Tuesday, December 18, 2012

ጽንስ የሚያጨናግፍ ወረተኛ ምላስ!

Read in PDF: Sense


/ ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
የሰው ልጅ በባህሪው ንጹሕ ፍጥረት ለመሆኑ ምንም አያጠያይቅም። ከልደት በኋላ ህይወት የማይገኝበት ኃይማኖት ጨምሮ በተለያዩ ውጫዊ ተጽዕኖዎች ራሱ "እኔ" ሲል የሚገልፀው/በሚቀርጸው ማንነት ግን ስብዕናው ከእውነት ይልቅ ሁለመናው ለሐሰት/ለስህተት እጅግ ቅርበት ያለውና በእንግዳ ነፋስ ለመወሰድም ጊዜ የማይፈጅበት ፈጣን ፍጥረት ለመሆኑ አንባቢ ይህን ጽሑፍ በሚያነቡበት ቅጽበት ለአፍታ ቆም ብለው የገዛ ራስዎትን ህይወት ቢመረምሩ ነገሩ በቀላሉ ሊያረጋግጡት የሚችሉት ሐቅ ነው። "የሐሜተኛ ሰው ቃል እንደ ጣፋጭ ምግብ ደስ እያሸኘ እስከ ውስጥ ሰውነት ይወርዳል" እንዲል።
ውሸትና በውሸት የሚፈጸሙት ወንጀሎች፣ እንዲሁም ውሸት በቁሙ ከአንድ ግለሰብ/ዜጋ ህይወት አልፎ በቤተሰብና በሀገር ደረጃ የሚያደርሰውና/የሚያስከትለውን መጠነ ሰፊ ጥፋት በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት አንስተን ተወያይተናል። በዛሬ ዕለት የመወያያ ርዕሳችንም በተመሳሳይ ሚድያና የሚድያ ሰዎች የተበላሽች፣ ሰላምና አንድነት የራቀባት በአንጻሩ ትርምስ ሁከትና የእርስ በርስ ጦርነት የማይለይባት ሀገርና ዓላማ የለሽ፣ ነህዘላል፣ ቀቢጸ ተስፋ ከዚህም አልፎ ወንድሙን አጋድሞ አንገቱን ከመቀንጠስ የማይመለስ በደም የሰከረና ደም የተጠማ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ ትውልድ በመፍጠርና በማፍራት ረገድ ሚድያ እያበረከተው ያለና የሚድያ ሰዎች የሚያበረክትቱን የጎላ አስተዋጽኦ/ድርሻ በመጠኑ በመዳሰስ በተለይ በያዝነው ዓመት የእምነት ተቋሞችን ወቅታዊ እንቅስቃሴዎችና የውስጥ ሃይማኖታዊ አሰራሮችን በማነጣጠር ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸውን የሚያመዝኑ ሥራዎችን በመስራት ስም እያተረፈ የሚገኘው "ኢሳት" በመባል የሚታወቀው "የዜና" ማሰራጫ ማዕከል ሥራዎች መካከል የኢ////ያን ወቅታዊሰጥገባ በተመለከተ በዚህ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ያሰራጨውን መሰረተ ቢስ ውንጀላ የሚያጠነጥን ይሆናል። ሙሉ የሐተታውን ይዘት ለማዳመጥ የሚከተለውን ሊንክ በመጫን ሊያዳምጡት ይችላሉ http://ethsat.com/video/?tubepress_video=HU2rYkmS3-c&tubepress_page=1
የራስህ ያልሆነ፣ ያልተገባህ ረብና የግል ጥቅምም ለማስጠበቅ/ለማግበስበስ፣ ከመቃብር የማያልፍ ጠፊ ሀብተ ንብረት ለመሰብሰብ ሲባልም ከምንም በላይ ደግሞ ቅንና የዋህ ልብ በቀላሉ ማዋለል ይቻል ዘንድ ጠማማ/ዋሾ አንደበት የጎላ ሚና ይጫወታል። በሰለጠኑ የዓለማችን ምዕራቡ ክፍል እንዲህ ዓይነቱን የሥራ መስክ ማለት መረጃዎችን ከማዛባት ጎን ለጎን የፈጠራ ወሬዎችን በመንዛት ረገድ በሚኒስትር ቢሮ ደረጃ የሚመራ ሲሆን በዘርፉ የሰለጠኑ፣ የፈጠራ ታሪክ በመስራት የተካኑ፣ የራሳቸውን ጥቅም እንጂ የሌላውን ሰው መጎዳት ትርጉም የማይሰጣቸው፣ ሐዘኔታም ሆነ ርህራሄ ብሎ ያልፈጠረባቸው፣ ማንኛውም ትልቅም ሆነ ትንሽ የሚሹትን ነገር ለማግኘት ሲባል ብቻ ነፍስ መጣል ካለባቸው በተፈጥሮው ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ መግደል ማለት ንጹሕ ውኃ ከመጠጣት የተለየ ስሜት በማይፈጥርባቸው ባለሞያዎችም የተደራጀ ነው።

