Saturday, February 2, 2013

አይቴ እረክቦ ለጋኔን ከመ እብሎ እንብየ ለጋኔን?

REad in PDF: Ayte Arekebo
መሪ ጥቅስ:
"በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። አመንዝሮች ሆይ፥ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። ወይስ መጽሐፍ በእኛ ዘንድ ያሳደረው መንፈስ በቅንዓት ይመኛል ያለው በከንቱ እንደ ተናገረ ይመስላችኋልን? ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል። (7) እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙከእናንተም ይሸሻል፤ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ። ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።" ያዕቆብ 4፣ 1- 8
የጽሑፉ ዓላማ: ለሸቀጥ፣ የዋኁን ሕዝብ ለማታለልና ብሎም ለማደናገር ሲባል ብቻ በቆርጠህ ቀጥል ሥጋዊ መርህ እንዲሁም ፈሪሐ እግዚአብሔር በሌለበትና በማን አለብኝነት መንፈስ በድፍረት ተጀምሮ በቁንጽል የተተወ ቃለ-እግዚአብሔር ለመሙላት ተፃፈ። ከዚህ ያለፈ ጸሐፊው ሆኑ ጽሑፉ አንዱን በመደገፍ ሌላውን የማጥቃት ዓላማ የላቸውም። አሁንም ከታሰበበት ተዘግቶ የሚዘጋ በር የለምና ሁለቱም የሃይማኖት መሪዎች ወደ ልባቸው ተመለሰው ከመከሩ ሰላም የማያወርዱበትና ዕርቅ የማይመጣበት ምንም ምክንያት የለም ብለው ያምናሉ። ስድስተኛ ፓትሪያሪክ ለመምረጥና ለመሾም እየተጣደፈ የሚገኘው ሥርዓት አልባው የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ በተመለከተ በሚቀጥለው ጽሑፌ በስፋት የምንዳስሰው ይሆናል። 


የጽሑፉ ውስኑነት: ጽሑፉ መቀመጫው ሰሜን አሜሪካ ያደረገ ጉባኤ የከሸፈውን "ዐርቀ ሰላም" ተከትሎ በያዝነው ወር 01/17/13 እ.አ.አ ለሰጠው መግለጫ ለማደናገሪያ እንደ መሪ ጥቅስ ሆኖ የተሰፈረውን አምላካዊ ቃል ዙሪያ ላይ የሚያትት ሥራ እንጅ ጽሑፉ ሙሉ የመግለጫውን ይዘት አይዳስስም። 
ሐተታ:
የሐዲስ ኪዳን መልዕክቶች በምናነብበት ጊዜ የደብዳቤው ይዘትና መንፈስ፣ የመልዕክቱ ተቀባዮች/የተደራስያኑ ማንነት፣ መልዕክቱ በተፃፈበት ወቅት የነበረውን የአማኞቹ ውስጣዊ ሆነ ውጫዊ ገጽታ፣ ፀሐፊው ደብዳቤው ይጽፍ ዘንድ ያስገደደበት በዋናነት ሊጠቀስ የሚችል ተጠቃሽ ምክንያት፣ በይዘቱም ታሪካዊ መዋቅሩና ስዋስዋዊ አገባቡ ለይተህ ማወቅና በተጨማሪም የመልዕክቶች የአተረጓገም ስልት/ዜዬ በመጠኑም ቢሆን ማጥናቱ አንባቢ የመልዕክቱን ጭብጥ በቀላሉ እንዲያገኘው ይረዳዋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን አንድ ተራ መጽሔትና ደብዳቤ በምናነብበት መነጽር መልዕክታትን ለማንበብ የተሞከረ እንደሆነ ለህይወት የተፃፈ ቃል ለስህተትና ለጥፋት ሊዳርገን እንደሚችል አያጠያይቀንም።
