ጥር 2005
(አቶ ዳንኤል ክብረት
በተለመደ ስሙ ዳንኤል ክስረት የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን አዲስ መጽሐፍ አስመልክቶ በጻፈው መደዴ ጽኁፍ ያዘኑት ፕሮፌሰሩ የአላዋቂ ሳሚ ሌላ ነገር እንዳይለቀልቅ
ብለው በብሎጋቸው ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ መልስ ሰጪ የለም ብሎ የድፍረት ጽኁፍን እያስነበበን የዘለቀውን አቶ ዳንኤል ከቤተክህነት
ተንኮሉን እንጂ ሙያውን ስላልያዘ ፕሮፌሰሩ በትክክለኛ መጠሪያ ስሙ አቶ ዳንኤል ሲሉ ጠርተው ወዳጆቹ ባስቀመጡት ወንበር ላይ ሳይሆን
በሚመጥነው ወንበር ላይ አስቀምጠውታል፡፡ ምላሹ ተገቢም ወቅታዊም አስፈላጊም በመሆኑ አንባቢያን እንዲያነቡት እንጋብዛለን፡፡ መልካም
ንባብ)
አቶ ዳንኤል ለመናገርና ለመጻፍ ያለው ፍጥነት በሚናገርባቸው ጉዳዮች ላይ ካለው እውቀት ጋር አይመጣጠንም፤ እንዲያውም ያውቃል እንዲባል የሚጽፍ አንጂ አውቆ የሚጽፍ አይመስልም፤ አቶ ዳንኤል ሳላውቀው በጻፈው ላይ አስተያየት ስሰጥ ይህ ሁለተኛዬ ነው፤ ከዚህ በፊት በአንድ ጋዜጣ ላይ በጣም የታወቀውን የአየርላንድ ችጋር በ150 ዓመታት ያህል አቅርቦት በማየቴ አስተያየት ሰጥቼበት ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ስለመክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ በጻፈው ላይ አጭር አስተያየት ልስጥ፤ እንዲያው እንትንን እንትን ካላሉት ገብቶ ይፈተፍታል የሚባለውን በመከተል እንጂ ትርፍ ይኖረዋል ብዬ አልገምትም፤ ከደርግ ዘመን ጀምሮ የተለያዩ ካድሬዎች ደብተራዎችም ጭምር ማነብነብን እንደተናጋሪነት ሠልጥነውበታል፤ ስለዚህም ሰውም ማነብነባቸውን እንደእውቀት እየወሰደው ይወናበዳልና በጊዜው መልስ መስጠት ግዴታ ይመስለኛል፤ የሰው ልጅ በምን ይታፈራል? በወንበር፤ በወንበር አይደለም በከንፈር፤ ይባላል፡፡
ነገር ሳላበዛ ጥቂት ነጥቦችን በማንሣት የአቶ ዳንኤልን የማንበብ ችሎታና የተንኮል ክህነት ብቻ ለአንባቢዎች ላሳይ፤ ስለአስተያየቱ አስተያየት መስጠት አስፈላጊ አይደለም፡፡