Monday, February 27, 2012

Tuesday, July 26, 2011 ማህበረ ቅዱሳንን ለመምራት የሚሞክር ሥውር አመራር አለ። (ዲ. ዳንኤል ክብረት) - - -

July 26, 2011



(ደጀ ሰላም፤ ጁላይ 26/2011/ READ IN PDF)ዕንቍየተባለ መጽሔት የማ/ቅዱሳን ዋና ፀሐፊ መምህር ሙሉጌታ ኃ/ማርያምን ባነጋገረበት እትሙ ስሙ ያለአግባብ መነሣቱን በመጥቀስ ጉዳዩን ግልጽ ለማድረግ መልስ መስጠቱን ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በተለይ ለደጀ ሰላም በላከው ደብዳቤ አስታውቋል።   ዕንቁ መጽሔት ከማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ማውጣታችሁ ይታወሳል፡፡ በቃለ መጠይቁ ውስጥ ስማቸው ከተነሡት አካላት አንዱ በመሆኔ ለጉዳዩ ያለኝን የተለየ ሃሳብ በማውጣት እንድትተባበሩኝ እጠይቃለሁያለው ዲ/ን ዳንኤል ዋና ፀሐፊው መምህር ሙሉጌታ ላነሧቸው ነጥቦች የግሉን አስተያየት ከመስጠቱም በላይ እርሱ ከማ/ቅዱሳን አመራር ጋር አለኝ ስላለው አለመግባባት በሰፊው ማብራሪያ አስፍሯል። ደጀ ሰላም ዕንቍመጽሔት ላይ የወጣውን ቃለ ምልልስ ለደጀ ሰላማውያን እንዳቀረበችው ሁሉ አሁንም ዲ/ን ዳንኤል ለጉዳዩ ያለውን የተለየ ሐሳብታቀርባለች።


መምህር ሙሉጌታ ኃ/ማርያም ከላይ ለተጠቀሰው መጽሔት በሰጡትና በዓይነቱ ለየት ባለው ቃለ ምልልሳቸው ውይይት የሚጋብዙ ቁምነገሮችን የጠቀሱ ሲሆን እውነቱን ለመናገር አብዛኞቹ የማህበረ ቅዱሳን አባሎች የኢሕአዴግ ደጋፊና አባላት ናቸው በሚለው ጥቅል ሐሳባቸው ብዙዎች ግር መሰኘታቸውን፣ አንዳንዶችም ይቅርታ ይጠይቁማለት መጀመራቸው ታውቋል። በቃለ ምልልሱ ከማኅበሩ ቋሚ ሠራተኝነት በመልቀቅ በትርፍ ጊዜው ብቻ በማገልገል ላይ የሚገኘው ዲ/ን ዳንኤል ክብረትን በተመለከተ ተጠይቀው በሰጡት መልስ አነስተኛነት ብቻ ሳይሆን ትክክለኛነት ቅሬታ አለን ያሉ አባላት ጉዳዩን በማንሳት ዋና ፀሐፊውን የሞገቱ ሲሆን በስም የተጠቀሰው /ን ዳንኤልም በፌስቡክ ገፁ ቅሬታውን ገልጾ አንብበነዋል።

/ን ዳንኤል እርምት የሚያስፈልገው መግለጫባለውና ጁላይ 4/2011 በለጠፈው አጭር ማሳሰቢያው የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ መምህር ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም በዕንቁ መጽሔት ላይ ስለ ማኅበሩ የተናገራቸው አብዛኞቹ ነገሮች መልካም ቢሆኑም፣ እኔን እና ቀሲስ ሰሎሞንን በተመለከተ የሰጠው መግለጫ ግን የማኅበሩንም የክርስትናንም ሕግጋት የጣሰ ነው፡፡  ከዚህም በላይ «አብዛኞቹ የማኅበሩ አባላት የኢሕአዴግ አባላት እና ደጋፊዎች ናቸው» ያለበትም ምክንያት ምንም ማረጃ እና መረጃ የሌለው ነው፡፡ እስካሁን በማኅበረ ቅዱሳን ታሪክ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የተሰጠ፣ የአባላቱን ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚገልጥ የመጀመርያው መግለጫ ነው፡፡ እኔ በግሌ ይህንን እቃወማለሁ፡፡ ነገ ደግሞ ሌላው አመራር ተነሥቶ «የቅንጅት አባላት እና ደጋፊዎች ናቸው» ከማለቱ በፊት እርምት ያስፈልገዋል፡፡”  ማለቱን አንብበናል።
እርሱን ተከትሎ 66 አስተያየቶች የተነበቡ ሲሆን ገሚሶቹ በድጋፍ ገሚሶቹም በተቃውሞ የሚመስላቸውን ጽፈዋል። የማ/ቅዱሳን አባላት የሆኑ ብቻ ሳይሆን አባላት አይደለንም ያሉም ጉዳዩን አስመልክቶ የሚሰማቸውን አካፍለዋል። ጉዳዩ በዚያው ሳይቋጭ ሰንብቶ አሁን ደግሞ ዲ/ን ዳንኤል አዘጋጅተው በላኩት በዚህ ሰፋ ያለ ጽሑፍ አንድ እርምጃ ወደፊት ገፍቷል።

ቀደም በሚለው የቃለ ምልልሱ ክፍል መጽሔቱ ማኅበረ ቅዱሳን ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያው ዋና ሓላፊ ጋራ ስላለበት ችግር ጠይቀው ማኅበሩ ከአባ ሰረቀ ጋራ ችግር የገጠመው ከጅምሩ (1998 .) አንሥቶ መሆኑን ዋና ጸሐፊው በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ አያይዞም ለማኅበሩ አገልጋዮች የውጭ ተልእኮ (ለምሳሌ፡- ዋና ሓላፊው በአሜሪካ ለሚካሄድ ጠቅላላ ጉባኤ ደብዳቤ እንዲጽፉ ሲጠየቁ እዚያ ራሱን ስደተኛው ሲኖዶስ እያለ ከሚጠራው ጋራ አብራችሁ እንደምትሠሩ መረጃዎች ያሳያሉእያሉ በመክሰስ) ዕንቅፋት መፍጠራቸው ተወስቷል፡፡


ለዚህም አባ ሰረቀ ራሳቸው ገለልተኛየሚባል ቤተ ክርስቲያን ማቋቋማቸው እንደተነገራቸው ያወሳው ዋና ጸሐፊው በውጭ የማኅበሩ አባላት በስደተኛው ሲኖዶስእንመራለን በሚሉቱ ደጋፊዎች የአቡነ ጳውሎስ ካድሬእየተባሉ በፖሊስ መባረራቸውን አትቷል፡፡ መስከረም 12 ቀን 2002 .ም የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተው በማኅበሩ ላይ የሙሉ ቀን ስብሰባ እስከማካሄድ ድረስ አባ ሰረቀ ከ1998 .ም ጀምሮ በ1999፣ በ2000 እና 2001 .ማኅበሩ በአስተዳደርና በፖሊቲካ ጣልቃ ገብቷል በሚል ማኅበሩን በጥፋተኝነት ለማስወገዝ፣ የውጭ ድርጅቶችንና ተቋማትን ደግሞ ይግቡበማለት የሚያበረታታ ከፍተኛ ዘመቻ አጠናክረው ማካሄዳቸውን አስረድቷል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በየስድስት ወሩ የሥራ አፈጻጸም፣ በየዓመቱ የኦዲት ሪፖርት ለመምሪያው እየላከ ጥሩ ግንኙነት መሥርቶ በቆየበት ሁኔታ አሁን የሚታየው የመምሪያው ሓላፊ የስም ማጥፋት ፕሮፓጋንዳ ማኅበረ ቅዱሳንን በተሳሳተ መረጃ ለመግፋትና ለማጥፋት ያላቸው ዓላማ ዋነኛ መገለጫ ተደርጎ እንደሚወሰድ መ/ር ሙሉጌታ ጠቁመዋል፡፡
++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ለደጀ ሰላም የጡመራ መድረክ
ባሉበት

ጉዳዩ፡- መልስ መስጠትን ይመለከታል፡፡

ዕንቁ መጽሔት ከማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ማውጣታችሁ ይታወሳል፡፡ በቃለ መጠይቁ ውስጥ ስማቸው ከተነሡት አካላት አንዱ በመሆኔ ለጉዳዩ ያለኝን የተለየ ሃሳብ በማውጣት እንድትተባበሩኝ እጠይቃለሁ፡፡ ከዚህ ደብዳቤ ጋር፦
1.   እኔን በተመለከተ ለተነሡት ጉዳዮች በግል፣
2.   ማኅበሩን በተመለከተ ለተነሡት ጉዳዮች እንደ አባልነት ሃሳብ አቅርቤያለሁ።
ለማንኛውም አክሽን ሪ አክሽን አለውና፡፡

ግልባጭ
·    ለሥራ አመራር ጉባኤ፣
·    ለሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ፣
·    ለኦዲት እና ኢንስፔክሽን አገልግሎት፣
·    ለዕንቁ መጽሔት ዝግጅት ክፍል፣
++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ከአመራሩ ጋር ልዩነቶቻችን ምንድን ናቸው?

(/ን ዳንኤል ክብረት)፦ መምህር ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም የእኔ እና የማኅበረ ቅዱሳንን ጉዳይ በተመለከተ የሰነዘረው ሃሳብ አለ፡፡ የእውነታም፣ የአካሄድም ችግር ያለበት ሀሳብ ነው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ አያሌ ሚዲያዎች በእኔ እና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል” ... “ተፈጠረስለሚሉት ችግር አንስተውብኝ ያውቃሉ፡፡ በእኔ እምነት ይህ ጉዳይ የማኅበር የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ከማኅበሩ አባላት ጋር ብቻ የምንነጋገረው እንጂ ለማኅበረሰብ ለገበያ የሚቀርብ ባለመሆኑ እንዲያነሡት አልፈቅድም ነበር፡፡ አሁን ግን መምህር ሙሉጌታ የውስጡን ጉዳይ ወደ ውጭ አወጣው፡፡ ያውም በፕሬስ ላይ፡፡ ስለዚህም የፕሬስን ጉዳይ በፕሬስ መልስ መስጠት የተለመደም የሚገባም አሠራር በመሆኑ በጉዳዮች ላይ ማብራርያ ልሰጥበት ግድ አለኝ፡፡

ቅድመ ነገር
መምህር ሙሉጌታ ስለ እኔ የተናገረውን ሳነበው እውነት ይህንን ስለ ዳንኤል ተናግሮታልን? ብዬ ራሴን ጠይቄአለሁ፡፡ ቢቻል ባይናገር፤ ከተናገረም እንዲህ ባይናገር መልካም ነበር፡፡ ሰው ጥላቸውን በሦስት መንገድ ይገልጣል፡፡ ስለሚጠላው ሰው ክፉ በመናገር፣ ስለሚጠላው ሰው የሚያውቀውን መልካም ነገር ባለመናገር እና ስለሚጠላው ሰው ተራ ነገር በመናገር፡፡

ስለ ቀሲስ ሰሎሞን ሲናገር የአመራር አባልእንደነበር የተናገረው መምህር ሙሉጌታ እኔ የት ላይ እንዳገለገልኩ እንኳን ለመናገር አልደፈረም፡፡ በመካከል ያነሳት የልማት ተቋማትን እንኳን በልማት ሥራዎች ላይ ተመድቦበማለት ነበር የገለጠው፡፡ ሙሌ ረስተኸው ይሆናል እንጂ የልማት ተቋማት ማናጂንግ ዳይሬክተር ሆነው እንዲያገለግሉየሚለውን ደብዳቤ የጻፍከው አንተው ነበርክ።

