Monday, December 3, 2012

ይድረስ ለመንጋው እረኞች አባቶቼ



  ከደቡብ አፍሪካ      
ይድረስ...........ይድረስ........ይድረስ፦ከጥቅም ጋር ሳይሆን ስለእውነት ለምትሰሩ አባቶች፤ ለዘር ሳይሆን ለእምነታችሁ ለቆማችሁ አባቶች፤ ከሀሰተኞች ጋር ሳይሆን ከእውነት ፊት ለምትቆሙ አባቶች። >> መቼም (ጉድ ሳይሰማ መስከረም ኣይጠባም)>>  የተባለው በዚህ ባለንበት በደቡብ አፍሪካ በተግባር መተርጎም ከጀመረ ዘመናትን አስቆጥሮኣል። ይሁንና (የአሁኑ ይባስ) ብሎ በጣም የሚያስግርሙና አረ ወዴት እንሂድ?..... ወደ ማንስ አቤት እንበል?..... የሚያሰኙና፡ እንዲሁም ቤተክርስቲያኗ የማናት?......... ባለቤቷስ ማነው?......... መንፈስ  ቅዱስ ወይስ የአንድ ፓለቲካ ድርጅት? የቤተክርስቲያኗ ባለቤቶችስ በውስጧ የሚያገለግሉና የሚገለገሉ አማኞች ወይስ የገቢዋ ተጠቃሚ የሆኑ (የሆነ)ግለሰብ? መልሱን በጽሑፍ ሳይሆን በተግባር ለሚመልስ አውነተኛ እረኛ ስለ በጎቹ (ምእመናን)ለሚገደው ሁሉ ትቼዋለሁ።  
መቼም ከላይ ለተዘረዘሩት አጅግ ጥቂት፡ ነገር ግን መሰረታዊ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ጊዜያችሁን እንደማትቆጥቡ በመተማመን ወደ ተነሳሁበትና፡ ለአንድ ሙሉ አመት የምእመናን ጭንቀትና መወያያ ሆኖ ከመቆየቱም ባሻገር አጅግ አስገራሚና ለሰሚ ጉድ ያሰኝውን በስላሴ ስም በተሰየመው ቤተክርስቲያን እየተከናወነ ስለ አለው እቃቃ_ እቃቃ ልበለው?........ ወይም አንቆቅልሽ?....... አሊያም . . . . . . . ብቻ ለኔ የሚመጥነው ቃላት ያላገኘሁለትንና፦ የብዙዎችን ልብ ክፉኛ ያሳዘነውን አስገራሚ ታሪክ ባጭሩ፡ በማስተዋል ለመጓዝና አውነቱ ምን አንደሆን አውቆ ለህሊና ዳኝነት ይረዳችሁ ዘንድ ብሎም ስለቤተክርስቲያኗ የሚገዳቸው አባቶች አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈልጉልን ይረዳ ዘንድ ከዚህ አንደሚከተለው በዝርዝር የታዘብኩትንና በአማኝነቴ ውስጤን የጎዳውን ለማሳየት አሞክራለሁ።

መቼም መናገርና ድካምን ለማገዝ መሞከር እጅግ ከባድ ወንጀል ሆኖ በሚታይባት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከታች ጀምሮ እስከላይኛው እርከን ድረስ ያለው ሰው ስህተት ይኖርብናል ወይም ልንሳሳት እንችላለን ብሎ የሚያስብ ማግኘት አዳጋች ነው።  