በድሮ ዘመን በዋናነት ከሚጠቀሱ የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች መካከል ከ95% በላይ የሚሸፍነው በሥነ መለኮት ሊቃውንት መካከል ይነሱ የነበሩት ጥያቄዎች፣ ሙግቶችና በአመለካከት ካለመግባባት የተነሳም ይፈጠሩ የነበሩ ልዩነቶች ነበር የብዙዎች ሰላም ያውክና ይረብሽ የነበረው። አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ በአንጻሩ ጵጵስና በድንቁርና ሆነና 95% የቤተ እምነቱ ተከታዮች ሰላም እየነሳ የሚገኘው የሃይማኖት መሪዎች ራስ ወዳድነት፣ በሙስና መዘፈቅ፣ ከግብረ ገብነት ጉድለት የተሳ የሚመጣው እልም ያለ ዓለማዊነትና ምንደኝነት መሆኑ ሳስበው እጅግ አሳዝኖኛል።  
ወደ የዕለቱ መልዕክቴ ልመለስ። አሁንም ተቆርጦ ለማጭበርያ የዋለውን ቃለ እግዚአብሔር ፍቺ ከመመከታችን በፊት የጽሑፉ መልዕክት በሚገባ በደንብ እንዲገባዎትና የእነ አቡኑ እርድና አይሉት እውቀትም ኩልል ቅልብጭ ብሎ ይታዮት ዘንድ ለአፍታ የምዕራፉ መነሻ ሐሳብ ወደ ሆነው ቃል ልመልሶት። እዚህ ስፍራ ላይ (ቁጥር 1 ማለት ነው) ያዕቆብ እንዲህ ሲል ነበር መልዕክቱን በጥያቄ መልክ የጀመረው "በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ?” እንዲል። ልብ ይበሉ! ያዕቆብ እንዲህ ብሎ ሲጽፍ እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ሳይሆን በእርግጠኝነት በመልዕክቱ ተቀባዮች መካከል ዘንድ የተፈጠረና የሰማው ነገር ለመኖሩ ምንም አያጠራጥርም። በእነዚህ "አማኞች" መካከል የተፈጠረ ችግርም ቀላልና ዕለታዊ የሆነ ሰጣ ገባ አሳስቦት የፃፈው መልዕክት እንዳይደለም ሙሉውን ምዕራፍ በማንበብ ልናረጋግጠው የምንችል እውነት ነው።
በእነዚህ ሰዎች መካከል ስለ ተፈጠረው በአማኞች ህይወት ዘንድ ፈጽሞ መታየት የማይገባውና የማይጠበቀው ዋልጌነት ምክንያቱ ሲያስረዳም ያዕቆብ እንዲህ ሲል ነበር የገለጸው "በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ሲል በማያሻማ አገላለጽ ግልጽ እንዳደረገው ያዕቆብ ትኩረት ሰጥቶ መልዕክት የጻፈበት ምክንያት:
Ø በመካከላቸው ሰላም የሚባል ነገር ጠፍቶ መራራ በሆነ ከልክ ባለፈ ጥላቻ መጠላለፋቸው፣
Ø በአማኞች ሕይወት ዘንድ ጨርሶ መታየት በማይገባው ህይወት በመዘፈቃቸው፣
Ø ሌላው ቢቀር በፍጥረታውያን ዘንድ አንኳ ሳይቀር እንደ ጽያፍ በሚቆጠረው አስነዋሪ ድርጊት በአንፃሩ ደግሞ በእነዚህ ሰዎች ህይወት የጌጥና የሽልማት ያክል ተከናንበው በውንብድና መሰማራታቸው፣
Ø ራሳቸው እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ቆጥረው ሲያበቁም በሥራቸው ሰይጣን የሚያሰለጥኑ፣
Ø ዓለምን ከመውደዳቸው የተነሳም ታማኝነት የጎደለበት ህይወታቸውንና ለመንፈሳዊ ነገር ያላቸው ደንታ ቢስነት የሚያስከፍላቸው ዋጋ ለማመላከትና፣
