Monday, January 28, 2013

የዳንኤል ክብረት ክሽፈት


ጥር 2005
(አቶ ዳንኤል ክብረት በተለመደ ስሙ ዳንኤል ክስረት የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን አዲስ መጽሐፍ አስመልክቶ በጻፈው መደዴ ጽኁፍ ያዘኑት ፕሮፌሰሩ የአላዋቂ ሳሚ ሌላ ነገር እንዳይለቀልቅ ብለው በብሎጋቸው ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ መልስ ሰጪ የለም ብሎ የድፍረት ጽኁፍን እያስነበበን የዘለቀውን አቶ ዳንኤል ከቤተክህነት ተንኮሉን እንጂ ሙያውን ስላልያዘ ፕሮፌሰሩ በትክክለኛ መጠሪያ ስሙ አቶ ዳንኤል ሲሉ ጠርተው ወዳጆቹ ባስቀመጡት ወንበር ላይ ሳይሆን በሚመጥነው ወንበር ላይ አስቀምጠውታል፡፡ ምላሹ ተገቢም ወቅታዊም አስፈላጊም በመሆኑ አንባቢያን እንዲያነቡት እንጋብዛለን፡፡ መልካም ንባብ)

አቶ ዳንኤል ለመናገርና ለመጻፍ ያለው ፍጥነት በሚናገርባቸው ጉዳዮች ላይ ካለው እውቀት ጋር አይመጣጠንም፤ እንዲያውም ያውቃል እንዲባል የሚጽፍ አንጂ አውቆ የሚጽፍ አይመስልም፤ አቶ ዳንኤል ሳላውቀው በጻፈው ላይ አስተያየት ስሰጥ ይህ ሁለተኛዬ ነው፤ ከዚህ በፊት በአንድ ጋዜጣ ላይ በጣም የታወቀውን የአየርላንድ ችጋር 150 ዓመታት ያህል አቅርቦት በማየቴ አስተያየት ሰጥቼበት ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ስለመክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ በጻፈው ላይ አጭር አስተያየት ልስጥ፤ እንዲያው እንትንን እንትን ካላሉት ገብቶ ይፈተፍታል የሚባለውን በመከተል እንጂ ትርፍ ይኖረዋል ብዬ አልገምትም፤ ከደርግ ዘመን ጀምሮ የተለያዩ ካድሬዎች ደብተራዎችም ጭምር ማነብነብን እንደተናጋሪነት ሠልጥነውበታል፤ ስለዚህም ሰውም ማነብነባቸውን እንደእውቀት እየወሰደው ይወናበዳልና በጊዜው መልስ መስጠት ግዴታ ይመስለኛል፤ የሰው ልጅ በምን ይታፈራል? በወንበር፤ በወንበር አይደለም በከንፈር፤ ይባላል፡፡
ነገር ሳላበዛ ጥቂት ነጥቦችን በማንሣት የአቶ ዳንኤልን የማንበብ ችሎታና የተንኮል ክህነት ብቻ ለአንባቢዎች ላሳይ፤ ስለአስተያየቱ አስተያየት መስጠት አስፈላጊ አይደለም፡፡