ይሁንና በተለይ አባት ተብለው የሚቀመጡት ግለሰቦች በመጀመሪያ ለመታረምና፡ ቢሳሳቱ አንኩዋን አባት፦ ተሳስተዋል ተብለው አንዳይስተካከሉ (አንዳይታረሙ)እንዲያውም የእነሱን መሰረታዊ ችግር ወደሌላው አላከው የራሳቸውን ጥፋት በሌላው ላይ እየፈረዱ በሀሰት ጭንብል ተሸፍነው ፡የአማኙን ማንነት በምን አገባኝና በአጉል ፈሩን በለቀቀ የአክብሮት ይሉኝታ አንዲታሰር አድርገው ተብትበውታል፡፡ ከዚያም በላይ በጥቅማ ጥቅም በዙሪያቸው ሰብስበው የግል ማንነታቸው ሰባኪ በሚያደርጉዋቸው ጥቂት ግለሰቦች የሐሰት ወሬ ተሸፍነው አጅግ በጣም በረቀቀና መንፈሳዊነትን የተላበሰ በሚመስል አቀራረብ የሌላውን ትጉህ አገልጋይም ሆነ ተገልጋይ ስም በማጥፋት ከቤተክርስቲያንና ከማህበረሰቡ ለማግለል ሌት ተቀን የሚደክሙ ጉደኞች ካከናወኑትና አያከናወኑት ካለው አጅግም በጣም የምእመኑን ልብ ካቆሰለው መካከል በቅርቡ የተከናወነውን በሁለት ታታሪ መንፈሳዊ አገልጋዮች ላይ የተሰራውን አስገራሚና አጅግ አሳዛኝ ታሪክና፦ እንዲሁም በቤተክርስቲያንያናችን ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ዘርፈ ብዙ መሰረታዊ ችግሮችን ለማውጣትና ለሚመለከተው የበላይ አካል ምናልባት ቢደርስልኝ ብዬ፡ አንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች የሚደርስ ተመሳሳይ ችግሮች ካሉ ሕዝበ ምአመኑ ነገሮችን በሚገባ አንዲያጤን በማለት እነሆ የእውነት አምላክ የሆነውን አግዚኣብሔርን አጋዥ አድርጌ አንድም ሳልቀንስ ወይም ሳልጨምር የታዘብኩትን ሁኔታውን ለማስረዳት እጀምራለሁ።
1 በዚህ በደቡብ አፍሪካ  ልባቸው አምልኮተ እግዚአብሔርን እጅግ በሚናፍቅ ስደተኛ ሕዝበ ምእመናን ከፍተኛ ክርስቲያናዊ ትግልና ያላሰለሰ ጥረት የተሰራችውን የቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ሕዝበ ምእመኑ ለልቡ ምኞት መሳካት ይረዳው ዘንድ ከሀገር ቤት ያስመጣቻው አባት ተብዬ የራሳቸውን ድብቅ ማንነት ግልጥልጥ አድርጎ ባሳየ ሁኔታ የቤተክርስቲያኗን አገልግሎት ለራሳቸው በሚመቻቸውና ባመኑበት መንገድ ከተለመደውና ከሕጉ ውጭ በሆነ  ሲያከናውኑት በነበረ አገልግሎታቸው  አብረዋቸው ያገለግሉ የነበሩት ካህናት ብዙ ሲጮሁ ሰሚ ቢያጡም በአንዳንድ ግለሰቦች ተጽእኖ እስከ አሁንም ድረስ የግብር ይውጣ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንዲት ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖት ሳይሆን በአስተዳደር ከሁለት ተከፍላ ዓመታትን በመሪር ኀዘን እና ትካዜ የማሳለፏ ህመም ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸው፡ በስደተኛው ቅዱስ ሲኖዶስ ስር ነኝ በሚል ቲያትራዊ ፈሊጥ የሁሉም ነገር ፈላጭ ቆራጭ ሆነው እንደግል የቢዝነስ ሴንተር ቤተክርስቲያኗን ከዚሁ ካሉበት እስከ ሀገር ቤት ድርስ ለተለያዩ ቢዝነሶች መጠቀሚያ አድርገዋል።
