Wednesday, December 5, 2012

ኢካቦድ!!! የመንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ክብር ከቅዱስ ሲኖዶስ ተለየ




·        የኅብረተሰብዓዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ስለቤተክርስቲያን ሲል በቀድሞው ፓትርያርክ በአቡነ ቴዎፍሎስ ላይ የወሰደውን እርምጃ ደግፈናል. . . (አቡነ ገብርኤል፣ አቡነ ፊሊጶስ፣ አቡነ ቄርሎስና ሌሎችም የዛሬው ሲኖዶስ አባላት )

·        ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ እየተመራ አይደለም

·        አስቆሮቱ ይሁዳውያን ሊቃነጳጳሳት በዛሬዋ ቤተክርስቲያን

በቀደመው የቤተክርስቲያናችን ወርቃማ ዘመን፣ ሊቃነጳጳሳት ማለትም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በክርስትና ሕይወታቸው ለሃይማኖታቸውና ለእግዚአብሔር ያላቸው ታዛዥነት ታላቅ ነበር፡፡ እንደዛሬው እግራቸው ጫማ ሳይለምድ ጋራ ሸንተረሩን እየተዘዋወሩ ወንጌልን ይሰብኩ፣ ሃይማኖትን ያቀኑ ነበር፡፡ በዚያን ወርቃማ ዘመን በአመዛኙ አገልጋዩም ምዕመኑም በተቻለው መጠን መንፈሳዊ ተጋድሎው የበረታ፣ ተንኮል የሌለበትና ቅን ነበር፡፡

 በዛሬው ዘመን ያሉት አንዳንድ ሊቃነጳጳሳት ድሎትን ለምደው፣ ወገናዊነትን ተጠግተው የሚሰብኩት ሌላ፣ የሚኖሩት ሌላ እየሆነ፣ "አይጥ የማይጨርስ ድመት" ይመስል ክፋት፣ ዘረኝነት፣ ተንኮል፣ ሙስናና ጠብ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሲንሰራፋ ዝም እያሉ፣ ነገር ግን አባ እከሌ ለምን ተነኩብን፣ አባ እከሌ ለምን "ማኅበረ ቅዱሳን" ይነኩብናል በማለት ከሥልጣን ለማውረድና ለማውገዝ የሚያደርጉት መሯሯጥ እጅጉን አስገራሚ ነው፡፡

 ጨፍጫፊው ደርግ፣ ሃይማኖት አጥፊው ደርግ፣ አምባገነኑ ደርግ፣ ፋሽስቱ ደርግ፣ አቡነ ቴዎፍሎስን ያለ ፍርድ በገመድ አንቆ ሲገድል ዛሬ የሲኖዶስ አባል የሆኑ ሊቃነጳጳሳት ደግፈውት እንደነበረ ስንቶቻችን እናውቃለን? ስንቶቻችንስ ይህንን ዜና እናምነዋለን? ነገሩ ግን እውነትና እውነት ነው፡፡



ከእግዚአብሔር በታች ሕዝብን እንዲጠብቁ አደራ የተቀበሉት ጳጳሳት ሕዝብ በጅምላ ሲጨፈጨፍ ሀብቱ እንዲያ ሲዘረፍ ምንም አለማለታቸው ሲገርመን፣ የገዛ መንፈሳዊ ወንድምና አባታቸውን ደርግ ከጎናቸው ነጥሎ በግፍ አንቆ ሲገድላቸው ይደግፋሉ ብሎ ማንም በንጹሕ ሕሊና ሊያስበው አይችልም፡፡ ግን አስበው፣ መዝነው፣ ለክተውና ቆርጠው አቡነ ቴዎፍሎስን አንቀህ መግደልህ ትክክልና ትክክልነው ለወደፊቱም የእኛ ድጋፍ አይለይህም ነው ያሉት - ደርግን፡፡ 
 

