Sunday, September 9, 2012

ዜማ እስኪታደስ ጆሮ ዳባ ልበስ!

Click hear to read in PDF:Zema
በዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

“ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በነበሩበት ዘመን በሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ሥራ የሠሩ አባት ነበሩ አሁንም ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለተናዊ ዕድገት ለሀገሪቱ ሰላምና አንድነት የሚበጅ ተተኪ አባት (ፓትርያርክ) ለቤተ ክርስቲያኗ እግዚአብሔር ባወቀ መርጦ እንዲያስቀምጥ በመላዋ ኢትዮጵያና በውጭ ሀገር በሚገኙት አህጉረ ስብከት፣ ገዳማት፣ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት ከጳጉሜን 1 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 10 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ጸሎተ ምህላ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል” ይላል።
ወደ ደብዳቤው ይዘትና መንፈሱ ዘልቀን ከመግባታችን በፊት እንዲሁም ጸሐፊው ደብዳቤውን ተንተርሰው ለማስተላለፍ የሚፈልጉትን መልእክት በቀላሉ ለማግኘትም ይረዳ ዘንድ ለመንደርደሪያ ያክል ስለ መዝሙረኛው አሳፍ ጥቂቱ ልበላችሁ። አሳፍ ማለት በዳዊትና በሰሎሞን ዘመን የነበረ የመዘምራን አለቃ ሲሆን ያን ዘመን ሲጠራም ከዘመኑ እኩል "በዳዊትና በአሳፍ ዘመን" ተብሎ ስሙ የሚጠራ ብርቅ የእግዚ አብሔር ሰው ነበር:: አሳፍ በንጉሱ ፊት የሚቆም: እጅግ የላቀ ክብርና ልዩ የዝማሪ እንዲሁም የድርሰት ተሰጥኦ ያለው የእግዚአብሔር ባሪያ ሲሆን ይህን ቅባቱም ዘሩ ጭምር የወረሰ ስጦታ ነበር::
በመዝሙረ ዳዊት ከተካተቱ ዝማሪዎች መካከልም ወደ አስራ ሁለት የሚደርሱ በዚህ ሰው የተደረሱ/የተጻፉ ናቸው:: እንግዲህ የእግዚአብሔር ሰዎች በቀላሉ የሚደርሱበት ቦታም ሆነ የሚያስመኝ ህይወት አያልፉምና ይህም ሰው በአንድ ወቅት “እግሮቼ ሊሰናከሉ፥ አረማመዴም ሊወድቅ ትንሽ ቀረ … በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ፥ እጆቼንም በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ … ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ፥ መሰደቤም በማለዳ ነው … አውቅም ዘንድ አሰብሁ፥ ይህ ግን በፊቴ ችግር ነበረ1 ልቤ ነድዶአልና፥ ኵላሊቴም ቀልጦአልና።” እስከ ማለት ደርሶ በተለይ አመጸኞች በቅንና ደጋግ ሰዎች የሚፈጹምትን በደል እያየና እየተመለከተ ምን ነው ፈጣሪ? ሲል ራሱን ሲረብሽና ስምታውንም ለእግዚአብሔር ሲያቀርብ የምናገኘው።

