Tuesday, March 20, 2012

ዛሬም ያልተፋቱት ኢትዮጵያና ግብፅ


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ግብጻውያንና የዓባይ ወንዝ፡-
ከቤተ ጳውሎስ ድረገጽ የተወሰደ 
ከትላንት በስቲያ በሥጋ የተለዩን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ሀገር የሆነችው ግብጽ የረጅም ጊዜ ሥልጣኔና ታሪክ ያላት አፍሪካዊት ሀገር ናት፡፡ እጅግ የዳበረ የሥነ ሕንጻ፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የፍልስፍና ማዕከል፣ በዓለማችን ከሚገኙት ታላላቅ ሥልጣኔዎች ተብለው ከሚጠቀሱት ከፋርስ (ፐርሺያ)፣ ከባቢሎን፣ ከአሴርያውያን፣ ከግሪክ፣ ከሮማ፣ ከቻይና፣ ከደቡብ አሜሪካዎቹ ከአዝቴክስና ከኢንካ እንዲሁም ከእኛዋ አክሱም ሥልጣኔ ጋር በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ሀገር ናት፡፡
በዓለማችን የመጀመሪያ እንደሆነ የሚነገርለትና በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የፍልስፍና፣ የታሪክ፣ የጥበብ፣ የአልጄብራና ጆሜትሪ፣ የሥነ ፈለክ፣ የሕክምና እና የመሳሰሉ የጥንት የብራና ጥቅልሎችን የያዘውና ግሪካዊው አሌክሳንደር ዘግሬት ግብጽን በወረረ ጊዜ ለቃጠሎና ለመዘረፍ የበቃው ቤተ መጻሕፍት አቻና ወደር የሌለው እንደነበር የግብጽን ሥልጣኔና ታሪክ የሚያጠኑ ምሁራን (Egyptologists) ይናገራሉ፡፡ እንደውም እንደ አንዳንድ አፍሪካውያንና አፍሪካ አሜሪካውያን ምሁራን ለግሪክ ሥልጣኔ ትልቅ መሠረት የጣለው ከዚሁ ከግብጻውያን ቤተ መጻሕፍት በተዘረፉት የዕውቀትና የጥበብ ምንጮች በሆኑት የብራና መጻሕፍቶች እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
በሃይማኖትም ረገድ ግብጽ እስራኤል ጋር ባላት ታሪካዊ ትስስር የተነሣም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፊ ቦታ ተሰጥቷት የተተረከላት ሀገር ናት፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሕጻንነቱ ወራት ከእናቱ ጋር ወደ ግብጽ ተሰዶ እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል፡፡ ግብጻውያን የክርስትና ሃይማኖትን በወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ አማካኝነት በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን እንደተቀበሉ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ የመጀመሪያው የግብጽ ኦርቶዶክስ ፓትሪያርክም ይኸው ቅዱስ ማርቆስ እንደሆነ የግብጻውያን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡ ዛሬ በሥጋ የተለዩንም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳም በቅዱስ ማርቆስ መንበር 117ኛው ፓትሪያርክ ነበሩ፡፡
4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስትና ወደ አክሱም ገብቶ በቤተ መንግሥት ተቀባይነትን ካገኘ በኋላ ክርስትናን በአክሱም ቤተ መንግሥት የሰበኩት ፍሬምናጦስ የመጀመሪው የአክሱም ሊቀ ጳጳስ ይሆኑ ዘንድ በግብጻውያን አባቶች መሾማቸውን ታሪክ ያስረዳል፡፡ ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከ1950 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በግብጻውያን አባቶች ትተዳደር