ጋዜጠኛነት ሊያሟላቸው ከሚገቡ የሙያ ሥነ ምግባራት መካከል አንዱ ሚዛናዊነት ነው፡፡ ጋዜጠኛ ሰው እንደ መሆኑ ራሱ የሚደግፈው ወይም የሚቃወመው ሐሳብ ሊኖር ቢችልም፣ የግል አቋሙን በዘገባው ውስጥ ሊያካትት እንደማይገባው የሙያው ሥነ ምግባር ያስገነዝባል፡፡ ይሁን እንጂ በአገራችን የጋዜጠኛነት ሙያ ብዙ ጊዜ ሚዛናዊነትን ሲጠብቅ አይታይም፡፡ አንዳንድ ሚዛናዊ ዘገባ የሚያቀርቡና ለሙያቸው ታማኝ የሆኑ ጋዜጠኞች ባይጠፉም፣ ብዙዎች ግን የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ፍጹም ወገንተኛ የሆኑና የሙያውን ሥነ ምግባር የሚያፈርሱ ሆነው ይገኛሉ፡፡
በተለይም የነጻ ፕሬስ ውጤቶች የሆኑ ብዙዎቹ የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ነጻ ሆነው አለመገኘታቸውና እውነትን በሚዛናዊነት ከማቅረብ ይልቅ ወገንተኛነት የሚንጸባረቅባቸው መሆኑ የጋዜጠኛነትን ሙያ እጅግ እየጎዳው ነው፡፡ በዚህ አገር ነጻ ፕሬስ ማለትም መንግሥትን ወይም የታላላቅ ሃይማኖታውያን ተቋማት መሪዎችን በመቃወም መዘገብ ተደርጎ እየተወሰደ መሆኑ ሌላው የተዛባ የነጻ ፕሬስ አካሄድ ሆኗል፡፡ መንግሥትንም ሆነ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችን በተገቢው መንገድ ተችቶ መጻፍ አግባብነት ያለው አይደለም እያልኩ አይደለም፤ ነገር ግን ከጭፍን ጥላቻና ከጭፍን ድጋፍ የጸዳ ዘገባ ሊቀርብ ይገባል ነው ክርክሬ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግል ፕሬሶችን ሰፊ ሽፋን ይዘው የሚገኙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የሚወጡ ዘገባዎች ናቸው፡፡ ለዜና ፍጆታ የሚውል ጉዳይ ከተገኘ መዘገቡ ትክክል ነው፡፡ በአዘጋገቡ ሁኔታ ግን በአብዛኛው የአንድን ወገን ሐሳብ ብቻ ደግፎና ሌላውን ተቃውሞ የመዘገብ ሁኔታ ነው የሚስተዋለው፡፡ ሚዛናዊት የሚባል የጋዜጠኛነት ሥነ ምግባር የሌለ እስኪመስል ድረስ፣ በጭፍን አንዱን ጻድቅ ሌላውን ኃጥእ፣ አንዱን ትክክል ሌላውን የተሳሳተ፣ አንዱን ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ፣ ሌላውን ቤተ ክርስቲያን አፍራሽ፣ አንዱን ሃይማኖተኛ፣ ሌላውን መናፍቅ ብሎ የመፈረጁ አደገኛ አካሄድ ብዙ እያስተዛዘበ ይገኛል፡፡ ይህ የጋዜጠኛነትን ሙያ በእጅጉ እየተፈታተነ ያለ አደገኛ አካሄድ ነው ብዬም አስባለሁ፡፡