Ø በአደባባይ ስለወጣ አሳፋሪና አስነዋሪ አመጸኛ ማንነታቸውን በመቃወም አፋጣኝ እርምጃ ይወስዱ ዘንድ ይህን ፃፈላቸው። እንደው ዝቅ ብለን ቁጥር 4 የተመለከትን እንደሆነ ያዕቆብ እነዚህ ሰዎች "እናንተ አመንዝሮች ሆይ!” በማለት ሃይለ ቃል በመጠቀም ሲጠራቸው ነው የምናገኘው። ታድያ የሊቃነ ጳጳሳቱ የእርስ በርስ መናከስና ትርምስ ዋና መንስኤ ከዚህ አልፎ ምን ሊሆን ይችላል ይላሉ ውድ አንባቢ? እንግዲህ ይህን የመሰለ የመልዕክቱ ማዕከል የሆነ ቃል ትተው ነው ቢቆረጥ ለማደናገር አመቺ ሆኖ ስላገኙት "ኦሆ በልዎ ለእግዚአብሔር ወእንብየ በልዎ ለጋኔን”? ሲሉ ከመናገር ያልተመለሱ። “አሳ ጎርጓሪ፣ ዘንዶ ያወጣል!" ይሉሃል ይሄ ነው።
እንደው ያዕቆብ አልጻፈልንም እንጅ ጠበኞቹ "ምክንያታችሁ ምንድ ነው?” ተብለው ተጠይቀው ቃላቸው በመጽሐፍ ቢፃፍ ኖሮ "ቀኖና ተጣሰ" ከማለት እንደማይመለሱ ነው የማምነው። ከሁሉም በላይ የገረመኝ ግን የእግዚአብሔር ቃል የደርግ መፎክር ሆኖ ለመግለጫችን ምን ርዕስ እንስጠው ተብሎ አንዱን ሲጥሉ ሌላውን ሲመርጡ በስተ መጨረሻ "ኦሆ በልዎ ለእግዚአብሔር ወእንብየ በልዎ ለጋኔን”? ብሎ የጠቆመ ሰው ነው። ለመሆኑ ሰው ሰይጣን የሚቃወመው የት ቢያገኘው ነው? ከዚህ በላይ አስቀያሚና ሰይጣናዊ ገጽታና ሥራስ የት ተፈልጎ ቢገኝ ነው? እግዚአብሔር አይዘበትበትም!
 ጥበብ በጎዳና ላይ ትጮሃለች! አለ አግባብ ተቆርጦ ለልዩ አጀንዳ መጠቀሚያ ይውል ዘንድ የተደረገው ("ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ") የሚለውን ማለት ነው"እንግዲህ" ከሚል አያያዥ/"አሻጋሪ" ቃል ተከትሎ በመምጣቱ ቃሉ ራሱን የቻለ ሙሉ ዐረፍተ ነገር/መልዕክት ሳይሆን ቀደም ሲል ከቁጥር አንድ ጀምሮ ስድስት ያለውን በዋናነት ራስህን ለእግዚአብሔር ስለማስገዛት፣ ጠበኝነትና ትዕቢትን ስለማስወገድ ለተነገረው መልዕክት እንደ መቋጫ/ማሰሪያ የሰፈረ ቃል ነው። ለመሆኑየእግዚአብሔር ቃል ቆርጠህ ከመቀጠል የከፋ የጋኔን ስራ ኖሮ ነው ሰዎች ጋኔንን ፍለጋ ይሰማሩ ዘንድ መግለጫ መስጠት ያስፈለገው? ደግሞስዲያብሎስን መቃወም ማለት በሬድዮና በቴሌቪዥን መስኮት እየወጣህ መሸለልና መፎክር ማሰማት ማለት ነው ያለ ማን ነው? ቅድሳት መፃህፍት እንደሚያስተምሩት ዲያብሎስን መቃወም ማለትየዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ:
v የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።
v መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋርበሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ።
v እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤
v በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤
v የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።
v በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በመጨረሻም
v በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ …" (ኤፌ 6፣ 11-18) አለ እንጂ አዋጅ! አዋጅ! ወዮልህ/ሽ ሰይጣን! ማለት ለምን ተፈለገ? የምትሆኑት አጥታችሁ አጀንዳ ለማስቀየስ ካልሆነ በስተቀር። ለነገሩ እናንተ የሚያስፈልጋችሁ እኮ ባላንጣዎችን በመደራደርና በማነጋገር የተካነ ባለሞያ ሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር መንፈስ በጥበብ ቃል ልክ ልካችሁን የሚነግራችሁ የታጠቀ አንድ ሰው ነው ያጣችሁ።
ሌላው ሙሉውን መግለጫ አንብቤ እንደጨረስኩ በድጋሜ መለስ ብዬ ያነበብኩት እንደገና ርዕሱን ነበርና በዚህ ወቅት ሌላ ወደ አእምሮዬ የመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የበልአም መሰሪነትና የማትታጠፈው የእግዚአብሔር ክንድ ስለሚተርከው የመጽሐፍ ክፍል ነበር። በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በልዓም ከባላቅ የተቀበለው ዳጎስ ያለ ክፍያ እስራኤል ረግሞ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት እንጅ በእስራኤል ላይ "ከያዕቆብ ከኮብ ይወጣል ከእስራኤልም በትር በትር ትነሣል ብሎ" ለመተንበይ አልነበረም። እዚህ ላይ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ገብቼ ከመተንተን ለጊዜው መቆጠብን ብመርጥም ያልሞተ ምኞታችሁ ለማስደሰት በእግዚአብሔር ቃል አመካኝታችሁ ደጋፊ ለማሰባሰብ ያደረጋችሁት ድርጊት ግን ለጊዜው አለመሳካቱን ብቻ ውሎ አድሮ ለውርደት እንደሚሆንባችሁ ስገልጽላችሁ በአክብሮት ነው። እንደው አንድ አስተዋይ ሰው "እኮ እንዴት?” በማለት ይጠይቅ ይሆናል። መልሱ እንደሚከተለው ይሆናል።
የሀገሬ ሰው "ሲባል ሰምታ ዶሮ ...” ሲል እንደሚተርተው ቁምነገሩ ያለው ወዲህ ነው።"እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት። ክፉው መንፈስ ግን መልሶ ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ? አላቸው። ክፉው መንፈስም ያለበት ሰው ዘለለባቸው ቆስለውም ከዚያ ቤት ዕራቁታቸውን እስኪሸሹ ድረስ በረታባቸው አሸነፋቸውም።" (የሐዋ. ሥራ 19፣ 15) ተግባብተናል ብዬ ስለማምን ወደ ሚቀጥለው ክፍል ልለፍ።
ደግሞም አታፍሩምና በገዛ ራሳችሁ ምኞትና ፍትወት ሰክራችሁ አሻፈረን ስትሉ በሰላም ፈንታ ሁከት መርጣችሁ ስታበቁ ወዳችሁ ለገባችሁበትና ሰላም ላለመፍጠርም ቆርጣችሁ ለወሰናችሁት ውሳኔ ከበረቱ ውጭ የሰፈሩት፣ የሚያስቡትና የሚያልሙት ህልም ሁሉ እውነትና የሆነም የሚመስላቸው ህልመኞች፣ ለቃሚዎችና አደጋ ጣዮች ያሉትን በመድገምና በማስተጋባት እጁና እግሩ ሰብስቦ የተቀመጠውን መንግሥት ያለ አንዳች ጭብጥ፣ በቂ መረጃና ማስረጃ ተጠያቂ ከማድረግ፣ ከመወንጀልና ከመክሰስ  አለመቦዘናችሁም ገርሞኛል። ይህን መሰረተ ቢስ ክሳችሁን ሳነብ/ስሰማም አእምሮዬ በድጋሜ በቀጥታ ያመራኝ ወደ ዘፍጥረት መጽሐፍ ነበር።
