Thursday, August 30, 2012

ታሪክ የማይረሳው ብቸኛው ፓትርያርክ


Cllick Here to read in PDF: Abune pawlos history
                                                                    በመምህር መላኩ
አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፤ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ፤ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንትና የዓለም ለሰላም አምባሳደር ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለዩ!
በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን የልዩ ልዩ እምነት ተከታይ መሪዎችና እንዲሁም የሮማ ቤተክርስቲያን መሪ የሆኑትን ፖፕ ፔነዲክ 16ኝን ጨምሮ የዓለም የሃይማኖት መሪዎችና ዓለም አቀፉ ሕብረተ ሰብ የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን በአካልና በልዩ ልዩ የዜና ማሰራጫዎች በመግለጥ ላይ ይገኛል ። 

ቅዱስነታቸው ከሐምሌ 5 ቀን 1984 /ም ጀምሮ ለ20 ዓመታት ቤተክርስቲያንን በርዕሰ አበውነት ሲመሩ ከቆዩ በኋላ በ76 ዓመት ዕድሜያቸው ነሐሴ 10 ቀን 2004 /ም ሐሙስ ከንጋቱ 11 ስዓት ላይ በደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል የሕክምና ርዳታ ሲደረግላቸው ከቆዩ በኋላ የዘመናት ባለቤት እግዚአብሔር የመደበላቸውን ጊዜ በታማኝነትና ይህ ቀረ በማይባል ስኬት አጠናቀው ከዚህ ዓለም በሞተ-ሥጋ ተለይተዋል ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በ1928 ዓ/ም በትግራይ ክፍለሃገር በአድዋ አውራጃ ተወለዱ ፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአቅራቢያቸው በሚገኘው የአባ ገሪማ ገዳም መንፈሳዊ ትምህርታቸውን በመጀመር ። በዚሁ ገዳም ከዲቁና እስከ ምንኩስና ማዕረግ የደረሱ ሲሆን በመቀጠል የቤተክርስቲያንን ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ትምህርቶች አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ በመግባት በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጨርሰዋል ።
በነበራቸው ትጋትና ልዩ የመማር ፍላጎት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መልካም ፈቃድ ወደ አሜሪካ ለከፍተኛ ትምህርት ተልከው በሴንት ቭላዲሚር ኦርቶዶክስ መንፈሳዊ ኮሌጅና በሌሎችም የትምህርት ተቋማት በመማር ተደራራቢ ዲግሪዎችን አግኝተዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በጵጵስና ጊዜያቸው በደርግ አገዛዝ ለ7 ዓመታት በእሥር ቤት ቆይተዋል ከዚያም ከእሥር ቤት ከተፈቱ በኋላ ወደ አሜሪካ በመመለስ የጀመሩትን ትምህርት በመቀጠል በታላቁ በፕሪስቶን ዩኒቭርሲቲ ፒኤችዲያቸውን ሠርተዋል ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከህፃንነት ዕድሜ ጀምረው በገዳማዊ ሥርዓትና ሕግ ያደጉ፤ በክርስቶስ ወንጌል ምክንያት የታሠሩ በአጠቃላይ እንደ ወርቅ ተፈትኖ ያለፈ ሕይወት የነበራቸውና ፤ በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ዕውቀት በጣምራ ችሎታዎች የተካኑ ዓለም አቀፍ ሰው ነበሩ።
ቅዱስነታቸው ረቡዕ ነሐሴ 9 ቀን በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሱባዔውን ጸሎት ሲመሩ ከቆዩ በኋላ በተሰማቸው ህመም ምክንያት ወደ ሆስፒታል እንደ ተወሰዱና ያለምንም ስቃይና ጻዕረ ሞት ዕንዳረፉ ይነገራል ። ይህም የቅዱስነታቸውን ጻድቅነትና ከአምላካቸው ጋር ያላቸውን ቀረቤታ ይመሰክራል ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ዕውቀት ጣምራ ችሎታ የነበራቸው ለመንበረ ማርቆስ የተገቡ ዓለም አቀፋዊ የጥበብ ሰው ነበሩ ።
