Sunday, October 28, 2012

ሲኖዶሱ በስድስተኛ ቀኑ ውሎው

Click here to read in PDF:Sinodos Day 6
  • የአሜሪካው አህጉረ ስብከት ጉዳይ አነጋግሯል
  • የካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር ብጹአን እነ ማን ናቸው? የሚለው መጽሐፍ ሰበር አጀንዳ መሆኑ አስገርሟል፡፡
  • ሊቀ ኤጲስ ቆጶስ ወይስ ሊቀ ጳጳስ?

በሲኖዶሱ የስድስተኛ ቀን ውሎ የአሜሪካው አኅጉረ ስብከት ጉዳይ ተነስቶ ያነጋገረ ሲሆን የአህጉረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ የሊቀ ስዩማን ኃይለጊዮርጊስ መልዕክት በንባብ ተሰምቷል፡፡ አንዲሁም የክህነት እገዳው ጉዳይ ይታይልኝ ያለው የማኅበረ ቅዱሳኑ ኦሪታዊው “ካህን” አቶ መስፍን ደብዳቤም በንባብ ተሰምቷል፡፡ አቡነ ፋኑኤል አለ የተባለውን ነገር ሁሉ በጥሩ ሁኔታ አብራርተዋል፡፡ ከአሜሪካ መነሳታቸው ሁሌም የሚያንገበግባቸው የጉድ ሙዳዩ አቡነ አብርሐም በሰሞኑ የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ የነበራቸው ዝምታ ተሰብሮ ካልመለሳችሁኝ የሚል አይነት ጩኸት ሲያሰሙ ውለዋል፡፡ አቡነ ማቲያስም እኔም እኮ በአሜሪካ ስንት ስራ ሰርቻለሁ አትርሱት እንጂ እዛ የነበርኩ መሆኔን አይነት መልዕክት ሲስተላልፉ አቡነ ማርቆስ ደግሞ አቡነ ማቲያስን ለመገሰጽ ሞክረዋል፡፡ አቡነ ሳሙኤልም አቡነ አብርሃምን ደግፈው ለመናገር ሞክረዋል፡፡ ምነው ቢሉ የሁለቱም ማዘዣ ጣቢያ አንድ ነዋ የሚል ምላሽ ያገኛሉ፡፡

