Thursday, October 25, 2012

የሲኖዶሱ ስብሰባ በሶስተኛ ቀን ውሎው


  • የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለአራት እንዲከፈል ተወስኗል

የዛሬው የሲኖዶስ ስብሰባ የእርቁን ጉዳይ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በተመለከተ ነው፡፡ እርቁን አሁንም አላላቅ ያለ አጀንዳ ሲሆን በማንያዘዋል አማካኝነት ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋር የተነጋገሩት አቃቤ መንበሩ አቡነ ናትናኤል ዛሬም በድጋሚ ሄዶ የመነጋገር ፍላጎቱን ቢያሳዩም ሲኖዶሱ በሲኖዶስ ተወክለው  እርቁን የጀመሩት እነ አቡነ ገሪማ እርቁን ይጨርሱ ሲሉ በድጋሚ ወስኗል፡፡
እርቁን በሚለመከት በተደረገው ውይይት ከሁለተኛው ቀን የከረረ ክርክር በሶስተኛው ቀን የተደረገ ሲሆን አንዳንዶቹ ሀሳቦች በቀጥጣ እርቁ ላይ እንቅፋት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በግልጽ አንስተው የተነጋገሩባቸው ነበሩ፡፡ እርቁ ቢሳካ ለቤተክርስቲያን ሰላም እና አንድነት እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እርቁን ተግባራዊ ለማድረግ ግን ከሁለቱም ወገኖች ሙሉ ፈቃድ እና አላስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ከማቅረብ መታቀብ ወሳኝ ነው፡፡
 በዛ ላይ የተለየ አጀንዳ ያላቸውን ሰዎች እና ፖለቲከኞችን ከእርቁ ሀሳብ በድፍረት ገፍቶ ለማውጣት መወሰን እና የማመለከታቸውን ግለሰቦች እና ቡድኖች ማግለል ያስፈልጋል፡፡ እርቅ የሚከበረደው የልብ ዝግጁነት ሲጠፋ ነው የልብ ዝግጁነት ካለ ቀላል ነገር ነው፡፡ መንግስትን ወደ ሀይማኖት ጉዳይ አትምጣ የሚሉ አባቶቸ እነርሱም ከፖለቲካዊ ሀሳብ እስረኝነት ነጻ ሊወጡ ይገባል፡፡ በእኛ እምነት የኢትዮጵያ መንግስት በእርቁ ላይ እንቅፋት ይሆናል የሚል እምነት የለንም፡፡ ነገር ግን በይፋ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ቡድን ጋር ተደራጅተው ሰልፍ የሚወየጡ እና ፖለቲካን ለእርቅ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያቀርቡ አባቶች መንፈሳዊ ስራቸውን ብቻ እንዲሰሩ ይፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ከወሰኑ ችግር አለ ብለን አናምንም ቀን ቆጥሮ ቂም መዝኖም አባቶችን ያጠቃል አንልም፡፡ ይህን ማድረግ ቢፈልግ አቡነ ገብርኤል ላይ እርምጃ ይወስድ ነበር፡፡ ከእሳቸው የከፋ ፖለቲከኛ ጳጳስም የሚኖር አይመስለንም እንደ እሳቸው መግለጫ የሰጠ ሰልፍ የወጣ እና ለተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት ድጋፍ ያደረገ ጳጳስ አይገኝም፡፡ ወደ ሀገረ ውስጥ ለመምጣት ሲወስኑ ግን መንግስት ምንም አላላቸውም፡፡ ለእርቁ ተገቢውን ዋጋ ለመክፈል ሁለቱም ወገኖች ዝግጁ እንዲሆኑ እንመክራለን፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የተነሳው እና በእጅጉ ያከራከረው ጉዳይ የአዲሰ አበባ ሀገረ ስብከት ጉዳይ ሲሆን በነ አቡነ ሳሙኤል አቡነ ሉቃስ እና አቡነ አብርሃም የቀረበው አጀንዳ ሀገረ ስብከቱ ለአራት ይከፈል የሚል ነበር፡፡ ጉዳዩ ከፍተኛ ክርክርን ያስተናገደ ሲሆን ይከፈል የሚሉ በአንድ ወገን አይከፈልም የሚሉ በሌላ ወገን ከፍተኛ ክርክር አድርገዋል፡፡ በተለይም አቡነ ቄርሎስ እና አቡነ ማርቆስ እንዴት ተደርጎ በሚል እንዳይከፈል እስከ መጨረሻው ተሟግተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የመሆን ተስፋ የነበራቸው አቡነ ህዝቅኤልም ከተቃማዊዎቹ ወገን ነበሩ፡፡
በስተመጨረሻ ግን ጉዳዩ በድምጽ ብልጫ ይወሰን ተብሎ ይከፈል ያሉት ድምጽ ስለበለጠ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ማዕከል ልክ ለአራት ተከፍሏል፡፡ ለአራት እንዲከፈል ያስገደደው ዋነኛ ምክንያት የገቢ ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለልማት የማይውል ቁጥጥር የማይደረግበት ከልካይ የሌለበት ገንዘብ ክምር ላይ መውደቅ የሀሳቡ አንሺዎች ፍላጎት መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ በልቼ ልሙት ባይ ሁሉ በተሰበሰበባት ቤተክርስቲያን የአዲስ አባባን ከፍተኛ ገቢ በአራት ሊቀ ጳጳስ ተቀራምቶ መብላት አስፈላጊነቱ ጎልቶ የወጣ ይመስላል፡፡ በተለይም ይከፈል ባዮቹ ገንዘብና ሌላ ጉዳይ በቀላሉ ማለፍ የማይችሉ የጉድ ሙዳዮች መሆናቸው ሲታይ ጥርጣሬያችንን መስመር ያስይዘዋል፡፡
ከአንድ ቀን መንገድ በላይ የሚራራቁ ከተሞች በአንድ ሊቀ ጳጳስ እየተመሩ ከጥግ እስከ ጥግ ቢጓዙ ቢበዛ ከአንድ ሰዓት በላይ የማትራራቀው ከተማ ላይ አራት ሊቀ ጳጳስ ለማድረግ መወሰን ከምቾች አና ንዋይ ናፍቆት ውጭ ምን ሊሆን ይችላል?
አቡነ ጳውሎስ በሕይወት እያሉ ይህ ጉዳይ ተነስቶ ተቃውሞ አስነስቶ የነበረ መሆኑ ሲታወቅ አሁን እሳቸው ካረፉ ጉዳዩን ለማንሳት እና ለመወሰን መድፈራቸውም አስደምሞኗል፡፡

1 comment:

  1. That is really shame! What is the importance of having four bishops for 130 churches? It looks that the bishops don't want to go outside of Addis. Previously we have been blaming Abune Paulos regarding this issue but this happened once he departed.

    ReplyDelete