 (የገበያ ግርግር ለቀጣፊ) ይበጃል ሆነና ቤተክርስቲያኗንን የግል ቢዝነስ ሴንተር አድርገው ያለ ማንም ሀይ ባይነት ለአስር አመት የቤተክርስቲያኗ ገቢ የእርሳቸውና 10 አመት ገንዘብ ያዥ ያደረጉት የቅርብ ቤተሰባቸው መጠቀሚያ ሆኖ ሕዝቡን ያለምንም ክፍያ የሚያገለግሉትን ካህናት የተለያየ ስም በመስጠትና አላከበሩኝም በሚል ደካማ የስጋ አስራር ከቤተክርስቲያኑ እንዲርቁ በማድረግ በሚያከናውኑት እጅግ አሳፋሪና ኢክርስቲያናዊ ስነምግባራቸው፡ በተለያየን አማኞች እስከ አሁንም ድረስ ቢመለሱ ምናልባት ብለን ብንወቅሳቸውም ብንመክራቸውም ለቤተክርስቲያኗ በሚጠቅም አሊያም መከራውን አይቶ በብዙ ፈተና ይህችን ቤተክርስቲያን ያስገኘውን አማኝ ልብ ሊያሳርፍ ከሚችል አባታዊ ተግባር ይልቅ እንደ አንድ የፖለቲካ መሪ ለግል ጥቅማቸውና ሰብእናቸው በሚያመቻቸው የተንኮል አሰራር ለቤተክርስቲያኗ በማንኛውም ሁኔታ ሁሉ ቀድመው የሚገኙትን ምእመናን አባቶች በተለያየ ስልት በማሳደድ እጅግ አሳፋሪና ከአንድ የቤተክርስቲያን አባት የማይጠበቅ ስራ ሰርተዋል እየሰሩም ይገኛሉ።
 ለወንጌል አላማ ወይም ለሕዝቡ በረከት ሳይሆን በውስጥ ለሚፈጥሩት የአስተዳደር ችሎታ ችግሮቻቸው መሸፈኛነት እንዲያመቻቸውና የራሳቸውን ክብር እንዲሰብኩላቸው በሚያስመጡአቸው ሰባኪዎች ለመሸፈን ከሚያደርጉት አሳዛኝ ተግባር ባሻገር፦ ጥቂት የፖለቲካ ጥማታቸውን ያልተወጡ፡ ወይ ፖለቲካው አለበተዚያም ክርስትናው በአግባቡ ያልገባቸው የነፍሰ ገዳዩ ድርጅት የውስጥ አላማ አስፈጻሚ ግለሰቦችን መጠቀሚያ በማድረግ፡ እኛ እንደምንሰማው እንደምናየውም የውስጥ የአስተዳደር መሰረታዊ ችግሮች እንዳሉ ሁኖ ነገር ግን (ምንትስ በማያውቁት ሀገር . . . . . አንጥፉልኝ) አለ እንዲሉ ድካማቸውን በማገዝ እጅግ ዘርፈ ብዙ የሆኑ አገልግሎቶችን ይሰጡና ምንም ያልነበረውን ቤተክርሰቲያ በሕዝብ እንዲሞላ ያደረጉትን ከፍተኛ ተወዳጅነት የነበራቸውን፡ አገልጋዮች  እኝህ ግለሰብ ግን በሚታወቁበት ምድር ተሐድሶ ናቸው ብለው ሲነግሩን እጅግ በጣም ያሳዘነኝ ከመሆኑም በላይ አንድ ጊዜ ወንጌል ስማር የሰማሁትን ምሳሌ አስታወሰኝ።