 
ኢሳት በኢ////ያን ጉዳይ ላይ መልኩና አቀራረቡ እየለዋወጠ ሲያሻው ለቤተ እምነቱ ተከታዮች ልዩ ጠበቃና ተቆርቋሪ በሚመስል በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ ገለልተኛ ቢጤ በሚመስል አቀራረብ የማይገናኘውን ሁሉ እያገናኘ እንደ ድንግል መሬት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ አንድ ጊዜ የተከለውን ማረሻ እያመላለሰ በቤተ እምነቱ የኃይማኖት መሪዎች ያለውንና የሚታየውን አለመግባባትና አለመደማመጥ በተመለከተ ጉዳዩ ከቤተ እመነቱ ተከታዮች አልፎ በመላ ዜጎች አእምሮ ውስጥ የተሳሳተ ምስል ለመቅረጽ ቀን ተሌሊት "ዓይኔን ግንባር ያድርገው!” በማለት የመውጋት ዘመቻው ገፍቶበታል።
በነገራችን ላይ ይህ ወደ አሥራ አራት ደቂቃዎችን አከባቢ የሚጠጋ አጭር ሐተታ ጭብጥና ማዕከል ሁለት ነገሮችን አልሞ የተሰራ ሥራ ነው። አንደኛ ላይመለስ አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተበነውንና የተሰራጨውን የኢ////ያን ከድህረ ቅዱስ ፓትሪያርክ አባ ጳውሎስ ዕረፈተ ሥጋ በኋላ የተገጠማትን የኃይማኖት መሪዎች የሥልጣን ሽኩቻ ነገሩ ከሰማይ እንደወረደ ህብስት አድርጎ አጋጣሚውን ለመጠቀም ቋምጦ የነበረውን ኃይል ቅስም የሰበረ ከኢፈድሪ መንግሥት ፕረዚደንት ቢሮ ተፈርሞ የወጣውን ደብዳቤ ለማሳጣት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ "ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል" ብሎ ፈሊጥ እንደ መርህ በመውሰድ አሁን ባለው ነባራዊ የኃይማኖት መሪዎች የእርስ በርስ በማነካከስ በኩል ትልቁና የተጣለውን መልአክ የክንፉ ስብርባሪው "ማኅበረ ቅዱሳን" በማለት ራሱን የሚጠራ ግብረ እኩይ ስመ መንፈሳዊ ድርጅት ትቶ ያለ አንዳች ተጨባጭ ማስረጃ የተለመደው መንግሥትን የመወንጀል አባዜ ለመወጣት ያክል ነው። ብርቄም ተንታኝ! ጥበብ በዚህ አለ።
ክቡራን አበው ካህናት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጭው ዓለም የምትገኙ የምሥራች ቃል ተናጋሪዎች አግብርተ እግዚአብሔር መምህራን: የጌታ ሐዋሪያ የሆነው ቅዱስ ያዕቆብ በጻፈው መጽሐፍ ምዕራፍ ሦስት "እነሆ፥ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፥ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን። እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ። እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል።" ሲል ስለ ጠማማ አንደበት አደገኝነት ማብራሪያ በማያስፈልገው ሁኔታ በማያሻማ አገላለጽ ፍንትው አድርጎ እንደ ገለጸው ብርሃናተ ዓለም ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስም በበኩሉ እንዲህ ያለውን ፈረሰኛ የማይመልስው ቆማጣ ከሚነዛው ወሬና አሉባልታ በተጨማሪም ከሥራ ፈቶች ውሸትና ጠማማ አንደበትም የተነሳ የሚነደው እሳት/ሰደድ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ጉባኤ መታደግ ይቻለን ዘንድ "እነዚህም ስለ ነውረኛ ረብ የማይገባውን እያስተማሩ ቤቶችን በሞላው ስለ ሚገለብጡ፥ አፋቸውን መዝጋት ይገባልሲል እንዳስተማረን በዋናነት ብቸኛ የደህንነት መንገድ የሆነውን ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ከመመስከር ጎን ለጎን የነውጠኞችና የሲዖል መልዕክተኞች (መልካም ነገር የማይወጣበት/የማይገኝበት ለማለት ተፈልጎ ነው።) አንደበትም ጥበብ የተሞላበትን ቃል በሥልጣን በመናገርና በመግለጥ ዝንጉ ምላስ ዝም የማሰኘት ግዴታ አለብን።