የዘፍጥረት (የሰው ልጅ ዘር) ሁሉ መጀመሪያ የሆነው አዳም በኤደን ገነት ውስጥ ሲኖር ስላ ከእግዚአብሔር በታች ሆኖ ፍጥረታትን የሚገዛ ሙሉ ሰው እንደ ነበር ተጽፎ የምናገኘው የመጻህፍት ሁሉ መጀመሪያ በሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ ነው። እንደ መጽሐፉ ምስክርነት አዳም በዚህ ፍጹም አንፃራዊ የሆነ ሰላምና ዕረፍት የሞላበት ቦታ ሲኖር (እስከ ዕለተ ውድቀቱ ድረስ ማለት ነው) ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠውን ቃል ጠብቆ ይመላለስ እንደነበረም ያስነብበናል። ታድያ ከዕለታት አንድ ቀን አዳም የተሰጠውን ቃል ከመተላለፉ የተነሳ ይህንን መተላለፉን ተከትሎም ከዚህ ቀደም በህይወቴ ይሆናል ብሎ አስቦት የማያውቅ እንግዳና አስደንጋጭ ነገር በህይወቱ ይከሰታል። ማንም ሳይነገረው የሰራውን ስራ ትክክል አለመሆኑና ስምምነቱን መጣሱ ስለታወቀበት ከተሰማው ሃፍረት ለመሸሽ ዋሻ ፈልጎ ራሱን ለመደበቅ ወሰነ።
በምዕ. 3 ቁጥር 9 ላይ "እግዚአብሔር አምላክ ግን አዳምን (ሊቃ ጳጳሳቱን) ተጣርቶ "የት ነህ? … ከእርሱ እንዳትበላ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን?” አለው እንዲል። አጥፍቶም የሰራው ስራ ስህተት/ጥፋት መሆኑን አምኖ "አዎ! አጥፍቻለሁ!" የሚል አጭር መልስ መስጠት ሲጠበቅበት የሰጠው መልስ ግን "ይህችን ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፍ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ" ሲል ነበር ሔዋንን ለመወንጀል የሞከረ። ሔዋንም እንደዚሁ ወንጀልዋ በራስዋ ላይ ከመጥራት ይልቅ "እባብ አሳሳተኝና በላሁ" ስትል እባብን መወንጀል የቀናት። አንዱን ሌላውን የመወንጀሉ ነገር ልብ ብለው ይያዙልን የመልዕክቴ ማሰሪያ ነውና። ታድያ ከቁጥር 14 ጀምሮ እስከ ቁጥር 19 በሚዘርቀው ክፍት ችሎት እግዚአብሔር በሦስቱ ላይ እኩል የሆነ ቅጣት ሲያስተላልፍና አንዳቸውም ከተጠያቂነት እንዳላመለጡ እናነባለን። ወድ አንባቢ! ይህን በመጽሐፍ የተጻፈውን ሐቅ እንደያዙ በነቃ አእምሮ ቀጥሎ ወደ ሚገኘው አንቀጽ በዝግታ ያዝግሙ።
እንደ ክርስትና እምነት አስተምህሮ አይደለም መሪ አማኝ ሁሉ ሰላምን አጥብቆ ይሻና ይከታተላትም ዘንድ ለመታትዘዙ የሚያጠያይቀን አይሆንም። የሃይማኖት መሪዎች በተከታዮቻቸው ዘንድ መልካም አርአያ/ምሳሌ መሆን እንደሚገባቸውም የሚያጠያይቀን አይመስለኝም። አንባቢ ሆይ! "መሆን ያልቻልነው እገሌና እገሊት በመሃከላችን ስለገቡ ነው" በሌላ አነጋገር ከፍ ሲል በሰፊው ከላይ እንደተመለከትነው "ባል: ያሳተችን ሚስቴ ናት! ሚስትም: ያሳተኝ እባብ ነው!” እንደማለት ይህ ሰንካላ ምክንያት ሊቃነ ጳጳሳት ከፍርድና ከተጠያቂነት ይታደጋቸዋል ብለው ያምንኑ ይሆን? ከተሳሳትኩ ለመታረም ዝግጁ ነኝ።
