Saturday, March 31, 2012

ጋዜጠኞች ሆይ የጣላችሁትን ሚዛን አንሡ!


ጋዜጠኛነት ሊያሟላቸው ከሚገቡ የሙያ ሥነ ምግባራት መካከል አንዱ ሚዛናዊነት ነው፡፡ ጋዜጠኛ ሰው እንደ መሆኑ ራሱ የሚደግፈው ወይም የሚቃወመው ሐሳብ ሊኖር ቢችልም፣ የግል አቋሙን በዘገባው ውስጥ ሊያካትት እንደማይገባው የሙያው ሥነ ምግባር ያስገነዝባል፡፡ ይሁን እንጂ በአገራችን የጋዜጠኛነት ሙያ ብዙ ጊዜ ሚዛናዊነትን ሲጠብቅ አይታይም፡፡ አንዳንድ ሚዛናዊ ዘገባ የሚያቀርቡና ለሙያቸው ታማኝ የሆኑ ጋዜጠኞች ባይጠፉም፣ ብዙዎች ግን  የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ፍጹም ወገንተኛ የሆኑና የሙያውን ሥነ ምግባር የሚያፈርሱ ሆነው ይገኛሉ፡፡

በተለይም የነጻ ፕሬስ ውጤቶች የሆኑ ብዙዎቹ የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ነጻ ሆነው አለመገኘታቸውና እውነትን በሚዛናዊነት ከማቅረብ ይልቅ ወገንተኛነት የሚንጸባረቅባቸው መሆኑ የጋዜጠኛነትን ሙያ እጅግ እየጎዳው ነው፡፡ በዚህ አገር ነጻ ፕሬስ ማለትም መንግሥትን ወይም የታላላቅ ሃይማኖታውያን ተቋማት መሪዎችን በመቃወም መዘገብ ተደርጎ እየተወሰደ መሆኑ ሌላው የተዛባ የነጻ ፕሬስ አካሄድ ሆኗል፡፡ መንግሥትንም ሆነ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችን በተገቢው መንገድ ተችቶ መጻፍ አግባብነት ያለው አይደለም እያልኩ አይደለም፤ ነገር ግን ከጭፍን ጥላቻና ከጭፍን ድጋፍ የጸዳ ዘገባ ሊቀርብ ይገባል ነው ክርክሬ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግል ፕሬሶችን ሰፊ ሽፋን ይዘው የሚገኙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የሚወጡ ዘገባዎች ናቸው፡፡ ለዜና ፍጆታ የሚውል ጉዳይ ከተገኘ መዘገቡ ትክክል ነው፡፡ በአዘጋገቡ ሁኔታ ግን በአብዛኛው የአንድን ወገን ሐሳብ ብቻ ደግፎና ሌላውን ተቃውሞ የመዘገብ ሁኔታ ነው የሚስተዋለው፡፡ ሚዛናዊት የሚባል የጋዜጠኛነት ሥነ ምግባር የሌለ እስኪመስል ድረስ፣ በጭፍን አንዱን ጻድቅ ሌላውን ኃጥእ፣ አንዱን ትክክል ሌላውን የተሳሳተ፣ አንዱን ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ፣ ሌላውን ቤተ ክርስቲያን አፍራሽ፣ አንዱን ሃይማኖተኛ፣ ሌላውን መናፍቅ ብሎ የመፈረጁ አደገኛ አካሄድ ብዙ እያስተዛዘበ ይገኛል፡፡ ይህ የጋዜጠኛነትን ሙያ በእጅጉ እየተፈታተነ ያለ አደገኛ አካሄድ ነው ብዬም አስባለሁ፡፡