ይህ ሁኔታ የማኅበሩ የመጀመርያ ጆርናል ምረቃ በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ሲከናወን የተፈጸመውን እንዳስታውሰው አድርጎኛል፡፡ ዳንኤል በማኅበሩ የነበረውን ቦታ ሆን ብሎ አለመጥቀስ በሥውሩ አመራር ዘንድ እንደ ስትራቴጂ መያዙን አውቃለሁ፡፡ ይህንንም የኢንተር ኮንቲኔንታል ክስተት እና የመምህር ሙሉጌታ መግለጫዎች አጠናክረውልኛል፡፡ ለዚህም ነው የሙሉጌታ ሃሳቦች ድንገቴ አይደሉም ታስቦባቸው፣ ተመክሮባቸው የተሰጡ ናቸው ያልኩት፡፡

የሥራ አመራር ጉባኤው በአመራሩ እና በእኔ መካከል ያለውን ልዩነት ለመነጋገር በደብዳቤ ጠርቶኝ፣ በጉዳዮቹ ላይ ተወያይተን፣ ኮሚቴ አቋቁሞ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ያ ውይይት የተጠራው በጥቂት ወንድሞች ግፊት እና በወቅታዊ ሁኔታዎች አስገዳጅነት ቢሆንም፡፡ ኮሚቴው አጥንቶ የደረሰበትንም ማቅረቡን አውቃለሁ፡፡ አመራሩ ግን ችግሮች እንዲፈቱ ስለማይፈልግ ነገ ዛሬ እያለ የውኃ ሽታ አደረገው እንጂ፡፡

ይህንን በኮሚቴ የተያዘ ጉዳይ ወደ ውጭ አውጥቶ የሕዝብ መወያያ ማድረግ የአንድ ዋና ጸሐፊ የመጀመርያ ስሕተት ነው፡፡ ከተነገረም አመራሩ የሄደበትን መንገድ መግ ለጥና ነገሮች አሁን ያሉበትን ሁኔታ መጨመር ነበረበት፡፡  ማኅበረ ቅዱሳን አባላቱን በተመለከተ ያላቸውን የሃሳብ ልዩነት በዚህ መልኩ ለአደባባይ እየሸጠ የሚያገኘው ትርፍ ምንድን ነው? አሁን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ከተጋረጠው አደጋ አንፃርስ ልዩነቶቹን አቻችሎ ለበለጠው ዓላማ የሚጓዝበት ጊዜ ነው ወይስ የአባላቱን የልዩነት ሃሳብ ወደ አደባባይ የሚያወጣበት? መልሱን መምህር ሙሉጌታ እና ሥውሩ አመራር ብቻ ያውቁታል፡፡

ማኅበሩ በአሁኑ ጊዜ ከውጭም ከውስጥም ከፍተኛ ጫናዎች አሉበት፡፡ ምንም እንኳን ለጫናዎቹ መፈጠር ዋነኛው ምክንያት ራሱ ቢሆንም፡፡ እነዚህን ጫናዎች ተቋቁሞ፣ ብሎም ረትቶ ለማለፍ ከሚያስፈልጉት ነገሮች ደግሞ ውሳጣዊ የመንፈስ አን ድነት እና ዝግጁነት ናቸው፡፡ ይህንን በመፍጠር ረገድ ከመሥራት ይልቅ አመራሩ ልዩነቶችን ማስፋት፣ አባላቱን ማስከፋት እና ጭር ሲል አለመውደድን እንደ ስትራቴጂ መያዙን ይህ የዋና ጸሐፊው መግለጫ ያሳያል፡፡

አውላላ ሜዳ ላይ የተኛውን በሬ፣
ነካክተው ነካክተው አደረጉት አውሬ። እንደተባለው፡፡ አባላቱ የሚሰጡት ምላሽ ዋና ጸሐፊው ከገለጠው የባሰ እንደሚሆን ቀድሞ ማሰብ ለምን አልተቻለም?

ስሕተት ሁለት
እኔ ከማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ አገልጋይነትም ሆነ ከአመራርነት ራሴን ያገለልኩት መምህር ሙሉጌታ እንዳለው በልማት ሥራዎች ላይ ተመድቤ ስሠራ በተፈጠረ ድክመት አይደለም፡፡ በእኔ እና በአመራሩ መካከል የአመለካከት ልዩነት ስለተፈጠረ፤ ይህንንም ልዩነት ተነጋግሮ ለመግባባት አመራሩ እምቢ ስላለ ነው፡፡

ይህ የዋና ጸሐፊው ገለጻ ሆን ተብሎ ነገሮችን ለመሸፋፈን ወይንም አዲስ ታሪክ ለመፍጠር የተደረገ ነው፡፡ የልማት ተቋማቱ ጉዳይ የመጨረሻው ክስተት ነው፡፡ የኢትዮጵያን አብዮት የመጨረሻ ክስተት ሆኖ ያስነሣው የወሎ ረሃብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አብዮት ግን የወሎ ረሃብ ውጤት አይደለም፡፡ የሕዝቡ የዘመናት ብሶት ውጤት እንጂ፡፡

ባለፈው ጊዜ ከማኅበሩ አመራር ጋር ስንወያይ የማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢ የሆነው አቶ ታደሰ አሰፋ እንዳቀረበው እኔ ከአመራርነትም ሆነ ከመደበኛ አገልጋይነት ስለቅቅ በማኅበሩ አመራር ላይ ያለኝን የአካሄድ ችግር ዘርዝሬ አቅርቤያለሁ፡፡ ከዚያ በኋላም ቢሆን የኦዲት እና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ኃላፊዎች ሲያናግሩኝ በተጠናከረ መልኩ ገልጫቸዋለሁ፡፡

እኔ ከማኅበረ ቅዱሳን ዓላማ ጋር ልዩነት የለኝም፡፡ ከማኅበሩ አመራር ጋር ግን ልዩነቶች አሉኝ፡፡ ልዩነቶችንም ዘርዝሬ ገልጫለሁ፡፡ አሁንም የግድ እንዳብራራ ተገፍቻለሁና እንደ ሚከተለው አራቱን ብቻ እገልጣቸዋለሁ፡፡

ልዩነት አንድ
ማኅበሩ ስትራቴጂክ አመራር የለውም፡፡

የማኅበሩ አመራር የዕለት ተዕለት ነገሮችን ለማየት የሚሰባሰብ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱም በቂ መረጃ የሌለው ነው፡፡ ቤተ ክህነቱን በተመለከተ የተጠራቀመ፣ የተተነተነ፣ የተብራራ እና ፕሮፋይል ያለው መረጃ የለውም፡፡ የራሱን የማኅበሩን ኅትመቶች እንኳን አያነብም፡፡ የዋና ጸሐፊውን ቃለ መጠይቅ እንኳን ብዙዎቹ የአመራር አባላት ያነበቡት እባካችሁ አንብቡ እየተባለ ተደውሎላቸው ነው። አቡነ እገሌን አናግሬያቸው ከሚል ያለፈ የመረጃ መሰብሰቢያ መንገድም ሃሳብም የለውም፡፡ የማኅበሩ ጉዞ ቤተ ክርስቲያኒቱን የት ለማድረስ እንደ ሆነ ግልጽ ግብ የለውም፡፡

የማኅበሩ የአመራር አካላት ወደ ሁለት እርከን ሲሸጋገር አንድ ዋነኛ መሠረተ ሃሳብ ነበረ፡፡ የፖሊሲን ሥራዎች ከአፈጻጸም ሥራዎች ለመለየት፡፡ የሥራ አመራሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን እና ማኅበሩን የተመለከቱ የፖሊሲ፣ የሃሳብ እና የርእዮት ጉዳዮችን እንዲያይ ለማስቻል ነበር፡፡ የሥራ አመራሩን ያለፉ ሦስት ዓመታት ቃለ ጉባኤያት ብናያቸው ብቻ ይህ አለመሆኑን እናያለን፡፡ የሥራ አመራሩ የማኅበሩ የፖሊሲ አውጭ አመራር መሆን አልቻለም፡፡ በሥራ አስፈጻሚው ሊሠሩ የሚችሉ፣ ሌላው ቀርቶ በዋና ጸሐፊው ብቻ ሊያልቁ የሚችሉ ጉዳዮችን የሥራ አመራሩ ወራት በፈጀ ስብሰባ ሲያያቸው እናገኛለን፡፡

አዲስ ያዘጋጀውን የሥልጣን እና የሥራ ዝርዝር ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ ለአመራሩ፣ ለአስፈጻሚው እና ለክፍሎች የተዘጋጀው ይህ መመርያ ምን ያህል አመራሩ የአስፈጻሚው ተግባር ውስጥ እንደገባ ያሳየናል፡፡

ለምሳሌ የሥራ አመራሩ ስለ መደበኛ አገልጋዮች የደመወዝ እና አበል አወሳሰን ፖሊሲ ማዘጋጀት ሲገባው የሥራ አስፈጻሚውን ሥራ ወስዶ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ በመግባቱ ከመደበኛ አገልጋዮች ጋር ቅራኔ ውስጥ እንዲገባ እና ይግባኝ ሰሚ እንዲጠፋ አድርጎታል፡፡ የኅትመት ፖሊሲን ማውጣት የነበረበት አመራር አንድን ልዩ እትም ሲወስን እና የዝግጅት ክፍሉን ሥራ ወስዶ በልዩ እትሙ ምን ምን መካተት እንዳለበት ሲወያይ እና ሲወስን እናገኛለን፡፡

ለመሆኑ የዛሬ አሥር ዓመት ማኅበረ ቅዱሳን የት ይደርሳል? ቢሉት አመራሩ መልስ አለው፡፡ ከቤተ ክህነት ወሬ መጣ፣ አቡነ እገሌን እገሌ አናገራቸው፣ መንግሥት እንዲህ አለ፣ እገሌን ታክሲ ውስጥ አግኝቼው እንዲህ ያለ መረጃ ነገረኝ ከሚለው ያለፈ የተጠናከረ መረጃ የሌለው አመራር ነው፡፡ ቤተ ክህነቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ እና ልማታዊ ጉዞ በሚመች መልኩ እንዴት ሊሻሻል ይችላል? ቤተ ክህነቱ በሀገሪቱ ዕድገት ውስጥ አውራ ድርሻ ይዞ እንዴት መጓዝ ይችላል? የቤተ ክርስቲያኒቱ አንኳር ችግሮች ምንድን ናቸው? የማኅበሩ ድርሻስ? እያለ በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ከመነጋገር ይልቅ አንድ ዋና ጸሐፊ ሊሠራው በሚችለው ጉዳይ ላይ ሲነጋገር እድሜውን ጨረሰው፡፡ የጋዜጣ ጽሑፍ የሚተችበት ዳግማዊ ኤዲቶርያል ቦርድ ነው አመራሩ፡፡ በአንድ ስብሰባ የተወሰነን ጋዜጣ ታላላቅ ወንድሞችእንደገና ስብሰባ ጠርተው ለማስቀረት የሚሯሯጡበት ሜዳ ነው አመራሩ፡፡ በሲኖዶሱ የርክበ ካህናት ዋዜማ የወጣውን ልዩ እትም ያስታውሷል፡፡

አመራሩ ስትራቴጂክ አለመሆኑ ከመደበኛ አገልጋዮቹ ጋር እንኳን እንዳይጣጣም አድርጎታል፡፡ ዛሬ አመራሩ የሚለውን ለመስማት በጎ ፈቃደኛ ያለው መደበኛ አገልጋይ አነ ስተኛ ነው፡፡ አመራሩ በብቃት እና በዕውቀት ይወስናል ብሎም አያምንም፡፡ የመወሰኛ ግፊቱ ፍርሃት የሆነ ነው አመራሩ፡፡ እኔ እንደምገምተው የማኅበሩ አባላት መንግሥትን እንዲፈሩ እና እንዲጠሉ የሚፈልጉ አካላት በአመራሩ ውስጥ ሳይኖሩ አይ ቀርም፡፡ ምንጊዜም አንዳች ከባድ ነገር ሲነሣ መንግሥት እንዲህ ብሎናል፣ በዚህ ስብሰ ባው እንዲህ ብሏል፣ ሊዘጋን ነው፣ ሊያስረን ነው፣ ሊጨርሰን ነው ከማለት ያለፈ አን ድም ቀን በጎ ነገር ስለ መንግሥት የማያነሡ አካላት አሉ፡፡