የውጭ ምሁራን ሳይቀሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፤ በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት ታላላቅ ምሁራን ውስጥ አንዱ የሆኑና በኢትዮጵያ አርእስተ አበው (ፓትርያርኮች) ታሪክ ውስጥ ፤ ወደር ያልተገኘላቸው ብቸኛው ፓትርያርክ ናቸውበማለት ይናገሩላቸዋል ። ስም ወደሥራ ይመራል እንዲሉ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የመናገር ተሰጦ የነበራቸው ፤ በወንጌል ስብከታቸው የብዙሃኑን ልቡና የዳሰሱና አጥንትን የሚያለመልም አንደበት የነበራቸው የወንጌል ገበሬ ነበሩ ።
ቅዱስነታቸው በወንጌል ያላፈሩና በዚህ የፓትርያርክነት ዘመናቸው ያስመዘገቡት አስደናቂ ታሪክ ሁሉ በተጋድሎና በፍጹም የእምነት ጽናታቸው መሥዋዕትን ከፍለው የሠሩት እንጂ የአልጋ ባልጋ የሆነ ውጤት አልነበረም ።
በዚህም ኢትዮጵያውያን ምሁራን ሰማዕት ዘእንበለ ደምበማለት ደማቸው ሲፈስ አይታይ እንጅ ፈደዩኒ እኪተ ሕየንተ ሰናይት ሆኖባቸው ለሠሩት መልካም ሥራ በመመስገን ፈንታ ይወረወርባቸው የነበረውን የቃላት ሰይፍ ለመግለጽ ይናገራሉ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና ለኢትዮጵያውያን ፤ ከዚያም አልፎ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ በሰላምና በመተሳሰብ በእግዚአብሔር ዓለም በፍቅርና በአንድነት እንዲኖር በማስተማርና እንዲቀራረብ በማድረጉ ሥራ ታሪክ የማይዘነጋው ውጤትን አስገኝተዋል ።
በአገር ውስጥና በአፍሪካም ፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ ፤ እንዲሁም በሱማሌ የእርስ በርስ ጦርነትን ለማስቆም ፤ በጦርነቱ የተጎዱትንም በመርዳት ፤ ሌት ከቀን በትጋት ሠርተዋል ። ቅዱስነታቸው ከአፍሪካውያን የበለጠ አፍሪካን የሚወድ ማንም የለም ስለዚህ በአፍሪካ ላለው የሰላም ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ ማግኘቱ ወሳኝ ነውበሚሉት ስሜት ቀስቃሽና በጥበብ የተቀመሙ አነጋገራቸው በብዙሃኑ የውጪው ኅብረተሰብ ጭምር ይታወቃሉ ::
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የልዩ ልዩ ሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ለሃገር ሰላምና ዕድገት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ መልኩ በሐገራዊ ፍቅር በመተሳሰር በሰላምና በፍቅር በጋራ እንዲሠሩና አገራቸውን እንዲገነቡ ከፍተኛ ጥረትን አድርገዋል ::
የቅዱስነታቸውን ታላቅ የሥራ ፤ የሰላምና የፍቅር ሰውነት በአገር ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥትን ጨምሮ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ድርጅቶች፤ እንዲሁም የልዩ ልዩ እምነት ተከታይ መሪዎች በኃዘን መግለጫቸው ደጋግመው በመዘገብ የቅዱስነታቸውን ታላቅ ሰብእናና ማንነታቸውን መስክረውላቸዋል ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለዓለም ሰላምና ለሰብአዊ ርኅራሔ ሥራዎች ባደረጓቸው ጉልህ ዓለም አቀፍ ውጤቶች በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኮምሽን የናንሰን (Nansen) ሜዳልን ተሸልመዋል ።
አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፤ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፡ ዓለም የፍቅር ዓይኑን ያሳረፈባቸው፤ በታላቅ ሰውነታቸው ያመነባቸው የሰላምና የመቀራረብ መፍትሄ ነበሩ ።
ለዚህም ምስክሩ
Ø የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት
Ø የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንት
Ø የዓለም የሰላም አምባሳደነትን ሥልጣን በማግኘት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊና የመጀመሪያው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ መሆናቸው ነው
ሌላው ቅዱስነታቸውን ልዩ የሚያደርጋቸው ለዚህ ታላቅ መንፈሳዊ ሥልጣን ከተለዩባት ዕለት ጀምረው የእረፍት ጊዜ ሳይኖራቸው በየሆስፒታሉ በየግል ቤቱ ሳይቀር እየሄዱ የታመሙትን በመጠየቅ፤ ለሞቱት ከካህናት ጋር እኩል ቆመው ጸሎተ ፍትሃትን በማድረስ የኅብረተሰቡን የዕለት ከእለት ሕይወት የሚጋሩ ትሁትና ሰው አክባሪ አባት ነበሩ፤
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ  በተጠሩበት ከፍተኛ የፓትርያርክነት ሥልጣን በሥራቸው የሚተማመኑ የመወሰንና በሚያደርጉት ሁሉ በልበ ሙሉነት ሃላፊነትን ለመውሰድ ወደ ኋላ የማያፈገፍጉ ፍጹም የአመራርና የእውነት ሰው ነበሩ ለዚህም ችሎታቸው አገር አቀፉና ዓለም አቀፉ ሕያው ሥራቸው ቋሚ ምስክር ነው ።
ወደ ፊት የሚተካውን ባናውቅም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ወደ መንበረ ማርቆስ ከወጡባት ቅጽበት ጀምሮ ያለ ዕረፍት በመሥራት ጽሁፍ የማይወስነው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ከቤተ ክርስቲያኒቷም አልፎ ለመላው ኢትዮጵያዊ ኩራት የሆነ ሕያው ሥራን በማከናወን እስካሁኗ ቅጽበት ድረስ ወደር ያልተገኘላቸው ብቸኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ነበሩ
አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እስከ አሁን በኢትዮጵያ መንበር ከተቀመጡት ወይም ከነበሩት አርእስተ አበው መካከል ፍጹም አዲስና ጉልህ የሆነ የታሪክ ምዕራፍን ያስመዘገቡ ብቸኛው ፓትርያርክ ናቸው ፡፡
በዘመናቸው ቤተክርስቲያን የተረሣውን ታሪኳን አድሳ ፤ የተወረሰውን ንብረቷን አስመልሳ ፤ እንደገና በሕያውነት የተንቀሳቀሰችበት ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታሪክና የሉአላዊነት ብኩርናዋን ያረጋገጠችበት ፤ ድምጿ በዓለም ጆሮ ተሰሚነትን ፤ ሥራዋ ትኩረትን ያገኘበት ጊዜ ነበረ ፡፡
ቤተክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ ዓለም አቀፋዊ ቅርጽን ይዛለች ፤ በየአብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ መክነው የነበሩ ጥቅም አልባ ቦታዎች ዛሬ የከፍተኛ ትምህርት ፤ የህክምናና የሌሎችም ለኅብረተሰቡ ጥቅምና ለቤተ ክርስቲያኒቱ የገቢ ምንጭ የሆኑ ወደፊትም የሚሆኑ ተቋማት ማዕከላት ሆነዋል ፡፡
ሌላው አምስተኛውን ፓትርያርክ ልዩ የሚያደርጋቸው ሰዎች በፖለቲካ ፤ በዘር ፤ በጎሣና በቋንቋ ተከፋፍለው ዘርን እንጂ ሥራን ፤ ሥጋዊ ወገናዊነትን እንጂ ክርስቶሳዊነትን ማስተዋል ተስኗቸው ሕገ-እግዚአብሔርን ሳይሆን ራሳቸው ለሥጋዊ ዝንባሌያቸው የሚመች ሥርዓትንና ሕግን እያወጡ በመከተል ባመጹበት ጊዜ በዙሪያቸው የከበባቸውን ተቃውሞና መሰናክል ሁሉ በመታገሥ ከቅዱስ ተልዕኳቸው ሳይዘናጉ በስኬታማነት በመሥራት ያስመዘገቡት ከአገር ውጪም አልፎ ዓለም አቀፋዊ የሆነው ተጨባጭና አኩሪ ታሪካቸው ነው፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እስከ አሁን ድረስ በአገር ውስጥ ካከናወኗቸው አበይት የሥራ ውጤቶች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
Ø ከ50 በላይ የቤተክርስቲያኒቱ ተተኪ የሆኑ አባቶች ኤጲስ ቆጶሳትን ሹመዋል፤
Ø ለብዙ ዓመታት ተወርሰው የቆዩትን የቤተክርስቲያን ሀብታት አስመልሰው የቤተ ክርስቲያንን መብት በማስከበር ቤተክርስቲያናቸን በሐብቷ እንድትጠቀም አድርገዋል ፤ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሆነውንና በደርግ ዘመን ተወርሶ የነበረውን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን አስመልሰው አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገዋል ፤ አዳዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትንም በየክፍላተ ሀገራት አቋቁመዋል።
Ø ቀደም ባሉት ዘመናት የቤተክርስቲያኒቱ የገቢ ምንጭ የነበሩና በደርግ ዘመን የተወረሱትን ታላላቅ ሕንጻዎች አስመልሰዋል።
Ø በደርግ ዘመን ተዘግተው የነበሩትን የአብያተ ክርስቲያናት ዋና በሮች እንዲከፈቱ በማድረግ ምእመናን እንደ ልብ በሚቀርባቸው የመግቢያ በር በነጻነት ገብተው ጸሎታቸውን ማድረስ እንዲችሉ አድርገዋል።
Ø ቤተ ክርስቲያን የልዩ ልዩ ከፍተኛ መንፈሳዊና ሕዝባዊ ትምህርት ቤቶች ፤ የሕክምና ፤ የተግባረ ዕድና የሌሎችም የመሳሰሉት ከፍተኛ ተቋማት ባለቤት በመሆን ራሷን እንድትችል አድርገዋል ፤