ፍቅር የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሆኑ ሁሉ ከሌላው ዓለም ተለይተው የሚታወቁበት ሁነኛ መለያ ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቴ ለመሆናችሁ ሰዎች አንገታችሁ ላይ በምታንጠለጥሉት መስቀልና በምታስሩት ክር ያውቃችኃል አላለም። ያለው “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሎ ተናገረ እንጅ።ፍጥረት እጁን በአፉ እስኪጭን ድረስ ልክ ያጣ ጸብነታችሁ "ግድ የለም አትገረሙብን እንዲህ ያለ ጸብ ከፍቅር ሁሉ ይበልጣል" ካላላችሁን በስተቀር በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ እናንተ ከእግዚአብሔር ልትሆኑ አትችሉም። እንዲህ ከሆነማ ጥፋቱ የእናንተ ሳይሆን ክርስትና በራሱ ቀልድ ነው የሚሆነው። እናንተ ያዬ እግዚአብሔርን አዬ ማለት ከሆነ ደግሞ እነ ጳውሎስ ቀልጠው ቀሩኧ።
በተጨማሪም በ1ኛ ዮሐ. 3:15 ላይ "ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።" ተብሎ እንደተፃፈ ፍቅርን የማያውቅ ግለሰብ ነፍሰ ገዳይ ብቻም ሳይሆን እግዚአብሔርም የማያውቅ አውሬ/አራዊት ነው። እግዚአብሔርን ከማያውቅ ግለሰብ መልካምነት መጠበቅ ደግሞ ነፋስ የመከተል ያክል ነው። ነፍሰ ገዳይን የምትከተል ነፍስ ደግሞ ነፍሰ ገዳይ የገባበት ትገባለች እንጅ ከህይወት መጽሐፍ ዘንድ ዕድል ፈንታ የላትም። "… ከእናንተም ይሸሻል" የምትለዋን ቃል የቆረጣችኃትም ወዳችሁ አይደለም። ይህን ያነበበ/የሰማ ሰው መጀመሪያውኑ ጥሎ የሚሸሸው ከሌላ ከማንም ሳይሆን ከእናንተ ራሳችሁ ነውና። ይህን ስለምታውቁ ደግሞ የሕዝብን ልብ ለመደለልና ቲፎዞ ለማሰባሰብ ስትሉ ብቻ በእግዚአብሔር ላይ ማመጽና መዝመትን መረጣችሁ።
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በሙሉ! ሕግን አለማወቅ በወንጀል ከመጠየቅ እንደማያድን ሁሉ በድንቁርና የምትገኝ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደሌለችም በቅድሳት መጽሐፍት በግልጽ የሰፈረ ሐቅ ለመሆኑ ማናችንም እንስተዋለን የሚል እምነት የለኝም። እርስዎ የማንም አይደሉም። አንድ በስሙ አምኖና በመንፈሱ ታጥቦ የተቀደሰ አማኝ "እኔ አቡነ እግሌ ነኝ!” አንተስ? "እኔም የአባ እገሊት ነኝ!” እያለ በየአደባባዩ መፎክር ይዞ የሚጮህበትና  ፌርማ የሚያሰባስብበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለውም። ምን ለመሆን? በመኖክሴ ቀሚስ ተወሽቀው የሚያልፉት ኬላ እንደሆነ የለም። ቀሚሱ እንደሆነ ብዙ ጉድ አለበት። በተረፈ እየተሰማና እየታዬ ያለው ጫጫታ ከ/የ እግዚአብሔር የሆነውን በረከት ፍለጋ የሆነ እንደሆነ ግን መንገዱ ግልጽና ግልጽ ነው ይኸውም ከእግዚአብሔር ጋር እውነትና ጽድቅ ከሞላበት ጉያ ሥር መግባት ብቻ ይሆናል። እነ አባን ተከትለው እንዳይጠፉ እንጂ አባ እግሌ ተከትለው አልመጡም ተብለው የሚዘጋቦት በር የልቦንና።  

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
United States of America

2 comments:

  1. megmria ante manhe?

