Saturday, March 17, 2012

በዚህስ አትበለጡ

/ከጌድዮን/

ዘመኑ የውድድር ዘመን አይደል! የፉክክር የሩጫ፣ የትግል፣ የእሽቅድምድም፣ የንፅፅር፣ የእኔ እበልጥ የእኔ እበልጥ አይነት የጥርስ መሰበር፣ ዘመን ማንም ከማንም አንሶ ላለመገኘት እልክ አስጨራሽ ፍልሚያ የሚደረግበት መድረክ፡፡ የምድራችን መርህ አለመበለጥ ነው ከቶስ ትግሉ ውስጥ የሌላ ዳር ቆሞ የሚታዘብ ጉልበት እስኪርድ፣ ላብ እስኪፈስ ደም ስኪንጠባጠብና አጥንት እስኪሰበር የሰው ልጅ በምድሪቱ መድረክ ላይ ከሁሉ ልቆና ገዝፎ ለመታየት የሚያደርገውን የፍጻሜ ጦርነት እንደተራ ጉዳይ ቆጥሮ የራሱን ኑሮ ብቻ የሚያስታምም ይኖር ይሆን? ወንድሜ ዘመኑ አለመበለጥን ነው የሚሰብክህ፡፡ ከነተረቱስ አለመቀደም ነው አይደል የሚለው? ሌላው ቀርቶ ታላቁ መጽሐፍ ‹‹የአንዱ ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይበልጣል›› ይል የለ፡፡ እዚያም ታላቅ የውድድር መድረክ መኖሩ መች ይቀራል፤ መልኩንና ጠባዩን ቢቀይር እንጂ!

ለመሆኑ እናንተ የማታወቁት የትግል የውድድርና የፍልሚያ መድረክ አይኖር ይሆን? እውነት እላችኋለሁ፡፡ በሔዳችሁበት በደረሳችሁበት አደባባይ ሁሉ አንገት ለአንገት የሚተናነቅ፣ ሞቼ እገኛታለሁ እንጂ! ካንተ አላንስም አይነት ፍልሚያ ይጠብቃችኋል፡፡ ዝግጁ ካልሆናችሁ ዛሬም ለሌላ ትግልና ትንቅንቅ ትሰናዱ ዘንድ ሹክ እላችኋለሁ፡፡ ለነገሩ እናንተም ሆነ እኔ የማናውቀው የትግልና የፉክክር መድረክ የቱ ይሆን? አርሴና ማንቼ፣ ኃይሌና ቴርጋት፣ ጥሩነሽና መሰረት፣ ማድሪድና ባርሴሎና፣ ቡናና ጊዮርጊስ ሞሪኖና ቬንገር፣ ታይሰንና ዳግላስ፣ አሜሪካና ቻይና፣ ጃፓንና ኮሪያ፣ እስደራኤልና አረብ፣ ሪፓብሊክና ዴሞክደራት፣ ኢህአዲግና ቅንጅት፣ በአሉ ግርማና ሀዲስ አለማየሁ፣ ፀጋዬ /መድህንና መንግሥቱ ለማ፣ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲና ቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ፣ ቀሲስ እገሌና ቀሲስ እገሌ፣ / እገሌና / እገሌ፣ ዘማሪት እገሊትና ዘማሪት እገሊት፣ እንትን ማኅበርና እንትን ማኅበር፣እንደሀገርም፣ እንደህዝብም፣ እንደማኅበረሰብም፣ እንደተቋምም እንደ ግለሰብም ትውልድ ፍጻሜና መቋጫ በታጣለት እልክ አስጨራሽ ፉክክር ውስጥ ወድቋል፡፡