እነዚህ አካላት ዋና ዓላማቸው መረጃ መስጠት ሳይሆን ውሳኔዎች «ፍርሃት ገፍ» እንዲ ሆኑ ማድረግ ነው፡፡ አሁን አሁን እንዲያውም አመራሩ ጠንከር እንዲል ያደረጉት ወደ ኋላ ላይ አንዳንድ ወንድሞች መጨመራቸው ነው፡፡ እነዚህ ሥውር አካላት ከራሳቸው የፈለቀ ፍርሃት የሞላው መረጃ መስጠታቸው አመራሩ በመረጃ ላይ ሳይሆን በፍርሃት ላይ ተንተርሶ እንዲወስን አድርጎታል፡፡

ለአመራሩ በቂ መረጃ ይሰጣል ተብሎ የተቋቋመው «የመረጃ ክፍል»ም የፕሮቴስታንት ኅትመቶችን ከመግዛት ባለፈ መሥራት አልቻለም፡፡ እንዲያውም ሥራውን ትቶ የገዛ አባላቱን እስከ መሰለል ነው የደረሰው፡፡ ወሬ እና መረጃ መለየት የተሳነው ክፍል ነው፡፡ ይህ ክፍል በዚህ የዐቅም ችግር ላይ እያለ በምንም መልኩ አመራሩ ዕውቀት እና መረጃ ተኮር የሆነ ስትራቴጂ ሊኖረው አይችልም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን ያህል ተቋም የሚመራ አመራር የሚዲያ ሞኒተሪንግ አካል የለውም፡፡ አብዛኞቹ አመራሮች በሀገር ቤት ጋዜጦች እና መጽሔቶች የወጡትን፣ ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ያሠራጫቸውን ነገሮች የሚሰሙት ሲሰበሰቡ ብቻ ነው፡፡ ይህንን የነዚህ ወንድ ሞች ድካም በመረዳት የአዲስ ዘመንን ጋዜጣ ፎቶ ኮፒ አድርገው መረጃ አገኘን የሚሉ «የመረጃ ሰዎች» ተፈጥረዋል፡፡

በነገራችን ላይ በማኅበሩ የግል ጋዜጦችን ማንበብ በሥውር የተከለከለ ነው፡፡ የትምህርት ክፍል መደበኛ አገልጋዮች መረጃ ለማግኘት እንድንችል የግል ጋዜጦችን የምናገኝበት መንገድ ይመቻች ብለው ይጠይቃሉ፡፡ አንዳንድ ወንድሞችም የጋዜጦቹን የዓመት ሂሳብ ለመክፈል ቃል ይገባሉ፡፡ ነገር ግን አሠራሩ ማዕከላዊ እንዲሆን ክፍሉ እንዲይዘው ይባላል፡፡ በመጨረሻ ጽ/ቤቱ የግል ጋዜጦችን ገዝቶ በቢሮ ማምጣት ማኅበሩን ሊያስ መታ ስለሚችል መቅረት አለበት ብሎ ይወስናል፡፡ በዚህ ዓይነቱ አመለካከት የሚመራ ማኅበር የት መድረስ ይችላል)

አወጣሁት ያለውን ስትራቴጂክ ዕቅድ እንኳን 50 በመቶ ያህል መፈጸም ያልቻለ ደካማ አመራር ነው አመራሩ፡፡ በሌላ ተቋም ቢሆን ሁለት ዓመት ሠርቶ ከ48 በመቶ በላይ ማስመዝገብ ያልቻለ አመራር ይቅርታ ጠይቆ ሥልጣኑን መልቀቅ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ይህ ማኅበረ ቅዱሳን በመሆኑ ይኼው እስከ ዛሬ አለ፡፡

የማኅበሩ አመራር የሃሳብ አመራር ከመሆን ይልቅ እንደ ሥራ አስፈጻሚው ሁሉ የመ ዋቅር አመራር ሆኗል፡፡ የሥራ አመራሩ አዳዲስ መንገዶች የሚተልም፣ ችግሮችን አስ ቀድሞ የሚተነብይ፣ ተንብዮም የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ፣ የሃሳብ ክርከር የሚ ደረግበት፣ የሃሳብ ልዕልናም የሚታይበት መሆን ነበረበት፡፡ እስካሁንም የባለጉዳይ መሥመር እንጂ የሃሳብ መሥመር የለውም፡፡ አሁን አሁን ማኅበሩ ከሃሳብ መሪነት እያፈገፈገ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እመር ሊያደ ርጉ የሚችሉ ሃሳቦችን አመንጭቶ በማኅበረሰቡ ውስጥ አስርጾ ተገቢ ለውጥ እንዲመጣ ከማድረግ ይልቅ የተለመደው ዓይነት መሥሪያ ቤታዊ ሂደት ውስጥ ገብቷል፡፡ ቤተ ክህነቱ ከዕለት ወደ ዕለት እየተበላሸ ሲሄድ አመራሩ አያገባንም በማለት ነው የተጓዘው፡፡ ቤተ ክህነትን የተመለከተ ሃሳብ የሚያመጣውን ሁሉ በአፈንጋጭነት እየከሰሰ ነው የተጓዘው፡፡

የማኅበሩ ደንብ በሲኖዶስ ሲጸድቅ የተሻሻለ አንድ ሃሳብ ነበር፡፡ «ማኅበሩ በቤተ ክርስ ቲያን አስተዳደር ጣልቃ አይገባም» የሚለው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ሲበላሽ ዝም ካለማ ማኅበረ ቅዱሳን ለምን ይጠቅማል) ብለው ነበር አባቶች የነበረውን ሕግ ያሻ ሻሉት፡፡ የአመራሩ የሂደት መዘውር «ፍርሃት» በመሆኑ የሲኖዶሱን ደንብ እንደገና አሻሽሎ «ግቡ አላሉንም» የሚል ትርጓሜ ሰጠው፡፡

በዚህ ርእዮቱ ምክንያትም «ራስ ደኅና» ብሎ ቤተ ክህነቱን ለመጠቀሚያነት ብቻ ይገለገልበት ጀመር፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም ማኅበሩ ቤተ ክህነቱን ከማጠንከር ይልቅ ከቤተ ክህነቱ ድክመት ተጠቃሚ መሆንን የመረጠ ያስመስለው ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ሊመጣ የቻለው ደግሞ የሥራ አመራሩ ከሃሳብ ወይንም ከስትራቴጂያዊ መሪነት ይልቅ ወደ መዋቅራዊ እና የዕለት ተዕለት ሥራ መሪነት በመውረዱ ነው፡፡ በአ ሁኑ ጊዜ ሥራ አስፈጻሚው ባይኖር ማኅበሩ የሚጎዳውን ያህል ሥራ አመራሩ ባይኖር የሚመጣበት ጉዳት ኢምንት ነው፡፡

አንድ ተቋም በየጊዜው ራሱን እየመገመ እና እንደገና እየተወለደ ካልተጓዘ ያረጃል፤ ይሞታልም፡ ለተነሣበት ችግር መፍትሔ አምጭ መሆኑ ይቀርና ራሱ ችግር ይሆናል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም በአመራር እጦት ምክንያት ለቤተ ክህነቱ ችግር መፍትሔ ያመጣል ሲባል እርሱ ራ የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር እየሆነ ነው፡፡ ምናልባትም የማኅበሩ አሠራር እና አመለካከት ጊዜ ያለፈበት/ኤክስፓየር እያደረገ/ ያለም ይመስላል ፡፡ ከዚህ በኋላ ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ አስተሳሰቡ፣ አካሄዱ እና አሠራሩ ለውጥ አምጭ ሆኖ መቀጠል አይችልም፤ ቆሟል/ስታክ አድርጓል/፡፡ ምናልባት እንግሊዝኛ ተናጋሪ ቤተ ክህነት ሆኖ ሊቀጥል ይችል ይሆናል ፡፡

የኔ ልዩነት አካሄዳችንን እንገምግም፣ አመራሩን እንገምግም፣ አሠራችንን እንገምግም፤ እንደ ገና መነሣት/ ሬናይዛንስ/ ያስፈልገናል፡፡ ሁሉን አቀፍ የሆነ የሂደት ግምገማ ያስፈልጋል፡፡ ሲሆን በገለልተኛ አካል፡፡ ከዚያ በኋላ በዚያ ዶክመንት መሠረት እንወያይ የሚል ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡

ልዩነት ሁለት
ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከት ስትራቴጂያዊ ጉዞ የለውም፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረታዊ ችግሮች ለይቶ፣ ለዚያም የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀ ምጦ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ጭፍጫፊ ችግሮች ላይ ብቻ እያተኮረ በመጓዝ ላይ ነው፡፡ ማኅበሩ በተመሠረተባቸው ዓመታት ገና የቤተ ክህነቱን ጠባይ ማወቅ፣ የውስጥ ውህደ ትንም መፍጠር፣ ብሎም በቂ የሰው ኃይልም ማፍራት ነበረበትና አይታማም፡፡ አሁንም ግን በዚያው መንገድ የሚጓዝ ከሆነ ችግሩ ከማኅበሩ አመራር አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው ማለት፡፡

እስካሁን ድረስ አመራሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን የወደፊት ሂደት ተግዳሮቶች እና ዕድ ሎች የሚመለከቱ ዶክመንቶች የሉትም አመራሩ፡፡ መናፍቃንንም በተመለከተ የረዥም ጊዜ የተጠና አካሄድ ሳይሆን «ከኮከብ አዳራሽ ያላለፈ»  አሠራር ነው ያለው፡፡ እርሱንም ተዘጋ፣ ተከፈተ፣ ተፈቀደ፣ ተከለከለ እያለ ልብ አንጠልጣይ ፊልም አድርጎታል፡፡  ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የማያልቅ የመፍትሔ አቅጣጫ ነው የሚከተለው፡፡ ውሻዋን ከማስባረክ ይልቅ ውሻዋ የለከፈችውን ዕቃ መርጨት ነው የተያያዘው፡፡ በአንድ በኩል የዕለት ችግሮችን እየፈታ በሌላ በኩል ደግሞ ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማምጣት እየሠራ አይደለም፡፡ የዕለት ችግሮችን መፍታት የሚጠቅመው ወደ ዘላቂ መፍትሔ የሚያሸጋግሩን ከሆነ ብቻ ነው፡፡

ገዳማትን ለመርዳት እንጂ ገዳማትን ወደ ችግር የወሰዳቸውን መሠረታዊ ችግር ለመ ፍታት፣ ዕጣን ጧፍ ለመስጠት እንጂ የዕጣን እና ጧፍ እጥረትን ያመጣውን መሠ ረታዊ ችግር ለመፍታት፣ ለካህናት ደመወዝ ለመክፈል እንጂ የደመወዝ እጥረት ያመ ጣውን መሠረታዊ ችግር ለመፍታት፣ ሰባክያንን ለማሠማራት እንጅ 400 ሺ ካህናት ባሏት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሰባክያንን እጥረት ያመጣውን መሠረታዊ ችግር ለመ ፍታት፣ ተሐድሶን ለማጋለጥ እንጂ ተሐድሶን ያመጣውን መሠረታዊ ችግር ለመፍ ታት ያስቀመጠው ስትራቴጂ የለም፡፡ በማኅበሩ አመራር ውይይቶች ውስጥ የቤተ ክህነቱ ጉዳይ ሲነሣ የፍርሃት ድባብ ነው የሚነግሠው፡፡ ይህ የፍርሃት ድባብ ደግሞ «ቤተ ክርስቲያናችን አንዳች ትሆናለች» ከሚል የመጣ ሳይሆን «ማኅበራችን ይፈርሳል» ከሚል የሚመነጭ ነው፡፡ አመራሩ ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን የተመሠረተ መሆኑን ዘንግቶታል፡፡ አሁን ቤተ ክርስቲያን ለማኅበሩ ወደሚል አመለካከትም ዞሯል፡፡ ይህ ፍርሃት ማኅበሩ የሚጠበቅበትን ከመሥ ራት ይልቅ ራሱን ለመከላከል ከፍተኛ ወጭ እንዲያወጣ አድርጎታል፡፡ ቤተ ክህነቱ ቢበላሽ፣ ቤተ ክርስቲያን ብትጠፋ፣ ችግሮች እየተባባሱ ቢመጡ እርሱን እስካልነካው ድረስ ዝምታን ይመርጣል፡፡