እንደነበር የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር የነበራት ግንኙነት ከሰላም ይልቅ ብዙ ጊዜ አለመግባባትና ግጭት የሰፈነበት እንደነበር በቤተ ክርስቲያናችንና በሀገራችን ታሪክ በግልጽ ተዘገቦ ይገኛል፡፡ በተለይም ደግሞ ግብጻውያን በዐረቦች ከተወረሩና ግብጽም የእስልምናን ሃይማኖት ብሔራዊ ሃይማኖቷ አድርጋ ከተቀበለች በኋላ በግብጽ የተፈጠረው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ሃይማኖታዊ ቀውስ በሀገራችን ኢትዮጵያና በቤተ ክርስቲያናችንም ጭምር መጥፎ ጥላ አጥልቶበት እንደነበረ በርካታ የታሪክ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የግብጻውያን ሕይወት የሆነው የዓባይ ወንዝ ነው፡፡ 
በተለምዶ ‹‹የታሪክ አባት›› ተብሎ የሚጠራው ሄሮዱተስ ግብጽን ‹‹The Gift of Nile››(የዓባይ ስጦታ) በሚል ቅጽል ነው ታሪኳን የጻፈላት፡፡ ለግብጻውያን ሕይወትና ኑሮ የሕልውና መሠረት የሆነው የናይልን ወንዝ 86 በመቶ የውኃ አቅርቦት የሚሄደው ከእኛው ዓባይ ወንዝ መሆኑና የዓባይ ወንዝም ከኢትዮጵያ ከፍተኛና ተራራማ ቦታዎች እየጠራረገ የሚወስደው ለም አፈር ለግብጻውያኑ የህልውና መሠረት በመሆኑ ግብጻውያን በሙሉ ዓባይን በስስት ዓይን  የሚያዩት ወንዛቸው እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከዚህም የተነሣ ይኸው የዓባይ ጉዳይ በግብጻውያንና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ዙሪያ እንደ ትልቅ አጀንዳ/መነጋገሪያ አልፎ አልፎም የግጭት መንስዔ የሆነበት አጋጣሚዎች እንደነበሩ አያሌ የታሪክ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለ1600 ዓመታት ጳጳስ ታስመጣ የነበረው ከግብጽ ስለነበር እነዚህን አባቶች የማግኘት ጥያቄና የግብጻውያኑ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ፀጥታና ደኅንነት ጉዳይ በከፊልም ቢሆን ከዓባይ ጋር ተያያዥነት እንደነበረው ብዙ መረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ (ካልኣይ) በጻፉት "የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ" መጽሐፋቸው እንደገለጹት፡-
ዛግዌ ዘመነ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ ተልከው የነበሩት ጳጳስ አቡነ ሳዊሮስ በግብጽ ሲኖዶስ የተመረጡ ሳይሆን በእስላማዊው ንጉሥ (በከሊፋው) በበድር አል ጀማል ትእዛዝ የተላኩ ጳጳስ እንደነበሩና ከሀገራቸው ንጉሡ ጋር ባደረጉት ስምምነት መሠረትም፤ በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ሥራ ከመጀመራችው በፊት በኢትዮጵያ ለሚኖሩ ዐረብ እስላሞች መስጊዶች እንዲሠሩ አደርገዋል፡፡ እስላሞቹም በኢትዮጵያ ላይ ሃይማኖታቸውን እንዲያስፋፉ የሐሳብ ድጋፍ ይሰጧቸው ጀመር፤ በእርግጥ እኚህ አባት ይሄን ያደረጉበት ዋንኛው ምክንያት እንደ አቡነ ጎርጎርዮስ ገለጻ በግብጽ ያሉ ክርስቲያን ወገኖቻቸው የመከራ ቀንበር እንዲቀልላቸው ብለው እንደሆነ ያስረዳሉ፤
ይሁን እንጂ በወቅቱ ከኢየሩሳሌም በመቀጠል ቅድስት የክርስቲያን ምድር ተብላ በምትጠራው በኢትዮጵያ ምድር መስጊዶች መታነጻቸው ያላስደሰታቸው ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችና ንጉሡ በአስቸኳይ መስጊዶቹ እንዲፈርሱ በማድረጋቸው ይሄን ዜና የሰማው የግብጽ ንጉሥ ለኢትዮጵያው ንጉሥ ለግርማ ሥዩም በላከው አስቸኳይ መልእክት፦