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ በፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ የጥቅምት 14 ቀን ዕትም ላይየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሳሳቢ ፈተና ላይ ወድቃለች ተባለበሚል ርእስ የወጣው ዘገባ ነው፡፡ ዘገባው ሕጋዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ውክልና በሌላቸው ክፍሎች ቀረቡ በተባሉ አቤቱታዎች፣ ተጠየቁ በተባሉ ጥያቄዎችና ተሰጡ በተባሉ መግለጫዎች፣ እንዲሁም ስለ ጥቅምት 11/2004 .. የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተቃውሞ ሰልፍ እጅግ የተዛቡ የጋዜጠኞቹ አስተያየቶች የተሞላ ነው፡፡
ሌላ ሌላውን በመተው ከላይ ጨምቄ በጠቀስኳቸው ነጥቦች ላይ ብቻ ማተኮር እፈልጋለሁ፡፡
ነጥብ አንድ

ስለሃይማኖት ትምህርት ተጠያቂው ማነው?
ፍኖተ ነጻነት የቤተ ክርስቲያኒቱ ትልቅ አደጋ አድርጎ ያቀረበው ዘገባ፣ የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አቀረቡት የተባለውንና 12 የተለያዩ ፊርማዎችን የያዘውን ስም አይጠሬ ባለ 41 ገጽ ዘገባ ነው፡፡ ዘገባው የተዘጋጀው በአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ነው የሚለውን ግን ከማይቀበሉት ወገን ነኝ፡፡ በዚህ ዘገባ ውስጥ የተካተቱት ሐሳቦች ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ማኅበረ ቅዱሳን ሲያስተጋባቸው የነበሩ የራሱ ሐሳቦች ናቸው፡፡ የማኅበሩ አንዳንድ ሰዎች በአንዳንዶቹ ዘገባዎች በስም ማጥፋት ወንጀል ተከሰው ብዙ ዋጋ እንደ ከፈሉበትም ይታወቃል፡፡ ይህን በተሟላ ማስረጃ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡
ታዲያ ያው የማኅበረ ቅዱሳን ሐሳብ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ስም መቅረብ ለምን አስፈለገውከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያኒቱ በመናፍቅነት ያልፈረጀቻቸውን ሰዎችና በማኅበረ ቅዱሳን ተከሰው ነጻ የወጡትን፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ደግሞ በስም አጥፊነት ተጠያቂ ያደረጉትን ሰዎች ዳግም መክሰስ ለምን አስፈለገ? አስፈላጊ ከሆነ ያኔውኑ ይግባኝ አይጠየቅባቸውም ነበር ወይ? የአቤቱታው አቅራቢዎችስ ለምን ፈራ ተባ አሉ? ፊርማቸውን ብቻ አሳርፈው ስማቸውን ለምን ምስጢር አደረጉት? የሚሉት ጥያቄዎች በቸልታ የሚታለፉ ሊሆኑ አይገባም፡፡
የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ወጣቶች እንደ መሆናቸው የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢዎች፣ የዛሬዋም ቤተ ክርስቲያን ጌጦችና ድምቀቶች መሆናቸው አይካድም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸው ቦታም ትልቅ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ዛሬ ለቤተ ክርስቲያኗ ትምህርትም ሆነ ሥርዐት ዋናዎች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያኗን ትምህርት ገምጋሚዎች፣ እገሌ ይግባ እገሌ ይውጣ ባዮች፣ ለዚህ ጉዳይም ውክልና የተሰጣቸው አካላት አይደሉም፡፡ በዕውቀትም በዕድሜም ያልበሰሉ እንደ መሆናቸው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ከአባቶች እግር ሥር ተቀምጠው መማር፣ ምስጢር ማደላደል፣ የቤተ ክርስቲያናቸውን ታሪክ ማወቅና በዚሁ መሠረት ማደግ ይገባቸዋል፡፡

