Saturday, March 10, 2012

በሀዋሳው ህገ ወጥ ጉባኤ የዳንኤል፣ የዘበነና የአባ ገብርኤል ቋንቋ መደበላለቁ ተሰማ


      ከየካቲት 23 – 25 ዓ.ም. አባ ገብርኤል የሲኖዶሱን ህግና የስብከተ ወንጌል መምሪያን መመሪያ በማንአለብኝነት በመጣስ ባካሄዱት ጉባኤ ላይ በአገልጋይ ተብዬዎቹ መካከል አለመግባባት እንደ ነበረ ተሰማ፡፡ ቀድሞም ቢሆን ፍቅራቸው የሄሮድስና  የጲላጦስ አይነት ፍቅር መሆኑ ቢታወቅም፣ እነመጋቤ ሀዲስ በጋሻውን ከህዝብ ልብ ለማስወጣት በከፈቱት ዘመቻ ምክንያት አንድነት ያላቸው መስለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በጉባኤው ላይ ዘበነ ህዝቡን ‹‹እልል በሉ አጨብጭቡ›› በማለት እልል የማያሰኝና የማያስጨበጭብ ንግግሩን ምእመናን ተሰምቷቸውና ልባቸው ተነክቶ ሳይሆን በእርሱ ቅስቀሳ እልል ማሰኘቱና ማስጨብጨቡ፣ እልልታና ጭብጨባ በአቢይ ጾም ክልክል ነው ከሚለው የማህበረ ቅዱሳን ቀኖና ጋር አልተስማማም፡፡ ስለዚህ ዳንኤል ክብረት ‹‹በአቢይ ጾም እልልታና ጭብጨባን ቀኖና ቤተክርስቲያን አይፈቅድም›› ሲል ይቃወማል፡፡ አባ ገብርኤል ግን ‹‹ሲኖዶስ ማለት እኛ አይደለንም ወይ? አጨብጭቡ! እልል በሉ!›› በማለት ለዘበነ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡

        በቅድሚያ እልልታና ጭብጨባ በቅስቀሳ መደረግ ነበረበት ወይ? በፍጹም!!! እንኳን በመንፈሳዊ ጉባኤ ይቅርና በማንኛውም ስብሰባ ላይ ሰው እልል ሊልና ሊያጨበጭብ የሚችለው ባየውና በሰማው ነገር ስሜቱ ሲነካና ውስጡ በሀሴት ሲሞላ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን እንደ ዘበነ ያሉት አንዳንዶች ንግግራቸው የሰውን ስሜት ሳይነካ ሲቀር በግድ ‹‹ሞራል ስጡ እንጂ …. አጨብጭቡ …. ›› ወዘተ ማለታቸው የተለመደ ነው፡፡ ሊሆን የሚገባው ግን በእግዚአብሔር መንፈስ ተሞልቶና በተመስጦ ቃለ እግዚአብሔር መናገር፣ ሕዝቡም በዚያው ድባብ ውስጥ ሲገኝ ሳይቀሰቀስና የአጅቡኝ ጥያቄ ሳይቀርብለት ልቡ ሲነካና ስሜቱ ሲያስገድደው በጭብጨባም ሆነ በእልልታ የተሰማውን (አሜንታውን) መግለጽ ነበር፡፡ እንደ ማህበረ ቅዱሳን ቀኖና ግን ይህን የሰው ስሜት ለማፈን መሞከርና የተሰማህን አትግለጽ አፍነህ ያዘው ማለት ከሰብአዊነት የወጣ ብቻም ሳይሆን በህገ ቤተክርስቲያንም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው፡፡

     ለመሆኑ በአቢይ ጾም እልልታና ጭብጨባ ተልክሏል ወይ? ከዚህ ቀደም በወሊሶው የነመጋቤ ሀዲስ በጋሻው አገልግሎት የቀናው ማህበረ ቅዱሳን የሀገረ ስብከቱን ሊቀጳጳስ ብጹእ አቡነ ሳዊሮስን ጨምሮ በአቢይ ጾም ከበሮ አስመትተዋል፤ ቀኖና ቤተክርስቲያንን አፍርሰዋልና አገር ይያዝልኝ ሲል መክሰሱ ይታወሳል፡፡ በነህምያ መጽሀፍ ተጽፎ እንደምናነብው ከአሞንና ከሞአብ ሴቶች እንደተወለዱትና አይሁድ እየተባሉ ግን በኣዛጦን ቋንቋ ይናገሩ እንደነበሩት አይሁድ፣ ኦርቶዶክስ ነኝ እያለ የኦርቶዶክስን ቀኖና ጨርሶ የማያውቀው አዛጦናዊው ማህበረ ቅዱሳን በማያውቀው ገብቶ በሌለው መብት፣ ዕውቀትና ሥልጣን ከሜዳ ተነስቶ አንድን ሊቀጳጳስ ቀኖና ጣሱ ማለቱ እጅግ አሳፋሪ ነው (መጽሀፈ ነህ. 13፡23-24)፡፡

