Thursday, September 6, 2012

ለአቡነ ገብርኤል የጉጂ ቦረና ሀገረስብከትን ደርበው እንዲያስተዳድሩ ደብዳቤ ተጻፈላቸው፡፡


  • click to read in PDF: Abune gebrel 
  • ደብዳቤውን የጻፉት ብጹዕ አቡነ ናትናኤል ናቸው፡፡
  • ተስፋዬ ውብሸት የማኀበረ ቅዱሳን ወገንነቱን በተግባር እያሳየ ነው፡፡
  • ሲያምርን የጉጂ ቦረና ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ አድርጎ ሊሾመው ነው፡፡
ብጹዕ አቡነ ገብርዔል የጉጂ ቦረና ሀገረ ስብከት ጉዳይ ገና በማጣራት ላይ እያለ ደርበው እንዲያስተዳድሩ ደብዳቤ ተጻፈላቸው፡፡ የደብዳቤውን መጻፍ አቡነ ህዝቅኤል አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡ ምክንያታቸውም ጉዳዩ መንግስት የገባባበት ስለሆነ ማጣራቱ ሳያልቅ እሳቸውን ወደዛ መላኩ ያስነቅፈናል የሚል ነው፡፡
በተያዘ ዜና የጠቅላይ ቤተክህነቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተስፋዬ ውብሸት በቅዱስነታቸው እና በመንግስት የተሰጠውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው ለሲያምር ተክለማርም የጉጂ ቦረና ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅነቱን ሊሰጡው እንደሆነ ጠቅላይ ቤተክነት አካባቢ ያሉ ምንጮቻችን ገለጹ፡፡ ቅዱነታቸው ከማረፋቸው በፊት የጉጂ ቦረና ሀገረ ስብከት ምዕመናን በተደጋጋሚ ስለችግሩ ስፋትና ጥልቀት እና ሊያስከትል ስለሚችለውም አደጋ ለመንግስት እና ለቅዱስነታቸው በደብዳቤ በማሳወቃቸው ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እና ከቤተክህነት የተወጣጣ አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ የማጣራት ስራውን ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ቅዱስነታቸው በማረፋቸው ምክንያት ማጣራቱን አቁሞ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸው ታውቋል፡፡
አጣሪ ኮሚቴው ከፌዴራል ጉዳዮች ሁለት ሰው ከኦሮሚያ አንድ ሰው እና ከጠቅላይ ቤተክህነት አራት ሰዎች ያሉበት የነበረ ሲሆን ከቤተክህንት በኩል ተወክለው የነበረው ተስፋዬ ውብሸት፣ እስክንድር፣ ፋንታሁን ሙጬ እና ፍስሀ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡
በቅዱስነታቸው ዕረፍት ምክንያት ማጣራቱን አቋርጠው መምጣታቸው ትክክል ቢሆንም የጉጂ ቦረና ሀገረ ስብከት ህዝብ ከቅዱስነታቸው እና ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሀዘን በሃላ ይመጡልናል እና ህዝቡን አናግረው እውነታው ይረዳሉ ብሎ እየጠበቀ ሳለ እነ ተስፋዬ ግን አደራ በል ሆነው ለሲያምር ስራ አስኪያጅቱን ለመስጠት ማሰባቸው በርካቶችን አሳዝኗል፡፡ በሲያምር ምክንያት ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂው ሲኖዶሱ ይሆናል ብለው ያስገቡትን ደብዳቤው ክብደት ሳይረዱ በምን አለብኝነት ሲያምርን ለመሾም ማሰብ ሊፈጠር ለሚችለው ችግር ሲኖዶሱም ሆነ እነ ተስፋዬ ከተጠያቂነት የሚያመልጡበት አይሆንም፡፡
ሀገር ሁለት መሪዎችዋን አጥታ መረጋጋት በሚያስፈልግበት በዚህ ወቅት ወደ ብጥብጥ የሚያመሩ ነገሮችን ማድረግ አስፈላጊነቱ ለምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ የሚሰጡት መልስ ምን ሊሆን እንደሚችል እነ ተስፋዬ እና አለቃቸው ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ነው የሚያውቁት፡፡
ሰሞኑን ጠቅላይ ቤተክህነት አካባቢ የማይጠፋው ሲያምርን በተስፋዬ ወደ “ስራ አስኪያጅነቱ መመለስ እፈልጋለሁ ብለህ ደብዳቤ ጻፍ” ጉዳዩን አንቀሳቅስ ከዛ በኃላ ቦታውን እንሰጥሀለን ተብሎ መመከሩ እና አቡነ ገብርኤልም የልብ የልብ ልብ እንደሰጡት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከቅዱስነታው ዕረፍት በኋላ በሽፋን ያደርገው የነበረውን ማኅበረ ቅዱሳንነቱን ግልጽ እንዳወጣው እና የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎችም ተስፋዬም ሆነ እስክንድር የኛ ናቸው በቤተክህነቱ አስተዳደር የምንፈልገውን እናደርጋለን ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
አሁን የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ ዝም ብለን ቦታውን ከምንሰጥህ በመንግስት በኩል ያለውን ተጠያቂነት ለማጥፋት ተመልሰን ሄደን ማጣራቱን ጨርሰናል ህዝቡ ይፈልገዋል ብለን እንጽፍልሀለን እያሉት እንደሆነም ታውቋል፡፡ የሆነ ሆነ በቦታው ላይ የሲያምር መሾም የሚያስከትለው ችግር ሰፊ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ህዝብ አንፈልግም እያለም ከህዝብ ጋር እልህ ተጋብቶ ለማኅበረ ቅዱሳን ፍላጎት ይህን ያህል እራስን ማስገዛት ለሚፈጠሩ ችግሮች ከሚፈጠረው ተጠያቂነት እንደማያስጥል እነ ተስፋዬ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡
ዘግይቶ በደረሰን ዜና የሲያምርን የሹመት ዳር ዳርታ አቡነ ፊሊጶስ አጥብቀው ተቃውመውታል፡፡
የጉጂ ቦረና ህዝብ ለቅዱስነታቸው አቅርቦት የነበረው አራተኛው ደብዳቤ ሙሉ ቃል ይህን ይመስላል፡፡
ሐምሌ 5 2004 ዓ.ም
ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት

ጉዳዩ፡- ከመከራ ከሰቆቃና ከእንግልት እንዲታደጉን ስለመጠየቅ
ቅዱስ አባታችን
ችግራችን ከዕለት ወደ ዕለት እየከበደ የሰቆቃው ቀን እንደ ዔሊ እድሜ ረዝሞብን እየተንገላታንብዎ ያለን እኛ በጉጂ ቦረና ሊበን ዞን ሀገረ ስብከት እና ቡሊ ሆራ ነዋሪዎች የሆንን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ልጆችዎ ማኅበረ ቅዱሳን በሚባል አዲስ የሐይማኖት አስተሳሰብ ይዞ የመጣው የፖለቲካ ድርጅት እና ስያሜውን ያወጡለትና ያቋቋሙት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እያደረሰብን ያለውን ግፍና በደል ገደብ በማጣቱና ሃይ የሚለው በመጥፋቱ የተከፋነውን መከፋት በእርስዎ በአባታችን ፊት በተደጋጋሚ አቤት ማለታችን ይታወሳል፡፡ ይህ ምስጢሩ አልፈታ ያለ የነገር ቅቤ የሆነ ማኅበር ማኅበረ ቅዱሳን በተለያየ መንገድ እያስፈራራ የሚያደርስብን እንግልትና ጉዳት ልባችንን ክፉኛ የሰበረው መሆኑንና በገዛ ሀገራችን አገር እንደሌለን እስኪሰማን ድረስ ስላቆሰለን ጉዳታችንን በቶሎ መፈትሔ እንዲሰጡልን አሊያም ደግሞ ለመንግስት አካል ለጉዳዩ መፍትሔ እንዲፈልግለት እንዲጽፉልን አሁንም እንደ ቀድሞው በሰማይና በምድር ጌታ ስም አቤት እንላለን፡፡
ቅዱስ አባታችን
በገዛ አገራችን የሚገርፈን የሚቀጣን የሚያሳድደን ቤተክርስቲያንን የተከለለው የወንጀል ድርጅት ማኅበረ ቅዱሳን በሚያራምደው የዘር ፓለቲካ ምክንያት የአካባቢው ተወላጅ የሆኑትን ካህናት እያሳደደ ይገኛል፡፡ እኛ እንደ ሃይማኖታችን ሥርዓት ለመኖር ስንሞክር እነርሱ ግን ለራሳቸው በፈጠሩት፤ የአሳደህ በለው፣ እያዋከብክ ሰላም ንሳው፣ የሚል ፍጹም ኢክርስቲያናዊ የሆነ አስተሳሰብ መሰረት ስልቱን እየቀያየረ የሚደርስበንን ሁከትና ማሳደድ ምክንያት በእውነት እኛም ኢትዮጵያዊያን ነን ወይ? የሚል ጥያቄ በልባችን መመላለስ ከጀመረ ሰንብቷል፡፡ ምነዋ ቸል ተባልን? ምነዋ ግፍ ገነነብን? ምነዋ ስቃይ በዛብን? ግፉ ልባችንን አዝሎበን ግራ ስለገባን የተገፋ ቃል አይመርጥምና ይቅር እንዲሉን እየጠየቅን ከአሸባሪው ማኅበረ ቅዱሳንና ከባራኪው አባቱ አቡነ ገብርኤል እንዲገላልሉን እንደገና በከበረው ጌታ በልዑል እግዚአብሔር ስም እንለምናለን፡፡
ቅዱስ አባታችን
በተደጋጋሚ በሰራቸው ወንጀሎች ማለትም የሀገረ ስብከት መኪና ይዞ በመሰወር ማኅተም ይዞ በመጥፋትና ቢሮ አላስረክብም ብሎ በማንገራገር ፍርድ ቤት ቀርቦ የተወሰነበት መጋቤ ጥበባት ሲያምር ተክለማርያምና ከእርሱ ጋር ወግኖ ማኅበረ ቅዱሳን ወይም ሞት እያለ እየረበሸ የሚገኘውና እርሱም ቢሆን ተዘዋውረህ ሊበን ወረዳ ስራ ሲባል አልሄድም ብሎ ማኅተም ሳያስረክብ እየረበሸ የሚገኘው ሊቀስዩማን ልሳነ ወርቅ ሁንዴን አቡነ ገብርኤል በቁጥር 258/11/1/04 በቀን ግንቦት 30/2004 ዓ.ም ወደ ስራቸው እንዲመለሱ የሚያዝ ደብዳቤ በመጻፍ በሌላቸው ሥልጣን አገሩን በማኅበረ ቅዱሳን እያሸበሩት ይገኛሉ፡፡
ይህ ሲያምር የሚባል ግለሰብን አቡነ ገብርኤል የእናንተ ደርቤ እሰራለሁ አንተንም መልሼ እሾማለሁ ብለው ስለነገሩት ፍርድ ቤት አስረክብ ብሎ የወሰነበትን ማኅተም ይዞ ወደ ስራ አስኪያጅነት ስራዬ ተመልሻለሁ በማለት በግንቦት 12 ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ላይ ሲበጠብጥ የተቃወሙትን ሰዎች አሳስሯል፡፡ ሰዎቹ እስካሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
ለዚህ ተግባሩ ትልቅ እርዳታ የሚያደርጉለት የጉጂ ዞን አስተዳደር የሆኑት አቶ ገዳ ሮቤ እና ጉጂ ዞን ጸጥታ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ጉቱ ፍትህ እንዳያጓድሉ ፍርድ እንዲያደላድሉ መንግስት በሚከፍላቸው ደሞዝ የማኅበረ ቅዱሳንንን ሥራ በመስራት ለመረጣቸው ህዝብ ሳይሆን ለማኅበረ ቅዱሳን በመታዘዝ እያስቸገሩ ስለሆነ ሚናቸውን እንዲለዩ እንደደረግልን ለመንግስት እንዳሳስቡልን እንለምናለን፡፡
ቅዱስ አባታችን
ከዚህ በፊት እነዚህ ባለስልጣናት ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር እየተማከሩ አያገባቸው ገብተው አጣሪ ኮሚቴ ሲመጣ የማኅበሩን ተቃዋሚዎች አግልለው የማኅበሩን ሰዎች ብቻ በማገናኘት የሻኪሶው ጉዳይ ችግሩ ባልተፈጸመበት ነገሌ ላይ እንዲታይ በማድረግ ለችግሩ መስፋፋትና አለመቆም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጉ ሰዎች ናቸው፡፡ ችግሩ መቆም ስላልቻለም ለሁለተኛ ጊዜ የመጡ አጣሪዎች የማኅበረ ቅዱሳን ተላላኪ አለመሆናቸውን ሲያውቁ አናውቃችሁም ስለዚህ ማጣራት አትችሉም ወደመጣችሁበት ተመለሱ በማለት በቤተክርስቲያን ጉዳይ እውነት እንዳይወጣ በመከላከል በቤተክርስቲያኑቱ ላይ ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ እንዲነግስ በማድረግ ለማኅበሩ አድረው መንግስት ያልሰጣቸውን ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሰዎች መንግስት እንዲያስታግስልን እዲነግሩልን እንለምናዎታለን፡፡
ቅዱስ አባታችን
በጠቅላይ ቤተክህነት በማይታወቅና ባልጸደቀ ሹመት መጋቢ ጥበባት ሲያምር የነገሌ ኪዳን ምህረትን አስተዳዳሪን 24000 ሺህ ብር አምጡ ቢል እምቢ ስልጣንህ ያልተረጋገጠ ነው በማለታቸው ከስራቸው አግዶ ለአቡነ ገብርኤል ግልባጭ የጻፈ ሲሆን እንዲሁም የነገሌ ቦረና ገብርኤል ሰበካ ጉባኤና ህንጻ አሰሪ ኮሚቴ አውርዶ የራሱን ሰዎች ሕንጻ አሰሪና ሰበካ ጉባኤ አስደርጎ አስመርጧል፡፡ ህዝቡ ይህንን አሰራር ሲቃወምም ሕጋዊ ስልጣን እንደሌለው እያወቁ የመንግስት ኃይሎች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉለት ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም የሞያ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑትን ሊቀ ማዕምራን ቆሞስ አባ ኤፍሬም ኢያሱን እና የአዶላ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑትን መሪ ጌታ ቀሲስ መንክር ፀሐይን አግዶ ሌሎችንም እያስፈራራ ፈሰስ እየተቀበለ ይገኛል፡፡ ሥልጣኑ የማይታወቅ ሕጋዊ ያልሆነ ሰው ህጋዊ ሰዎችን እያገደና እያሸማቀቀ ስናይ በገዛ ሀገራችንን እንግድነት እየተሰማን እየተሸማቀቅን እንገኛለን፡፡
ቅዱስ አባታችን
እንደ ሲያምር ሁሉ ከስልጣናቸው ከተነሱ በኋላ ማኅተም አላስረክብም በማለታቸው በፍርድ ቤት ማኅተም እንዲያስረክቡ ተጠይቀው ማኅበረ ቅዱሳንን ተተግነው እምቢ ብለው ያሉት ሊቀስዩማን ልሳነ ወርቅ ሁንዴ እና ቀሲስ መኮንን ጉተማ በቦታቸው የአዶላ ዋደራ ወረዳ ቤተክህነት ሊቀካህናት ጸሐፊ ተደርገው የተሾሙትን ቀሲስ ጌታነህ እንዳለን እና ቀሲስ ብርሃን ክፍሌን ማኅተምና ቢሮ አላስረክብም በማለት ሥራ እንዳይሰሩ ስላደረጉ አስቸኳይ ማስተካከያ እንዲደረግልን እንጠይቃለን፡፡
ቅዱስ አባታችን
ቤተክርስቲያን በከፍተኛ ወጪ አስተምራ ያስመረቀቻቸው የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ባለፉት ሁለት አመታት በማኅበረ ቅዱሳን አዝማችነት ተሀድሶ መናፍቅ እየተባሉ ሥራ ሊሰጣቸው ያልቻለ ሲሆን እንዲሁም ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊገቡ የሚፈልጉ የቤተክርስቲያን ልጆች ደግሞ የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅና ሊቀ ጳጳስ ስለሌለ መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን እንጂ ማኅበራትን የማያገለግል ሊቀጳጳስና ሥራ አስኪያጅና ተመድቦልን ሁለገብ ችግሮቻችን ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲየገኙልን እንለምናለን፡፡
ቅዱስ አባታችን
ማኅበረ ቅዱሳን ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እኔ ነኝ የሚል እምነት በመጀመሩ የነገሌ ቅዱስ ገብርኤል ሰነበት ትምህርት ቤትን የማኅበሩ አባላት ካልናችሁ ከቤተክርስቲን ውጡ በማለት በ27/10/2004 ዓ.ም. ዘግቶታል፡፡ ይህ አሸባሪ ማኅበር ከትናንት ዛሬ እብሪቴ እየጨመረ እየመጣ ለመሆኑ ይሔ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ቅዱስነትዎ የችግሩን ጥልቀት ተመልክተው ሰንበት ትምህርት ቤቱን በአስቸኳይ እንዲያስከፍቱልን እና ችግሩን ለመንግስት አካል አስረድተው ማኅበረ ቅዱሳን ከአካባቢው ዘወር እንዲደረግልን በከበረ ትህትና እንለምናለን፡፡
ቅዱስ አባታችን
በመጨረሻም ተስፋ መቁረጥ እያንገላታን የችግሩ ክብደት እየመረረን ነውና እንደ ክርስቲያን እዲሆን የማንፈልገው ስር ሰደደ አለመረጋጋት ብጥብጥና ደም ማፍሰስ ከመከሠቱ በፊት አቡነ ገብርኤል አካባቢያችን እንዳይደርሱ እዲደረግና ማኅበረ ቅዱሳን የተባለ አፋኝ ቡድን ከቤተክርስቲያን ገለል እንደደረግልን እንዲሁም እግዚአብሔርን የሚፈራ ለእውነት የሚቆም ሰላማዊ አባትና ሥራ አስኪያጅ እንዲመደብል እና ችግራችን ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲያገኝ ለመንግስት እንዲሳውቁልን በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን፡፡
ቅዱስ አባታችን
እኛ ለጆችዎ ከእግርዎ ሥር ወድቀን የምንለምንዎ፤
1ኛ. የዲያቢሎስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ሰላም እየነሳን የሚገኘውን ማኅረ ቅዱሳን የሚባለውን የሁከትና የረብሻ ማኅበር ከመንግስት ጋር ተባብረው እንዲያስታግሱልን፡፡
2ኛ. ጭር ሲል የማይወዱትና ከሁከት በቀር በመልካም ነገር የማይገኙትን አቡነ ገብርኤልን ሀገረ ስብከቱን ከመረበሽ ነጻ እንዲያወጡን፡፡ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር እንዲህ ያፋቀራቸው ጉዳይ ምንጩ ምን እንደሆነ መንግስት እንዲያጣራ እንዲደረግልን፡፡
3ኛ. አለስራው እየገባ እየበጠበጠ እያስቸገረ ያለውን መጋቢ ጥበባት ሲያምር ተክለማርያምን አርፎ የሚቀመጥበትን መንገድ እንዲፈለግልን እና ያለሕጋዊ ሹመት ቤተክርስቲያንን በማወክ እንዲከሰሰስልን፡፡ እንዲሁም በመጋቤ ጥበባት ሲያምር አስገዳጅነት እንዲያስረክቡ እንዲደረግልን፡፡
4ኛ. ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ሀገረ ስብከቱ ለቤተክህነት ማስገባት የነበረበት ገቢ እንዳልተላከና ወደየትኛው ድርጅት እንደ ገባ ኦዲተር ተልኮ ማጣራት እንዲደረግልን፡፡
5ኛ. ለማኅበረ ቅዱሳን አድረው ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳሳ እያደረጉ ያሉትን የዞኑ ባለስልጣናትን መንግስት እንዲፈትሸልን እና እንዲያስታግስልን፡፡
6ኛ. ቤተክርስቲያንን እንጂ ማኅበረ ቅዱሳንን የማያገለግሉ ሊቀ ጳጳስና ሥራ አስኪያ እንዲመደብልን በማክበር እንጠይቃለን፡፡
የቅዱስነትዎ ቡራኬ ይድረሰን!
እግዚአብሔር አገራችንን ይባርክ
የቀርጫ፣ የሐገረ ማርያም፣ የሶሎሞና ኡራጋ፣ የገርባ፣ ሻኪሶና የአዶላ ወረዳ ቤተክህነት ተወካዮች
ግልባጭ፡-
Ø  ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት
Ø  ለጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት
Ø  ለመንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት
Ø  ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት
Ø  ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር
Ø  ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት

1 comment:

  1. እንዴት ነው ነገሩ ሁሉ። አባቶች በአንድ በኩል ሱባኤ ያውጃሉ። በሌላ በኩል የማቅ አባላትን ፍላጎት ያስተናግዳሉ። የሀይማኖት ስራ እና ቅን ፍርድ አብሮ መራድ አልቻሉም። ለምን ቀድሞ የተቋቋሞ አጣር ኮሚቴ ገዳዩን አይመረምርም ። ችግሩ ከፓትርያርኩ ሳሆን ማቅ የሚሰራው ተንኮል ነው። አሁን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አርፈዋል በማን ልያሳቡ ነው? በቤተ ክህነት አከባብ ትልቅ የተደበቀ በሽታ አለ ማለት ነው። ኤረ ብዙ ገና እንሰማለን።

    ReplyDelete