ዲያቆን በጋሻው ማስተማር የጀመረው መቼ ነው) ማኅበሩ በነዲያቆን በጋሻው ላይ ሃሳብ ዛሬ መሠንዘር ለምን ጀመረ) በጋሻው ለቤተ ክርስቲያን አደጋ ነው ብሎ ስላሰበ አይደለም፡፡ በጋሻው ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ ስለ ተናገረ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ምንም ያልተናገረው ማኅበር ስሙ ሲነሣ ቤተ ክርስቲያን ተነካች ብሎ ተነሣ፡፡

ማኅበሩ አቡነ ጳውሎስን በተመለከተ የተለየ አቋም መያዝ የጀመረው መቼ ነው) «እር ሳቸው ማኅበሩን ሊያፈርሱ ነው» ብሎ መሥጋት ከጀመረ በኋላ፡፡ አባ ሠረቀንም ቢሆ ንኮ ዛሬ ዛሬ በእምነት ችግር ይከሳቸዋል እንጂ፣ ከእርሳቸው ጋር ያለው ዋናው ችግሩ ማኅበሩ መነካቱ ነው፡፡ አባ ሠረቀ ማኅበረ ቅዱሳንን ሳይነኩ የፈለጉትን ቢሆኑ ኖሮ አይናገራቸውም ነበር፡፡

ባለፈው ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ላይ ችግር ሲፈጠር፣ ዝምታን መርጦ የነበረው አመራር የመንግሥት አካላት ከቤተ ክህነቱ ባለሥልጣናት ጋር ሆነው ስለ ማኅበሩ ሲያወያዩት ግን አገር ይያዝልኝ አለ፡፡ የአዋሳ ምእመናንን ችግር በዝምታ ያለፈው አመራር አባ ሠረቀ አንዳች ነገር ተናገሩ ብሎ ድምፁን አሰምቶ ተናገረ፡፡ እነዚህ እና መሰል ሁኔታ ዎች አመራሩ የሚቆረቁረው ማኅበሩ ሲነካ እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስትነካ አለመሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ይህ በዋናነት ራስን ከአደጋ ለመከላከል ብቻ የተሠራው መንገድ ነው ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ ስትራቴጂ እንዳይኖረው ያደረገው፡፡ ይህ ፍርሃት የወለደው አሠራር ነው ማኅበሩ ራሱን እያስፋፋ ከመሄድ ባለፈ በቤተ ክህ ነቱ ውስጥ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ሥራ እንዳይሠራ ያደረገው፡፡ ማኅበሩ ከተመሠ ረተ በኋላ በቤተ ክህነት ምን ዕድገት መጣ? ምን ዓይነት የአሠራር መሻሻል መጣ? ምን ዓይነት የዕውቀት ሽግግር ተደረገ ምናልባት አንድ ሁለት ኮምፒውተሮች ተገዝ ተው ተሰጥተው ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው የአመራ ተወካይ ከአቦይ ስብሐት ጋር ሲወያይ ማኅበሩ በቤተ ክህነቱ ምን ለውጥ አመጣ? ለተባው ጥያቄ መልስ መስጠት ያቃተው?

ዛሬ ያጋጠመውን የቤተ ክርስቲያኒቱን እና የማኅበሩን ወቅታዊ ችግር በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመርኩዞ ለመተንበይ ቢችል ኖሮ በቀን ሁለት ጊዜ በጭንቀት ለመሰብሰብ እና አያሌ ኮሚቴዎችን ለወቅታዊው ችግር ማቋቋም ባላስፈለገው ነበር፡፡

ልዩነት ሦስት
ማኅበሩን ለመምራት የሚሞክር ሥውር አመራር አለ
ለብቻው ተወያይቶ፣ ለብቻው ወስኖ ወደ አመራሩ እየመጣ አጀንዳዎቹን የማኅበሩ አጀንዳ የሚያደርግ፤ አንዳንዴም ጽ/ቤቶቹን ተጠቅሞ ውሳኔዎቹን የሚያስኬድ አመራር አለ፡፡ ለዚህ ማሳያዎቹን ላቅርብ፡፡ ወንድማችን ዐሉላ ጥላሁን የማኅበሩ የረዥም ዘመን አባል ነው፡፡ በሐመር መጽሔት እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት የደረሰ፣ ለማኅበሩ ዕድገት ጉልሕ አስተዋጽዖ ያደረገ ወን ድም ነው፡፡ ይህ ወንድም በአንድ ወቅት ወደ ማኅበሩ ጽ/ቤት ግቢ እንዳይገባ በወቅቱ በነበረው ዋና ጸሐፊ ታግዶ ነበር፡፡ ይህንን ዕግድ የማኅበሩ ሰብሳቢ ቢያውቅም ምንም የማረሚያ ሥራ አልሠራም፡፡ ለምን) ተስማምቶበታልና፡፡

አንድን አባል ለማገድ የሚቻለው በአባላት መከታተያ ደንብ መሠረት በሥራ አመራሩ ነው፡፡ ያውም ከአባልነት ለማገድ፡፡ ዋና ጸሐፊው ያንን ውሳኔ እንዲወስን ያደረገው ሥውሩ አመራር የሰጠው መመርያ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በዐሉላ ላይ ብቻ አላበቃም፡፡ እኔም ወደ ጽ/ቤት እንዳልገባ እግድ ተላልፎ ነበር፡፡ የጥበቃ አባላቱ ግን «ከታላላቅ ወንድሞች» ተሽለው «ዳንኤልን አትግባ ማለት አንችልም» ሲሉ ለመተግበር እንደሚቸገሩ ገለጡ፡፡ ለእኔም ተነገረኝ፡፡ በወቅቱ ዋና ጸሐ ፊውን ገብቼ አናገርኩት፡፡ ነገሩ መክሩሩን ሲያይ አላልኩም አለ፡፡ ዛሬ ግን የነበረውን ሁኔታ በፀፀት የሚያስታውሰው ይመስለኛል፡፡

ይኼው ሥውር አመራር ዳንኤል ማስተማር የለበትም ብሎ ወስኖም ነበር፡፡ ጎንደር ሄጄ ግቢ ጉባኤ ሳስተምር ምክትል ዋና ጸሐፊው ደውሎ ለምን እንዲያስተምር ፈቀ ዳች ሁለት) ሲል ከማዕከሉ ትምህርት ክፍል ጋር ተሟገተ፡፡ እኔ ከማስተማር መታገዴንም ተናገረ፡፡ ማዕከሉ ግን ሊቀበለው ባለመቻሉ ይኼው ዛሬም አስተምራለሁ፡፡ ሥውሩ አመራር የኔ ጽሑፍ በሐመር እና በስምዐ ጽድቅ እንዳይወጣም ወስኖ አስፈጽ ሟል፡፡ በወቅቱ የክፍሉ መሪ የነበረው አሥራት ከበደ «ይህ መመርያ በጽሑፍ ብቻ ሊሰጠኝ ይገባል» በማለቱ ጫናው በሌላ አካል በኩል እንዲፈጸም ተደርጓል፡፡ በየማዕከሉ ስጓዝ አባላቱ ለምን በሐመር እና ስምዐ ጽድቅ ላይ መጻፌን እንዳቆምኩ ሲጠይቁኝ የኔን ስንፍና ነበር እንደ ምክንያት የማቀርበው፡፡ አሁን እውነቱን ልንገራችሁ፡፡ ሥውሩ አመራር በመወሰኑ እና ይኼንንም ሰብሳቢው እና ዋና ጸሐፊው በማስፈጸማቸው ምክንያት ነው፡፡

ሰሞኑን ተሐድሶን በተመለከተ ገለጣ ለባለ ሀብቶች ሲደረግ ባለ ሀብቶች ከአንድ በመመ ሥረት ላይ ካለ ባንክ ጋር ተባብረው እንዲሠሩ እየተነገራቸው ነው፡፡ ይኼንን ባንክ በተ መለከተ አመራሩ የወሰነው ነገር እንደሌለ ዐውቃለሁ፡፡ ውሳኔው የተላለፈው በሥውሩ አመራር በመሆኑ፡፡ ሥውሩ አመራርም ይህንን የወሰነበትን ምክንያት እኛም እነርሱም ያውቁታል፡፡ የማኅበሩ ዓይን የሆኑት ሐመር እና ስምዐ ጽድቅ እንዲዳከሙ በሥውር አመራሩ ተፈር ዶባቸዋል፡፡ ዋና ክፍሉ መሪ የለውም፡፡ በየዝግጅት ክፍሉ የነበሩ ጋዜጠኞች ሲለቅቁ ሌሎች እንዲተኩ አይደረግም፡፡ ቢደረግም ሆን ተብሎ ከዐቅም በታች ሊጫወቱ የሚች ሉት ይመደባሉ፡፡ በዚህም የተነሣ በሐመር መጽሔት ላይ የጎን ጽሑፍ /ፊለር/ የሽፋን ጽሑፍ /ከቨር ስቶሪ/ ሆኖ እስከመቅረብ ደርሷል፡፡ በጋዜጣውም አሥራት ባይኖር ኖሮ ምን ይደርስ እንደነበረ ራሷ ጋዜጣዋ አፍ አውጥታ ትናገራለች፡፡

ይህ ክፍል የሚከራከር፣ የሚወያይ፣ አዳዲስ ሃሳቦችን የሚያቀርብ፣ ለመረጃ ቅርብ የሆነ፣ በመሆኑ በሥውር አመራሩ አልተወደደም፡፡ በቅርቡ በተደረጉ የሰው ኃይል ምደባ ዎች የታየው ሁኔታም ይህንኑ የክፍሉን እና የአመራሩን ልዩነት ያሳየ ነበር፡፡ 

ልዩነት አራት
ማዕከላት እና ግቢ ጉባኤያት ተረስተዋል
የግቢ ጉባኤያት እና የማዕከላት ቁጥር ጨምሯል፡፡ የአመራሩ አስተሳሰብ ግን በ85 ዓም ላይ ነው፡፡  የግቢ ጉባኤያት ሁኔታ ግን ተቀይሯል፡፡ በአንድ ግቢ ያሉ ተማሪዎች ቁጥር ጨምሯል፤ ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚገቡ ተማሪዎች እድሜ ቀንሷል፤ የተማሪዎቹ ዓይነትም በዝቷል፡፡ የግቢ ጉባኤ አባላት የፖለቲካ መልክዐ ምድርም ተቀይሯል፡፡ የማዕ ከላቱም እንዲሁ፡፡