"በሀገርህ የፈረሱት መስጊዶቻችን እንደገና ካልተሠሩ እኔም በግብጽ የሚገኙትን የኮፕት አብያተ ክርስቲያናትን እንዳልነበሩ አደርጋቸዋለሁ" በማለት ዛቻ የተቀላቀለበት መልእክት ላደረሳቸው የግብጽ ንጉሥ የኢትዮጵያዊው ንጉሥ በላኩት የአጸፋ መልእክት፥ "ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ድንጋይ ብታነሣ መካ ተሻግሬ የካአባን ድንጋይ አመድ አድርጌ ትቢያውን ካይሮ እልክልሃለሁ" በማለት ምላሽ እንደሰጡት አቡነ ጎርጎርዮስ በመጽሐፋቸው ገልጸውታል። በሌላ በኩል አንዳንድ የዐረብ ታሪክ ጸሐፊዎች እንደዘገቡት ደግሞ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ "ከመካ የመስጊዱን ድንጋይ አስመጥቼ የፈረሱትን መስጊዶች አሠራልሃለሁ" በማለት የምጸት ምላሽ እንደሰጡት ዘግበዋል፡፡
በግብጽ ክርስቲያኖችና በኢትዮጵያውያኑ ክርስቲያኖች መካከል ለረጅም ዘመናት የቆየው ግንኙነት በመጥፎም በመልካም የሚነሡ ብዙ ታሪካዊ እውነታዎች ቢኖሩም በዋነኝነት ግን ግብጽ በእስላሞች እጅ ከወደቀች በኋላ በኮፕት ክርስቲያኖች ላይ ይደርስ የነበረውን ግፍ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖችም ሆኑ ነገሥታቱ በዝምታ ያለፉበት ጊዜ እንደሌለ ከበቂ በላይ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ግብጻውያኑ ሙስሊሞች በክርስቲያኑ ላይ ያደርሱት ለነበረው ግፍ በዋነኛነት የግብጽ እስትንፋስ የሆነው የዓባይ ወንዝ ክርስቲያኖቹ ላይ ይደርስ የነበረውን ግፍ ለመከላከል ከማስፈራሪያነት ባሻገር በተግባር ዓባይን ለመገደብና የውኃውን አቅጣጫ ለማስቀየር የሞከሩ የኢትዮጵያ ነገሥታት እንደነበሩ ታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ።

ጆን ስፔንሰር ትሪሚንግሃም የተባለ አውሮፓዊ የታሪክ ተመራማሪና ምሁር ‹‹Islam in Ethiopia›› በሚለው መጽሐፉ እንደጠቀሰው ዓባይን በመገደብና የውኃውን አቅጣጫ በማስቀየር ረገድ በጉልህ ከሚጠቀሱት ኢትዮጵያውያን ነገሥታት መካከል ንጉሥ ይምርሐነ፣ ንጉሥ ሐርቤ፣ አጼ አምደ ጽዮን፣[1] አጼ ዳዊትና አጼ ዘርዐ ያዕቆብ ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ ንጉሥ ይምርሐነ ክርስቶስ ዓባይን የመገደብ ሥራ በመጀመሩ በእጅጉ የተደናገጡት ግብጻውያን ወደ ኢትዮጵያ በላኳቸው መልእክተኞች ዓባይን በመገደብ የሚያልቁት ግብጻውያን እስላሞች ብቻ ሳይሆኑ ክርስቲያን ወንድሞቻችሁም ጭምር ናቸው በማለት የተማጽኖ መልእክት በእስክንድሪያው ሊቀ ጳጳስ በአቡነ ሚካኤል በኩል ተልኮ እንደነበረ ይኸው አውሮፓዊ ጸሐፊና የሀገራችን ታሪክ ጸሐፊዎችም የታሪክ መዛግብቶች ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያና በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ግንኙነት ላይ የዓባይ ወንዝ የነበረውን ታላቅ ሚና ከታሪካችን አንጻር በጣም በጥቂቱ ይሄን ያህል ካልን በሥጋ ስለተለዩን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳን ለመዘከር ይቻለን ዘንድ በቅዱስነታቸው ሕይወትና አገልግሎት ዙሪያ አንዳንድ ሐሳቦችን እናንሣ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ፓትሪያሪክ መሾም ከጀመረች ከ1950ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የነበረው ግንኙነት ይሄን ያህል ብዙ ሊባልለት የማይችል እንደሆነ የቤተ ክርስቲናችን አባቶች ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዝዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት መልካም ጥረት በሁለቱ እህት አብያተ ክርስቲያናት መካከል የነበረው ግንኙነት ወደ መልካም ደረጃ እያደገ እንደሆነና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ዕሥራ ምዕትን ባከበረችበት ጊዜም ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ ከግብጻውን ኮፕቲክ አባቶች ጋር በታላቅ ድምቀት በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ በመገኘት አባታዊ ቡራኬያ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስም በቅርቡ በቅዱስነታቸው የ40ኛ ዓመት ሢመተ በዓል ላይ የመላው አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ከብፁዕ አቡነ ያዕቆብና ከሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት አባቶች ጋር በበዓሉ ላይ መገኘታቸውንና እንዲሁም ሀገራችን በዓባይ ወንዝ ላይ እያደረገችው ያለውን ልማት በተመለከተ ቅዱስነታቸው ከቅዱስነታቸው ከአቡነ ሺኖዳ ጋር፣ ከግብጽ ጠቅላይ ሚ/ር እና እንዲሁም ከግብጽ የእስልምና ሃይማኖት ተወካዬች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ለሁለቱ እህተ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት ትልቅ እመርታ እንደሆነ እናስባለን፡፡
ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ በግብጻውያን እና በዓለማችን ክርስቲያኖች ዘንድ ትልቅ ከበሬታና  መወደድን ያተረፉ አባት ነበሩ፣ በሕይወት ዘመናቸው ከ80 በላይ በመንፈሳዊ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጻሕፍትን የጻፉ ነበሩ፣ እነዚህ መጻሕፍቶቻቸውም በሀገራችን በብዛት ተተርጉመው ለአንባቢያን በቅተዋል፡፡ የቅዱስነታቸው የዕረፍታቸው ዜና እንደተሰማም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ባሰተላለፉት መልእክታቸው፡- ‹‹አቡነ ሺኖዳ ትልቅ የሃይማኖት አባትና በሃይማኖቶች መካከል ሰላም፣ መቀራረብና መቻቻል ይኖር ዘንድ የሰበኩ ሰው ነበሩ፡፡›› ማለታቸውን የአሜሪካ ሲ ኤን ኤን እና የእንግሊዙ ቢቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዘግበዋል፡፡
ቅዱስነታቸው ከሁለት ዓመት በፊት በግብጻውያን ክርስቲኖች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ለመጣው ስደትና መንገላታት ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ የቪዲዮ ንግራቸው በማኅበራዊ ድረ ገጾች በሆኑት በፌስ ቡክ፣ በቲዊተርና  በዩ ቲዩብ የተላለፈው የቅዱስነታቸውን የአቡነ ሺኖዳ እንባ የተቀላቀለበት ንግግር በዓለም ላሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ትልቅ ትኩረትን ስቦ የነበረ ነው፡፡ ቅዱስነታቸው እንዲህ ነበር ያሉት በእንባና ሳግ በታጀበው ንግግራቸው፡-
‹‹… እኛ የምንለው ነገር የለንም፤ እግዚአብሔር ሁሉን ያያል… በጸሎት ከመማለድ በስተቀር ምን ማድረግ ይቻለናል፡፡ ዝም ብለን የእግዚአብሔርን ማዳን እንጠብቃለን፡፡››
እንዲሁም በግብፅ ርዕሰ ብሔር አንዋር ሳዳት ጊዜ አክራሪ ሙስሊሞች በክርስቲያኖች ላይየሚያደርሱት ጥቃት መጨመርና መፋፋም ያሳሰባቸው ቅዱስነታቸው በመንግሥቱ ላይ ባነሡትተቃውሞ፣ 40 ወራት ከመንጋዎቻቸው ተለይተው ወደ ቅዱስ ቢሶይ ገዳም ተግዘው የአባቶቻቸውንበረከት ተካፍለው እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን በኋለኛው መሪ ሆስኒ ሙባረክ ዘመን ወደ መንበራቸውተመለሰው እስከ ዛሬ ድረስ ጠቦቶችን ሲጠብቁ፣ ግልገሎችና በጎችን ሲያሰማሩ ቆይተው በሰላም ወደ አምላከቸው ክርስቶስ ሄደዋል፡፡
ወደ እኛው ታሪክ ስንመለስ ግን ትንሽ ነገር ለማለት ፈለግን፤ ዛሬም ቢሆን በቀደመው  ዘመን የኢትዮጵያ ወጣት ከራሺያና ከቻይና በመጣ በተውሶ አብዮትና ፍልስፍና ወንድምና ወንድም ማዶ ለማዶ ሆነው በቃላት ሲጠዛጠዝና ጎራ ለይቶ ሲተላለቅ፣ ምድሪቱ በደም ጨቅይታ አኬልዳማ በሆነችበትና በርካታ እናቶች ምነው መካን ሆነን በቀረን እያሉ ማኅፀናቸውን በተራገሙበት በዛ አስከፊ የደርግ ዘመን መንግሥታትን በድፍረት የገሰጹ፣ ወጣቶችንም ተው ብሎ የመከረ የሃይማኖት አባቶች ነበሩን እንዴ?! ምድሪቱ እንዲያ በደም በታጠበችበት ጊዜስ ፈጣሪ አምላክን ለመማጸን ወደ ገዳም የተሰደዱ አባቶች ነበሩን ይሆን?! በደርጉ ግዞትና ሞት ውሳኔ የተላለፈባቸውን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን እስራትና ሞት የተቃወሙ አባቶችስ በዚያን ዘመን ድምጻቸው ተሰምቶ ይሆንን?!
በእኛስ ዘመን በቅርቡ በምርጫ 97 ሰበብ ያ ሁሉ ብጥብጥ ሲነግሥስና ደም ሲፋሰስ ድምፁን ያሰማ የሃይማኖት አባት ነበር እንዴ?! የሚበዙት አባቶቻችን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለነገሠው የሞራል ውድቀት፣ ዘረኝነት፣ ጉቦና አሥተዳደራዊ ብልሽት እንዲሁም ሀገራችን ስለተዘፈቀችበት ፖለቲካዊም ሆነ ማኅበራዊ ቀውስ ለጸሎትና ለምልጃ ወደ ገዳም ከመሄድ ይልቅ የሕዝባቸውን ዋይታ፣ ጩኸትና እሮሮ ወደማይሰሙበት ወደ አውሮፓና አሜሪካ ቢሰደዱ የሚቀላቸው መሆናቸውን በተለያየ ጊዜ ታዝበናል፡፡ የልባችን ናፍቆት የሕዝባቸው ጉስቁልናና ውርደት ዕረፍት እየነሣቸው ሌትና ቀን በእንባና በልቅሶ ወደ ፈጣሪ የሚጮሁ አባቶች እንዲበዙልን ነው፡፡
ዘወትር የልባችን ጸሎት እና ናፍቆት አምላካችን እንደ ኤልያስ ዘመን እርሱ የሚያውቃቸው ስለ ቤተ ክርስቲያናችን አንድነት፣  ስለ ልጆቿ ፍቅር፣ ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የሚማጸኑ እናንተ የማታውቋቸው ቅሬታዎች አሉ እንዲለን ነው፡፡ በሀገራችንና በቤተ ክርስቲያናችን ያሉትን ችግሮች ለመዘርዘር አይደለም ለማሰብ እንኳን አንዳንድ ጊዜ አቅም ያጥራል፣ ኅሊናም ይደክማል፡፡ ችግራችን ብዙ፣ ዋይታችንና ልቅሶአችንም ማባሪያ ያለው አይመስልም፣ በዘመናችን መፍትሔውም የሰማይ ያህል የራቀ ነው የሚመስለው… ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ምን ማለት ይቻለን ይሆን፣ ዝም ብለን የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ማዳን በትዕግሥትና በጸሎት ከመጠበቅ ውጭ፡፡
በሰላምና በፍቅር ወደ አምላካቸው ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ በሰላም የሄዱት ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳስ በእንባ ሆነው ለልጆቻቸው ያሉት ይሄን አይደል፡- ‹‹…ዝም ብለን የእግዚአብሔርን ማዳን እንጠብቃለን… ፡፡››
እግዚአብሔር የአባታችንን ነፍስ በሰላም ያሳርፍልን ለግብጻውያን ክርስቲያን ወንድሞቻችንም መጽናናቱን ይስጥልን!
ከhttp://www.betepawlos.com/የተወሰደ

No comments:

Post a Comment