አንደኛ ደጋግሜ እንብቤዋለሁ ይላል፤ ይህንን ባይነግረን ጥሩ ነበር፤ በመናገሩ ብቻ እንዳናምነው ማስረጃ ይሰጠናል፤ ያላነበበውን ደጋግሜ አንብቤዋለሁ ማለት ያስፈለገበት አስገዳጅ ምክንያት ምንድን ነው? አውቃለሁ ብሎ በመነሣት ለማሞኘት ወይም ለማታለል ካልሆነ በቀር ሌላ ምክንያት ያለ አይመስለኝም፤ እንደአቶ ዳንኤል ያለውን ለማስጠንቀቅ ደጋግሜ አነበብሁት በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ‹‹የዩኒቨርሲቲን ዓለም የማያውቁ ሰዎች ሌላ ትርጉም በመስጠት እንዳይሳሳቱ ማስጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ በአካል በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሆነው ልባቸው ከደብተራ ተንኮል ላልጸዳም ቀናውን የእውነት መንገድ እንዲያመለክታቸው እመኛለሁ፤›› የሚል ተጽፎ ነበር፤ ይህንን አቶ ዳንኤል አላነበበውም፤ ካነበበውም አልገባውም፡፡
ሁለተኛ ‹‹ለመሆኑ ታሪክ ይከሽፋል? የክሽፈት ታሪክ ሊኖር ይችላል እንጂ የከሸፈ ታሪክ ሊኖር ይችላል? የስኬት ታሪክ ይኖራል እንጂ የተሳካ ታሪክ ይኖራል? አንድን ታሪክ ከሽፏል ወይም ተሳክቷል የሚያሰኘው ምን ምን ሲሆን ነው? … በመጽሐፉ የምናጣው ታላቁ ነገር ይሄ ነው፤›› በዚህ ትርጉም የማይሰጥ የቃላት ድርደራ ላይ ምንም አስተያየት መስጠት አይጠበቅብኝም፤ ይቀጥልና ‹‹.. የታሪክን ክሽፈትና ስኬት መበየኛ ነገሮችን አስቀድመው በማሳየት አንድ ታሪክ ከሸፈ ወይም ተሳካ የሚያሰኙትን መመዘኛዎች …›› ይላል አቶ ዳንኤል፤ ካላነበበውደጋግሜ አንብቤዋለሁበማለት ብቻ ጭንቅላቱ ውስጥ አይታተምለትም፤ የሚከተለው እንደሚነበብ ሆኖ የተጻፈ ነበር፤ ‹‹መክሸፍ የምለው አንድ የተጀመረ ነገር ሳይጠናቀቅ ወይም ሳይሳካ እንቅፋት ገጥሞት መቀጠል ሳይችል ዓላማው ሲደናቀፍና በፊት ከነበረበት ምንም ያህል ወደፊት ሳይራመድ መቅረቱን ነው፤›› ይህ ተጽፎአል! አላነበበውም፤ ካነበበውም አልገባውም፡
ሦስተኛ፤ ‹‹ታሪክ ጸሐፊዎቹን ከታሪኩ ጋር አብሮ መውቀጥ ከተልባ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ ዓይነት ይሆናል››! ይላል፤ ይህ ሰው አንብቤአለሁ፤ አውቃለሁ፤ ሲል በመሃይም ድፍረት ነው፤ የሚከተለው ተጽፎአል፤ ‹‹አንድ ሰው በአገርና በሕዝብ ጉዳይ ላይ ከጻፈ ‹‹ማንም ዜጋ በጉዳዩ ላይ የመሳተፍና ሀሰቡን በሙሉ ነጻነት የመስጠት መብት አለው፤ አለዚያ በየጓዳችን በሐሜት ብቻ እየተዘላዘልን እውነትን አንጥሮ በአደባባይ የማውጣቱን ዘዴ ሳንማር ሌላ ሦስት ሺህ ዓመታት እንቀጥላለን፤›› ይህንን አላነበበውም፤ ካነበበውም አልገባውም፡፡
አራተኛ በራሱ ላይ ሲፈርድ ቶሎ ሳይጽፍ መቆየቱን ለማስረዳት ምናልባት ከእሱ የተሻለ ሰው ቢጽፍ፣ ምናልባት ፕሮፌሰር ባሕሩ ቢጽፍ፣ ምናልባት የታሪክ ሊቃውንትቱ ተማሪዎች ቢጽፉ፣ ምናልባት የታሪክ ክፍሉ ቢጽፍ በማለት ጠብቆ እንደነበረ ይገልጻል፤ እነዚህ ሁሉ የሱን ምኞት እሱ በፈለገው ፍጥነት ሳያሙዋሉለት ቀሩና እነፕሮፌሰር ባሕሩን ላጨበት ሥራ ራሱንአቀረበ፤ የሱ ድፍረት የሌሎቹን እውቀት የሚበልጥ ለማስመሰል ጻፈ፤ ድፍረቱን ልናደንቅለት ይገባል፤ በማያውቁት ጉዳይ ደረትን ገልብጦ በሙሉ እምነት ማነብነብ የካድሬዎች ባሕርይ ሆኖ በቤተ እግዚአብሔርም ገብቶአል፡፡

አምስተኛ አቶ ዳንኤል ከአዋቂነት ወደመንፈሳዊነት ይሸጋገርና ‹‹አንድን አካል መልስ ለመስጠት በማይችልበት ጊዜና ሁኔታ መሄስና መውቀስ ከሞራል አንጻር ፍትሐዊ አይሆንም፤ የሀገሬ ሰውሙት ወቃሽ አትሁን››› እዚህ ደግሞ ጭራሽ ሊወጣበት ከማይችለው የአለማወቅ ማጥ ውስጥ በድፍረት ገባ! ‹‹ሞራል›› ስለሚለው ነገር ምንም እንደማያውቅ ሳያውቅ አወጀ፤ ድፍረት ብቻውን በምንም መንገድ እውቀት አይሆንም፤ ለመራቀቅ ፈልጎ ራሱን በአለማወቅ አዘቅት ውስጥ ከተተ፡፡
ስድስተኛ፤ በጽሑፉ መደምደሚያ ላይ የደብተራ ተንኮል አፈትልኮ ይወጣል፤ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ያነሣና በደብተራ ተንኮል አንዱን ‹‹ዶክተር›› የሚለውን መልክ የሌለውና ስም የሌለው የደብተራ ምሥጢር ያደርግና፤ ‹‹እኒህ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ዶክተር ወደመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘንድ በማን በኩል እንደሄዱ ፕሮፌሰር መስፍን ያውቃሉ፤›› ብሎ ይለጥፍብኛል፤ እግዚአብሔር ያሳያችሁ ስሙን ያልጠቀሰውንና የማላውቀውን ሰው የእኔን ስም ጠርቶ እንደማውቀው አድርጎ ሌላ ስሙን ያልጠቀሰውንና እኔ የማላውቀው ‹‹ዶክተር›› ወደመንግሥቱ ያቀረበ እያለ ውሸት ሲያጠነጥንና ሲፈትል ጊዜ ያጠፋበት ምክንያት አልገባኝም፤ ተንኮሉ እዚህ ላይ አያበቃም፤ ታደሰ ታምራትን ‹‹መንግሥቱ ከመሸኘቱ በፊት ግንከዶክተር እገሌ ጋር ቅሬታ አላችሁ መሰል፤ አንዳንድ ነገር ነግሮኝ ነበር፤ እዚያው ተነጋግራችሁ ፍቱት፤ አላቸው፤›› ይልና የመጨረሻዋን የደብተራ ተንኮል ጣል አድርጎ ይደመድማል፤አሁን እዚህ መጽሐፍ ላይ ቤተ መንግሥቱን አየሁት፡፡›› ምን እንዳየ፣ የት እንዳየ፣ ምንና ምን እንደተገናኘ የደብተራ ምስጢር ነው፤ ያቀረበውን ሁሉ የማን ባለሙዋል ሆኖ ያገኘው እንደሆነም አይናገርም፤ እንዲህ ያለ ሞላጫነት! ስለእውቀት ከተጻፈ መጽሐፍ ተነሥቶ ወደመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጓዳ ገብቶ፣ ስሙ የማይጠራ ዶክተርን መነሻ አድርጎ፣ ይህን ሁሉ እኔ እንደማውቅ ተናግሮ በድንቁርና ምርጊት ይደፍነዋል! እንዲህ ያለ ሰው ስለእውቀት ለማውራት ለምን ይነሣል? ከበሽታ በቀር ምን ሌላ ይገፋፋዋል?

No comments:

Post a Comment