ይህ የኖረ የቤተ ክርስቲያናችን ባህል እየጠፋ የመጣው በማኅበረ ቅዱሳን ምክንያት ነው ቢባል ስሕተት አይሆንም፡፡ ማኅበሩ እኔ ብቻ ልክ ነኝ የሚል አባዜ የተጠናወተው በመሆኑ፣ ለእርሱ ዕንቅፋት መስለው የታዩትን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሁሉ መናፍቃን ናቸው ሲል እንደ ኖረ ይታወቃል፡፡ የእርሱን ሐሳብ ደጋፊዎች ደግሞ የተለዩ አድርጎ ሲያወድሳቸውና ሲያሞግሳቸው ነው የኖረው፡፡ እንዲህ ማድረግ መብቱ ሊሆን ቢችልም፣ እንዲህ የማድረግ ሥልጣን ግን የለውም፡፡ ውክልና የሰጠው የቤተ ክህነት አካልም የለም፡፡ በማኅበሩ ፈር የለቀቀ አካሄድ ትክክለኛው የቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዐት እየተበላሸ ነው፡፡ ስለ ሃይማኖት የሚጠየቁ ሊቃውንት እያሉ፣ ስለ ሃይማኖት ጉዳይ ምንም የማያውቁግልቦችቤተ ክርስቲያንን እኛ ካልመራን ቤተ ክርስቲያን ትልቅ አደጋ ውስጥ ናት ብሎ ከማሰብና ከመንቀሳቀስ የበለጠ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተቃጣ ትልቅ አደጋ የለም፡፡

ወጣቶቹ አቀረቡት የተባለው ባለ 41 ገጽ ሰነድ ውስጥ የተዘረዘሩት የአገርና የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የተሐድሶ አራማጆች ናቸው ለማለት ወጣቶቹ እነማን ናቸው? በምን መስፈርትና በምን ሥልጣን ነው እንዲህ ለማለት የበቁት? ተሐድሶስ ምንድን ነው? የእነዚህን ወጣቶች ግልብ አስተሳሰብ ይዞ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ አደጋ ውስጥ ናት ብሎ መዘገብስ ከአንድ ጋዜጠኛ ነኝ ከሚል ሰው ይጠበቃል ወይ? እነዚህ ልጆች እኮ፣ ከጥንት እስከ ዛሬ ለአገርና ለወገን፣ ለቤተ ክርስቲያንም ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱና አሻራቸውን ያሳረፉ ታላላቅ ሰዎችን፣ ለሃይማኖት ነጻነትና እኩልነት የታገሉ እንደ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ያሉ ብርቅዬ ኢትዮጵያውያንን፣ ከኋላ ቀር አኗኗር እንላቀቅ፤ እንሻሻል ያሉትን ተራማጁን ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴን፣ በአንድ፣ ተቀብሮ በኖረና ከጥቂት ዓመታት በፊት የኅትመት ብርሃንን ባየ የደቂቀ እስጢፋኖስ መጽሐፍ ላይ አስተያየት የሰጡትን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምን ይወገዙልን እያሉ እኮ ነው፡፡  ታዲያ ሌሎች እንደ ጫኗቸው አገር ይወገዝልን ሲሉ ከማየት የከፋ ምን አደጋ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ተጋርጧል ማለት ይቻላል?
እነዚህ ልጆች የኑፋቄን ምንነት ያልተረዱ፣ የሃይማኖትንና የአብዮትን ዳር ድንበር ያልለዩ የሌሎች መሣሪያዎች ናቸው፡፡ በሃይማኖት ስም የሰውን ክብር ለመንካትና ሰብኣዊ መብትን ለመግፈፍ ታጥቀው የተነሡ አላዋቂዎችም ናቸው፡፡ ታዲያ እንዲህ ላለው የልጆች ጨዋታ የጋዜጣ ገጽ እንዴት ተሰጠው? ፍኖተ ነጻነት በጭፍን የልጆቹን ጥሬ ሐሳብ ሳያበስል እንደ ወረደ መዘገቡ ራሱን ትዝብት ላይ ከመጣል በቀር አንዳች ትርፍ አይኖረውም፡፡ ጋዜጣው በአንድ ወገን ሐሳብና በስሜታዊነት መነዳት አልነበረበትም፤ እነዚህ ሁሉ በአገር ላይ ታላላቅ አሻራቸውን ያሳረፉ ሰዎች የተሐድሶ አራማጆች ናቸው የሚለውን አዲስ ሐሳብ ቆም ብሎ ሊመረምረውና የተሻለ ዘገባ ሊያስነብበን በተገባ ነበር፡፡

ነጥብ ሁለት
ትምህርተ ክርስትና በድጋፍ ፊርማ አይጸድቅም  
ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ 10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተፈራረሙበትን የመጠይቅ ሰነድ ለሚመለከታቸው የቤተ ክህነትና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በግልባጭ ገቢ ማድረጋቸውን፣ እንዲሁም 22 ሺህ በላይ የሆኑ የቤተ ክርስቲያኗ ሰዎች አሁን ለሚታዩት የቤተ ክርስቲያኗ ችግሮች የመፍትሔ ሐሳብ ያሏቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ገቢ ማድረጋቸውን ነግሮናል፡፡ ለመሆኑ ይህን ለማድረግ የተንቀሳቀሱት እነማን ናቸው? እንዲህ የማድረግስ ምን ሥልጣን አላቸው? ለሚሉት ጥያቄዎች ግን በቂ ምላሽ የሚሰጥ ዘገባ አላስነበበንም፤ የጉዳዩ ትክክለኛ ባለቤቶችም አልተጠቀሱም፡፡

እውን ወደ 22 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ተደራጅተው ተንቀሳቅሰዋል ወይ? የሚለው አሁንም አጠያያቂ ነው፡፡ በእኔ እምነት ከጉዳዩ በስተ ጀርባ ያለው አካል ሌላ ሳይሆን ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ ከላይ ስለ ሰንበት ተማሪዎች እንደ ጠቀስኩት ማኅበረ ቅዱሳን ስለ ሃይማኖት ጉዳይ ተጠያቂ ሊሆን የሚችል፣ ብቃቱም ሥልጣኑም ያለው አካል አይደለም፡፡ ነገር ግን በብዙዎች የሚታመነው ማኅበሩ ያለውን ድብቅ ፖለቲካዊ አጀንዳ በሃይማኖት ሽፋን ስለሚያራምድ፣ ያን እንዳይፈጽም እክል በገጠመው ቁጥር ሃይማኖታዊ ስሕተት የተፈጸመ በማስመሰል አባቶች የሚከፋፈሉበትና የእርሱ ድምፅ የሚሰማበት አጋጣሚ እንዲፈጠር ነው የሚፈልገው፡፡ ፍኖተ ነጻነት የአንድነት ፓርቲ ልሳን እንደ መሆኑ ከዚህ የሚያገኘው አንዳች ትርፍ ይኖር ይሆን