 ልብ አድርጉ! እነዚህ ጉዶች፣ ደርግ ያንን መዓት በሕዝብ ላይ ሲያወርድ አቤቱ ሕዝብህን አድን ብለው ወደ እግዚአብሔር አልጮሁም፡፡ ሞቃቸው እንጂ አልበረዳቸውም፡፡ እንኳን አንድነታቸው በክርስቶስ ደም የታተመ ወንድማማቾችና ከአንድ ማዕድ የቆረሱ የአንድ የቤተሰብ አባላት ቀርቶ በአንድ አውቶቡስ ተሳፍረው ከተዋወቁት ሰው ጋር መለያየት ምን ያህል  ያሳዝናል? ያዕቆብ በስተርጅና የወለደው ዮሴፍ እንኳን ለወንድሞቹ ሕልም ቢነግራቸው በቅናት መንፈስ ቢነሳሱም ከመግደል ይልቅ መሸጥ ይሻላል ብለው ለባዕዳን አሳልፈው ሸጡት እንጂ እጃቸውን ሊያነሱበት አልደፈሩም፡፡ እነዚህ ጉዶች ግን የወንድማቸው፣ የአባታቸው እንደ በግ መታረድ የዶሮ ደም ያህል እንኳን ሳይቆጥሩት ደርግን ደግ አደረግህ አሉት፡፡

 ጲላጦስ አይሁዳውያን ጌታ ኢየሱስን ያለ ኃጢአቱ እንደከሰሱት ባወቀ ጊዜ፣ ለመግደልም ቆርጠው እንዳሤሩበት በተረዳ ጊዜ ቢያንስ በእዚህ ንፁሕ ሰው ምንም ጥፋት አላየሁበትም፣ እጄ ከደሙ ንፁሕ ነው ብሎ እጁን ታጠበ እንጂ ሊሞት ይገባዋል አላለም፡፡ እንደቤተክርስቲያን አስተምህሮ ጲላጦስ ከደሙ ንጹሕ ነኝ ማለቱ ከበደል የራቀ አላደረገውም፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስን መገደል አለባቸው ያሉት እነዚህ የዘመኑ ጉዶችማ በደላቸውና ክፋታቸው ምንኛ የጠለቀ ይሆን?

 አቡነ ፊሊጶስ፣ አቡነ ገብርኤል፣ አቡነ ቄርሎስ እና ሌሎች አሥራ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ቴዎፍሎስ መገደላቸውን የደገፉ እና ለፋሽስት ደርግ ያላቸውን ድጋፍ በቅዱስ ሲኖዶስ ስም በፊርማቸው ያጸደቁ ናቸው፡፡ እኝሁ አቡነ ገብርኤል፣ አቡነ ፊሊጶስ፣ አቡነ ቄርሎስና ሌሎችም በአቡነ ቴዎፍሎስ ግድያ ላይ የስምምነት ፊርማ ያኖሩ ሊቃነ ጳጳሳት ያሉበት ሲኖዶስ እውነት በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ነው? ለምን ራሳችንን እናታልላለን? መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መንፈሶች የእግዚአብሔር መሆናቸውንና አለመሆናቸውን መርምሩ 1ዮሐ. 41፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ አሠራር አንፃር ስንመረምረው፣ እነዚህ ጉዶች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተን ነው የአቡነ ቴዎፍሎስን ያለፍርድ በገመድ ታንቀው እንዲሞቱ ድጋፍ የሰጠነው ቢሉም መንፈስ ቅዱስ ግን ይህንን አይልም፤ አይዋሽምም፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ምክንያቱ በግልፅ ባልታወቀ ሁኔታ ከያዙት የፓትርያርክነት ሥልጣን ወደ ውጭ ሀገር ከሄዱ በኋላ በምትካቸው ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ተቀቡ፡፡ የቤተክርስቲያናችን ቀኖና እንደሚያዘው አንድ ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ሌላ አይሾምበትም፡፡ ይሁን እንጂ፣ በአንድ ወገን የብፁዕ አቡነ ጳውሎስ መሾም ትክክል ነው እንደተባለው ሁሉ በሌላ ወገን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሥልጣናቸው ማገልገል እንደማይችሉ ሳይታወቅ በላያቸው ላይ ሌላ መሾም አልነበረበትም፣ ቀኖና ተጥሷል፤ የሚሉ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በአንድ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ለሕክምና በሄድኩበት ነው ሹመቱ  የተካሄደው ማለታቸው ጭምር አይዘነጋም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ያለበት ሲኖዶስ አይዋሽም፡፡ ስለዚህ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በምን ምክንያት በላያቸው ላይ ሌላ ሊሾም እንደቻለ እስከዛሬ ሚስጥር መሆን አልነበረበትም፡፡