ለመሆኑ አንተ/አንቺ አንባቢዬ ከቶስ ያልገባችሁበት የውድድር መድረክ የለም ይሆን? የትምህርት ደረጃ፣ የደሞዝ ልክ፣ የአለባበስ ፋሽን፣ የወንድና የሴት ጓደኛ ብዛት፣ የቤተሰብ ክብር፣ የአገልግሎት ብቃት፣ የአነጋገር ዜይቤ፣ የስብከት ብልሀት፣ የአድናቂ ቁጥር እንዴ! እኛ የምንጋፋበት ላለመበላጥ የምንታገልበት ምንስ አለንና፡፡ ህይወት የማታቋርጥ ኡደት ናት እኛ ደግሞ በዙሪያዋ የተኮለኮልን አጫፋሪ ገጸ ባህርያቶቿ፡፡ ሁሌም ስንታገል፣ ሁሌም ከቤላው ተሽሎ ለመገኘት ስንጣጣር፣ አንዳንዴም ሌላውን ጥሎ ለማለፍ ደም እስከማፍሰስ ነፍስ እስከማጥፋት የምንደርስ ነን፡፡ የሚገርመው የፉክክርና ትንቅንቅ መድረኩ ከዓለም አልፎ በአብያተ ክርስቲያናት ማለትም በመንፈሳዊው አለም ውስጥም እጅና እግሩን ዘርግቶ፣ ክቡድ ጥላውን አጥልቶ መገኘቱ ነው፡፡ ያውም በባሰና በላቀ ደረጃ፡፡

የሚገርመው የፉክክሩ ጠባይ ሰው ባለው ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን ሌላው ባለውም ጉዳይ ላይ የተንጠላጠለ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ጠባይ ነው ሌላውን ለመጥላትና ለማጥፋት ተፎካካሪን ጥሎ ለማለፍ ያልተቋረጠ ጥረት እንድናደርግ የሚገፋፋን፡፡ ይህ ክፉ አመል ነው እኛ ስለሌለን ነገር ከመጨነቅ ይልቅ ሌላው ስለበዛለት ጉዳይ ስለምንጨነቅ መንፈሳችን ይታወካል፣ ህሊናችን ይታመማል፣ ሥጋችን ይዝላል፡፡ ስለዚህም ወደ ማይቋረጥ የትግል መድረክ ውስጥ እንገባለን በልጦ ለመገኘት፡፡ ይህ ደግሞ የሌላውን በረከት ቆርሶ እስከመውሰድ ካልሆነም ቆርሶ እስከመጣል የሚደርስ ይሆናል፡፡ እኛ ከቶስ ምን መቆሚያ አለን፣ ለምኞታችን፣ ለፍላጎታችን፣ ለረሀባችንትውልዱ ‹‹Material Mind›› ሆኗል፡፡ የቁስ ረሀባችንን የሚያጠግብ የትኛው ማዕድ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ከምኞትሽ ማን ይመልስሻል›› ያለው እኛንና የእኛን ዘመን ትውልድ ይሆን?

ለነገሩ የቃየል መንፈስ ያልገባበት የትኛው ጻድቅ የእግዚአብሔር ሰው ይሆን? ‹‹በሰው በረከት የማይናደድና ፊቱ የማይጠቁር›› ልክ ቃየል እንደተባለው ‹‹ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች? ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው አንተ ግን በእርስዋ ንገስባት፡፡›› (ዘና. 48) ከዚያ በኋላ የሆነውን ታሪክ ሁሉ የምትዘነጉት አይመስለኝም ቃየል የብስጭቱ በፉክክር የመሸነፍና የመበለጡ ብስጭት የሰው ነፍስ ወደ ማጥፋት እርምጃ እንዲወስደው አደረገው፡፡ ወገኖቼ ላለመበለጥ የሚደረገው ትግል ኃጢያት ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ግን በየትኛው መድረክ፣ በየትኛው ጉዳይ ስለምንስ አላማና ስለምንስ መንስኤ (Motivation)? አሁን ስለክርስተናው ዓለም እያወራን እንደሆነ ልብ ይበሉ፡፡ የክርስትናው ዓለም ደግሞ ወንድምን ዝቅ ብሎ ስለማገልገል ዕንጂ ስለገዢነት፣ ስለበላይነት፣ ከሌላው ልቆ ስለመገኝት የሚወራበት፣ የሚሰብክበት፣ የሚቀመርበትና የሚደመርበት መድረክ አይደለም፡፡ የዓለምን መርህና አስተሳሰብ ደግሞም የአኗኗር ስርዓት Bench Mark ተሞክሮ እየወሰድን እያደረግን የእግዚአብሔርን ቤተ መበጥበጥና የሌላውንም የራሳችንንም ህይወት ማወክ ተገቢ አይደለም፡፡