    ReplyDelete
  2. ለተወደዳችሁ ወገኖቼ እንደምን ሰነበታችሁ?ሰሞኑን ወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በአዲስ ጉዳይ መጽሔት "ቅዱስ ኤልያስ በአራት ኪሎ"በሚል የጻፉትን ተመልክቼ እኔም የድርሻዬን ለማለት ብዕሬን አነሳሁ፡፡በመጀመርያ ግን ማኅበረ ሥላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ የተባሉትን ለማግኘት ሞከርኩ ተሳካልኝ ምክንያቱም አንዱ ላይ ብቻ ተመርኩዞ ሀሳብ መስጠት አስቸጋሪ ወይም ወገናዊነት ስለሚሆን ግድ እነሱን ማነጋገር ነበረብኝና አግኝቼ አነጋገርኳቸው፡፡ እነርሱ እንደሚሉት "ሕግና ነቢያት፣ ሰንበት ይከበር በተዋህዶ እንጽና ልክ በቅዱስ ኤልያስ ዘመን እንደነበረው ጳጳሳቱ፣ካህናቱ እና ዲያቆናቱ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የተባሉት እግዚአብሔርን ማምለክ በመተዋቸው እርኩሰት በደል፣ዝሙት፣ጣኦት ማምለክ፣አስመሳይነት፣ዘረኝነት፣ሴሰኝነት፣ስርቆት እና እጅግ በርካታ በደሎች በቤተክርስቲያናችን እየተፈጸሙ በመሆናቸው ቅዱስ ኤልያስ በእሱ ዘመን እንደነበሩት የበዓል ካህናት ሁሉን ሊያስተካክልና ሊያጠራ ወርዷል" እያሉ እንደሚገኙ እንዲሁም ልብሳቸው ጸአዳ በቀስተደመና፣"ኦርቶዶክስ የእኛ ሳይሆን የባዕድ ቋንቋ ነው ልንባል የሚገባው ተዋህዶ ነው ይኸውም ቃል ሥጋ ሆነ ማለት ነው፣ሕግ እና ነቢያት አንዲቷ ዕለተ ሰንበት(ቅዳሜ) ትከበር እሁድ ሰንበት አይደለም አሕዛብ የፀሐይ ቀን ማምለኪያቸውን ቀን ነው በሰንበትነት የደነገጉት እንጂ ሰንበት ልትባል አይገባም እሑድ አሃዱ አንድ ማለት ነው ስለዚህ ሰባተኛዋ ቀን ጌታ ያረፈባት ቅዳሜ በመሆንዋ ሰንበት ቅዳሜ ነች" በማለት እያወጁ እንደሚገኙ ነገሩኝ ግራ ገባኝ ነገሩን ሳጤነው መጽሀፍ ሳገላብጥ አንድም ስህተት አላገኘሁበትም ከመተቸት መጋገር አይሻልም አረ ጋርዶብን ነው እንጂ አንድም ስህትት የለበትም፡፡ምንድነው? የቱጋ ነው ስህተቱ? በጭፍን ጥላቻ ተነሳስተን የማይሆን ነገር እየጻፍን ምዕመኑን ግራ አናጋባው እኛ ከመናፍቃን ጋር ምን ህብረት አለን? ወንድሜ ዲ/ን ዳንኤል ምናልባት ግብጾች የሰሩብን ደባ አላወቁት ይሆን አረ መጽሀፍትን ይፈትሹ ብዙ ጉድ አለ እኔ እንኳ በዚህች አጭር ጊዜ ብዙ ነገር ተገነዘብኩ፡፡ቸር ሰንብቱ

    ReplyDelete