 <<ሌባ ነው አሉ በተዘራፊና ተዘራፊውን ለማገዝ ሌባውን ለመያዝ የሚሮጡት ሰዎች ተጨማሪ እርዳታ ለማግኘት ሌባ....ሌባ...ሌባ እያሉ ሲከተሉት ሌባውም ታዲያ በቀላሉ ሊያዝ እንደሚችል ስለገባው እርሱም ሌባ...ሌባ እያለ ሲሮጥ ሌሎች ማን ማንን እንደሚያባርር ግራ ገብቷቸው ቆመው ይመለከቱ ነበር>> ይህንን በግልጽ እያከናወኑት ያሉት ግለሰብ እራሳቸው ቃለመጠይቅ ባደረጉበት ጸባኦት በተሰኘች መጽሔት ገጽ 24 ላይ ካስቀመጡት የግል ሓሳባቸው ጋር የሚጋጭና፡ እርሳቸውን የሚመለከት ጉዳይ የያዙ ሰዎችን ለመምታት ሲሆን የሚተኮስ የዘመኑን ጥይት በንጹህ የቤተክርስቲያኑዋ ልጆች ላይ ያለማቋረጥ ሲተኩሱት ከአንድ የቤተክርስቲያን መሪ መስማት ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
ለነገሩማ ከራሳቸው እንደተማርኩት << የሚናገሩትን የማያደርጉ>> ጉደኞች መሆናቸውን ጌታ በማቴዎስ ወንጌል ነግሮን የለ፡!!! እኛ ምእመናኑ አገልጋዮቻችንን እንፈልጋቸዋለን ዝም ብለው አገልጋይ የሆኑ አይደሉም ቤተክርስቲያን ዋጋ ከፍላላቸዋለች እነሱም ሕይወታቸውን ጊዚያቸውን ሰጥተው ነው ከዚህ የደረሱት ስለዚህ ማንም ሲፈልግ የሚጠቀምባቸው ደግሞ የሚያገላቸው የግለሰብ ቤት አገልጋዮች አይመስሉኝም። ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር አላማና የሕዝብ መንፈሳዊ ፍላጎት ማስፈጸሚያ እንጂ የግለሰቦች ጥቅም ማስጠበቂ ካምፓኒ እንዳልሆነች ሊታሰብበት ይገባል። ይህንንም እያንዳንዱ ሕዝበ ምእመን በሚገባ ማወቀ ብቻ ሳይሆን የእለት ተእለት የመወያያው አጀንዳው ካደረጋቸውም ዘመናት ተቆጥረዋል።
2  የስደተኛው የትዳር በረከት የሆኑ ህጻናት መብዛትና ብሎም ሀይማኖታቸውን፤ ታሪካቸውን፤ ቋዋንቋዋቸውንና ባሕላቸውን የሚያጠኑበት ምንም አጋጣሚ ያለመኖሩ ሁኔታ በእጅጉ ያሳዘናቸው ወጣት አርቲስቶችና ነጋዴዎች በመንፈሳዊ ተነሳሽነት በመሰባሰብ በአንድ ለጉዳዩ ልዩ አትኩሮት በሰጠ ታታሪ አገልጋይ ያላሰለስ ጥረት ለረጅም ጊዜ ሰልጥነው ባቀረቡት የዝማሬ መርሐ ግብር የትምሕርት ቤት መግዣ የሚሆን ከፍተኛ የሆነ ገቢ መሰብሰቡ የሚታወቅ ከመሆኑም በላይ እያንዳንዱ ሕዝበ ምእመን ከነገ ዛሬ ትምሕርት ቤቱ ተገዝቶ ለማየት፡ ባይሆን እንኩዋን የገባውን ገቢ የጎደለውን የገንዘብ መጠን ሊያሳይ የሚችል አጭር ሪፖርት እየተጠባበቀ ባለበት እልህ አስጨራሽ ወቅት ይባስ ብለው እኝሁ ቀልደኛ አባት ከነ ሰበሰቡዋቸው የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አቀንቃኞች ጋር በመሆን የትምሕርት ቤቱ ጉዳይ ምን ላይ ደረሰ ብለው ለሚጠይቋቸው አማኞች፡ አስር ሺህ ራንድም(R10,000) አልገባም እንደውም ከስረናል እያሉ ማላገጡን ስራዬ ብሌው መያያዛችው በእጅጉ የጆሃንስበርግን የኦርቶዶክ አማኝ ያሳዘነ እንቆቅልሽ ከሆነ ሰነባብቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለም በግል ለሚጠየቁት