ከለበሱት ልብስ በስተቀር የሚታይ ነገር የሌላቸውና "እናንተን ብሎ መንፈሳውያን/ሊቃነ ጳጳሳት" ሲል ምእመን ዕንባውን እያፈሰሰባቸው የሚገኙ የኃይማኖት መሪዎች ልብ ይገዙ ዘንድ፣ የቆሙበትም መንገድ ይሰልሉና ከእልከኝነትም ይልቅ ነን የሚሉት የተቀመጡበትን መንበር ይመስሉ ዘንድ፣ ልባቸውም ለሰላምና ለአንድነት ያነሳሱ ዘንድ በተለይ በምዕራቡ ዓለም የምትገኙት አብያተ ክርስቲያናት የተጀመረውን ምእመናንን የማስተማር፣ የማንቃትና የማደራጀት እንቅስቃሴ ሌላ እክል ሸልኮ እስካልገባበት ድረስ ጅማሬው የሚበረታታና በተጠናከረ መልኩም ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት "ተመክሮ" በመቅሰም ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ የሚገባቸው ሲሆን እንቅስቃሴው/መሰባሰቡ ከዚህ ባለፈ መልኩ መጽሐፍ "እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል፤ ሐሜት ከሌለም ጠብ ይቆማል፡፡ ከሰል ፍምን፣ እንጨትም እሳትን እንደሚያበዛ ሁከተኞችም ጠብን ያባብሳሉ፡፡ (ምሳ. 26 20- 22) እንዲል ትመሩት፣ ታስተምሩትና ትመግቡትም ዘንድ አደራ በተጣለባችሁ ሕዝብ መካከል ላይ የመቃብር አፈር የሚነሰንሱ፣ ጥርጣሬና ጥላቻ ይነግስ ዘንድም ቀለብ እየተሰፈረላቸው ነገርን በማሴርና ወሬንም በማጠንጠን የቅኖችን ልብ ለመስለብና ለማዋለል የማይተኙ ሁከተኞች ላይም "የቤትህ ቅናት ይበላኛል!" ስንል ፊት ለፊት ተመሳሳይ የሆነ እርምጃዎችን እንወስድና ወረተኛ ምላስም ዝም እናሰኝ ዘንድ ጥሬዬን አቀርባለሁ።
ሌላ እንዲህ ያለውን የመንታ ምላስ ውጤት የሆነውን ድምጽ ለቤተ ክርስቲያን "ቁመናል" በሚሉ ድረ ገጾች ሳይቀር ሲስተጋባ ማየቱ እጅግ የላቀ የልብ ሐዘን እንደሚሰማኝ ስገልጽ፤ በእግዚአብሔር መንፈስ፣ ህይወት ይሆነን ዘንድም በተሰጠን ቃል መነጽር ድርጊቱ የተመዘነ እንደሆነ ነገሩ የዕድገት መገለጫ መሆኑ ቀርቶ መንፈሳዊ ክሳራ/ዕውርነት ተከትሎ የሚመመጣውን ዝቅጠት መሆኑ ስገልጽ በአክብሮት ነው። መንፈሳዊ ሥራ የሚሰራም በሞቅታ፣ በስሜት፣ "እኔስ
ብሆን ከማን አንሼ ነው" በማለትና በስማ በለው ሳይሆን እግዚአብሔርን በመጠየቅ፣ በቃሉ እንደ ተፃፈም ባለው ሳንጨምርና ሳንቀንስ እንደ መልዕክተኛ እንዲሁ ማስተላለፍ እንደሚገባን በአጽንዖት ለመግለጽ እወዳለሁ።
በመጨረሻ በሀገሬ ሳለሁ በቅድሥት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአንደኛ ዓመት የሥነ መለኮት ተማሪ ሁኜ አራት ኪሎ አካባቢ ከምትገኘው በደንበኝነት ጸጉሬን ከምስተካከልባል አነስተኛ የጸጉር ቤት አስተካካል ጠረጴዛ ያገኘኋትን የክርስትና ቤተ እምነት መጽሔት መንፈሳዊ ግጥም መጠነኛ ማሻሻያ በማድረግ ያዘጋጀኋት ግጥም በማስነበብ ልለያችሁ።
የማያስተውል ዝንጉ ምላስ፣
የሚዘለዝል እንደ መቀስ፣
ያልተቀደሰ ተራ አንደበት፣
ሹክታው ሃሜት፣
ጩኸቱ ኩራት የሆነበት፣
ከመሃል ገብቶ እንዳያምሰን፣
እንዲህ አይነቱን እሳት አርቀን አይተን፣
ልናስተምረው ይገባል ቆርጠን፤
ልንገስፀው ይገባል ደፍረን።
ጥብቅ ማሳሰቢያ
በጥቂት ሰዓት ልዩነት ውስጥ ጽሑፎቼን ከተስተናገዱበት ድረ ገጾች እያደንክ በመንቀልና በማስነቀል እንዲሁም በእከክልኝ ልከክልህ የተመሰረተ ተራ ጓደኝነትና ጌዚያዊ ወዳጅነት የተነሳም ኢሳትን እንደ ታቦት አትንኩብኝ በሚል የልጅነት መንፈስ በአንዳንድ መካነ ድሮች ሥራዎቼን ላለማስተናገድ እየተደረገ ያለው - ዲሞክራሲያዊ አካሄድና የዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አፈና ውሎ አድሮ ሌላ የከፋ ችግር ይወልድ እንደሆነ እንጂ የሚመጣው መፍትሔ ይኖራል የሚል እምነት የለኝም። በዚህ አጋጣሚ ለኢሳት "የዜና" ማሰራጫ ማዕከል እንደ ተቋም፣ ለድርጅቱ ቅጥረኞችም እንደ "ባለሞያዎች" የማስተላልፈው መልዕክት ቢኖር ጉልህ የሆኑ የማዕከሉ ሕጸጾች፣ ግድፈቶችና ሆነ ተብለው የሚፈጸሙ የማሳሳት ስራዎች ሲነቃና ሲደረስበት ራስህን ከማስተካከል ይልቅ "የአድማጮች አስተያየቶች" እየተባለ በሚቀርበው ቅንብር ሕዝብን ማደናገር፣ ሀገርን ከመክዳትና ራስህንም ከማታለል አልፎ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልምና ከታሰበበት አሁንም ቢሆን ሀገርንና ትውልድን የሚጠቅም ስራ ለምስራት ጊዜው እንዳልመሸ ለመጠቆም እወዳለሁ።
/ ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com
Las Vegas, NV