ሰው ከልብ በሆነ ሐዘንና የህይወት ስብራት የተነሳ ያመረረና ያለቀሰ እንደሆነ እግዚአብሔር ካልደረሰለት ቀጣይ እርምጃው ገመድ ነው የሚሆነውና እግዚአብሔር ወደ አሳፍ ህይወት መጣ። ታድያ አመጣጡ ለኤርምያስ በመጣበት መንገድ በመምጣት እንዲጸልይ አልተናገረውም። ይልቁንስ ባስጨነቀው ጉዳይ ላይ ብዙ ከማሰላሰል የተነሳ ራሱን ወደ ከፋ አደጋ እንዳይጨምር ጉዳዩን በሚገባ ያስብበት ዘንድ ነበር ያነቃቃው። በዚህ ቅጽበት ነበር እንግዲህ አሳፍ የጾም ጸሎት ጊዜ መድቦ በር ዘግቶ መጮህ ሳያስፈልገው ችግሩና የችግሩ መፍትሔ ዓኑን ከፍቶ ማየት የጀመረው። እንዲህም አለ “የልቤ አምላክ ሆይ፥ ልቤና ሥጋዬ አለቀ፤ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም እድል ፈንታዬ ነው። እነሆ፥ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና ከአንተ ርቀው የሚያመነዝሩትንም ሁሉ አጠፋኻቸው። ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ መታመኛዬም እግዚአብሔር ነው በጽዮን ልጅ በሮች ምስጋናህን ሁሉ እናገር ዘንድ።”
ውድ አንባቢ እዚህ ላይ ልብ ሊሉት የሚገባ ዋና ነጥብ ቢኖር ድሮም ችግሩ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ የሚፈታ ጉዳይ አልነበረምና አሳፍ ወደዚህ እረፍትን ወደሚሰጥ ድምዳሜና ውሳኔ የደረሰበትን ምክንያት ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እስክገባ ድረስ (እይታዬን እስካስተካክል ድረስ)፥ ፍጻሜአቸውንም እስካስተውል ድረስበማለት ከማስተዋል ጉድለት የተነሳ ራሱን ለአደጋ አጋልጦ እንደነበር እንመለከታለን።
ጥበብ በዚህ አለ! ችግር ሁሉ በጸሎት አይፈታም:: ይህ ማለት ግን ጸሐፊው በምንም ዓይነት ሁኔታ ጸሎት አያስፈልግም እያሉ እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል:: እየተባለ ያለው አንድ ሰው ካጋጠመው ከአቅሙ በላይ የሆነ ሁኔታ/ችግር የተነሳ ለጸሎት ከመነሳቱ በፊት ቢያንስ ቢያንስ ስለምን ርእሰ ጉዳይ እንደሚጸልይ ማወቅ ይጠበቅበታል:: ምን ነው ቢሉ? ከላይ ከፍ ስንል ከአሳፍ ህይወት ለመማር እንደቻልነው እንደ የአሳፍ ዓይነቱ ችግር በጸሎት ሳይሆን ራስን በመመርመር በማስተዋል የሚፈታ ችግር አለና። በአሁን ሰዓት ከሃይማኖት መሪዎች የተነሳ በቤተ- ክርስቲያናችን የተፈጠረው ሰጣ ገባም በተመሳሳይ በጸሎት የሚፈታ ጉዳይ ሳይሆን ራስህን ለጽድቅ ስራ በማስገዛት በማስተዋል የሚፈታ ችግር ነው:: የሃይማኖት መሪዎች የጸሎት መለከት የሚነፉበት ምንም ዓይነት ምክንያት የላቸውም::
1 “አውቅም ዘንድ አሰብሁ፥ ይህ ግን በፊቴ ችግር ነበረ” የሚለውን ቃል የእይታው ቅኝት የሚያመላክት ነው:: ኦይኖቼ በሰዎች ህይወት ላይ ተክዬ እንዲህ ያለ ሃጢአትና ነውር እያየሁ ለምን ራሴን እረብሻለሁ በማለት ራሱን ከማረጋጋት ይልቅ ከሚያልፍበት ህይወት በተጨማሪ ተደራቢ መከራ ያመጠበት የሃጢአተኞች ህይወት እያያ ይህንንም በማሰላሰል በራሱ መንገድ ለማጥናት በመወሰኑ ነበር::
እርስ በርስ ይቅር መባባል ካቃታቸው፣ እርስ በርስ መዋደድ ካልሆነላቸው፣ ልዩነቶቻቸውን በማጥበብና እርቅም በማውረድ አንድ መሆን ከተሳናቸው እንጸልይ/ጸልዩ ማለት ምን ማለት ነው? ሰላም: እርቅ: ፍቅርና: አንድነት ካልተፈለገ ጸሎት ለምን አስፈለገ? ምን ለመሆን? ጸሎት ማለት ጥያቄ ማለት አይደለም ወይ? ጸሎት ማለት እኮ ጥያቄ ነው::
v አቅቶናል እርዳን:
v ደክመናልና ብርታቱ ስጠን
v ተንገዳግደንና ደግፈን:
v ስተናልና መልሰን:
v ተለያይተናልና አንድ አድርገን ማለት ነው'ኮ ነው:: ታድያ'ኮ ለዓመታት የዘለቀው መደረቋቀስ ከድካም የተነሳ ሳይሆን ከጥጋብ የመነጨ ነው።
ጸሎት መልካም ነው። ጸሎት እንደሚቀበሉ አምነው ለሚጸልዩ ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ ያሰጣል ያስገኛልም። ጥያቄው ምን ተብሎ ነው የሚጸለየው? የሚል ነው። አምላክ ሆይ ስማን! ተብሎ ፈጥሪ ለመማጸን እኮ ችግሩ ማወቅ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር አባት እንዲሰጠን እንጸልይ ከማለት ይልቅም እግዚአብሔር አባት መሆኑ ከታመነበት ጸላዩ እንደ ልጅ በእግዚአብሔር ፊት እንደ እግዚአብሔር ንብረት በእግዚአብሔር ፋቃድና ትእዛዝ መመላለስ ነው የሚቀድመው:: ዳዊት "እግዚአብሔር እረኛዬ ነው!" በማለት ሲዘምር'ኮ አፉ ስላመጣለት አይደለም:: እረኛ በጉን ያሰማራል እንጂ በግ እረኛውን እንደማያሰማራ ሁሉ እግዚአብሔር እረኛዬ ነው ለማለት እግዚአብሔር በሚያሰማራህ ስፍራ ላይ ስትሰማራ ነው:: ሰው በሰይጣን (ጸብ: ንትርክ: ክፋት: አመጸኝነት: አድመኝነት: እልከኝነት: ነውር ሁሉ በሞላበት) መንግስት ተሰማርቶ ሲያበቃ ኡ ኡ ቢል ማን ይሰማዋል?
ሌላው የጸሎት አዋጁ ገጽታ እስቀድማችሁ ምን ማድረግና ማንን መሾም እንዳለባችሁ ጨርሳችሁ ስታበቁ ያደረግነው ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ለማለት ከሆነ ጸሎቱ፤ ሰውን ብቻ ማታለል አይበቃም ወይ? እግዚሃሩ ላይ ምን አንጣራራችሁ? እንግዲህ ጠቢቡ “ቅኖች ቅንነታቸው ትመራቸዋለች፤ ወስላቶችን ግን ጠማማነታቸው ታጠፋቸዋለች” (መጽ. ምሳሌ 11:3) እንዲል አያያዛችሁ በገዛ እጃችሁ መጥፊያችሁ ማበጃጀታችሁ ነው የሚመስለው።
ኤልዛቤል ናቡቴን ለመግደል ባሰበችበት ጊዜ እርምጃዋ ሁሉ ተገቢና ሕጋዊ እንደሆነ ለማስመሰል አስቀድማ ያሰበችውና ያደረገችው ነገር ቢኖር በአይሁድ ባህልና ወግ መሰረት የጾም ጸሎት ጊዜ (ሱባዔ) ነበር ያወጀችው።
“በአክዓብም ስም ደብዳቤ ጻፈች፥ በማኅተሙም አተመችው በከተማው ወደ ነበሩትና ከናቡቴም ጋር ወደ ተቀመጡት ሽማግሌዎችና ከበርቴዎች ደብዳቤውን ላከች። በደብዳቤውም ስለ ጾም አዋጅ ንገሩ፥ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀምጡት ሁለትም ምናምንቴ ሰዎች በፊቱ አስቀምጡና። እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው ይመስክሩበት አውጥታችሁም እስኪሞት ድረስ ውገሩት ብላ ጻፈች። በከተማውም የተቀመጡት የከተማው ሰዎችና ሽማግሌዎች ከበርቴዎችም ኤልዛቤል እንዳዘዘቻቸውና ወደ እነርሱ በተላከው ደብዳቤ እንደ ተጻፈ እንዲሁ አደረጉ። የጾም አዋጅ ነገሩ፥ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀመጡት። ሁለቱም ምናምንቴ ሰዎች ገብተው በፊቱ ተቀመጡ ምናምንቴዎቹ ሰዎችም በሕዝቡ ፊት። ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው በናቡቴ ላይ መሰከሩ። የዚያን ጊዜም ከከተማ አውጥተው እስኪሞት ድረስ ወገሩት።”
በተነገረው አዋጅና በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት ጸሎቱ ተጸለየ: ሕዝብ በእንባ ተላቀሰ ተራጨ የናቡቴም ደም ፈሰሰ። የዚህ ንጹህ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ መሞትም በጾም ጸሎት የታጀበ ስለ ነበር በእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ ተብሎ ሕዝብ መለከት እየነፋ ነጋሪትም እየጎሰመ ደስታውን ገለጠ። ጥያቄው የናቡቴን በግፍ መገደል የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበረ ወይ ነው? የጸሎት አዋጁስ ቢሆን ናቡቴን ለማትረፍ ነበር ወይስ የዋሁን ሕዝብ ለማደናገር የተሸረበ ተንኮል? መልሱ ቀጥሎ የሰፈረውን ቃል/አንቀጽ በማንበብ ያገኙታል።
“የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ። ተነሥተህ በሰማርያ የሚኖረውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ እነሆ፥ ይወርሰው ዘንድ በወረደበት በናቡቴ የወይን ቦታ ውስጥ አለ። አንተም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ገድለህ ወረስኸውን? ብለህ ንገረው። ደግሞም፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ የአንተን ደም ደግሞ ውሾች ይልሱታል ብለህ ንገረው።” ይላል
አሁንም ቢሆን የሚጸለየው ጸሎት ያለውን ለመድፋት፣ እውነቱን ለመቅበር፣ ብዙሐኑም ለማታለል ካልሆነ በስተቀር የትኛው ችግራችሁ ነው ለጸሎት የሚያበቃ/በጸሎት የሚፈታ ሆኖ የጸሎት ሱባኤ የሚታወጀው? ወይስ “ሊበልዋት የፈለጉ አሞራ ዝግራ ጅግራ ይሏታል” መሆኑ ነው:: እውነት ነው! ነገራችሁ ከሰው ዘንድ ለመሰወር ተችሎአችኋል ቢሆንም እናንተ ራሳችሁም ሆነ እግዚአብሔር የሚያውቀው ችግር እንዳላችሁ ግን ሁለታችሁ በየፊናችሁ አሳምራችሁ ታውቃላችሁ። ታድያ ለእንዲህ አይነቱ አዙሪት ምን ጸሎት ያስፈልገዋል? በማሰብና በማስተዋል የሚፈታ ችግር እንጅ በጸሎት የሚፈታ ችግር የላችሁ። በአጭር አገላለጽ ዘሩ ያለው በእጃችሁ ላይ ነው። እንክርዳድ ዘርቶ ስንዴ ያጨደ ማን ነው? ይቅርታ፣ ምህረት፣ ፍቅርን … ዝሩ ሰላም፣ አንድነትና ህብረትን ታጭዳልችሁ።
በእንቢተኝነት ጸንታችሁ እልከኝነትም ነግሶባችሁ አሻፈረኝ ከሆነ ቋንቋ ግን አፋቹ በሰማይ አንደበታችሁም በምድር ውስጥ ባታመላልሱና ባታኖሩ ነው የሚመከረው። ይቅር ተባባሉ: እርቅ ሰላምም አውርዱ: ይህን ለማድረግ ደግሞ ይቅርብኝ ማለት ብቻ እንጅ ምንም ዓይነት ጸሎት አያስፈልገውም! ይህን ስታደርጉ ደግሞ አይደለም አባት ሌላውንም ግዛት አሳልፎ ለክብሩ ይሰጣችኋል:: በተረፈ ግን ከነፈሰ ጋር የሚነፍሰውን እውነት እንደ ሰማይ ከዋክብት ለራቀችበት ሕዝብ ግን ከልብ አዝናለሁ::
አንድ ነገር ጨምሬ ልንገራችሁና ጽሑፌን ላጠቃልል። ማናችሁንም ብትሆኑ የሕዝቡ ባለባለቤት የሆነው እግዚአብሔር ከሚያስብለት በላይ ለዚህ ሕዝብ/ለዚች ቤተ ክርስቲያን ልታስቡ አትችሉም! ውሸት ነው! ከመስዋእት ይልቅ መታዘዘን የሚማርከው እግዚአብሔር ደግሞ ከምንም በላይ አስቀድማችሁ እርስ በርሳችሁ ተስማሙ: ተዋደዱ: ተፋቀሩ ብሎ ካዘዘ እርቅ በሰማችሁ ቁጥር አንገቴ ለካራ የምትሉበት ምክንያት ምንድነው? ምናችሁ ቢነካ ነው? ይቅር ለማለት ምህረትንም ለመስጠት ያልተሰላቸ/መቼም የማይሰላች እግዚአብሔር በትልቁ እያለ የእናንተ መጨናበርና ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ምን ያባላል? ማን ቤት ሆናችሁ ነውና እንዲህ ደጅ የሚጸናባችሁ? እግዚአብሔር ወርዶ እናንተን ይለምን? የቀራችሁ ይሄ ነው። እንግዲህ የለም! ቅድሳት መጻህፍት እንደሚያስተምሩት እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ጸሎት አይሰማም። ዜማ እስኪታደስ ጀሮ ዳባ ልበስ! በተጨማሪም እግዚአብሔር ሲያከብራችሁ ካልከበራችሁ ዓለም ቅዳሴ ታዜሙላት ዘንድ እንደማትፈልጋችሁ ልታውቁ ይገባል:: በዚያን ጊዜም የሰው ክንድ ደግፎ አያቆማችሁም!