ይሚሰጡት የማላገጥ መልስ ሳያንስ በምን ያመጣል የሕዝብ ንቀት ይባስ ብለው የቤተክርስቲያኗን ገንዘብ የሱቃቸው ማሟያ ያደረጉት ግብረ አበሮቻቸው ሪፖርት ብለው ባቀረቡት የስድብ ጽሁፍ በአደባባይ በሕዝቡ ላይ አላግጠዋል። በመሆኑም ይህችን በስደት ባለው ሲኖዶስና በስደተኞች ስም የሚነገድባትን ቤተክርስቲያን የሚመለከተው እውነተኛ አካል ካለ በየዋሁ አማኝ ሕዝብ ገንዘብ ላይ በሚያላግጡትም ግለሰቦች ላይም ሆነ የውስጥ ኦዲትን በተመለከተ እውነተኛ ድርሻውን እንዲወጣ ከመጠቆም ወደ ኍላ አልልም። ድረሱልን እያልንም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። 
3 የገበያ ግርግር . . . . . . . . . . እንዲሉ የቤተክርስቲያኗን ለሁለት መከፈል እንደታላቅ አጋጣሚ በመጠቀም እራሳቸውን በስደተኛው ሲኖዶስ ስር እንዳደረጉ በመለፈፍ ስደተኛው ሲኖዶስ በቃለ አዋዲው መሰረት የሚመለከተውን የክፍሉን ሰራተኞች ልኮ ኦዲት እንደማያስደርግ፤ የሰበካ ጉባአኤ እንደማያስመርጥ፤ አገልጋዮችን እንደማይመድብ፤ አስተዳደር ይበደል አይበደል እንደማይመለከት በአጠቃላይ ለሕዝበ ምእመኑ አገልግሎት የሚያደርገው ምንም ነገር የቅርብ ክትትል እንደሌለ የተገነዘቡት መንፈሳዊ ነጋዴዎች ይህችን በጥቂት ጠንካራ ስደተኛ አማኞች የተመሰረተች ቤተክርስቲያን የግል የገቢ ምንጭ በማድረግ እነዚያን ታላላቅ አባቶች ከገንዘባቸው እስከ ሕይወታቸው መስጠት ዋጋ ከፍለው ለዚህ ያደረሱዋትን ጀግና አባቶች በተለያየ ሰይጣናዊ የተንኮል ሴራ እንዲያዝኑና ከቤተክርስቲያናቸው እንዲርቁ በማድረግ ለዛሬው የህልማቸው እውን መሆን ቀላል የማይባል ሰይጣናዊ ሴራ ሲሰሩባት ኑረዋል። 
     4 የሰበካ ጉባኤ የሚመረጠው የሚሻረው በአንድ ግለሰብ ፍላጎትና መራጭ አስመራጭ እና ወሳኝነት ነው ቃለ ጉባኤ የሚባለው የቤተክርስቲያኗ ሕግ እዚህ የሚሰራ አይደለም፦ በስደተኛው
ሲኖዶስ ስር መሆን ሌላ ሕግ የማውጣት አጋጣሚ እንደሚፈጥርም አልገባንም እኔ የሚገባኝ የሁለቱ ሲኖዶሶች መንበራቸው መለያየቱን እንጂ በሰላሙ ወቅት አብረው የቀረጹትን ቤተክርስቲያኗም ለዘመናት ስትመራበት የኖረችውን ሕግ የግለሰቦችን ጥቅም ሊያስጠብቅ በሚያስችል ሁኔታ እንደተቀየረ አልነበረም እዚህ ለአስር አመታት የተመለከትኩት ጉድ ግን ብዙ የሚያስብልና ምነው አባቶቻችንስ ምን ነካቸው ስለ ልጆቻቸው አይገዳቸውም ወይስ የአንድ ሰው ፍላጎት እስከተሟላ ድረስ ምንቸገርን ይሆን፡ አይሰሙም እንዳንል እንደሚሰሙ እኛም እንሰማለን፡ አረ የመፍትሄ ያለህ አንድ በሉን። 