እነዚህን ከግምት ውስጥ ያስገባ አሠራር ዘርግቶ ተማሪዎቹን ወደሚፈለገው ደረጃ ማድ ረስ አልተቻለም፡፡ ማዕከላቱ በቢሮ እጥረት እየተቸገሩ፡፡ ብቃት ያለው ጸሐፊ ማግኘት እያቃታቸው፣ የቢሮ መሣርያዎችን ማሟላት መከራ እየሆነባቸው፣ ያሏቸው ቢሮዎችም ለሥራ አመቺ ያልሆኑ ናቸው፡፡ ለሌሎች አርአያ የነበሩት እነ መቀሌ ማዕከል ከተሟላ ጽ/ቤት ወጥተው ወደ ደሳሳ ጎጆ ገብተዋል፡፡ ይህ የሆነው ማኅበሩ ሃያኛ ዓመቱን በሚያ ከብርበት ዋዜማ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡
ግቢ ጉባኤያት የቦታ እና የመምህራን እጥረቶቻቸው በሃያ ዓመታት ውስጥ አልተፈ ቱም፡፡ አንዳንድ ግቢ ጉባኤያት በሚሊዮኖች ሲያንቀሳቅሱ የሚከታተሏቸው ማዕከላት ግን በገንዘብ እጥረት ይጠወልጋሉ፡፡ አንዳንድ ግቢ ጉባኤያት በማዕከላቱ ላይ አመኔታ በማጣት ራሳቸው በጀት መድበው መምህር ከአዲስ አበባ ይወስዳሉ፡፡ የመማርያ መጻሕ ፍቱን በብቃት ማዳረስ ሳይቻል ካሪኩለሙ ቀድሞ ተቀየረ፡፡

ማኅበሩ ግቢ ጉባኤያትን ያስተምሩልኛል እያለ በየዓመቱ «መምህራንን» በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ እና በሌሎችም ቦታዎች ያሠለጥናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ሠልጣኞች ግን በመድ ረኩ የሉም፡፡ እስካሁን ከ500 በላይ ሰባክያን አሠልጥኖ አሥር አላገኘም፡፡  ይህ ሁኔታ እየተደጋገመ ዘወር ብሎ የሚቃኘው ባለመኖሩ ግቢዎች አሁንም በመምሀራን እጥረት ይቸገራሉ፡፡

በዋና ማዕከል ደረጃ የሚገኙ መምህራን ቁጥራቸው እየቀነሰ ይገኛል፡፡ አዳዲስ መምህ ራንንም ለመቅጠር ማስታወቂያ ቢወጣም ደመወዙ እና የሥራ ሁኔታው አይጋብዝም እያሉ ጥለውን ሄዱ፡፡ የመምህራኑ ቁጥር መቀነስ ደግሞ ትልቁ ችግሩ በግቢ ጉባኤያት ላይ ነው፡፡ ግቢ ጉባኤያቱ ዓይናቸውን ከዋና ማዕከል ትምህርት ክፍል እያነሡ ወደ «ግል ሰባክያን» እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል፡፡

በየግቢው ማኅበረ ቅዱሳንን የማያውቅ አዲስ ትውልድ እየመጣ ነው፡፡ ዓላማ ያለው፣ በሀገሪቱ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ዕድገት ተገቢ ሚናውን የሚወጣ፣ በተነሣሽነት እና በቆራጥነት የሚሠራ፣ ነጥሮም የሚወጣ ትውልድ ማፍራት አልተቻለም፡፡
እናም ማኅበሩ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተቀበለውን ግቢ ጉባኤያትን የማብቃት ሚናውን አልተወጣም፣ ለመወጣት የሚያስችል ዝግጁነት፣ አደረጃጀት እና በቂ የሰው ኃይለም የለውም፡፡ ይህ መቀየር አለበት ነው፡፡

በእኔ እና በአመራሩ መካከል ያሉት ልዩነቶች እነዚህ እና ሌሎች ጉዳዮች መፈታት አለባቸው ከሚለው የመነጨ እንጂ መምህር ሙሉጌታ እንዳለው በልማት ሥራዎች ላይ ተመድቤ ስሠራ የተፈጠሩ ነገሮች አይደሉም፡፡

እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ ደብዳቤ ጽፌ፣ ተገኚቼ አስረድቼ፣ ተከራክሬያለሁ አመራ ምንጊዜም የሚከተለው አንድ አሠራር አለ፡፡ የውስጥ ጥያቄ ሲመጣበት የውጭ ጠላት ያመጣል፡፡ «እነ እገሌ ሊያጠፉን ነውና የእነርሱን ጉዳይ ከጨረስን በኋላ እንወያያለን» ይላል፡፡ ማዳፈን ዋናው ስትራቴጂ ነውና፡፡ እኔም እስኪ ይለፍ እያልኩ ብዙ ጊዜ ታገሥኩ፡፡ ችግሮቹ ግን እየባሱ እንጂ እየተሻሻሉ በመሄድ ላይ አይደሉም፡፡

ከስድስት ወራት በፊት ባደረግነው ስብሰባ እነዚህ ልዩነቶች እንዲፈቱ አደርጋለሁ ብሎ ነበር አመራሩ፡፡ ነገር ግን በሥውሩ አመራር ሤራ ምክንያት ጉዳዩ አንድ ዓመት ሙሉ ተራዝሟል፡፡ ወደፊትም የሚቀጥል አይመስልም፡፡ አመራሩ በእሳት ማጥፋት ሥራ ላይ ተሠማርቷልና፡፡ አሁን ደግሞ ምንም ዓይነት ውይይት አይኖርም፡፡ ያላችሁ አማራጭ ወይ ያልኩትን መቀበል፣ ያለበለዚያም ለቅቃችሁ መሄድ ነው ብሏል፡፡ ለቅቀን አንሄ ድም፡፡ ማንም እንዲለቅቅም አንፈልግም፡፡ ያልተስተካከሉ አስተሳሰቦች ግን ማኅበሩን መልቀቅ አለባቸው፡፡

¥Q /Ä!ÇN s!ST
ሰሞኑን የማኅበረ ቅዱሳን በዕንቁ መጽሔት ላይ የሰጡት ቃለ መጠይቅ የአባላት እና የሌሎችም መወያያ ሆኗል፡፡ እኔ ካነበብኩት በኋላ ሁለት ዓይነት ስሜት ነበር የተሰ ማኝ፡፡ እውነት ወንድሜ ይህንን ተናግሮታል) የሚል እና ምናልባት ሳናውቀው ማኅበረ ቅዱሳን ተቀይሮ ይሆን የሚል፡፡ ይህ ጉዳይ ከሌላ አቅጣጫ ሃሳብ ሊሰጥበት ይገባል ብዬ አመንኩና መጻፍ ጀመርኩ፡፡ ዓባይነህ ካሤን የመሳሰሉ አንዳንድ ወንድሞች የአመራሩን ውሳኔ መጠበቅ የተሻለ ነው ብለው የሰጡኝን ማዕቀብ ተቀብዬ ታገሥኩ፡፡ አሁን ግን ሁሉም መንገዶች ተሞክረው አመራሩ በሩን መዝጋቱን ነገሩኝ፡፡ እኔም ከሰብሳቢው እና ከኦዲት እና ኢንስፔክሽኑ ይህንኑ ሰማሁ፡፡ እንግዲህ ያለን አማራጭ በአደባባይ የተሠ ራውን ስሕተት በአደባባይ ማረም ነው፡፡

እኔ በአብዛኛው ከቃለ መጠይቁ በፊት እና በኋላ በሆኑት ክስተቶች ላይ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡ ለቃለ መጠይቁ መነሻ የሆነው ቤተ ክርስቲያንን እናድሳለን ብለው የተነሡ አካላት ያደ ረጓቸው ቅርብ እና ግልጽ አደጋ አምጭ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ እነዚህ እንቅስቃ ሴዎች ሚዲያ ተኮር ሆነው መራመድ ጀምረዋል፡፡ ይህ ያሳሰባቸው አንዳንድ ሰዎች ማኅ በሩስ በተመሳሳይ ሚዲያዎች ለምን ሃሳቡን አይገልጥም የሚል አስተያየት ሰነዘሩ፡፡

የዕንቁ መጽሔት ዝግጅት ክፍል ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ጉዳዮችን አስተናግዶ ስለነበር ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ጠየቀ፡፡ ሙሉጌታ ኃይለ ማርያምም ፈቃደኛ ሆነ፡፡ ቃለ መጠይቁም ተደረገ፡፡ መምህር ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም ቃለ መጠይቁን በመስጠቱ እስማ ማለሁ፡፡ «አፍ ያለው ያግባሽ ከብት ያለው ቢሏት» አፍ ያለው ያግባኝ ያለችው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ መናገር የሚያመጣውን ነገር ስለምታውቅ ነው፡፡ ደጃዝማችነትም የሚቀረው ካለመናገር ነው፡፡ የማኅበሩንም አቋም መቀየር ያወቅነው በመናገሩ ነውና ለወደፊቱም ይናገር፡፡

በቃለ መጠይቁ አሠራር ላይ የተፈጠሩ ግድፈቶች
ቃለ መጠይቁ ሲወጣ ሁለት ዓይነት ችግሮች ነበሩበት፡፡ የመጀመርያው የአርትዖት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአመለካከት ናቸው፡፡ የአርትዖት ስሕተቱን የሠራው መጽሔቱ ነው፡፡ መምህር ሙሉጌታ በዚህ ጉዳይ ተጠያቂ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጥያቄዎች ተቀይ ረዋል፣ አንዳንዶቹ ተጎርደዋል፣ ሌሎቹም ተጨምቀዋል፡፡ በዚህ ሂደት የአርትዖት ስሕ ተት ተሠርቷል፡፡ ምንም ቢሆን ግን ያልተናገራቸው ነገሮች አልወጡም፡፡
1.   ሁለተኛው እና ከባዱ ስሕተት ሙሉጌታ ራሱ የሠራቸው ስሕተቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ስሕተቶች በሦስት መልኩ ሊታዩ ይችላሉ፡፡
2.   ከልምድ ማነስ የመጡ ስሕተቶች

መምህር ሙሉጌታ ከሕዝብ እና ከሚዲያ ጋር የተገናኘ ልምድ የለውም፡፡ የማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢም ሆነ ሰብሳቢ ሆኖ በቆየባቸው ዘመናትም በስብሰባ ካልሆነ በቀር በሚዲያ ሃሳቡን ሰጥቶ አያውቅም፡፡ እንዲህ ላለው ሰው የሚዲያ አማካሪ ሊኖረው በተገባ ነበር፡፡ የአንድ መሪ ጥንካሬ ከመማክርቱ የሚመነጭ ነውና፡፡ ምን መመለስ እንዳለበት፣ ጥያቄውን ለመልሱ እንዲ ሆን አድርጎ እንዴት መልሶ ማቀናበር እንደሚችል፣ መመለስ የሌለበትንም ጥያቄ ኦፍ ዘሪከርድ አድርጎ እንዴት ማለፍ እንዳለበት የሚያማክረው ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህንን ባለማድረጉ ዋናው ተጠያቂው ከሙሉጌታ በላይ የሥራ አመራሩ ነው፡፡

በኋላ በሥራ አመራር ሲጠየቅ እንደ ሃርድ ቶክ ሆነብኝ ያለው ከልምድ ማነስ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሃርድ ቶክን ያህል የሚጠይቅ ጋዜጠኛ ማግኘት መታ ደል እንጂ መጎዳት አይደለም፡፡ ሙሉጌታ ግን ለጉዳዩ እንግዳ በመሆኑ ሃርድ ቶክ ሆነብኝ አለ፡፡

2. በቂ ዝግጅት ካለማድረግ የመጡ
ቃለ መጠይቁን ላነበበ ሰው ሙሉጌታ በቂ ዝግጅት ያደረገ አለመሆኑን ይረዳል፡፡ ለም ሳሌ በማኅበሩ ታሪክ ዋና የሚባለውን ብላቴን ዘሎታል፡፡ ማኅበሩ የሠራቸውን ሥራዎች በዝርዝር እና በስታትስቲክስ ማስቀመጥ አልቻለም፡፡
3. ከአመለካከት የመነጩ