ዛሬም ሆነ ነገ የሰው ሕይወት ከሌላው ተሽሎ ለመገኘት በሚደረገው የማያቋርጥ ጥረት፡- ላለመበለጥ ማለት ነው፤ አሰልቺ አድካሚና ተስፋ አስቆራጭ ሆና መቀጠሏ አይቀሬ ነው፡፡ በዕርግጥ መበለጥን የሚሻና የሚናፍቅ ማን ይሆን? ከትልቁ ጌታችን በቀር ራሱን ዝቅ አድደርጎ ከተገለጠው ጌታችን በቀር? የትናንሾቹን ደቀመዝሙርት እግር ለማጠብ እጅጌውን ከሰበሰበው ቢቀር? በተራ ሰዎች ተራ አቅም ተበልጦ በመስቀል ላይ ለመንጠልጠል ከፈቀደው የዋህ ሰው ቢቀር? እኮ ከጌታችን በቀር የፉክክርና የትግል አውድ ላይ ያልተገኘ ማን ይሆን?

እኔ ግን ዛሬ አንድ ነገር ላስታወስችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ላለመበለጥ፣ ላለመቀደም የምታደርጉትን ጥረት ባላንኳስስም አላዳንቅ አላበረታታም፣ በርታ ጀግኔም አልልም፡፡ ምናልባት ከአንድ ጉዳይ በቀር ልንገራችሁ ወገኖቼ! ከጌታና ከጌታችን ጉዳይ በቀር በምንም ሆነ በምን ብትበለጡ ምንም እንዳጣችሁ አትቁጠሩ፡፡ ! በጌታ ጉዳይ አትበለጡ፡፡ ለዚህ ነው በዚህስ አትበለጡ ያልኳችሁ የክርስቶስ ሐዋርያና ደቀ መዝሙር ስለዚህ እውነት እንደህ ብሎ ጽፏል፡፡
        
‹‹በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ
 ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ፡፡
የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል እነዚህም የማጠፋውን
አክሊል ሊያገኙ ነው እኛ ግን የማይጠፋውን››
(1 ቆሮ 924)   
በጌታችን ዘለዓለማዊ ሕይወትና የክብር አክሊልስ ጉዳይ አትበለጡ፡፡ ምንብትበለጡ፣ ምን ብትሸነፉ፣ ምን ቢጎድልባችህ፣ ምን ብትከስሩ በጌታ ጉዳይ አትበለጡ፣ በጌታ ጉዳይ አትሸነፉ በጌታ ጉዳይ አትክሰሩ፡፡ እያልኳችሁ ያለሁት ነገር ግልፅ ይመስለኛል ‹‹ምን ብትበለጡ በጌታ ጉዳይ አትበለጡ›› ነው ያልኳችሁ፡፡ ይኔ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰጠን ሕይወት ፍጹም ንቁ እንሁን ማለት ነው፡፡ ቸልተኝነትን እንቋቋም፡፡ ሌላው ነገር ጠቃሚ መስሎ ቢታየንም እንኳን እንደ ጌታችን የሚሆን የለም ሁሉንም ነገር ልናጣ እንችላለን፡፡ ጌታችንን ግን በፍጹም ልናጣው አይገባንም፡፡ ሌሎች ነገሮች በሙሉ ከሕይወታችን ተቆርጠውና ወልቀው ሊቀሩ ይችላሉ፡፡ ጌታ ግን የሕይወታችን አካል ብቻ ሳይሆን ሕይወታችን ነው፡፡ ገንዘብ፣ ስልጣን፣ እውቀት ሊቀር ይችላል ሌላው ቀርቶ መንፈሳዊ አገልግሎት እንኳን ሊገታ ይችላል፡፡ የጌታ ሕይወት ግን ለምንምና ከምንም ተነፃፅሮ የሚለወጥና የሚቀየር አይደለም፡፡ ሁሉን አጥተን ጌታን ካገኘን በስኬት መንገድ ላይነን፤ ሁሉን አግኝተን ጌታን ካጣን ኪሳራ ውስጥ እንዳለን እንወቅ፡፡ ምን ብናጣ ጌታን አንጣ፣ ምን ብንበለጥ በጌታ ጉዳይ አንበለጥ፡፡

