Thursday, January 23, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን በአዲሱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መዋቅራዊ ለውጥ ምክንያት እየደረሰበት ያለው ተቋሞ ተጋግሎ ቀጥሏል፡፡

REadin PDF:

በየሆቴሉ በድብቅ ይሰበሰባሉ ሲባሉ የቆዩት የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አለቆች በገሀድ በጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ ተሰብስበው ፓትርያርኩንና አንዳንድ የማኅበሩን ደጋፊ ሊቃነ ጳጳሳት አስጠነቀቁ፡፡ ጥያቄዎቻችን ምላሽ የማያገኙ ከሆነ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር በጥቁር ራስ (መነኮሳት ባልሆኑ) ሰዎች እንዲካሄድ በሕጋዊ መልኩ እንደሚጠይቁ አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ሰራተኞች ቤተክርስቲያኒቱ የአሰራር ለውጥ እንደሚያስፈልጋት አምነው ለውጡ ሁለንተናዊና መላውን የቤተክህነቱ ክፍል ሊያቅፍ እንደሚገባ ሕጉም ከዋናው ከሕገ ቤተክርስቲያን መጀመር እንዳለበትና በየደረጃው ደንቦችና መመሪያዎች ሊወጡ እንደሚገባው አስረድተው ይህንን የሚሰራው አካልም ከቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከሊቃውንት ጉባዔ፣ በየደረጃው ከሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር ሰራተኞች ፣ ከገለልተኛ ባለሙያዎች ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች በተወጣጣ ኮሚቴ መሰራት እንደሚገባው አስምረውበታል፡፡
ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጥያቄያችሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ትኩረት ይፈልጋል  በማለት ኮሚቴ እንዲቋቋም ፈቅደዋል በቤተክህነቱ አዳራሽ መሰብሰብ እንደሚችሉ አረጋግጠውላቸዋል፡፡
ስብሰባው ያበሳጫቸው አቡነ እስጢፋኖስ ግለቱ ከብዷቸው ወደ አሜሪካ እንደሚሄዱ ተናግረዋል፡፡