በአሁኑ ጊዜ እያነጋገሩን እና እየከፋፈሉን ያሉት ጉዳዮች የሙሉጌታ አመለካከቶች ናቸው፡፡ አመለካከቶቹ የሙሉጌታ ብቻ አይደሉም፡፡ የአመራሩም ጭምር መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ለምን ቢሉ አመራሩ እነዚህ አመለካከቶች መታረም እንደማያስፈልጋቸው አምኗልና፡፡
እነዚህ ነገሮች የአመራሩ አመለካከቶች ከሆኑ ደግሞ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች አሉ ማለት ነው፡፡ አንደኛ ማኅበሩ ይዞት የተነሣውን መሠረታዊ አመለካከት ቀይሯል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ አመለካከቱን ሲቀይር አባላቱን ሳያማክር እና ይሁንታ ሳያገኝ በጥቂት የአመራር አካላት ፍላጎት ብቻ አስኪዶታል ማለት ነው፡፡

ማኅበርን ማኅበር የሚያደርጉት መዋቅሩ አይደለም፡፡ ማኅበርተኞቹን ያሰባሰቡት አው ታር የሆኑት መሠረተ ሃሳቦች ናቸው፡፡ እነዚህ ሃሳቦች በማኅበርተኞቹ መካከል ስምምነት የተደረጉባቸው ሲሆኑ የዓላማዎቹ፣ የግቦቹ እና የአሠራሮቹ ብሎም የመዋቅሩ መመ ሥረቻ ይሆናሉ፡፡ በመሆኑም እነዚያ ያግባቧቸው ሃሳቦች ሲቀየሩ ጠቅላላው ማኅበርም ይቀየራል፡፡ እነዚህ ሃሳቦች መቀየር ያለባቸው በራሳቸው በማኅበርተኞቹ ስምምነት መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም በተተኩት ሃሳቦች የማይስማሙት ይለያሉ፣ የሚስማሙት ይቀጥላሉ፡፡
አሁን ግን የተደረገው ጥቂት አመራሮች የአባላቱን ይሁታ ሳያገኙ የማኅበሩን መሠረ ታዊ ሃሳቦች የመቀየር አካሄድ ነው፡፡
/ በማኅበሩ የምሥረታ ሃሳብ ፖለቲካ አንጓ/ቫርያብል/ አይደለም፡፡ አንድ አባል የፖለ ቲካ አመለካከቱን አይጠየቅም፡፡ የማኅበሩ ቅጽም ይህንን አይጠይቅም፡፡ የአባሉ የፖ ለቲካ ተሳትፎ የሚጠናበት ወይንም የሚገለጥበት አግባብም የለም፡፡ ይህም የሆነው አንደ አባል የማኅበሩ አባል የሚሆነው በሃይማኖቱ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ዘር፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ ሀገር፣ የወዘተ የአባልነት ሂደት ውስጥ ቦታ የላቸውም፡፡

በቃለ መጠይቁ ውስጥ «አብዛኞቹ የማኅበሩ አባላት የኢሕአዴግ አባላት እና ደጋፊዎች ናቸው» በማለት ተናግሯል፡፡ ሙሉጌታ ሲጠየቅ ስለዚህ የሰጠው ማብራርያ አብዛኞቹ የማኅበሩ አባላት የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች ሁሉ ደግሞ የኢሕአዴግ አባላት ናቸው፡፡ ስለዚህ አብዛኞቹ የማኅበሩ አባላት የኢሕአዴግ አባላት ናቸው ማለት ነው» የሚል ነው፡፡

ይህ ትንታኔ በራሱ ችግር አለበት፡፡ በመጀመርያ ደረጃ «የመንግሥት ሠራተኞች ሁሉ የኢሕአዴግ አባላት ናቸው» የሚለው የተናጋሪው ሃሳብ እንጂ የፓርቲው ሃሳብ አይ ደለም፡፡ ኢሕአዴግ አንድም ቀን የመንግሥት ሠራተኞች ሁሉ የእኔ አባል እንዲሆኑ አድርጌያለሁ ያለበት ጊዜ የለም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ዋና ጸሐፊው የማኅበሩን አባላት የፖለቲካ ተሳትፎ የሚገልጥ መረጃ የለውም፡፡ ሊኖረው የሚችለው ግምት ብቻ ነው፡፡ በቃለ መጠይቁ ላይ ግን «ይመስለኛል፣ እገምታለሁ» እንኳን አልተባለም፡፡ በርግጠኛነት ነው የተነገረው፡፡ ይህ ማለትኮ አብዛኞቹ የአመራር አባላት የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው፤ ይህ ከሆነ ደግሞ አብዛኞቹ የሥራ አመራር አባላት የፓርቲ አባላት ናቸው ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታም የሥራ አመራር አባላቱ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መሆን የለ ባቸውም ከሚለው ደንብ ጋር ይጋጫል ማለት ነው፡፡ የሥራ አመራር እና ሥራ አስፈ ጻሚ አባላት የየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባላት አለመሆናችሁን ከማኅበሩ ደንብ አን ፃር አረጋግጡ፡፡ ለማረጋገጥም በፊርማችሁ የታተመ የማረጋገጫ ደብዳቤ አስገቡ ሲባሉ አብዛኞቹ አሻፈረን ያሉት የሆኑትን ሳይሆን ይቀራል) እነዚህ የአመራር አካላት የየት ኛው ፓርቲ አባላት እንደሆኑ ለማወቅ አይቻልም፡፡

ሦስተኛ ደግሞ ይህንን ዓይነት መግለጫ ለመስጠት ዋና ጸሐፊው ሥልጣን የለውም፡፡ አባላቱ ራሳቸው የዚህ ወይንም የዚያ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ነን ባላሉበት ሁኔታ ከላይ ወደ ታች ናችሁ ብሎ መደምደም ከባድ ስሕተት ነው፡፡ መች ተጠየቅንና፡፡

በአራተኛ ደረጃም ማኅበሩ የአባላቱን ቁጥር በትክክል አያውቀውም፡፡ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ ከዚህ ቁጥር በላይ ይላል እንጂ በመዝገብ መዝግቦ የሚያውቀው ርግጠኛ ቁጥር የለም፡፡ በተደጋጋሞ መምሪያው ሲጠይቀው መስጠት ያልቻለውም ስለ ሌለው ነው፡፡ አን ዳንዴም በመዝገቡ የመዘገበው አሥር ሺ ይማይሞላ ይሆንበትና ይህንን መስጠት ያስገ ምተኛል፤ የማኅበሩንም ግርማ ሞገስ ይነካል ብሎ ይፈራል፡፡

አምስተኛም ማኅበሩ የአባላቱን የፖለቲካ ተሳትፎ መረጃ ካለው የኢሕአዴግ አባላት እና ደጋፊዎችን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ፓርቲዎችን አባላት እና ደጋፊዎችንም መጠን እና እነማን እንደሆኑ ሊነግረን ይገባል ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ አመራሩ ሁለት መንገዶች ከፊቱ ተቀምጠውለታል፡፡ አንድም መግለጫውን ማስተባበል አለያም እንደተቀበለው መቀጠል፡፡ መግለጫውን የሚያስተባብል ከሆነ በነበ ረን የማኅበሩ አስተሳሰቦች ተስማምተን እንቀጥላለን፡፡ በመግለጫው ቃል ተስማምቶ የሚ ቀጥል ከሆነ ግን እኔን ጨምሮ አያሌ አባላት ማኅበራችንን ለማስተካከል ሌላ መንገድ መከተል አለብን ማለት ነው፡፡

/ ዋና ጸሐፊው ሕገ መንግሥቱን በተመለከተ የተናገረውም ቢሆን የማኅበሩ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የምድሪቱ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም የዚህች ሀገር ዜጋ ይህንን ሕግ መጠበቅ እና ማስጠበቅ ይኖርበታል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ሃሳቦች አለመስማማት ይቻ ላል፡፡ የሕገ መንግሥቱን አሳቦች መጣስ ግን አይቻልም፡፡ በሀገሪቱ የሚወጡ ሕጎች፣ መመርያዎች እና አሠራሮች በሙሉ ይህንን ሕገ መንግሥት ባልጣሰ መንገድ መሆን ይገባቸዋል፡፡

«ሕገ መንግሥቱ ሳንሱርን ቢከለክልም ማኅበሩ ግን ሳንሱር ያደርጋልሜ የሚለው አባባል ሦስት መሠረታዊ ግድፈቶች አሉበት፡፡የመጀመርያው ራሱ ሕገ መንግሥቱን የተመለከተ ነው፡፡ ማኅበሩ ሕገ መንግሥቱን እየ ጣሰ በዚህች ሀገር መኖር አይችልም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የፈቀደውን መከልከል፣ የከለከ ለውንም መፍቀድ አይችልምና፡፡ የማክበር እና የማስከበር ግዴታ አለበት እንጂ፡፡ ይህ ትክክል ነው ብሎ አመራሩ የሚያምን ከሆነ ደግሞ አቦይ ስብሐት በፍትሕ ጋዜጣ ላይ እንዳሉት «ሕገ መንግሥትን መካድ ነው» ማለት ነው፡፡

ይህ አመለካከት ግን የአባላትን ይሁንታ ያገኘ አይደለም፡፡ አባላቱ ሕገ መንግሥትን የሚጥስ አሠራር ስለመዘርጋት ያመኑበት እና የወሰኑበት ጊዜ የለምና፡፡

ሁለተኛ ሕገ መንግሥቱን ማቃለል ሆኖ ሊቆጠር የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የሚሠራውን የ«ኤዲቲንግ» ሥራ ስቦ በመውሰድ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ማገናኘት ለምን አስፈለገ) ማኅበሩ ሳንሱር የሚያደርግም ከሆነ «ሳንሱር ያደርጋል» ብሎ መግለጥ ሲቻል «ሕገ መንግሥቱ ቢከለክልም» ብሎ በፍና ተሳልቆ መግለጥ ሕገ መንግሥቱን ለማቃለል ካልሆነ በቀር ምንም ማነፃፀርያ ሊሆን አይችልም፡፡

ሦስተኛው ደግሞ ከማኅበሩ አስተሳሰብ ውጭ የጥቂቶች አስተሳሰብ የማኅበሩ አስተሳሰብ ተደርጎ መገለጡ ነው፡፡ ማኅበሩ ኤዲቲንግ እንጂ ሳንሱር የለውም፡፡ ሳንሱር የሚል ቃልም በሕገ ደንቡ የለም፡፡ የክፍሉም ስም «ኤዲቶርያል ቦርድ» የሚል ነው፡፡ በርግጥ በልዩ ልዩ የፖሊሲ ክርክሮች ጊዜ ሙሉጌታ ይህንን ሃሳብ ሲያራምድ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ሃሳቡ ተሸንፎ ነበር የኖረው፡፡ አሁን የብዙኃን ሃሳብ ሳይሆን የጥቂት ግለሰቦች ሃሳብ የማኅበር ሃሳብ የሚሆንበት ዘመን ስለመጣ ሙሉጌታ የጥቂቶ ችን ሃሳብ የማኅበር ሃሳብ አድርጎ አቀረበው፡፡ አንዱ መታረም የሚያስፈልገው አመለ ካከትም ይሄው ነው፡፡

/ «የበጋሻው ዕውቀት ከሰንበት ት/ቤት የዘለለ አይደለም»

ማኅበሩ ሲመሠረት ጀምሮ ከያዛቸው አውታር ሃሳቦች አንዱ አባላቱ በሰንበት ት/ቤት ገብተው እንዲማሩ፣ እንዲያስተምሩ እና እንዲያገለግሉ ማበረታታት ነው፡፡ ይህንን ይበ ልጥ ለመተግበር ደግሞ አባላቱ የሰንበት ት/ቤት ወይንም የሰበካ ጉባኤ አባል እንዲሆኑ ሕገ ደንቡ ያስገድዳል፡፡ ራሱ ማኅበሩም በሰንበት ት/ቤቶች መምሪያ ሥር ተዋቀሯል፡፡ ይህ የዋና ጸሐፊው ገለጻ ሦስት መሠረታዊ ግድፈቶች አሉት፡፡