     አቢይ ጾም ምእመናን በንስሀ ወደፈጣሪያቸው የሚማለሉበት የሀዘን ጊዜ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፈንጠዝያና ጭፈራ የተከለከለ ነው፡፡ በመሰረቱ ይህ በአቢይ ጾም ብቻ ሳይሆን ሁሌም ሊደረግ የሚገባው ነው፡፡ በጾሙ ወቅት ግን ይበልጥ እንዲህ ሊደረግ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ በጾሙ በቋሚነት ከበሮ አይመታም፤ ማህሌት አይቆምም፡፡ በጾሙ ውስጥ በሚውሉ አንዳንድ የንግስ በዓላት ላይ ግን ማህሌት ይቆማል፤ ከበሮ ይመታል፤ ይጨበጨባል እልል ይባላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየዕለቱ ጾመ ድጓ ሲቆም በበዓላት ቀን ዝማሜው በጭብጨባ የሚታጀብበት ሥርአት አለ፡፡ ይህን ያላወቀው አዛጦናዊው ማህበረ ቅዱሳን ግን በአቢይ ጾም ከበሮ አይመታም የሚለውን ብቻ ይዞና የሚመታባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን ባለማስተዋል ቀኖና ፈረሰ፣ እነ አቡነ … ተሀድሶ ሆኑ ሲል የሰው ስም ያጠፋል፤ ቋንቋችንንም ደበላልቋል፡፡ ዳንኤልም ዘበነ በግድ እልል ሲያሰኝና ሲያስጨበጭብ የት ነበርክ እንዳይባል ‹‹ቀኖና ቤተክርስቲያን አይፈቅድም›› ሲል አዛጦናዊነቱን አስመስክሯል፡፡ ጉባኤውንም አዛጦን አድርጎታል፡፡

    ለበዓላት የተፈቀደውን ከበሮና ጭብጨባ እነመጋቤ ሀዲስ በጋሻው በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ መጠቀማቸውና ሊቀጳጳሱ ባሉበት ጉባኤው በዚህ መልክ መካሄዱን አዛጦናዊው ማህበረ ቅዱሳን ለምን ተቃወመ? አሁንስ ዘበነና አባ ገብርኤል በመስማማት ዳንኤልን መቃወማቸውንና ህዝቡን በግድ ማስጨብጨባቸውንና እልል ማሰኘታቸውን በቀኖና ጥሰት ይፈርጀው ይሆን? ወይስ ‹‹አሁን ጊዜው አይደለም፤ ጠላት ደስ አይበለው›› በሚል ያልፈው ይሆን? ይህ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡

     አባ ገብርኤል ‹‹ሲኖዶስ እኛ ነን›› ከማለታቸው በቀር በእልልታና በጭብጨባ ጉዳይ አዛጦናዊው ዳንኤልን በመቃወማቸው፣ እልልታና ጭብጨባን በመፍቀዳቸው፣ በዚህ አቋም ከማህበረ ቅዱሳን የተለዩ በመሆናቸው መልካም አድርገዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም በርካታ ጉዳዮች ማህበረ ቅዱሳን በማያገባው ገብቶ ባላዋቂነት ከእኔ በቀር ሌላው ተሳስቷል የሚለውን የተሳሳተ አቋሙን እንዲያስተካክል ቢነግሩት ደግሞ ይበልጥ መልካም ነው፡፡          






4 comments:

  1. ለአባ ገብርኤል
     ከድቁና እስከ ጵጵስና በክህደት ጎዳና
    ለዘበነ
     አቋምሽን ከድሮ ጀምሮ እናዉቀዋለን -- የቦንኬ ጊዜ የት ነበርሽ?
    ለዳንኤል
     የጾም ብፌ ትመስላለህ-- የማትገባበት የለም-- ፖለቲካ፤ስብከት፤ድቁና፤ምርምር፤…..

    ReplyDelete
  2. ለአባ ገብርኤል
     ከድቁና እስከ ጵጵስና በክህደት ጎዳና
    ለዘበነ
     አቋምሽን ከድሮ ጀምሮ እናዉቀዋለን -- የቦንኬ ጊዜ የት ነበርሽ?
    ለዳንኤል
     የጾም ብፌ ትመስላለህ-- የማትገባበት የለም-- ፖለቲካ፤ስብከት፤ድቁና፤ምርምር፤…..

    ReplyDelete