 ከዚያን ጊዜ በኋላም በሁለቱም ሲኖዶሶች በኩል ልዩነትን የሚያሰፋ እንጂ የሚያጠብ እንቅስቃሴ አልታየም፡፡ በተለይም፣ የሀገር ውስጡ ሲኖዶስ ለአብዛኛው የቤተክርስቲያን መሰነጣጠቅና መከፋፈል ምንም ዓይነት ቁጭት እንዳላደረበት ሁኔታዎች ያሳያሉ፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ሚዲያ በኩል ከሊቃነጳጳሳቱ ከአፋቸው እንደሰማነው  ቤተክርስቲያንን የሚከፋፍል፣ ሲኖዶስን የሚለያይ አካሄድ እንጂ ሁሉን ለእግዚአብሔር ትቶ ዕርቀ ሠላምን ለማውረድ፣ አንድነትን ለማምጣት እየተሠራ አይደለም፡፡

 ቀደም ባለው ጊዜ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ያሉት ሲኖዶሶች የተወጋገዙ ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ ውግዘቶቻቸውን ማንሳታቸው በመንፈስ ቅዱሰ እየተቀለደ ለመሆኑ አንድ ማረጋገጫ ነው፡፡ ጉዳዩ የፖለቲካ እንጂ የመንፈሳዊ ትግል ጉዳይ አለመሆኑ ቁልጭ ያለ ሐቅ ነው፡፡ በመካከላቸው ውሸት አለ ማለት ነው፡፡ የሀገር ውስጡ እንደ ሕጋዊ ተቋም ቤተክርስቲያንን ሲመራ በርካታ ውሳኔዎችን ያስተላለፈ ሲሆን ውሳኔዎቹ ግን ተግባራዊ ሳይሆኑ ማንም እየተነሳ በግል የሚጥሳቸውና ያወጣቸው መመሪያዎችም ጥርስ የሌለው አንበሳ እየሆኑ መሽመድመዳቸውን ስናይ፣ ውሳኔዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳልተወሰኑ እንረዳለን፡፡