በመሆኑም ዛሬ አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የ1ኛና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ የኮሌጆች ፤ የክሊኒኮች፤ እንዲሁም ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉ የታላላቅ ሕንጻዎች ባለንብረት ሆነዋል፡፡
ይህም ለቤተክርስቲያን የተሟላ ሕይወት የጀርባ አጥንት የሆነ ተደናቂ ሥራ በመላዋ የሐገሪቱ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመተግበር ላይ ይገኛል ፡፡
· የቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህናት ካላቸው ዕውቀት በተጨማሪ በቤተክርስቲያን አስተዳደራዊና ማኅበራዊ ችሎታዎች የተካኑና ለቤተክርስቲያን የውስጥም ሆነ የውጭ አገልግሎት ብቁዎች እንዲሆኑ ለማድረግ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎች እየተሰጣቸው በማነኛውም ቦታ ወይም የሥራ መስክ በልበ ሙሉነት እየሠሩ ይገኛሉ
በታሪክ ቅርስነቱ ለሀገርና ለቤተክርስቲያን አኩሪና መመኪያ የሆነው የአክሱምን ፤ የቅዱስ ላሊበላንና ፤ የፋሲልን ታሪካዊ ቅርሶች በማካተት የኢትዮጵያን ጥበብ ከታሪክ ጋር አስተባብሮ የያዘው ሕንፃ ወመዘክር መንበረ ፓትርያርክ በመሠራቱ፤ ለከተማዋ ማዕረግንና ውበትን፤ ለቤተክርስቲያኗ ክብርንና በራስ መተማመንን ሰጥቷታል ፡፡
በውጭ መንግሥታት ተዘርፈው የነበሩ የታሪክ ቅርሶችና ቅዱሳት መጻህፍት እንዲመለሱ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ስኬታማ በመሆን የሐገሪቱንና የቤተክርስቲያኒቱን ሐብታት አስመልሰዋል፤
· የተበታተነውና የአያያዝ ቅጥ ያጣው በጥራቱና በአስደናቂነቱ ወደር የሌለው የቤተክርስቲያንና የአገሪቱ ጭምር አኩሪ የሆነ ታሪክና የታሪክ ቅርስ በዘመናዊ አያያዝ ዓለም አቀፋዊ በሆነ ደረጃ ተሰብስቦ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጪ አገር ጎብኝዎች ዝግጁ ሆኖ እጹብ ድንቅ በሆነ ቤተ መዘክር ቀርቧል ፡፡
· የቤተክርስቲያኒቱ የእምነትና የሀገሪቱም የታሪክ ምንጭ የሆኑ ልዩ ልዩ መጻሕፍት ከግእዝ ቋንቋ ወደ አማርኛ የተተረጎሙ ሲሆን ሌሎች አዳዲስ መጻህፍትም እንዲዘጋጁ የተመቻቸ ዕድልን በመፍጠራቸው 81ዱን መጽሐፍ ቅዱስ ጨምሮ አያሌ መጻህፍት ታትመው ወጥተዋል ፡፡
· ቤተክርስቲያናችን ከሊቃውንቷ መካከል መንፈሳውያን መሪዎችን መምረጥ አትችልም ፤ ተብላ ለዘመናት ቋንቋዋን በማይናገሩ ፤ ባህሏን በማያውቁና በማያከብሩ ፤ ችግሯን በቀጥታ ከአንደበቷ መረዳትም ሆነ ማስረዳት በማይችሉ ፤ ግብጻውያን አባቶች በአስተርጓሚ ስትመራ ከቆየች በኋላ ፤ ሁሉን ማድረግ የማይሳነው አምላክ ፈቅዶላት በታማኝ ነገሥታቷና በምሁራን ልጆቿ የረጅም ጊዜ ጥረት ከሊቃውንት ልጆቿ ውስጥ መንፈሳውያን መሪዎቿን ሰይማ ራሷን በራሷ መምራትና መመራት ከጀመረች ቢያንስ 53 ዓመታትን አስቆጥራለች ፤
አሁን ደግሞ በአምስተኛው ፓትርያርክ ቤተክርስቲያናችን ራሷን ከመምራትም አልፋ የዓለም አብያተክርስቲያናት መሪ (ፕሬዚዳንት) ሆናለች ፡፡ ይህም የሚያሳየው የቤተክርስቲያናችን ዓለም አቀፋዊ ልዕልና በምሁራን አባቶቻችን ይልቁንም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አማካኝነት ምን ያህል እንደመጠቀና የዓለምን ትኩረት እንደሳበው ነው ፡፡
አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፤ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፤ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንትና የዓለም ለሰላም አምባሳደር ፤ ለቤተክርስቲያኒቱ ያበረከቱት ተጨባጭ የሆነው ይህ ሕያው ሥራ ከትውልድ ወደ ትውልድ በሕያውነቱ ይተላለፋል፡
ዋጋን የማያስቀር የእውነት አምላክ እግዚአብሔር የቅዱሱን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አባት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ነፍስ በወዳጆቹ በአብርሃም በይስሃቅና በያዕቆብ ቦታ ያኑርልን እያልኩ ለጊዜው ጽሁፌን እቋጫለሁ ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አዘጋጅ መምህር መላኩ