የመጀመርያው ማኅበሩ ለሰንበት ት/ቤቶች ያለውን ንቀት ያሳያል፡፡ ራሱ አባላቱን በሰን በት ት/ቤት ተሳተፉ የሚል ማኅበር የሰንበት ት/ቤት ዕውቀት ያልተማሩ ሰዎች መገ ለጫ አድርጎ ማቅረቡ አስተዛዛቢ ነው፡፡ ምናልባት ዛሬ ዛሬ አንዳንድ አባላቱ ቲዎሎጂ ኮሌጅ እየገቡ ተማሩ እንጂ ከሰብሳቢ እስከ አባል የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች እና ውጤቶች ነበሩኮ፡፡ ይህ አገላለጥ ሰንበት ት/ቤቶችን ከመናቅ ባሻገር ራስን መስደብም ጭምር ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ አሁን ሰንበት ት/ቤቶች የደረሱበትን የዕድገት ደረጃ ያለማገናዘቡ ነው፡፡ እንደ መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ጴጥሮስ ወጳውሎስ፣ ዓምደ ሃይማኖት፣ ወዘተ ያሉት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀዳማይ ካልኣይ እያሉ የሚሰጡት ትምህርት የሚያው ቅላቸው አጥተው እንጂ ከሴሚናሪ አልፎ ለኮሌጅ የሚበቃ ነበረ፡፡ በሰንበት ት/ቤቶች የሚሰጠውን ትምህርት በሚገባ መማርማ የክብር መግለጫ እንጂ የተዋርዶ ማሳያ አልነ በረም፡፡

በሦስተኛ ደረጃስ ቢሆን የሥራ አመራር አስፈጻሚ አባላቱ ከየትኛው የአብነት ትምህ ርት ቤት ወይስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ወጥተው ይሆን አመራር የሆኑት) አመራ በዚህ መንገድ ለመምራት ብቁ ካልሆነማ ከሰንበት ት/ቤት በላይ ዕውቀት ላላቸው ማስረከብ ነው፡፡

ማኅበሩ ይህንን አመለካከት ካላረመው አንደኛ ከተመሠረተበት ዓላማ ጋር ስለሚጣረስ ሁለተኛም የማኅበሩን አገልግሎት ከሚደግፉት ሰንበት ት/ቤቶች ጋር ስለሚያጋጨው ለአገልግሎቱ አደጋ ነው፡፡ እኛ አባላቱም የማንቀበለው ነው፡፡

4 የሕግ ጥሰቶች
በቃለ መጠይቁ ከተፈጸሙት ስሕተቶች አንዱ የራሱን የማኅበሩ ሕግ መጣሱ ነው፡፡ ማኅበሩ የአባላት መከታተያ እና መቆጣጠርያ መመርያ አለው፡፡ የአባላትን የሃይማኖት፣ የሥነ ምግባር እና የአሠራር ግድፈቶቸ የሚከታተልበት፣ የሚያርምበት እና የሚ ቀጣበት ሕግ፡፡ ስለ ቀሲስ ሰሎሞን ሙሉጌታ የተሰጠው መግለጫ ከዚህ ሕግ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ይህ ሕግ ከወረዳ ማዕከል ጀምሮ እስከ ሥራ አመራር የሚደርስ የመምከርያ እና የመቅጫ መሥመሮች አሉት፡፡ ቀሲስ ሰሎሞን በወረዳም ይሁን በማዕከል የአባላት እና ማዕከላት ዋና ክፍል አልተጠየቀም፣ አልተመከረም፡፡ ይህንን የሚያሳይ ቃለ ጉባኤም የለም፡፡

ቀሲስ ሰሎሞን በሚያደርጋቸው ሥራዎች አለመስማማት እና መቃወም ይቻላል፡፡ ሕገ ማኅበሩን መጣስ እና ግለሰባዊ ርምጃ መውሰድ ግን አይቻልም፡፡ ሙሉጌታ «ወንድምህ ቢበድልህ ብቻህን ንገረው፣ ሁለት ሦስት ሆነህ ንገረው፣ ካልሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገ ራት፣ ካልሰማ ከርሱ ተለይ» የሚለውን ለሰሎሞን ጠቅሶታል፡፡ ግን አመራሩ በዚህ መን ገድ ሄዷልን) እስኪ ቃለ ጉባኤውን እና ውሳኔውን ያሳየን) ይህንንስ ራሱ ቀሲስ ሰሎ ሞን ያውቃልን) እስኪ በመከታተያ እና መቆጣጠርያ መመርያው በየትኛው አንቀጽ መሠረት እንደተኬደ ይገለጥልን፡፡

ከሕገ ማኅበር ውጭ አንድ አመራር የተጣላውን እና የተቀየመውን ሰው ሁሉ እያወገዘ መግለጫ ከሰጠማ አባላት ምን ዋስትና አላቸው) በጣም የሚያስገርመው ነገር ሙሉጌታ ይህንን ከተናገረ በኋላ አመራሩ የወሰነው ችግሩ በሙሉጌታ እና በሰሎሞን ውይይት እንዲፈታ ነው፡፡ ሙሉጌታማ መናገር ያለበትን ተናግሯል፡፡ ማለት ያለበትን ብሏል፡፡ ጥይቱን ተኩሷል፡፡ ጲላጦስ እንዳለውም «የጻፈውን ጽፏል» ከዚህ በኋላ ከሰሎሞን ጋር ምን ይወያያል) ሰሎሞንን ማወያየት ያለበትኮ አመ ራሩ ራሱ ነበር፡፡ አንድ ሰው ተኩሶ ሌላን ሰው መታው፡፡ የተመታው ሰውዬ ተመታሁ ሲል እስኪ የትኛው አካልህ ላይ እንደተመታህ ከተኮሰው ጋር ተወያይ የሚለው ማነው)
ይህንን የሕገ ማኅበር ጥሰት አመራሩ በዝምታ ማለፍ ከመረጠ አበላቱ መጮኽ አለብን ማለት ነው፡፡ በቤታችን ሕግ ሳይሆን ሰው የበላይ ሆኗልና፡፡ ሕጉ ሰዎችን ሳይሆን ሰዎች ሕጉን መምራት ጀምረዋል ማለት ነው፡፡ ለማኅበር ከፈጣሪ በላይ ዋስትናው ሕገ ማኅበር ነው፡፡ ሕገ ማኅበሩን አመራሩ ካፈረሰው ሕግ የለምና ማኅበር ፈርሷል ማለት ነው፡፡ እናም አማራጫችን ሁለት ነው፡፡ ወይ ሕጉን ወደ ቦታው መመለስ፤ ያለበለዚያም ጥቂት ግለሰቦች በአናርኪስትነት ሕጉን ሲተኩት እና ማኅበር ሲፈርስ ማየት፡፡ እኔ ግን የመ ጀመርያውን እመርጣለሁ፡፡ ምናልባትም አብዛኞቹም አባላት ጭምር፡፡

5/ እውነትን መካድ
ዋና ጸሐፊው ዳንኤል ከመደበኛ አገልጋይነቱ እንዴት እንደለቀቀ አስረድቷል፡፡ ምንም እንኳን ጋዜጠኛው ባይጠይቀውም፡፡ ይህ መልሱ ሁለት ነገሮች ይነግረናል አንዱ በሥራ አመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ በሂደት ላይ ያለን ነገር ለገበያ ማውጣት የሥነ ምግባር ችግር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የሆነውን ነገር በመካድ አዲስ ታሪክ ለመተረክ መሞከር ቂመኛነትን የሚያሳይ ነው፡፡ በግሌ ደግሞ በደል ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሙሉጌታ ያደ ረሰብኝን ገልጬ እርሱም አለኝ የሚላቸውን ቅሬታዎች አቅርቦ ተነጋግረን ነበር፡፡ ያ መነጋገር ችግሩን እንዳልፈታው በዚህ ቃለ መጠይቅ አሳይቶኛል፡፡ ሆን ተብሎ የሰውን ስም ለማጥፋት የተነገረ ነውና፡፡

በዚህ ረገድ ሰፋ ያለ ማብራርያ ወደፊት እሰጥበታለሁ፡፡ አሁን ሌሎቹን ነገሮች እንዳ ያደበዝዝ ብዬ ለጊዜው ትቼዋለሁ፡፡

ድኅረ ቃለ መጠይቅ
ቃለ መጠይቁ በመጽሔቱ ታትሞ ከወጣ በኋላ በአባላትም ሆኑ አባላት ባልሆኑ ሰዎች ዘንድ መነጋገርያ ሆነ፡፡ እውነቱን ለመናገር አብዛኞቹ የአመራር አባላት መጽሔቱን አላ ነበቡትም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ዛሬ የመጣ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ አመራሩ የሚተችበት ጠባይ ነው፡፡ እንኳን የውጭ ጋዜጣ እና መጽሔት ሐመር እና ስምዐ ጽድቅንም የማያ ነብብ አመራር ነው እየተባለ ይተች ነበርና፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ አመራሩ ሲሆን ጊዜ ወስዶ ሚዲያዎችን መከታተል ካልሆነም የሚ ዲያ ሞኒተሪንግ አገልግሎት ሊኖረው ይገባ ነበር፡፡ በየትኛውም ተቋም ከፍተኛ የአመ ራር አካላት የሚዲያ ሞኒተሪንግ አገልግሎት አላቸው፡፡ ይህ ክፍል በወቅቱ የታተሙ፣ ብሮድካስት የተደረጉ እና በኤሌክትሮኒክስ ማስተላለፊያዎች የተለቀቁ መረጃዎችን ተከ ታትሎ፣ አጠናቅሮ እና የውሳኔ ሃሳብ አዘጋጅቶ የሚያቀርብ ክፍል ነው፡፡ አመራሩ ይህ ቢኖረው ኖሮ ብዙ መረጃዎች ባላመለጡት ነበር፡፡

በሌላም በኩል ይህ ወቅት የፍቅር እና የፋሽን መጽሔቶች ሳይቀሩ ቢያንስ አንድ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ይዘው የሚወጡበት ወቅት እንደመሆኑ አመራሩ ጉጉ ሆኖ ነገሮችን መከታተል ነበረበት፡፡ ያ አልሆነም፡፡ እኔም ጉዳዩን ለሰብሳቢው እና ለኦዲት እና ኢንስፔክሽን ክፍሉ አቀረብኩ፡፡ ሙሉጌታ እስኪመጣ ታገሥ፡፡ ከመጣ በኋላ ተነጋግረን ውሳኔያችንን እንነግርሃለን ተባልኩ እና ተቀበልኩ፡፡ መጀመርያ በጉዳዩ የተነጋገሩት ሁለቱ ጽ/ቤቶች ናቸው፡፡ ጉዳዩን ገምግመው ስሕተት መሆኑን እና መታረም እንዳለበት አመኑ፡፡ ነገር ግን ሙሉጌታ ከሀገር ውጭ ስለነበር እስኪመጣ እና ሃሳቡን እስኪገልጥ ለመጠበቅ አሰቡ፡፡ እንደ እኔ እምነት ይህ ትክክለኛ አሠራር ነው፡፡ ተጠያቂው ራሱ መልስ በማይሰጥበት ሁኔታ ስለ ተጠያቂው መወሰን አይገባምና፡፡ በጉዳዮቹ ጥያቄ ያላቸው አካላትም እርሱ እስኪመጣ እንዲጠብቁ ተነገ ራቸው፡፡