አንገታችሁ ያንጠለጠላችሁትን በደግ ዘመን የሸመታችሁት ወርቅ ሸጣችሁ ትበሉ እንደሆነ እንጅ::
ሳል ይዞ ስርቆት ቂም ይዞ ጸሎት!
v “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን
ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።” (የማቴዎስ ወንጌል 6:14, 15)
v “ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች
ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። (የማርቆስ ወንጌል 11:25)
ሰላም ከተፈለገ የጸሎት ሱባኤ አያስፈልግም!
/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
E-mail yetdgnayalehe@gmail.com
United States of America

2 comments:

  1. Thanks Brother for your detail Explanation. By the way, the prayer agenda was prepared by MK and given to Holy Synod members. SO, there is a hidden agenda behind it. You know? This folks donot want to reconcile and bring Abyne Merkorious onboard to Patriarchaet office. And, therefore, this is a dramma against the interest of EOTC laties and clergies. SILEZIH HULACHINIM BETETENKEK METEBABEK ALEBIN YE MAHIBERE KIDUSANINA YE MAHIBERU KITIREGNA ABATOCHIN AKAHED. kALIHONE HULACHINIM MIRICHACHININ ENASTEKAKILALEN.

    ReplyDelete
  2. Thank you, Deacon Mulugeta for you gave wonderful comment to our church selfish leaders.
    በእውነት በመንፈስ ወደ ቀራንኦ መውጣት ያስፈልጋል ነገር ግን ብዙ ድካም ስላሌበት አባቶች መውጣት አይችሉትም። ለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያንቱን ግራ የሚያጋቡዋት።የእዉነት አምላክ እያየ ስለሆን እኛም ለእርሱ ትክክለኛው ፍርድ መፍረድ ለምችለው እግዚአብሔር ጭንቀታችን ትተናል። እውነት እስከ መቼ ነው በጥቅማ ጥቅም ተሸፍና የምትኖረው? ልብ እንበል ነቢይ አይደሉሁም ነገር ግን ብዙ መከራ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ይጣል በእነዚህ የማቅ ወዳጅ በሆኑት አባቶች ምክንያት።
    አቤቱ በየዋህነቴ ሄጃለሁና ፍረድልኝ በእግዚአብሔር ታምኛለሁ እመናለሁና አልናወጥም። መዝ 25 ቄ 1 ። እኛ ልጆች ነን በየዋህነት ለእርሱ አሳልፍን ሁሉን ነገር እነሰጣለን። ማቅ ግን በገንዘቡ ምን እንደምያመጣ በትግስት እያየን ነው። የእውነት አምላክ ይህች ጥንታዊት ሐይማኖት ይጠብቅልን።አሜን ።

    ReplyDelete