     ታዲያ አልጠግብ ያለ.........................እንዲሉ አሁን ጊዜው ደርሶአል፡ ይሕ ሕዝብ እስከ ዛሬ የተዘረፈው የተሰራበት ደባ በቃ ብሎ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ላላስፈላጊ ነገር ከመንቀሳቀሱ በፊት የሚመለከታቸው አካላት ስለቤተክርስቲያን የሚገዳቸው ከሆነ በአፋጣኝ መፍትሄ ቢሰጡት ይሻላል እላለሁኝ። አለበለዚያ ግን አሁን በመለያየት የደረሰበትን ጉዳት የተገነዘበው አማኝ ጊዜው እንደደረሰ ተገንዝቧል ቤተክርስቲያኑን ሊመጣ ከሚችለው የበለጠ አሳዛኝ ነገር ለማትረፍ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ማወቅ ይቻላል።
      የእኛ ችግር ይሄ ብቻ አይደለም ሌላም እጅግ ብዙ በአደባባይም ለማውራት የማይደፈር ከአንድ ቆብ ከጫነ አባት የማይጠበቅ ተግባር እንደኔ በትዳራቸው በስራ ፓርትነር ጉዞአቸው እና በመሳሰሉት የበደል በደል የደረሰብን ወዴት እንሂድ ትሉናላችሁ? እንደውም አልፎ አልፎ እንደምሰማው በሂደት ብዙ ለቤተክርስቲያኗ ጥቅም የማይሰጥ ግን እጅግ የሚጎዱ ነገሮች እንደሚወጡ ይወራል ታዲያ ሳይቃጠል በቅጠል አይሻልም ትላላችሁ፡ የሚመለከታችሁ የበላይ አባቶች።?   
     >ይሄንንና የመሳሰሉትን መሰረታዊ ችግሮች በሚገባ የሚመለከተው አካል ተገንዝቦ አፋጣኝ መፍትሄ ቢሰጥበት አንደኛ በስደት የተለያዩ ሁኔታዎች እያሰቃዩት የሚገኘውን ሕዝበ ምእመናን ልብ ያሳርፋል።
    > ሁለተኛ ሕዝቡ በቤተክርስቲያኑ ስም ባለበት የስደት ምድር የተለያዩ መሰረተልማቶችን እንዲያቋቁም ከዚህ በፊት ካቀደው በላይ መነሳሳትን ይፈጥርለታል፡፡ 
     >ሌላው ደግሞ ከምንም በላይ በቤተክርስቲያን አባቶቹ ላይ ያለውን ጥላቻና ክፉ አመለካከት በማንሳት ያለ አንዳች ስጋት ከአባቶቹ ጋር ለመገናኘትና ያለ አንዳች ስጋት ስርአተ ንስሀውን ለመፈጸም የሚያስችለው መተማመንን ይፈጥርለታል። 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።
አፋጣኝ መልስ በጉጉት ከሚጠብቅ ልብ፦
ለመንጋው እረኞች አባቶቼ
  ከደቡብ አፍሪካ      

 

1 comment:

  1. የሰላም አምላክ ሰላማችሁን ያብዛላችሁ እያልኩኝ ከፍያለ ምስጋናዬን ከልብ አቀርባለሁኝ፡!!! የሚመለከታቸው አካላት የሚሉት ካለ እጠብቃለሁኝ። ለማንኛውም ቤተክርስቲያን የቢዝነስና የጎጠኞች ቤት መሆኗን በትንሹ መረዳቴ ተገንዝቢያለሁኝ ሀይ ባይ መጥፋቱ ያሳዝናል፦ እናንተ ግን የጸጋ ባለቤት አብዝቶ ይባርካችሁ፡፡ ሁሉ በማስተዋል አድርጉት በቀጣይ በገባሁት ቃል መሰረት ካነበብኩት ካየሁትና እንደባለፈው ከተጨባጭ መረጃ የማዘጋጀውን እልክላችሁአለሁ። ቸር ይግጠመን።

    ReplyDelete