7 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማያት ያዋርስልን።ታላቅና ውብ ታርክ ለቤተ ክርስቲያናችን በእውነት ትተውልን አልፈዋል። እንኮራባቸዋለን። ዛሬ ሁክት እንደዚህ ለምፈጥሩት ጳጳሳት በጥሩ ደመወዝና እጅግ መልካም የሆነ መኖርያና መጓጓዣ እንድደረግላቸው ያደረጉ ታላቅ መንፈሳዊ አባት ነበሩ። የብዙዎቹ ካህናት ጥጋብ ወደፊት እንዴት እደሆነ በእውነት የሚንመለከተው ነው። ለግዜውም ግዜ አለው ይባላል።ሌላው መንፈሳዊ ኮሌጅን በከፍተኛ የትምህርት ተቀቋም ማሳደጋቸው በራሱ የአንድ ሀይማኖት የጀርባ አጥንት ነው። ብቃት ያላቸውን ሰባኪያን የሌላት ቤተ ክርስቲን ነበረች። መንፈስ ቅዱስ መውረድ ያስፈለገበት ምክንያት አንዱ ነገር ሐዋርያቱ ወንጌል እንድሰብኩ ነበር።በሐማይማኖታችን ዛሬ እጅግ ብዙ የወንጌል መምህራን አፍርታና በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን አንድሰበክ ተደርጓል። ይህን የቤተ ክርስቲያናችን እድገት የማይወዱ ክፉ መንፈስ ያደረባችው አሉ። ታርክ እረሱን አይቀብርም ህያው ሆኖ ይኖራልና እንጅ። ቅድስት ቤተ ክርስቲያነችን የዐለም ቤተ ክርስቲያን መሪ መሆኗ በራሱ ለእኛ ኦርቶዶክሳዊያን እጅግ ታላቅ ኩራት ነው። ለምን ሌሎች ይህን የተዋህዶ ማደግ ጠሉ? መልሱን እራሳችሁ መልሱት የማናየው አምላክ ያየናልና

    ReplyDelete
  2. kale hiwotn yasemalen Memhir Melaku, betam des yemilna ewunt new Egziabhir Batechrstiyanachenen yitebk Amen!!!

    ReplyDelete
  3. ICT le bete kirstian yastewaweku ye mejemeriyawil ye betekirtian mereja mereb yezeregu mehonachewinim anrsa

    ReplyDelete
  4. Behulum zeref egziabher yeredachew Patriarch!!! Development, Peace, Conflict Resolution, ICT, ... Wedewnetegnaw Erefit wesedachew!! Abune Markos endalut Akatlenachew neber - nisha engiba

    ReplyDelete
  5. Memhir Melaku, this is exactly in my mind all the time. Every thing you write in this article is absolutly the truth. Next time when you write please, bring it aut his enemys are jelose at him, because of the true father of Abune Pawlose. Any way Melaku, God Blesse you many many years.
    keep up the good work for ever and take care of your self with God.

    your Sister in Christ.

    ReplyDelete
  6. bettam des yemil akerareb new yekidus abatachinin nefs bekidusan mender kesemay yasarflin.

    ReplyDelete
  7. ke-Kidus Abatachin segana bereket EgziAbehere yakafilen. We miss him so much.

    ReplyDelete