ሙሉጌታ መጣ፡፡ ሥራ አመራሩም ተሰበሰበ፡፡ ጽ/ቤቶቹ የደረሱበትን ሃሳብ አቀረቡ፡፡ ከዚያም ሙሉጌታ ተጠየቀ፡፡ መምህር ሙሉጌታ ነገሮችን በሦስት ዘውግ አብራራቸው፡፡ አንደኛ ጥያቄዎቹ ሆን ተብለው እርሱን አደጋ ውስጥ ለመጣል በጥቂት አባላት የተዘ ጋጁ መሆናቸውን፤ አቀራረባቸው ሃርድ ቶክ ይመስል እንደነበር፣ እና እርሱ ያላለው ነገር በመጽሔቱ መውጣቱን ተረከ፡፡ በተለይም ጥያቄዎቹን ሆን እርሱን ጠልፈው ለመ ጣል ብለው ተንኮለኛ አባላት አውጥተዋቸዋል የተባለውን በተመለከተ አንዳንድ የአመ ራሩ አባላት ስለ ተንኮለኞቹ ሃሳብ ሲጨምሩበት እና ሥራው ሤራ መሆኑ ሲገለጥ የአመራር አካላቱ ሃሳብ ተቀለበሰ፡፡ በጉዳዮቹ ላይ ከመነጋገር ይልቅም እንደ ተለመደው ወደ ኀዘኔታ እና ወደ ሤራ ማጋለጥ ሂደት ገባ፡፡ እርሱ የተናገራቸውን ባይናገር መል ካም እንደሆነ ታምኖ ነገር ግን ምንም ማስተካከያ መሰጠት እንደሌለበት ተወሰነ፡፡

ይህ ስብሰባ ሲደረግ ሦስት ነገሮች ታስቦባቸው ነበር፡፡ አንደኛ ለአመራሩ ምን መነገር እንዳለበት በሥውር አመራሩ ተመክሮበት፣ ሁለተኛ የችግሩ መነሻ መልሱ መሆኑ ቀርቶ ጥያቄው እንዲሆን ተደርጎ፤ ሦስተኛ ደግሞ ስለ ጉዳዩ በቂ መረጃ አለው ተብሎ የታሰበው ዓባይነህ ካሤ የማይኖርበት አጋጣሚ ተመርጦ፡፡ በወቅቱ ዓባይነህ ጎንደር ነበርና፡፡ እንደ ተባለው ግን ጥያቄው በሤራ የተዘጋጀ አልነበረም፡፡ ለሙሉጌታ ጥያቄዎቹ ቀድ መው ደርሰውታል፡፡ አይቷቸዋል፡፡ ተዘጋጅቶባቸዋል፡፡ ይህ ግን ለአመራሩ አልተነገረ ውም፡፡ ሌላው ቀርቶ ቃለ መጠይቁን ራሱ ጨምሮ እንዲቀዳ እና እንዲያስቀርም ተመ ክሮ ነበር፡፡ ግን አላደረገውም፡፡ አንድ ሰው ጥያቄዎቹ ቀድመው በደረሱት ሁኔታ ሃርድ ቶክ ሊኖረው አይችልም፡፡ ሃርድ ቶክኮ ጋዜጠኛው እዚያው እያፋጠጠ የሚጠይቀው ከቃለ መጠይቅም የወጣ ሂደት ነው፡፡

ደግሞስ የፈለገውን ዓይነት ጥያቄ ቢጠየቅ ምን ችግር አለው) እርሱ በመልሱ እስከ ተማመነ ድረስ ማንም ቢፈልግ ሰይጣን ቢፈልግ መልአክ የገለጠለትን ለምን አይጠይቀውም፡፡ አመራሩስ ቢሆን ጥያቄው ነው እንጂ መልሱ ችግር የለውም እንዴት ይላል) በአውሬዎች ኮሜዲ ላይ የበላሁሽ ከታች ሆነሽ ውኃውን ወደ ላይ ስላደፈ ረስሽብኝ ነው እንዳለውና በፍየሏ እንደፈረደው ነብር ሆንን ማለትኮ ነው፡፡

በሌላም በኩል እርሱ ያላለውን ነገር እነርሱ እንደጨመሩበት ለአመራሩ ገልጧል፡፡ ይህ ግን በኋላ ለዕንቁ መጽሔት ዝግጅት ክፍል ካቀረበው ምስጋና ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ ያወጡት ነገር የተናገረውን መሆኑን፣ በዚህም ደስተኛ እንደሆነ ገልጦላቸዋል፡፡ እንዲ ያርሙት የነገራቸው «ማኅበረ ሰላም» የሚለውን «ሰላማ» እንዲሉትና «የማኅበሩ ሥራ አመራር የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይሆንም» ከሚለው ላይ «ሥራ አስፈጻሚም» የሚል እንዲጨምሩ ብቻ ነው፡፡ በሌሎቹ ግን ተስማምቷል፡፡

ከሥራ አመራሩ ስብሰባ ቀጥሎ የተደረገው የአስፈጻሚው ስብሰባ ነበረ፡፡ አስፈጻሚው ሥራ አመራሩ በጉዳዩ ስለተነጋገረና ስለ ወሰነ ጉዳዩን ማየት እንደማይገባው ወሰነ፡፡ ይህ ችግር የሁለት ሰዎች ብቻ መሆኑን ገለጠ፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ማዕከላት በጠቅላላ ጉባኤ ያቸው እንዳላነሡት የሚንጫጩትም ሦስት የማዕከላት ሰዎች መሆናቸውን ጨምሮ አሳሰበ፡፡ እነዚህንም ጸጥ ማድረግ እንደሚገባ አመለከተ፡፡ በነገራችን ላይ አስፈጻሚዎቹ ወደ ስብሰባው ከመግባታቸው በፊት «የጀሞ ጉባኤ» ተደርጎ ከአንድ ሰው በቀር ተሰብ ስበው ወስነው ነበር የመጡት፡፡

ከዚህ ሁሉ በኋላ ሥውር አመራሩ አንድ ውሳኔ ወሰነ፡፡ ለመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ መልስ ሊሰጡ የሚችሉ አባላት እነማን ናቸው) የሚለው ተለየ፡፡ በእነዚህ አባላት ላይ መረጃ እንድትሰበስብም የመረጃ ክፍል ኃላፊዋ ተነገራት፡፡ እርሷም ባለፈው ሳምንት ሥራዋን ትታ መረጃ ስትሰበስብ ከረመች፡፡

በዚህ ሁኔታ አመራሮቹ የዘጉትን መንገድ ለማስከፈት የተለያዩ አካላት ሙከራ አድርገ ዋል፡፡ መንገዱ ሁሉ ግን ዝግ ነበረ፡፡ ዓርብ ሐምሌ 8 ቀን የአሜሪካ ማዕከል ሰብሳቢ ያደ ረገውን ጥረት ጨምሮ፡፡ መንገዶቹ ሁሉ ግን ተዘጉ፡፡ ውሳኔያቸው እንደ ሜዶን እና ፋርስ ሕግ የማይለወጥ ሆነ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም የቤተ ክርስቲያን መሆኑ ቀርቶ የጥቂት ግለሰቦች «ፒኤልሲ» ሆነ፡፡

እንግዲህ ከዚህ በኋላ የሚቀረው ምንድን ነው) ሌሎቹን መንገዶች መጠቀም ብቻ፡፡ እነዚህ መንገዶች አንደኛ ማኅበራዊ ኔትወርኮችን ተጠቅሞ ሃሳብን መግለጥ፣ ለሚመ ለከተው የበላይ አካል አቤቱታ ማቅረብ፣ ወይም ማዕከላቱ በማኅበራቸው ላይ ማስተ ካከያ እንዲያደርጉ ማድረግ፡፡ ሦስቱም የሚያስኬዱ መንገዶች ናቸው፡፡ የሚሰጠው መፍ ትሔው ግን ችግሩን ከሥሩ የሚነቅል እና እንዳይደገሙ የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡

ምክንያቱም በማኅበሩ አካሄድ ለመፍትሔ የሚያስቸግሩ ሁለት ሰንካላ አስተሳሰቦች አሉ፡፡ አንደኛው ምንጊዜም ችግሮችን በሽምግልና ብቻ የመፍታት አካሄድ ነው፡፡ ሽም ግልና አንዱ የችግር መፍቻ መንገድ እንጂ ብቸኛው አይደለም፡፡ በተለይ የሃሳብ ልዩ  ነቶችን በሽምግልና መፍታት አይቻልም፡፡ ለሁሉም ነገር ተጎራረሱ፣ ተሳሳሙ ማለት መፍትሔ አያመጣም፡፡ እንደ ብጉንጅ ፍርጥርጥ አድርጎ ችግሮችን ማውጣት እና መወ ያየት፣ ብሎም መከራከር እንጂ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ለማኅበራችን ያለን የድመት ፍቅርም አስቸጋሪ ነው፡፡ የማኅበሩን ስሕተቶች በመሸፈን እና በመሠወር ማኅበሩን የምናድነው ይመስለናል፡፡ ጭንቀታችን ችግር እንዳይኖር ሳይሆን ችግር እንዳይነገር ነው፡፡ ከችግሩ መኖር ይልቅ የችግሩ መገ ለጥ ያሳስበናል፡፡ ችግሩን ያልተናገረ ደግሞ መፍትሔ የለውም፡፡ እናም መሸፋፈኑ ማኅ በሩን ጎዳው እንጂ አልጠቀመውም፡፡ ስለዚህ ችግሩን ገልጠን እናስጣው፡፡ ፀሐይ ሲመታው ይደርቃል፤ ሽታውም ይጠፋል፡፡

ከስድስት ወራት በፊት ተፈጥረው በነበሩ ክስተቶች ምክንያት በኢሜይሎች ሃሳብ መለዋወጥ ሲጀመር «በውይይት ይፈታልና አቁሙ» ብለው ስድስት ታላላቅ ወንድሞች ገሠፁ፡፡ ብዙዎችም ተግሳፃቸውን ተቀብለው አቆሙ፡፡ ለካስ ዓላማው ችግሩን መፍታት ሳይሆን ኢሜይሎችን ማስቆም ነበር፡፡ እነዚያ ስድስት ወንድሞችም ከዚያ በኋላ ነገር ዓለሙን ርግፍ አድርገው ተውት፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የጥቂት ሰዎች አይደለም፡፡ የብዙኃን ነው፡፡ የአባላቱ ብቻም አይደለም የምእመናን ሁሉ ነው፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን ኪሳራ የትውልድ ኪሳራ ነው፡፡ ስለዚህም ማኅ በረ ቅዱሳንን ማዳን ትውልዱን ማዳንም ነው፡፡ እናም ዝም ሊባል አይገባውም፡፡ የው ስጥን ችግር በውጭ ችግር ማስቀየስም መፍትሔ አይሆንም፡፡ የውስጡ ችግር ሲባባስ መከረኛውን ተሐድሶ እያነሡ የአባላቱን እና የምእመናኑን ቀልብ ማሳትም የትም አያ ደርስም፡፡ አመራሩ በሩን ለውይይት ክፍት ማድረግ አለበት፡፡ ውይይቱም የማዕከላት አባላት ጭምር በተገኙበት መደረግ አለበት፡፡ ለመሆኑ ግን ይህንን ሁሉ ችግር የወለደው የማኅበሩ መሠረታዊው ወይንም አንኳር ችግር ምንድን ነው) እንዴትስ እዚህ ሊደርስ ቻለ) መፍትሔውስ) እቀጥላለሁ፡፡

ዳንኤል ክብረት
    አባል

ግልባጭ
·    ለማኅበሩ ሰብሳቢ
·    ለዋና ጸሐፊው
·    ለኦዲት እና ኢንስፔክሽን አገልግሎት
·    ለዋና ክፍሎች
·    ለሁሉም ማዕከላት
·    ለሚመለከታቸው አባላት

No comments:

Post a Comment