ጥናቱ ግልጽነት የጎደለውና ቤተክርስቲያኗን ለአንድ ማኅበር ድብቅ ዓላማ እና ፍላጎት አጋልጦ የሰጠ በመሆኑ፣ የካህናት ቅነሳ በሚል አገልጋዮችን የሚበትን ፣ ቤተክርስቲያኒቱ ያሏትን ሊቃውንት ያላካተተ በመሆኑ፣ የሰንበት ትምህርት ቤትን በማዳከም በአጥቢያ ቤተክርስቲያናት ብዙ ማኅበር እንዲደራጅና ሕጋዊ እንዲሆን በማድረግ በወጣቱ ዘንድ መከፋፈል የሚፈጥር በመሆኑ እንደማይቀበሉት  አስታውቀዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን  በጥቅምቱ የሰበካ ጉባዔ ምልአተ ስብሰባ በተወሰነው መሠረት  የ55 ሚሊዮን የቤተክርስቲያኗ ምእመናን ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በወሰኑትባ በአቋም መግለጫ ባጸኑት ውሳኔ  መሠረት  ሀብትና ንብረቱን እንዲያሳውቅና በቤተክርስቲያኗ አሰራር መሠረት በሕጋዊ ሞዴሎች እንዲጠቀም ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ለቅዱስ ፓትርያርኩ በ 5000 ሰራተኞች ፊርማ በቀረበውና ለመንግሥት አካላት ግልባጭ በተደረገው ደብዳቤ ተጠይቋል፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን በተዘጋጀውና ለአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት ብቻ እንዲተገበር በታለመው የመዋቅራዊ ጥናት ምክንያት  በሀገረ ስብከቱ ሥር በሚገኙ አድባራትና ገዳማት ሠራተኞችና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል ያለው አለመግባባት ቀጥሏል፡፡ መዋቅራዊ ጥናቱን ይቃወማሉ የሚባሉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአድባራት ሰራተኞች ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት በማምራት ቅዱስ ፓትርያርኩንና ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳትን አነጋግረዋል፡፡ የአቋም መግለጫቸውንም ለፓትርያርኩ ሰጥተዋል፡፡ በመድረኩ ማኅበረ ቅዱሳን አንድ የቤተክርስቲያን አካል ሆኖ እያለ ለመላዋ ቤተክርስቲያን መመሪያ አውጪ መሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣን ወዴት ነው ያለው እንዳስባላቸው ተሰብሳቢዎቹ ለፓትርያርኩ አስረድተዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን እራሱ ለቃለ አዋዲውና ለሕገ ቤተክርስቲያን ሳይገዛ እንዴት ሕግ አውጪ ሊሆን ቻለ? የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ መመሪያ የሚያስፈልግ በመሆኑ ከሕገ ቤተክርስቲያን ጀምሮ በየደረጃው መመሪያና ደንብ እንዲወጣና ይህንንም አንድ ማኅበር ሳይሆን የቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ያሉ እና ገለልተኛ አካላት ሊያዘጋጁት ይገባል ብለዋል፡፡ ተሰብሳቢዎቹ ማኅበሩ መዋቅራዊ ጥናቱን ለምን በድብቅ መስራት አስፈለገው፣ ሊቃውንት ለምን እንዲሳተፉ አልተፈለገም የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ለጥያቄዎቹ መልስ በሚሰጥበት ወቅት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የማኅበሩ የኢዲቶሪያል ኮሚቴ አባል ስለ መዋቅሩ አስፈላጊነት ለመግለጽ የሞከሩ ሲሆን አቡነ እስጢፋኖስ ግን ስለ ጥናቱ ብዙም መረጃ እንደሌላቸውና አንዳንዱንም ከተሰብሳቢው ወገን እንደሰሙ በመግለጽ እርስ በእርሱ የተምተታ መልስ ሰጥተዋል፡፡
መመሪያውና ጥናቱን ወድቆ ብናገኘውስ ምን ችግር አለው ሲሉ ምንጩን ለመደበቅ ሞክረዋል፡፡ ተሰብሳቢዎቹ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥያቄያቸውን ማይመልስ ከሆነ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር በጥቁር ራስ (መነኮሳት ባልሆኑ) ሰዎች እንዲካሄድ በሕጋዊ መልኩ እንደሚጠይቁ አስረድተዋል፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የተሰብሳቢዎቹ ጥያቄ አግባብ የሆነና በትኩረት መታየት እንዳለበት አስረድተው ከተሰብሳቢዎቹ ጉዳዩን የሚከታተል 15 ዐቢይ ኮሚቴ እና 20 ንዑሳን ኮሚቴዎች አስመርጠው በጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ በመሰብሰብ ጉዳዩን በይበልጥ በትኩረት እንዲያጠኑ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለጊዜው እንዲቋረጥ ብፁአን አባቶች ሀሳብ የሰጡበት የመዋቅራዊ ጥናት ስብሰባ በአቡነ እስጢፋኖስ ትእዛዝ እንደቀጠለ ሲሆን የሥልጠናው መሪ ማኅበረ ቅዱሳኑ አቶ ታደሰ ፍስሐ በሥልጠናው ተሳታፊዎች እናንተ እነማን ናችሁ? ከሊቃውንትስ ማንን ይዛችሁ ነው የምትሰሩት በሚል ለተነሳላቸው ጥያቁ በደፈናው የቤተክርስቲያን ልጆች ነን ከሊቃውንትም ታላቁን ሊቅ አቡነ እስጢፋኖስን ይዘን ነው የምንሰራው በማለት ምላሽ ሲሰጡ አዳራሹ በስላቅ ሳቅ ደምቋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ሠራተኛ አቶ ደስታን በሥልጠናው ሥፍራ በወሬ አቀባይነት መድቦ በሬኒ ካፊና ሬስቶራንት የምሳ እና የሻይ እየተከፈለው አንዳንድ መረጃዎችን ለማኅበሩ ሥውር ብሎጎች እንዲያቀብል መድቦታል፡፡ የአዲሱ ሚካኤል ሰንበት ትምህርት ቤት አባል የነበረውና ወደ ቤተክህነት እቃ ሊያደርስ ተልኮ በድንገት ሠራተኛ የሆነው አሁንም በጠ/ቤተ ክህነቱ ገዳማት አስተዳደር ተጧሪ ሆኖ ደመወዝ የሚበላውን ይህንን ጨዋ የአድባራት እና ገዳማት አለቆችንንና ሰራተኞችን ስም በማጥፋት ተግባሩ ማኅበሩ አንቱታን ቸሮታል፡፡ በተጨማሪ እነ ጳውሎስ መልክአ ሥላሴም በዚሁ ተግባር በመሳተፍ ከቤተክህነቱ አደባባይ መዋል ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment