Monday, September 3, 2012

ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ተቀበሩ

 Click here to read in PDF:meles funeral
“ሥልጣን መንታ ስለት ያለው ካራ ነው፡፡ ይህ ካራ ወይ ድህነትን ለማጥፋት አሊያም ህዝብን ለማረድ ይውላል፡፡”
መለስ ዜናዊ
(ዐውደ ምሕረት፤ ሰኞ  ነሐሴ 28 2004 ዓ.ም. /www.awdemihret.blogspot.com// www.awdemihret.wordpress.com) ኢትዮጵያን ለ21 ዓመታት የመሩዋት፣ ከፍተኛ የሆነ የማሳመን ብቃት ያላቸው ተብሎ የሚነገርላቸው የጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ቀብር ትናንት ነሐሴ 27 2004 ዓ.ም. ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የ19 ሀገር ፕሬዝዳንቶች፣ የ3 ሀገር ጠቅላይ ሚኒስቴሮች፣ በአጠቃላይ ወደ 671 የሆኑ የተለያዩ ልኡካን፣ ሌሎች ባስልጣናት፣ ቤተሰቦቻቸው እና በርካታ ህዝብ በተገኘበት በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ከቀኑ 9፡25 ላይ ተፈጸመ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ በፍጹም ጸጥታ ውስጥ የነበረች ሲሆን ህዝቡም የቀብር ስነ ስርዓቱን በቀጥታ ሲከታተል እንደነበር ለመታዘብ ችለናል፡፡
ግብዓተ መሬቱ ከመፈጸሙ ከደቂቃዎች በፊት በመላው ሀገሪቱ 21 ጊዜ መድፍ የተተኮሰ ሲሆን ከቀብሩ ሥነ ሥርዓት በኃላም በመላው ሀገሪቱ የ5 ደቂቃ የህሊና ጸሎት ተደርጎዋል፡፡በቅድስት ሥላሤ ቤተክርስቲያን በተከናወነው የጸሎት ስነስርዓት በአቃቤ መንበሩ በብጹዕ አቡነ ናትናኤል ተመርቷል፡፡


በመስቀል አደባባይ የነበረው ሥነ ሥርዓት የተጀመረው በብጹዕ አቡነ ናትናኤል በተመራ ጸሎት ሲሆን በአቶ ኩማ ደመቅሳ በተመራው የአሰኛኘት ሥነሥርዓት የመጀመሪያ ተናጋሪ የሆኑት ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ናቸው፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም በንግግራቸው በጠቅላይ ሚኒስቴሩ የተነደፉት ፖሊሲዎች እና እስትራቴጂዎች ይቀጥላሉ ብለው ተናግረዋል፡፡ ህዝቡንም በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ዕረፍት ያሳየውን ጥንካሬ እና ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ ያለውንም ፍቅር የገለጸበትን መንገድ “ቃልኪዳኑን ያደሰ ሕዝብ ነው” በማለት አመስግነዋል፡፡
ሁሉም መሪዎች በንግግራቸው ባለራዕይ ሲሉ የገለጹዋቸው መለስ በተለይ የሩዋንዳው መሪ ፓል ካጋሚ “ምን ያህል እንዳጎደሉን በግልጽ የሚታይ ነው”     “አዲስ ሀሳብ አፍላቂ፡፡ ከልብ የሚረዱን የሚደግፉን ሰው ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የዩጋንዳው ፕሬዚደንት ወንድሜ ሲሉ የገለጹዋቸው መለስን እጅግ በጣም አድርገው አመስግነዋቸዋል፡፡ በኤሌክትሪሲቲ በኢኮኖሚ እድገት በአካባቢ ሰላም ያስመዘገቡት ውጤትንም አድንቀዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት “ነሀሴ 12 ቀን ለመላው አፍሪካ እጅግ አዛኝ ቀን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡” መለስ ለሀገራቸው ያስገኙትን ውጤት በግልጽ የሚታይ መሆኑን አድንቀው ያመሰገኑት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮቭ ዙማ “በአፍሪካዊነቴ በመለስ ዜናዊ እጅግ በጣም እኮራለሁ” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን በመቀጠል “G8 እና G20 ጨምሮ የበለጸጉት ሀገሮች በሚያዘጋጁዋቸው ሁሉም ጉባኤዎች ይጋበዙ የነበሩት የኢትዮጵያ መሪ ስለሆኑ ሳይሆን የበለጸገ ሀሳብ አመንጪ ስለሆኑ ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ሚሊዮኖች  በአፍሪካ ደረጃ አዝነዋል ብለዋል፡፡ ታሪክ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን በልዩ ብቃታቸው በራዕያቸው እና ለኢትዮጵያ ባስመዘገቡት ውጤት ያደንቃቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በኔፓድ እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያደረጉትን አስተዋጽኦ አድንቀዋል፡፡       
“ናይጀሪያ ትልቅ ወዳጅዋን እና አፍሪካ ሁሉን አቀፍ መሪዋን አጥተዋል ብለዋል፡፡” ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አጅግ ለሚወዱዋቸው ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ እድገት እና ብልጽግናና ከተሟላ ሰላም ጋር እመኛለሁ” በማለት ንግግራቸውን አጠናቀዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሞት የ3ት ቀን ሀዘን ያወጀችው ደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚደንት ሳላቫኪርም “ያጣናው ትልቅ መሪ ነው፡፡ መለስን ያጣቸው ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አፍሪካም ነች፡፡ ለኛ ያለው የማያቋርጥ ድጋፍና በደቡብ ሱዳን እና በሱዳን መካለል ላለው አለመግባባት የነበራቸው አትኩሮቶችና ችግሩንም ለመፍታት ያደረጉትን መጠን የለሽ እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነበር” ብለዋል፡፡ “እኛ አሁንም ሀዘን ላይ ነን” ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ለበርካቶቻችን የመነሳሳት ተምሳሌት ነበሩም ብለዋል፡፡ ያጣነው ትልቅ ሰው ነው፡፡ ለአፍሪካ እድገት እና ሰላም የሰሩት ስራ ግን ሁሌም አብሮን ይኖራል ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በከፈቱትም ጎዳና እንጓዛለን ብለዋል፡፡
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦ ኢምቤኪም እኔ እና በጣም በርካቶች በአፍሪካ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ዕረፍት ምን ያህል ያሳዘነን መሆኑን ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ቀያሽ እና ከአዲሲቷ አፍሪካ ቀያሾች መካከል የሆኑት ታናሽ ወንድሜ መለስ የነበራቸው እውቀት እና ተነሳሽነት ከእሳቸው ጋር መስራትን እጅግ አስደሳች ደርገዋል ብለዋል፡፡ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ህዝብ ያበረከቱት አስተዋጽኦ መቸም ቢሆን የሚዘነጋ አይሆንም ብለዋል፡፡ እሳቸው በግብርና እና መሰረተ ልማት በሰላም እና በልዩ ልዩ መስኮች ያስመዘገቡት ውጤት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሰታት ዋና ጸሀፊ የባንኪ ሙን መልዕክተኛም “በተባበሩት መንግስታት ስም በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጊዜውን ያልጠበቀ ሞት በጣም አዝኛለሁ” ብለዋል፡፡ “ጉበዝ አደራዳሪ ባለጥልቅ ሀሳብ እና ትጉ አገልጋይ” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስቴሩን አመስግነዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት በጠቅላይ ሚኒስቴሩ አገልግሎት ተጠቃማ ነበር ብለዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር ሱዛን ራይስ እንባ እየተናነቃቸው  “አለም አፍሪካና ኢትዮጵያ እጅግ በጣም አሳዛኝ የሆነ እጦት ገጥሞን እዚህ ተሰብሰበናል፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ  እንዲህ ያለውን መሪ በዚህ ሁኔታ ማጣታችን እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ቀጥተኛ የማይደክሙ ራሳቸውን ለስራቸው የሰጡ በፍጹም ራስ ወዳድ ያልሆኑ ሰው ናቸው፡፡” ሲሉ ተሰምቷል፡፡ “አለም አቀፍ አስተሳሰብ ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ የማያቋርጡ ተማሪ ናቸው፡፡ የሚገርሙ ተደራዳሪ የማይዘነጉ መሪ ሀሳብ የማያልቅባቸው ሁለገብነትን የተጎናጸፈ በሳል መሪ” ሲሉ ገልጠዋቸዋል፡፡
“ያበሁለት ነገሮች ሁሌም እደነቃለሁ ሀሳብ ምክንታዊ በማድረግ ችሎታቸው እና በማይነቃነቅ አቋማቸው” በማለት ተናግረዋል፡፡ “የኢትዮጵያ ልጅ እና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አባት ነው ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡ የመለስ ራዕና ተጽዕኖ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ እና ለመላው አለም የተረፈ ነበር ብለዋል፡፡ አዲሲቷን ሱዳን ያዋለዱ እና በጥንቃቄም እንድታድግ ያደረጉ ሞግዚቷ ናቸው” ብለዋል፡፡
“መለስን ማጣታችን የማይካድ ቢሆንም የኢትዮጵያ የታላቅነት ጉዞ ግን የማይቋረጥ ነው” ብለዋል፡፡  “መለስ ልዩነት ያላቸው ባለ ልዩ ራዕይ እና የልብ ጓደኛዬ ነበሩ” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ተወካይም “ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሲሞቱ 57 ዓመታቸው ነበር ነገር ግን በ21 ዓመታት አመራራቸው ያደረጉት አስተዋጽኦ እና ያመጡት ውጤት እጅግ አስደናቂ ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ “ልዩነት ፈጣሪ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስቴሩን አመስግነዋል፡፡ የትኛውን ተደራዳሪ ማሳመን የሚችልም ብቃት ያላቸው ናቸው ሲሉም አመስግነዋል፡፡”
“ልዩ እይታውን አስደናቂ ራዕያቸውን እና ለሰላም ያላቸውን ጽኑ ፈቃድ ለዘላለም አጥተነዋል፡፡” ሲሉም ሀዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መለስን “አስተማሪዬ እጮኛዬ ጓደኛዬ የትግል አጋሬ ነው፡፡ ለኔ እና ለልጆቹ ሁሉን ነገር ሲሆን ለኛ የሚሆን ጊዜ ግን አልነበረው” በማለት እንባ እየተናነቃቸው ተናግረዋል፡፡ “የኢትዮጵያ ህዝብም ለመለስ ያለውን ፍቅር ገልጦዋል” ብለዋል፡፡ ህዝቡንም አመስግነዋል፡፡ “መለስ ዳኛው ህዝብ ነው” ይል ነበር ያሉት ወይዘሮ አዜብ ህዝብ ዳኝነቱን ሰጥቷል፡፡ ሲሉም አክለዋል፡፡
አቶ አዲሱ ለገሰ “ምስለ መለስ፤ የማንነቱ ገጽታ” የሚል የመለስን የሕይወት ታሪክ አንብበዋል፡፡ አቶ አዲሱ “አቶ መለስ በፍጹም ስለራሳቸው እንዲወራ የማይፈልጉ ሰው መሆናቸውን” እና “እኔ የምትለው ቃል በአንደበታቸው ቦታ የተነፈጋት ናት” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ያነበቡትም የህይወት ታሪክ በዕለቱ በታደለው መጽሔት ላይ መውጣቱን ተናግረዋል፡፡
አቶ አዲሱ ስለመለስ ሰብዕና እና ስለነበራቸው አመራር በርካታ ጉዳዩችን አንስተዋል “የህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት በ1971 ነው” ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ይህም በ23 ዓመታቸው መሆኑ ነው፡፡ በ29 ዓመታቸውም የድርጅቱ መሪ ሆነዋል፡፡ በ36 ዓመታቸው የኢትዮጵያ መሪ የሆኑ ሲሆን ከዛ በኃላ በሄዱበት መንገድ ባነሱት የራሳቸው የሆነ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ አስተሳሰቦች ባራዕይና ልዩ አስተሳሰብ ያለው ሰው የሚልን ሰው አሰጥቷቸዋል፡፡ በብዙው ኢትዮጵያዊ የማይታወቀው የስነ ጽኁፍ ችሎታቸው ሲሆን አቶ አዲሱም ይህንን ነገር አብራርተው ተናግረዋል፡፡ መለስ ሁለት የትግርኛ ልብ ወለድ መጽኸፍ የጻፉ መሆናቸውም ይታወቃል፡፡
አቶ አዲሱ ባነበቡት ጽሁፍ “ሥልጣን መንታ ስለት ያለው ካራ ነው፡፡ ይህ ካራ ወይ ድህነትን ለማጥፋት አሊያም ህዝብን ለማረድ ይውላል፡፡” ሲሉ መለስ ይናገሩ ነበር ብለዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ስልጣን የድህነትን ለማጥፋት ውሏል ያሉ በርካቶች ከልብ አልቅሰዋል፡፡ ሌላ ያሰቡ ደግሞ ደስታቸውን እየገለጹ የሽግግር መንግስት አቋቁመዋል፡፡ ከማንም ጋር ስልጣናቸውን ድህነትን ለማጥፋት ወይም ለሌላ ነገር ተጠቅመዋል ብለን ሙግት አንጠቅምም፡፡ አጀንዳችንም እሱ አይደለም፡፡ የሀገራችን ሰላም መሆን ግን ግድ ይለናል፡፡ ሰላማችንን ለመጋፋት የሚሞክሩ ሰዎችን ስናይ የችግሩ ቀጥተኛ ተጎጂዎች ስለምንሆን እንከፋለን፡፡
ባለፉት 13 ቀናት የኢትዮጵያ ህዝብ ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ዕረፍት በኃላ ያሳየው መረጋጋት አስደናቂ ነው፡፡ ህዝብ ለሰላሙ ከቆመ ምንም የሚደፍረው ሀይል እንደማይኖርም ያሳያል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ዕረፍት ያን ያህል ያዘነው ሙሉ በሙሉ ኢህአዴግ ስለሆነ አይደለም ነገር ግን ምንም አይነት ተራ አስተሳሰብ ያልዋጠው አስተዋይ ህዝብ ስለሆነ ነው፡፡ እንዲህ ባለው ክፍተት እጅ ለእጅ ተያይዞ መቆም ለሀገር ሰላም እና አንድነት የሚከፈል ትክክለኛ ዋጋ ነው፡፡
አንዳንድ ዲያስፖራ ወገኖቻችን የሚያገኙት ትርፍ ምን እንደሆነ ባይታወቅም ሲመኙልን የነበረው ብጥብጥም ማሳየት ስላልቻለ የሚደነቅ ነው፡፡ ከህዝብ ርቆ ለህዝብ መታገል ከባድ መሆኑን ያልተገነዘቡት “ፖለቲከኞች” ያሰቡት አልሆነም፡፡ ኑሯችንን የምናውቅ እኛ በሚፈጠሩ ችግሮች የሚገጥመንን ጉዳት የምናውቅ ወገኖቻችሁ ነንና እባካችሁ ስሙን፤ የሰሞኑን ሀሳባችሁን የተቃወምነው ኢህአዴግ ስለሆንን አይደለም ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ስለሆንን ነው፡፡
በሌሊት ወጥቶ የጠቅላይ ሚኒስቴሩን አስከሬን የተቀበለው እና ቤተ መንግስት ሄዶ ሀዘኑን የገለጸው ህብረተሰብ የኢህአዴግ ደጋፊ ስለሆነ አይደለም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ስለሆነ እና የኢትዮጵያዊነት ባህሉም ስለሚያስገድደው ነው፡፡ ከሚያዝኑ ጋር አብሮ እንዲያዝን የሚያምነው አምላኩ እና የወንጌሉም ቃል ያስገድደዋል እና ነው፡፡ አንዳንዴ ኢትዮጵያዊ ለመሆን መሞከር እናንተም ነገ ለሚኖራችሁ ተቀባይነት ይጠቅማችኋል፡፡ እንደሱማሌ አይነት ሀገር ቢገጥማችሁ ያቁዋቁዋማችሁት የሽግግር መንግስት ይዛችሁ ለመምጣት ፈቃደኛ ትሆናላችሁ? አይመስለንም፡፡ ያቋቋማችሁት የሽግግር መንግስት ሥልጣን ላይ ሊወጣ የሚችለው ለሀገሪቱ ሰላምን መመኘት ሲቻል ነው፡፡ አሁንም ስልጣን የምትመኙት ሀገሪቱ ሰላም ስለሆነች ነው፡፡ ስለዚህ ለሰላምዋ ስሩ፡፡
ርቃችሁ ቆሞችሁ የሰላም አየር እየተነፈሳችሁ ሰላም ማጣትን አትስበኩን ኢህአዴግን መጥላት ሌላ ለኢትዮጵያ ማሰብ ሌላ ነው፡፡ ሰርዶው በቅሎ ሌላው ከሚበላው ድብልቅልቁ ይውጣ በሚል “ፍልስፍና” መመራት ተገቢ አይመስለንም፡፡ እዚህ ሆነው ከነ ችግሮቹ ለሚታገሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የበለጠ ከበሬታ አለን፡፡ ችግሮች ቢገጥማቸውም እዚሁ ናቸው፡፡ ምንም ቢሆን ብጥብጥን አይመኙልንም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ልጆች ላለው ሰው ሞት ደስታቸውን አልገለጹም ጊዜው የኛ ነው ብለው የሽግግር መንግስት ለማቋቋም አልሮጡም፡፡ ቅድሚያ ለሰላም በመስጠት ሀገሪቱ እንድትረጋጋ ተገቢውን እንቅስቃሴ ግን አድርገዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ የምትመሩን እኛን ስለሆነ በሰላማችን አትጣሉን፡፡ ቀብሩ ብጥብጥ እንዲነሳበት ናፍቆም በዌብሳይቶቻችሁ እና በብሎጎቻችሁ መጻፍ ምን ማለት እና ከብጥብጥብ የምታገኙት ትርፍ ምን እንደሆነ ከቶውንም ሊገባን አይችልም፡፡ መንግስትን መቃመም ግን መብታችሁ ነው፡፡ ስለሱ አይመለከተንም፡፡ ሰላማችንን ለመጋፋት ስትሞክሩ ግን የመጀመሪያ ተጎጂዎች ስለምንሆን ደስተኞች አንሆንም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ  ዛሬ ተቀብረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን አሁንም አለ፡፡ ስለዚህ ለዚህ ህዝብ ሰላም እየሰራችሁ ያለውን መንግስት ግን መቃወም ትችላላችሁ፡፡ ፖለቲካችሁ አያገባንም፡፡ ሰላማችንን ግን ከብዙ ጸሎት ጋር ለሰላሙ ንጉስ ለእግዚአብሔር ክብር የምናቀርበው መስዋዕት እና የምስጋናም ርዕሳችንን መሆኑን እንገልጻለን፡፡
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ህዝቡ ላሰየው መረጋጋት እና ማስተዋል ያለንን አድናቆት እንገልጻለን!!

No comments:

Post a Comment