3 comments:

  1. Amen!!! Qale Hiwot Yasemalen?

    ReplyDelete
  2. ማህበረ ቅዱሳን ብሎ ራሱን የሰየመ ማስበር ስሙ ቢቀይር
    የተከበራቹ አባቶች /ተዋህዶአውያን /እኛ ቤተክርስትያናቱ ሲታመሱ ዝምብለን ማየት ሰልችቶን የምንይዘው የምንጨብጠው ባጣንበት ግዜ አሁን ስለ ማህበረ ቅዱሳን እኩይ ተግባር ስለተደለጠላቹ እግኢአብሄር ይመስገን፡፡እኔ በኢትዮጱያን አቆጣጠር በ1984-85 ዓ.ም በደብረአባይ የዲቁና ትምህርት ቀማምሸ ወደ አስኩዋላ ገባሁ እየተማርኩ አገልግሎቴን አላቆምኩም ነበር ፡፡መ1996 ዓ.ም በአላማያ ኒበርስቲ/አሁን ሀረማያ/ የመጀመርያ ድግሬ ስማር የሰንበት ትምህርትቤት አዲስ ፕሮቲሰታንት እየሆኑ እንደሆነ በተለያዩ መንገድ ከተገነዘብኩ በሁዋላ በክርታስ ልገልጥላቸው መኮርኩ ነገር ግን አላማቸው ሌላ ነበር እና ሊሰሙኝ ቀርቶ በ1997 ቤተክርስቲኒትዋ የፖለቲካ ማስተማርያ አደረጉዋት እኔም ትቸው እስፖርት ቤት ገብቸ መቆየት ተያያዝኩ፡፡
    "ድሮ ግዜ ጥሩ ነበር አሉ ሰባኪው'እነ ጃንሆይ የተሸሙት በፀሎት በእግዚአብሄር ፈቃድ ነበር አሁን ግን በአፈሙዝ ሆነ ……ሰውን የገደለ ቅባ ቅዱስ አይቀባም ..አሁንማ ወገኖቸ …..አሁንማ በጠመንጃ ነገሱ "አለና ቀጠለ በጠመኘጃ ወገኖቸ ..ቅባ ቅዱስ ሳይቀቡ አረ ሀይማኖትም ሳይከተሉ …ሲል ተነስቸ ወደጥናቴ ሄድኩ፡፡እኔ የማንም ደጋፊ አልነበርኩም ነገር ግን ጃንሆይ/ሀይለስላሴ/ ልጅ እያሱን እና ዘውዲቱን ገድለው መንገሳተውን ታሪክ አስተምሮኛል እንደውም ኢተገ መነን ከመጀመርያ ባላቸው አፋትቶ ወንድማቸው ልጅ እሱ ለመታረቅ ና ሰላም ለመፍጠር እንደነበርና በሀረር ከተማ አስረው እንደገደሉት የማወቃቸው መሪ እንዴት ቅባቅዱስ የተቀቡ ዲያቆን ከሰማይ የወረዱ እየተባለ ስለሳቸው ለዘመናት እንደሚዋሽ አልዋጥ ብሎኝ ነው እንጂ፡፡
    እኔ ስለ መንግስት መቃወማቸውን ሳይሆን ትውፊታችንን እና ስነ-ስርአታችንን ያሬዳዊ ዜማችን ህግጋታችንን ማፋለሳቸው ደሜ ያፈላዋል፡፡
    ስለባህረ ሀሳብ አስተምራለሁ ብሎ አንድ ወጠጤ መጣና በኢትዮጱያ ባህረ ሀሳብ የሚያውቁ ካህናት ከሁለት አይበልጡም አለን፡፡ከዚ ሰአት ጀምሮ ሰንበት ትምህርት ቤቱን ተውኩ፡፡
    አሁንም ደብዳቤ ፅፌ አንዱ አንተ ነህ ሁለተኛውስ ማን ነው ? ብየ በመጀመር ትንሽ ለማተት መኮርኩ፡በሴት እና ወንድ መካከል ያለው ግኑኝነት ስርአት እንዲያጣ ያደረገችው ትውፊታችን የምታፋልሰው በራስዋ ማህበረ ቅዱሳን ብላ የሰየመች ህገወጥ ማህበር እንደዚህ እስክትወነብድ መቆየቱ የሚያሳዝን ቢሆንም አሁን ለጀመራችሁት የደጀሰላም ድረገፅ አበርትታችሁ ትቀጥሉበት ዘንድ እግዚአብሄር ይርዳቹ፡፡
    በጥንታዊ ቤተክርስትያናችን መሰረት በ መዝገብና ቅኔ ሊቃውንት ያልተገመገሙ የመፅሀፍ ቅዱስ ይዘት የሌላቸው ግጥሞች እና ዜሞች ቢታተሙ በርካታ ህዝብ የማሳሳት አቅም ስላላቸው እዚህ ላይም አሳታሚ ድርጅቶች በተዋህዶ ስም ህገ ወጥ ዘፈን አይሉት መዝሙር እንዳያሳትሙ ህገደንብ ቢወጣ፡፡ቢያሳትሙ የሚቀጡበት ቢሆን፡፡እያንዳንዶቹ ዘመነመጣ መዝሙር ተብየዎች ዘፈን ከማዳምጥ የ አያሌው መስፍን እናቴ ናፈቅሽኝ ባህላዊ ዘፈን ባዳምጥ መንፈሳዊ ትርፍ ያለው ይመስለኛል፡፡እነሱም ዘፈን ናቸዋ በስህተት የተዘፈኑ ዘፈኖች፡፡ብቻ ገንዘብ ይገኝበት እንጂ ማንም እየተነሳ ማንጎራጎር ነው፡፡
    ብፁዓን አበው እስከመቸ ዝም ትላላቹ ?ቤተክርስትያናችን ብዙ አርዮሳውያን እያጋጠሙዋት ባሉበት ሰአት በዌብሳይት ብቻም ሳይሆን እንደ ሌሎቹ ሀይማኖቶች በበራሪ ወረቀቶች በመፅሄቶች በሚድያ የመስበኩ ስራ ላይ ይቀረናል ቤተ ክርስትያናት ትልልቅ ህንፃወች ማሰራታቸውን አልቃወምም ግን እንደኔ እምነት አንድ ማተሚያቤት ተቁዋቁሞ በጎቻችሁን የመጠበቅ ስራ ብትሰሩ የተሻለ ይመስለኛል፡፡
    ሌላ ጉዳይ ህዝቡን እያናጉት ያሉ ከዛው ከውስጥ ናቸው እነሱን በአግባቡ ማስተዳደር ይበጃል አሉባልታ ሰይጣናዊ ወሬ የሚስወሩ ካህናት መሰል መናፍቃን በሰአቱ ማሰናበት የምእመናኝ ድምፅ መስማትና መፍትሄ ማበጀት ላይ ጠንክራቹ ትሰሩ ዘንድ እግዚአብሄር ርዳቹ፡፡

    ReplyDelete
  3. ማህበረ ቅዱሳን ብሎ ራሱን የሰየመ ማስበር ስሙ ቢቀይር