22 ሺህ የተባሉት ሰዎች አቀረቧቸው የተባሉት የመፍትሔ ሐሳቦች በምን መሠረት ላይ የቆሙ ናቸው? እነዚህ የማኅበረ ቅዱሳን ወይስ የቤተ ክርስቲያኒቱ የወቅቱ አንገብጋቢ ችግሮች ናቸው? በእውነቱ እነዚህ ጉዳዮች መፈተሽ አለባቸው፡፡ በእኔ እይታ የቀረቡት ወደ ስድስት የሚጠጉ ነጥቦች በአሁኑ ወቅት ኪሳራ እየደረሰባቸው ያሉ ወገኖች እያስተጋቡት ያለ ጩኸት እንጂ የቤተ ክርስቲያኒቱ አንገብጋቢ ችግሮች አይደሉም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ላሉባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚያስፈልጋት መፍትሔ ከግል ጉዳይ ጋር መያያዝ በፍጹም የለበትም፡፡ እነዚህ የቀረቡት የመፍትሔ ሐሳቦች ተቀባይነት ቢያገኙ፣ የማኅበረ ቅዱሳንን የመጫወቻ ሜዳ ከማስፋት የዘለለ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ለቤተ ክርስቲያኗ መለወጥና መሻሻል ግን ከዚህ በላይ የሆነና ከአስተምህሮዋ ጀምሮ እስከ አስተዳደሯ ድረስ ያሉት ጉዳዮች የድጋፍ ፊርማ በሚያሰባስቡና ደብቅ አጀንዳ ባላቸው ክፍሎች ሳይሆን በሊቃውንቷ ተፈትሸውና ተመርምረው ውሳኔ ሊያገኙ ይገባል፡፡
ፍኖተ ነጻነት እንደ ጋዜጣ ይህን ሐሳብ በተመለከተ የአንድ ወገን ሐሳብ ብቻ አቅርቦ ቤተ ክርስቲያኗ አደጋ ላይ ነች በማለት ትልቅ ስሕተት ከሚፈጽም ይልቅ፣ ስለ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የቤተ ክርስቲያኗን ሊቃውንት በማነጋገር ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ ነበረበት፡፡ ሌሎቹም ብዙዎቹ የፕሬስ ውጤቶች አንዳንድ ዘገባዎችን እንደ ጋዜጠኛ በገለልተኛነት ሳይሆን እንደ ሃይማኖተኛ ሆነው ነው የሚዘግቡት፡፡ ይህን ለማድረግ ምናልባት ሃይማኖታዊ ጋዜጣ ወይም መጽሔት መሆን ይጠበቅባቸው ይሆናል፡፡ በሌላ ዐላማ የተቋቋሙ እስከ ሆነ ድረስ ግን ለጋዜጠኛነት ሙያና ለሥነ ምግባራቱ ተገዢ መሆን አለባቸው፡፡ አንድ ጋዜጠኛ ሃይማኖተኛ ሊሆን ቢችልም፣ የግል አቋሙን የማራመድ መብት ቢኖረውም፣ ለሕዝብ በሚያቀርበው የዜና ዘገባ ውስጥ ግን እውነትን በሚዛናዊነት ማቅረብ እንጂ የእርሱ ሃይማኖታዊ አቋም እንዲያዝለት አንባብያንን መጠምዘዝ የለበትም፡፡

ብዙዎቹ የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች በዚህ ሥራ እንደ ተጠመዱ ከሚያወጧቸው ዘገባዎች መረዳት ይቻላል፡፡ አንዳንዶቹ ታይተው የሚጠፉና ጊዜ እየጠበቁ ብቅ የሚሉት መጽሔቶችና ጋዜጦችም ቢሆኑ ዐላማቸው ቤተ ክህነቱን በወሬ ለመፍታት ከመሞከር ያለፈ አይደለም፡፡ ታዲያ ይህ ሌላ ድብቅ አጀንዳ እንጂ እንዴት እውነትን ይፋ ማውጣት ሊሆን ይችላል? ስለዚህ ጋዜጠኞች ሆይ! የጣላችሁትን ሚዛናችሁን አንሡ! ሚዛናዊ ዘገባም አስነብቡን፡፡

ነጥብ ሦስት
በጥቅምት 11/2004 ሰልፍ ያጠፋው ማነው?
ፍኖተ ነጻነት በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ አስመልክቶ ያቀረበው ዘገባ ፍጹም የተዛባ ነው፡፡ ጉባኤውን የጠሩት ማኅበረ ቅዱሳን የከፈተባቸውን የስም ማጥፋት ዘመቻ በመቃወም ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተሰባሰቡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ናቸው፡፡ እነርሱ የጠሩትን የተቃውሞ ሰልፍ ለማደፍረስ የተሰባሰቡት ደግሞ የአዲስ አበባ ሰንበት /ቤቶች የተባሉ (የአዲስ አበባ ሰንበት ተማሪዎች መሆናቸው መጣራት ያለበት ቢሆንም) ክፍሎች ናቸው፡፡ እነዚያ ቀደም ብለው ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ባለ 41 ገጽ የክስ መዝገብ አስገብተዋል፡፡ የዚያን ውጤት መከታተልና ተገቢውን ውሳኔ መጠበቅ የጨዋ ደንብ ሲሆን፣ እነዚህ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው ድምፃቸውን እንዳያሰሙ ማደናቀፍና ለዱላ መጋበዝ ከመንፈሳዊነት የወጣ የዐመፅ ተግባር ነው፡፡ ታዲያ ጋዜጠኞቹ የት ሆነው ቢመለከቱ ነው የሰልፉን አዘጋጆች በመንቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተባሉትን ትክክለኛ አስመስለው በማቅረብ የተዛባ ዘገባ ያወጡት? ነው ወይስ የዚያ ወገን ሰዎች የነገሯቸውን ብቻ ነው የዘገቡት?

በዕለቱ በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገኝተው በጩኸትና  በልዩ ልዩ የረብሻ መንገዶች ሲበጠብጡ የነበሩት ፍኖተ ነጻነት በበጎ ጎን ያቀረባቸው የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተባሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ትክክለኛ ቢሆኑ ኖሮ አገር ይወገዝ ብለው ያቀረቡትን ክስ መከታተልና ውሳኔውን መጠባበቅ ነበረባቸው፡፡ ሌሎቹ ድምፃቸውን እንዳያሰሙ እንቅፋት መሆን ግን እውነተኛ ነን ባይነታቸውን ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡ እንዲያውም ችግር ቢኖርባቸው እንጂ እውነተኞች ቢሆኑ ኖሮ ወደ ዐመፅ አይሄዱም ነበር የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡

ከምንም በላይተሐድሶ - መናፍቃንየሚለውን ስያሜ ያወጣው ማኅበረ ቅዱሳን ሆኖ ሳለ፣ የሚመለከተው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል ማንንም ተሐድሶ መናፍቅ ብሎ ባላወገዘበት ሁኔታ፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች ከሜዳ ተነሥተውተሐድሶ - መናፍቃንብለው በድፍረት መጻፋቸው ሕገ ወጥ ተግባር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በፍርድ ቤት ጉዳዩ ያላለቀና ጥፋተኛ ተብሎ ያልተፈረደበት ወንጀለኛ እንኳ ተጠርጣሪ ይባላል እንጂ ወንጀለኛ አይሰኝም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ግን በሌለው ብቃትና ሥልጣን ይህ ሕጋዊ አሠራር በየጊዜው ሲጥስና ሌሎችም እንዲጥሱት ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ የዐይናችሁ ቀለም አላማረኝም ያላቸውን የቤተ ክርስቲያንን ሊቃውንትና መምህራን ሁሉተሐድሶ - መናፍቃንየሚል ስም እያወጣላቸው፣ ራሱ ስቶ የመገናኛ ብዙኃንንም እያሳተ እንደሚገኝ ከግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት፡፡

በአጠቃላይ የመገናኛ ብዙኃን የአንድ ወገን ዘገባ ብቻ ይዘው እርሱኑ ከሚያራግቡ ይልቅ በሁለቱም ወገኖች በኩል ያለውን ጉዳይ ፈልፍሎ በማውጣት ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሊያ የእርሱን ሐሳብ ደግፈው የጻፉለት ወገን ልሳን እንጂ ነጻ ፕሬስ መሆናቸው ይቀራል፡፡

3 comments:

  1. Talking about journalists first you guys need to look in to your own actions you don't have to point your fingers into others & start blaming them. Who are you to say that any way?

    ReplyDelete
    Replies
    1. የተፃፈው እውነት ነው አይደለም ብለህ ከመጠየቅ ብትነሳ አይሻልም? ዝም ብለህ ከምትቀባጥር። አኔ እንዳየሁት ከሆነ ፅሁፉ ምክንያታዊ ነው። አቅም ካለህ እሱን ተች። ወይም በጥሞና አንብበህ ተመከርበት

      Delete
  2. ግሩም ነው። ይበል ብለናል። ምክር ሰሚ ከተገኘ ግሩም ምክር ነው። ጋዜጠኞች ተመከሩበት።

    ReplyDelete