በተለይም ሲኖዶስ ኃይል እያጣ አባላቱ በዘር በጎሳና በጥቅማ ጥቅም በመደለል ውሳኔዎቹን ሆን ብለው ሲያጣምሙ ስናይ በእርግጥም መንፈስ ቅዱስ ከቅዱስ ሲኖዶስ መለየቱን ልናይ ችለናል፡፡ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሐረር ላይ "ማኅበረ ቅዱሳን" ሠራዊት ባቀነባበረው የሐሰት ክስ ሰባት ዓመት እሥራት ሊፈረድባቸው ጫፍ በደረሰ ጊዜ ጉዳያቸውን ሲኖዶስ በቸልታ ነበር ያለፈው፡፡ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ሀዋሳ ላይ ጥቂት የኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች ቡድን በአሮጌ ሰበካ ጉባዔ ስም ተሰግስገውና "ማኅበረ ቅዱሳን" ጋር ተባብረው የሐሰት ክስ አቀነባብረው በወነጀሏቸው ጊዜ ቋሚ ሲኖዶስ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የተመራ አጣሪ ቡድን ወደ ስፍራው ቢልክም የጥቅምት 2003 የሲኖዶስ ጉባዔ ስለ ንጽሕናቸው የሚመሰክረውን ሪፖርት ሊያዳምጥ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ይልቁንም ችግሩን አድበስብሶ በወቅቱ ከፍተኛ ሁከት ወደ ነበረበት ወደ ድሬዳዋ ሀገረ ስብከት የመደባቸው ሲሆን እባካችሁ ቀይሩልኝ ብለው ቢማጸኑም ከዚያ ያልተሻለ ወደ ሰዋስወ ብርሃን ወጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ላካቸው፡፡ እርሳቸው ቢያንስ ንጽሕናዬ ተመስክሮልኝ የምትወስኑትን ወስኑ ብለው ቢማፀኑም የሰማቸው አልነበረም፡፡ ለአንድ ንፁሕ ሊቀጳጳስ ከመመስከር ይልቅ እንደ ቁራ ለሚንጫጫ "ማኅበረ ቅዱሳን" ያጎበደደ ሲኖዶስ ነው፡፡ ጉባዔውም መንፈስ ቅዱስ የሚመራው የሲኖዶስ ጉባዔ አልነበረም፡፡

 በአሁኑ ወቅት ያለው የፓትርያርክ መምረጫ ሕግ ችግር ያለበት ወይም ሕጉ ጨርሶ የሌለ ይመስል የምርጫ ሕግ የሚያረቅ የአፍቃሬ "ማኅበረ ቅዱሳን" ሊቃነጳጳሳት ቡድን ተቋቁሟል፡፡ ይህ ቡድን በተለይም ከአባላቱ ጥንቅር ባህርያት ስንነሳ በሥጋዊ አስተሳሰብ "ማኅበረ ቅዱሳን" እየተመራ፣ "ማኅበረ ቅዱሳን" በሚመች መልኩ ደንቡን ያወጣ እንደሆን እንጂ መቼም እግዚአብሔር የሚወደውን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ይሠራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡  የፓትርያርኩን አቅም የሚያዳክም፣ የቋሚ ሲኖዶስን ሕልውና የሚሸረሽር የቡድን ስምንት ኮሚቴ መቋቋም በሥጋዊ አስተሳሰብ እንጂ ለመንፈስ ቅዱስ መገዛትን አያሳይም፡፡

 የወለዱ ጳጳሳት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይህ ዓለማዊ ልምምድ በተለይም ከቀኖና ቤተክርስቲያን አንፃር ሲታይ "ብፁዕነቱን" ለስሙ ብቻ አዝለውት የሚዞሩ እንዳሉ የሚያሳይ ነው፡፡ ሲኖዶስንና ቤተክርስቲያንን የሚያዋርድ ይህ ዓይነቱ ውስልትና በተለይም በሟቹ በአቡነ ሚካኤል ላይ ፍርድ ቤት ያረጋገጠው ጉዳይ ሲሆን ሌሎችም በዚህ ድርጊት የተጠመዱ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ የተሰገሰጉበት ሲኖዶስ እንዴት በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ነው ሊባል ይችላል?

 በዛሬዋ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ እየወሰነ አይደለም፡፡ ሲኖዶስ ቦታውን "ማኅበረ ቅዱሳን" ለቆ ከሳሽ፣ ምስክርና  ፈራጅ "ማኅበረ ቅዱሳን" ሆኗል፡፡ ለዚህም ነው ኃላፊነታቸውን የዘነጉ ራሳቸውን "ማኅበሩ" ያስገዙ ሊቃነጳጳሳት "ማኅበረ ቅዱሳን" ባዘጋጃቸው የምግብ ግብዣ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ". . . የቤተክርስቲያናችን ጠባቂ 'ማኅበረ ቅዱሳን' ነው" ብለው እስከ መመስከር የደረሱት፡፡ የቤተክርስቲያን ጠባቂ እግዚአብሔር፣ የሲኖዶስ ጉባዔ ጠባቂ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር መሆኑን ፈጽመው፣ ፈጽመው ረስተውታል፡፡

 

ወደ ቀደመው ነገራችን ስንመለስ በአቡነ ቴዎፍሎስ ግድያ ጉዳይ ደርግ ግንባር ቀደም ተጠያቂ ቢሆንም፣ 16 ሊቃነ ጳጳሳት ድጋፍ በመስጠታቸው በሃይማኖታቸው ላይ ክህደት የፈጸሙ ከመሆኑም በላይ የአስቆሮቱ ይሁዳ ደቀመዛሙርት መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ታዲያ እነዚህ ናቸው ቤተክርስቲያንን የሚመሩት? በተለይም አቡነ ገብርኤል ውግዘት ተላልፎባቸው አቶ ኢያሱ ከተባሉ በኋላ በይፋ ውግዘቱ ሳይነሳላቸው ተመልሰው የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መሆናቸው ሰዎቹ ምን ያህል መንፈስ ቅዱስን ለማታለል እንደደፈሩ እንረዳለን፡፡ ሀዋሳ ላይ ከፍተኛ ብጥብጥ ሲያካሂድ በነበረው ዓለምሸት /ፃዲቅ ላይ አጣሪ ኮሚቴ ተመድቦ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት ሲኖዶስ ከሲዳማ ሀገረ ስብከት እንዲነሳ የወሰነበት ሲሆን፣ አቡነ ገብርኤልና አቡነ ፊሊጶስ በሚስጥር ተስማምተው በስርቆት ወደ ሀገረ ስብከቱ መልሰውታል፡፡ ግለሰቦች በዘፈቀደ ተነስተው ውሳኔውን የሚሽሩበት ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ነው ማለት በራሱ ሹፈት ይሆናል፡፡

በየጠረፉ ጣራቸው የሚያፈስ፣ ግድግዳቸው የተዳሰ፣ ካህናትና ንዋየ ቅድሳት የሌሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት በርካታ ናቸው፡፡ ታቦታት መጎናፀፊያ አጥተው በግለሰቦች ጋቢ የሚሸፈኑባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ ነገር ግን፣ ነቢዩ ሐጌ ይህንን እያዩ ለማያስተውሉ የእሥራኤል መሪዎች ያስተላለፈው መልዕክት ነበር - "የእግዚአብሔር ቤት ፈርሶ ሳለ፣ በውኑ ባማረ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን" (ሐጌ 13)፡፡ ከተሞች ላይ ባማረ መኖሪያ ቤታቸው እየተንደላቀቁ፣ ከመበለቶች በሚሰበሰብ ገንዘብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላነሰ ወይም በላይ ደመወዝ እየተከፈላቸው በሀገረ ስብከታቸው የሚገኙ ገጠር አብያተክርስቲያናትን በዓይናቸው ለማየት የማይፈልጉ ሊቃነ ጳጳሳት ባሉበት፣ የሁሉ ነገር ፍትሐዊነት የጎደለበት የቤተክርስቲያን አስተዳደር በሰፈነበት ሁኔታ ሲኖዶስን መንፈስ ቅዱስ ይደግፈዋል ማለት ራስንም ማታለል ነው፡፡