2 comments:

  1. እሳት ራዲዮ ጣቢያ፡ አሁን ደግሞ ሁሉ አልሳካለት ስለው ወደ አረብ አገሮች ስርጭት ጀምራለሁ ብሎ ዛሬ አውጆዋል እስላሞች ወንድሞቻችን በከርስቲያኑ ህዝብ ላይ ጦርነት ለማነሳሳት ይሆን? ይህ ሁሉ ሩጫ ገንዘብ ማግኛ መንገድ ለመፍጠር እንደሆነ አንዳንድ ምንጮ ይናገራሉ። ታዲያ እሳት ሬዲዮ ለገንዘብ ብሎ እሳላሙን ህብረተሰብ በማታለል የመንግስት ተቃዋም ነኝ በማለት ገንዘብ ርዱኝ ለማለት የማይቻለውን አምላክ ስም ለማጥፋት የጥፋት መንገድ ጀምሮዋል። እባካችሁ አትቸኩል በሉት እንደ ልጅ ቀስ ብለህ እደግ የምለው ሰው አጣ። አያዋጣውም መንገዱ ክፉ ነው የጀመረው። የአረብ ገንዘብ ለማግኘት ተብሎ በሀይማኖት ሽፋን የራስ ጥቅም ለመሰብሰብ የምደረገው ጉዞ አያዋጣም እሳቶች ።ነገሩ ከፊት ለፊት ሞት መቃብር አለ !!!!!!!!!!ኦኦኦ ህዝባችን እስላሙና ክርስትያኑ ተቻቸለው የኖሩ ስለሆኑ እንኮራባቸውለን ። ብዙ የመካራ ዘመን በመቻቻል አሳልፈዋል። የእሳቶች ጉዞ ከዲስ የምወጣው ድምጽ ህይወት የሌለው ባዶ ነው። የማቅ ወዳጅነት አለዋጣውም መስለኝ። ጉድ ጉድ ጉድ ነው..........

    ReplyDelete