ጠያቅያችሁም ነው፣
         ከምንም በላይም ካህን አገልጋያችሁ ነውና ከዚህ ቀደም የሆነውን ሁሉ ባለማወቅም ሆነ በድፍረት የተደረገ እንደሆነ ከእንግዲህ ወዲህ ግን አገልጋያችሁ የሆነውን ካህን መበደል በእናንተ ላይ አይሁኑባችሁ። ምናልባትም የካህን ህይወት/ኑሮ በምትጥልዋት ሳንቲም ላይ የተመሰረተ ይመስላችሁ እንደሆነም እምነታችሁ ስህተት ነው። የእግዚአብሔር ዓይኖች በፊቱ ይቆምና በቀደሰውም ጉባኤ ፊት ይሻገር ዘንድ በጠራው በባሪያው ህይወትና ቤት ናቸውና። 
በተጨማሪም በምእመን ዘንድ እንደ ተከታዮች በዋናነት የተዘነጋና መታወቅም የሚገባው ሌላ ዓብዪ ቁምነገር ቢኖር ቤተ ክርስትያን ሲባል ማንም እየተነሳ እንዲሁ "መብቴ ነው!" እያለ የፈለገውን የሚሆንባትና የሚፈነጭባት አለኝ ሲል አፉን ከፍቶ የሚዘባርቀውን ሁሉ የሚለማመድባት ቤት ሳትሆን ባለ ቤት ያላት የሥርዓት ቤት መሆንዋን ሊሰመርበት ይገባል። ሰው የቱንም ያክል ስም ቢያተርፍ/ቢኖረው፣ ቢማርና የብዙ ሀብት ባለቤት ቢሆን ለራሱ ነው። ሰው በሚያየውም ሁሉ የቱንም ያህል እጅግ የተትረፈረፈ ሀብት ቢኖረውም በቤተ ክርስትያን/በካህን ላይ ይሰለጥናል ማለት አይደለም። የቤተ ክርስቲያን ባለቤት፣ ካህንም የሚቀባ፣ የእውቀትና የሀብት ሁሉ ምንጭ የሆነው እግዚአብሔር ነውና።
ሰካራም ምንም ያህል ቤቱንና አከባቢውን እያተረማመሰ ቢመጣም ቀበሌ አከባቢ ሲደርስ አደብ ገዝቶ እንደሚያልፍ ሁሉ የሰላምና የዕረፍት ቤት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ነገር ከማይታጣበትና ከሞላባት የቀበሌ ያህል ክብርን ታጣለች? ካህኑስ ቢሆን እንዴት የአንድ የቀበሌ ሊቀ መንበር ክብር ይነፈገዋል? እንደ ብሉይ ኪዳይ አጥፊነታችንና አመጸኝነታችንን ለማሳየት ሰው የሚያየው፣ ፊታችንና መላ ሰውነታችን በለመጽ/በእባጭ መመታት አለበት? የእግዚአብሔር ምሕረትና ቸርነት እግዚአብሔር የለም! ያስብላል ወይ?   
ጽሑፌን ከማጠቃለሌ በፊት በድጋሚ አጽንዖት ሰጥቼ ላስተላልፈው የምፈልገው መልዕክት አለኝ። ይኸውም አሜሪካ በመኖር ብቻ የማይጠገን፣ ቁሳቁስ የማይደፍነው፣ የገንዘብ ብዛት የማይሞላው፣ ዕንቅልፍ ያሳጣህ ቀዳዳ የሚሞላ ቃል የሚመግብህ ሌላ ማንም ሳይሆን ስሙ ካህን ይባላል። ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ብትል ደግሞ መንፈሳዊ አስተዳደር በሙላት ያከናውን ዘንድም የተጠራ፣ የተቀባና የተሾመ ካህን/ናት ጥሪ ነው። የሚፈጠሩ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመቀመጥ መነጋገር መፍታት ይቻላል። በተረፈ ግን ያመጣናችሁ/የቀጠርናችሁ እኛ እስከሆን ድረስ እኛ የምንላችሁ ሁሉ ሳታቅማሙ እሺ ብላቹ ታዝዛችሁ "የምታገለግሉ" ከሆነ በሰላም ትኖራላችሁ ከዚህ ውጭ ከእኛም ቃልና ሃሳብ ያፈነገጠ አቋም ይዛችሁ አንዳች ነገር ለማድረግ የሞከራችሁ እንደሆነ ግን ወዮላችሁ! እየተባለ
         ካህናትን ማስፈራራት፣
         በካህናት ላይ አፍህ እንዳመጣልህ መናገር፣
         ካህናትን እንደ ፈለግህ መሾምና መሻር፣
         ለካህናት ተገቢ የሆነ ክብር አለመስጠት፣
         ካህናትን እንደ "...” ከፍ ዝቅ ማድረግ፣
         ካህናትን ማመናጨቅና ማገላመጥ፣
         በካህናት ላይ ክፉ ወሬ ማስወራት፣
         በካህናት ላይ ማሴር፣ ማመጽና ማሳመጽ፣ በአጠቃላይ የነፍስ ምግብ የሥጋም መርህ የሆነው ቃለ ወልደ እግዚአብሔር መጋቢያን የሆኑትን አገልጋዮች ካህናትን ተገቢ ባልሆነና ባልተገባ መንገድ መበደል፣ ካህንን ማስለቀስና አንገት ማስደፋት ያለማደግና በመንፈሳዊ ህይወትም አለመብሰል ውጤት እንጅ ጀብድነትም አይደለም። ለጊዜው ይመስለን እንደሆነም ነው እንጅ ቀኑ መምጣቱ የማይቀርለት ለተገፉ የጽድቅ ጸሐይ የወጣች ዕለት መቆሚያ ስፍራ መደበቂያ ዋሻም አይኖርም። በነፃነት አገር የሰውን ነጻነት መግፈፍና ሰላምን መንሳት ደግሞ ፈጽሞ ከመንፈሳዊ አሰራር የወጣ ብቻ ሳይሆን ድርጊቱ አረመኔነትም ጭምር ነው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
Atlanta, GA

2 comments:

  1. zare melkam neger new yasnebebken

    ReplyDelete
  2. It is wonderfull, Muluye!!! As usual. God Bless u.

    ReplyDelete