 ዲያቆናት፣ አገልጋይ ካህናትና መነኮሳት ከሊቀጳጳሱና ከሀገረስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ጋር ሲነፃፀር ደመወዛቸው የሰማይና የምድርን ያህል ከመራራቁም በላይ አንድ የወረዳ፣ የአጥቢያ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ወይም የቤተክህነትና የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አንዱን አገልጋይ የዓይኑ ቀለም ደስ ስላላለው እና የእጅ መንሻን ስለማይሰጥ ብቻ ወደ ፈለገው ጠረፍ ሊልከው ወይም ሊያባርረው ይችላል፡፡ ይህንን ለምን ታደርጋለህ ብሎ ደፍሮ ሊጠይቀው የሚችል የለም፡፡ ዲያቆናት፣ ካህናትና ልዩ ልዩ አገልጋዮች ይህ ዕጣ እንዳይደርስባቸው እውነት ሲጨፈለቅ፣ ግፍ ሲፈጸም፣ ለቁራሽ ዳቦና ለእፍኝ ቆሎ ሲሉ አይተው እንዳላየ ዝም ይላሉ፡፡

 መጽሐፍ ቅዱስ 1 ሳሙ. 421 እንደሚነግረን ዔሊ የሚባል የእግዚአብሔር አገልጋይ ካህን ነበር፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ የሚባሉ ወንዶች ልጆችም ነበሩት፡፡ እነዚህ ልጆች ግን የሚፈጽሙት ጸያፍ ሥራ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ አልነበረም፡፡ ለእግዚአብሔር ከሚዘጋጀው መስዋዕት ውስጥ የሚቻላቸውን ያህል ከመብላታቸውም በላይ ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጡትን ሴቶች በመገናኘት ነውርን ይፈጽሙ ነበር፡፡ ዔሊም የልጆቹን ጥፋትና ኃጢአት እያወቀ አይገስጻቸውም ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ የእግዚአብሔር ቁጣ በላያቸው ነደደ፡፡ በብላቴናው በሳሙኤል በኩልም የዔሊን ዘር እንደሚቀጣ ገለጸ፡፡ በገለጸውም መሠረት እሥራኤላውያን በፍልስጤማውያን እንዲሸነፉ አደረገ፡፡ የቃል ኪዳኑም ታቦት ተማረከ፡፡ አፍኒንና ፊንሐስም በጦርነቱ ውስጥ ተገደሉ፡፡ ዔሊም የእሥራኤላውያን መሸነፍ እና የቃል ኪዳኑ ታቦት ተማርኮ መወሰዱንም በሰማ ጊዜ ከተቀመጠበት ወደ ኋላው ወድቆ አንገቱ ተሰብሮ ሞተ፡፡ የዔሊ ምራት የባሏንና የአማቷን መሞት እንዲሁም የቃል ኪዳኑ ታቦት ተማርኮ መወሰዱንም በሰማች ጊዜ ወዲያው ምጧ መጥቶ ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ ይሁን እንጂ እስትንፋሷ በሞት የተቋረጠው ለልጇ ኢካቦድ የሚል ስም አውጥታ ነው፡፡ ትርጓሜውም የእግዚአብሔር ክብር ከእሥራኤል ተለየ ማለት ነው፡፡

 በአሁኗ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሕዝብ በአሥራት እና በስለት መልክ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን ገንዘብ እንደፈለገው የሚጨረግዱ ካህናት እንዳሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ካህናትም ሆኑ ልዩ ልዩ ሥልጣነ ክህነት ያላቸው ኃላፊዎች ስካርም ሆነ ሌላ የሚያስነውር ድርጊት የሚፈጽሙም አሉ፡፡ "ማኅበረ ቅዱሳን" ቤተክርስቲያን ጉያ ውስጥ ተሸሽጎ የፖለቲካም ሆነ ሕገ ወጥ ንግድ ውስጥ ከመሠማራቱም በላይ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ሥርዓተ ቁርባን እየተቋረጠ ድብድብና ሁከት የሚያካሂድ ሲሆን የሐሰት ክስ እየተቀነባበረ አባቶች የሚበደሉበት ተንኮል የሚሸርብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር እንደ ካህኑ ዓሊ ጥፋትን አይተው የማያርሙ አባቶች የሚቀጡ ከመሆኑም በላይ የጥፋቱ ተዋናዮችም ከፍርድ የሚያመልጡ አይሆኑም፡፡

 የቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ እና ሊቀጳጳስ ወንድሙን፣ አጎቱን፣ የወንድሙን ልጅ፣ የአጎቱን ልጅ፣ ዘመዱን፣ ከዚህ አልፎ ተርፎም ወሎዬው ወሎዬውን፣ ጎንደሬው ጎንደሬውን፣ ጎጃሜው ጎጃሜውን፣ ሸዌው ሸዌውን እየሳበ ቤቱ የቤተዘመድ ኢንተርፕራይዝ እስኪመስል ድረስ ተወርሯል፡፡ ደቡብ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ፣ ክልሎች የሚመጣላቸውን ሰው ከመቀበል ውጪ ከራሳቸው፣ በራሳቸው ቋንቋ የሚያስተምርም ሆነ የሚቀድስ ሰው እንዳይኖር እጅ አዙር አፈና እየተካሄደባቸው ነው፡፡

 ይህ ሁሉ ችግርና ተውሳክ የበዛበት ሲኖዶስ እንደ ቃል ኪዳኑ ታቦት የቤተክርስቲያን ልጆች ከበረቱ ወጥተው እየተሰደዱ በሌሎች እየተማረኩ የሚወሰዱ ከሆነ፣ ሲኖዶስ ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ፣ የሃይማኖት ክህደት ተፈጽሞብናልና ማቅ ለብሰን፣ አመድ ነስንሰን መሪር ለቅሶ ልናለቅስ ይገባናል፡፡ እንደ ካህኑ ዔሊ ምራት - ኢካቦድ!!! የመንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ክብር ከሲኖዶስ ተለይቷል እንላለን፡፡

እግዚአብሔር አጽራረ ቤተክርስቲያንን ያስታግስልን!!!

አሜን!!!

4 comments:

  1. Your article is very good but you mixed up the information of those who are the late Bishops involved in the death of HH Abune Theophilos with those ordained later. Please correct! Thanks for the attachment. We know there are mahibere kidusan groups who were involved like Like Gubae Abera, Kesis Dagnachew Kasahun, Kesis Kinfegebriel Altaye

    ReplyDelete
  2. ሁሉም የስራውን አያጣም። ፍርዱ በዚህ ምድር ነው ወደ ሰማይ አይደርስም።

    ReplyDelete
  3. Abune Gabriel is the previous one not. He passed away long time ago. please read the history first Abune Gabriel Yeteshomut BeAbune Teklehaymanot new

    ReplyDelete
  4. አዬ ጉድ!አዬ ጉድ ያንተ ያለህ!ስንቱ ይሰማል ስንቱስ ይተረካል፣ ወይ አንቺ ቤተ ክርስቲያን የወደፊት ዕጣሽ ምን ይሆን? እነሆድ አምላኩ በሰው የሚመኩ ራስ ጉልላትሽ
    ላይ ተኮፍሰው ቅዱሳንን ተመሳስለው ግጠው ግጠው አጽምሽን ወርውረው ባዶ ሊያስቀሩሽ ነው። ምን አለ መንፈስ ቅዱስ እያሉ ሰውን ሳያታልሉ ተስማምተው ቢበሉ
    ቅዱሳን ወንድሞች ብጹዓን አባቶች ማለት ዕኮ ትንሽ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት--ዕውነት ስትኖር ነው። በባዶ እንዲህ መባል ራስን ማታለል ያማኞችን
    ወኔም መግደል ነው። የዐውደ ምሕረት አዘጋጆች ግን ተመስጋኞች ናችሁ የተደበቀ የግፍ ምሥጢር እያወጣችሁ ላላወቀው በማሳወቃችሁ እናም በዚሁ በርቱ ተበአስ በእንተ ጽድቅ
    እስከ ለሞት እግዜር ከናት ጋር ይሁን!

    ReplyDelete