እነ አቡነ አብርሃም አለ ሀገረ ስብከታቸው አያገባቸው ገብተው ሊቀ ስዩማን ኃይለ ጊዮርጊስ ከስልጣኑ ይነሳ ቢሉም አቡነ ፋኑኤል ህግ ይፈቅድልኛል ለስራዬ በበቂ ሁኔታ ያግዘኛል የምለውን ሰው መሾም እችላለሁ ሊቀ ስዩማኑ ስራውን በአግባቡ እየሰራ ስለሆነ አይነሳም በማለታቸው የይነሳ ሀሳቡ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ለተነሱት ጥያቄዎችም ሆነ አስተያየቶች አንደበተ ርቱዑ አቡነ ፋኑኤል በበቂ ሁኔታ መልስ ለመስጠት ችለዋል፡፡
 ለእርቅ የሚሄዱ አባቶች በእዛው ገለልተኛ የሆኑ አብያተ ክርስትያናትን እንዲያነጋግሩ እና ገለልተኛነታቸው የሚያበቃበት መንገድ እንዲፈለግ ታዟል፡፡ የእስክንድር እና የሰለሞን ቶልቻ ጉዳይ እንደገና በመጠኑ ያነጋገረ ሲሆን ውሳኔው አይለወጥም ከቦታቸው ይነሳሉ ተብሏል፡፡ በተስፋዬ ጉዳይ አቡነ ፊሊጶስን አግባብቶ ሀሳባቸውን ያስቀየረው የዘርአያዕቆብ የልጅ ልጅ ልጅ ልጅ ---ልጅ ነኝ የሚለው ህልመ ያርኩ ልጅ ማንያዘዋል የእስክንድር እና የሰለሞን ቶልቻን ጉዳይ ማሳካት ባለመቻሉ አዝኗል፡፡
ሌላው በቀኑ የተነሳው አጀንዳ በአቡነ ገብርኤል እና በአቡነ ገሪማ የቀረበ ሲሆን ሁለቱ ዶክተሮች በሲኖዶሱ ላይ የቀሩት ዶክተሮች እነርሱ መሆናቸውን ላማስታወስ ይመስላል ሊቀ ኤጲስ ቆጶስ እንጂ ሊቀ ጳጳስ ልንባል አይገባንም ስህተት ነው መታረም አለበት ሲሉ ሀሳብ አቀረቡ፡፡ በዚህ ጊዜ ሌሎቹ ጳጳሳት ሀሳቡን እንደ እንግዳ ትምህርት ቆጥረው የተኛም ያንቀላፋውም ሁሉ ስለተረባረበባቸው ጳጳሳቱ ከሊቀ ጳጳስነት ወደ ሊቀ ኤጲስ ቆጶስነት ሊያደርጉት የነበረው የክብር ሽግግር ለጊዜው ተገትቷል፡፡
ሲኖዶሱ በስድስተኛው ቀን ውሎው በከፍተኛ ደረጃ ሲሟገትበት የዋለው  “ብጹአን እነማን ናቸው?” የሚለው የካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር አዲስ መጽሐፍ ላይ ነው፡፡ ተደፈርን ክብራችን ተነክቷል በማለት ሲንገበገቡ የዋሉት አብዛኛዎቹ ብጹአን አባቶች ካህሳን ከስራ ይባረር በማለት ሀሳብ ቢያቀርቡም የካህሳይን ባህሪ እና ቆራጥነት የሚያውቁት አንዳንድ አባቶች ይከሰናል፡፡ አይለቀንም፡፡ በማለታቸው የመባረር ሀሳቡ ቀርቶ ከሚከሰን ጉዳዩ በአስተዳደር ጉባኤ ይታይ እና አስተዳደረ ጉባኤው ይወስን ተብሏል፡፡
በዮሐንስ ወንጌል ም7 ቁ18 ላይ “ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፡፡ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው” የሚለውን የጌታችንን ቃል ያላስተዋሉት አባቶቻችን የላካቸውን ጌታ ክብር ረስተው ለክብራቸው በመሟገት ትዝብት ላይ ወድቀዋል፡፡
ግራ ገብቷቸው ግራ የሚያጋቡት አባቶቻችን የካህሳይ ገብረ እግዚአብሔርን መጽሐፍ በገዛ እጃቸው ገናና አድርገዋታል፡፡ መጽሐፉ የሲኖዶሱ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ ላይ ይመረቃል ተብሎ ከተነገረ እና የምርቃቱ ዕለት ሌላ አዳራሽ እንኳ ለመፈለግ በማይቻልበት ጊዜ ላይ ለ11 ሰዓቱ ምረቃ 6 ሰዓት ላይ አዳራሹ በመከልከሉ ምርቃቱ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፊት ለፊት ሜዳ ላይ መደረጉ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ጭምር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ሜዳ ላይ መመረቁ ውርደቱ ለከልካዮቹ ነው እንጂ ለካህሳይ እማ ክብሩ ነው፡፡ አላደረገውም እንጂ ካህሳይ በሀሰት ወንጅሎዋቸው እንኳ ቢሆን ፍርዱን ለአንባቢው ትተው እንደ ወንጌል አገልጋይነታቸው ነቀፋው የሚጠበቅ መሆኑን ተረድተው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መኖር ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ አለመታደል ሆኖ በጎ እድላቸውን አባከኑት፡፡ ለነገሩ ለወንጌል ካልተነቀፉ እኮ በነቀፋ ደስታ የለም፡፡ አሁን ግን ሳይነቀፉም ስለተመከሩ እና እንደ እግዚአብሔር ቃል እና እንደ ቤተክርስቲያንም ስርዓት ተመላለሱ ስለተባሉ ብቻ አገር ይያዝልን ብለው ከስራ ለማባረር ማሰባቸው እና ማባረሩንም የተዉት ከሰብዓዊ ርህራሄና ከክርስቲያናዊ ባህሪ አንጻር ሳይሆን ክስ ፈርተው መሆኑን ማወቅ ልብን የሚያደማ እና በአባቶቻችንንም ማንነት ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡ ጥፋት አልነበረባቸውም ባንልም ቢያንስ ላለፉት 20 ዓመታት በአብዛኛው በበሬ ወለደ ውሸት ሲከሰሱ እና ሲወቀሱ የኖሩት እና መልካም ስራቸው እንኳ በክፉ እየተተረጎመባቸው ከነበሩት ቅዱስ ፓትርያርኩ ነገሮችን በዝምታ ማለፍን ሊማሩ ይገባቸው ነበር፡፡
የካህሳይ መጽሐፍ አስተውሎ ላየው ሰው በእውነት አንኳን የውግዘት ክርክር ሊያስነሳ ቀርቶ እንዲያው በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ያሉ አባቶች ሊያደርጉት የሚገባውን ስራ ከመጽሐፍ ቅዱስም ከቤተክርስቲያን ህግጋትም አወጣጥቶ በጥሩ ሁኔታ በማስቀመጡ ካሕሳይን ሊያስመሰግነው የሚገባ እና እያንዳንዱ ጳጳስም እንደ መመሪያ ሊጠቀምበት የሚገባ መጽሀፍ ነው፡፡ እነ ወንጌሌ ገንዘቤ ግን ለምን ስህተታችን የሚገልጽ እና እንደ አባትነታችንም ምን ማድረግ እንዳለብን የሚያስረዳ መጽሐፍ ተጻፈ ጳጳስ ከሆንን መስራት ያለብንን ስራ ለምን ሕዝቡ አወቀው ብለው ከስራ ለማባረር መነሳታቸው  ወንጌላቸው ክብራቸው እንጂ የኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ መስቀል አለመሆኑን ያሳያል እና በእጅጉ ያሳፍራል፡፡  
ብጹእ ሰው ለብጽእናው አይከራከርም፡፡ መልካም ሰው ለመልካምነቱ ሙግት አይገጥምም፡፡ ቅዱስ ሰው ለቅድስናው ጥብቅና አይቆምም፡፡ እነ መሸ በከንቱ ግን በ60 ገጽ መጽሐፍ ላይ ሲሟገቱ ውለዋል፡፡ ስንት መንፈሳዊ ጉዳይ ማየት የሚገባው ሲኖዶስ ለክብራቸው ባደሩ ጳጳሳት ምክንያት በጊዜው ቀልዷል፡፡ በዚህም ሲኖዶሱ ከቅዱስ ሲኖዶስነት ወደ የጉድ ሙዳዮች ሸንጎነት በሚደረግ የሽግግር ሂደት ላይ መሆኑን አውጇል፡፡ ወይ አባቶቻችን!!!!!! ባለፉት ሀያ አመታት የችግሮቻችሁም የአስቸጋሪነታችሁም ምንጭ ቅዱስ ፓትርያርኩን ስታደርጉ ኖራችሁዋል፡፡ ዛሬስ ማንን ታደርጉ ይሆን?
የካህሳይን መጽሐፍ ርዕስ እንዋስና ብፁአን እነማን ናቸው? ብለን ብንጠይቅ ከእግዚአብሔር ቃል እንዲህ የሚል ምላሽ እናገኛለን፡፡ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው”፡፡ ወዴት ናችሁ አባቶቻችን?

1 comment: