Monday, November 26, 2012

የደሴ ተክለ ሃይማኖት ምዕመናን "ተስፋዬ ሞሲሳን ያያችሁ ወዲህ በሉን" እያሉ ናቸው

Read in PDF:Yedese Tekelehaymanote
ምንጭ ፡-http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com
  • የማኅበሩ አባላት ሌሎችን በሚኮንኑበት የንቅዘት ችግር መጠለፋቸው ዝንጀሮ የራሷን መቀመጫ ካለመመልከቷ ጋር የሚነፃፀር ነው
  • ንቅዘት የዘመኑ የቤተክርስቲያናችን ዋነኛ ችግር ሆኗል
  • ከዚህ በታች የቀረበውን ዘገባ የምትጠራጠሩ ካላችሁ ራሱን ተስፋዬንና በዚህ ዘገባ ስማቸው የተጠቀሱትን በተለይ የደሴ የገዳማት አለቆችንና የቤተክህነት ባለሥልጣናትን ጠይቁ፡፡
 የዛሬ ስድስት ወራት ገደማ ግንቦት 12/2004 . ዝቅተኛ ገቢ ባላት የደሴ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን የገቢ ማሰባሰቢያ መንፈሳዊ ጉባዔ ለማካሄድ ከሳምንታት ቀደም ብሎ ዝግጅቱ ቀጥሏል፡፡ አንድ የቤተክርስቲያን ልጅ፣ የተክልዬ ወዳጅ  የጉባዔውን ሙሉ ወጪ ለመሸፈን ቃል ገባ፡፡ ቃል መግባትም ብቻ ሳይሆን ከአዲስ አበባ ሰባክያንንና ዘማርያንን ጋብዙበት ብሎ 20 ሺህ ብር ለገሠ፡፡ የደብሩ የስብከተ ወንጌል ክፍል ሠራተኞችም ብሩ በእጃቸው ይግባ እንጂ የትኛውን ሰባኪ፣ የትኛውን ዘማሪ እንደሚጋብዙ አልተዘጋጁበትም፡፡ የጥቂቶቹን አገልጋዮች ስም የሚያውቁ ቢሆንም እንኳን የስልክና የመኖሪያ አድራሻቸውን አያውቁትም፡፡ ስለዚህ በአዲስ አበባ የሚኖረውን የሀገራቸውን የወንዛቸውን የደሴውን ልጅ በላይ ወርቁን ያገኙትና ለግንቦት 12 መንፈሳዊ ጉባዔ እያዘጋጀን ነው፤ ግን አገልጋዮችን ስለማናውቃቸው በአንተ በኩል ብታፈላልግልን ይሉታል፡፡
በላይ ወርቁም ሰባኪ ሲባል በዓይነ ኅሊናው የመጣለትን የጥቅም ተጋሪው ተስፋዬ ሞሲሳን አስቦ እሺ ችግር የለውም አገናችኋለሁ ይልና ተስፋዬን ያገናኛቸዋል፡፡ ሰዎቹ መቼም በበላይ በኩል የመጣ ያውም በቤተክርስቲያን ጉዳይ ችግር የለውም በማለት ሙሉ እምነት ጥለውበት ተስፋዬ ራሱንና ሌሎቹንም አገልጋዮች ይዞ እንዲመጣ ይነግሩትና ለትራንስፖርትና ልዩ ልዩ ወጪ መሸፈኛ የሚሆን 20 ሺህ ብሩን አስይዘውት ወደ ደሴ ተመለሱ፡፡
ከቀናት በኋላ በደሴ ተክለ ሃይማኖት ደብር የሚካሄደው ዝግጅት ተጠናቆ ጉባዔው የሚጀምርበት ሰዓት ላይ ተደረሰ፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዕለቱ ተስፋዬና ሌሎች አገልጋዮች ይመጣሉ ተብሎ ቢጠበቁ፣ ቢጠበቁ ሳይመጡ ቀሩ፡፡  ተስፋዬን የበላው ጅብ አልጮኽ አለ፡፡ ራሱንም ስልኩንም ሸሽጎ እስከናካቴው ጠፋ፡፡ ወይ እርሱ አልመጣ ካልተመቸው ደግሞ ብሩን አልመለሰ፣ ተስፋዬ አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብሎ ብሩን ይቆረጥመዋል ተብሎ ሳይገመት እንደዋዛ፣ እንደ በረሃ አሸዋ ብሩን አሰረገው፡፡
በዚህ ሁኔታ ግራ የተጋቡ የደሴ ምዕመናንና ካህናት ቢያንስ ብራችን እንኳን ይመለስልን ብለው የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጁ አባ /ሥላሴ፣ የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ፀሐፊ አባ ብርሃነ ሕይወት እውነቱ ዘንድ ቢመላለሱም ጥረታቸው መና ሆኖ ቀረ፡፡
ለነገሩ ተስፋዬ ሞሲሳ ብሩን ድንገት ያሰጠመው ቢመስልም፣ ለእርሱ ግን የመጀመሪያው አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ "ሶመሰ" ባርና ሬስቶራንት 38 ጃምቦ ድራፍት ዱቤና ከአስተናጋጆች የተበደራቸውን ጥቂት ብሮች ባለመመለሱ በአራዳ ክፍለ ከተማ የገዳም ሠፈር ፖሊስ ጣቢያ በወጣ ማዘዣ ሲፈለግ ራሱን ሰውሮ መሰንበቱን የሚያውቁት ያውቁታል፡፡
ተስፋዬን "ቁርዓን ኢየሱስን አያውቀውም - ለዶክተር አህመድ ነጃት የተሰጠ መልስ" በሚል ስብከቱ ወደ ሕዝብ ብቅ ቢልም፣ ሳዲቅ ከተባለ ሌላ የሙስሊም አስተማሪ  ጋር ባደረገው ክርክር ራሱን መግለፅ ሳይችል፣ የተልፈሰፈሰ ምላሽ በመስጠት ጭራሹኑ በማጎብደድ መመለሱን ያስተዋሉ ሰዎች እምነቱን እስከመጠራጠር አድርሷቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ፣ ማንንም ሰው ከአቅምህ በላይ አስብ ማለት ስለማይቻል፣ ተስፋዬ ካለው ከአማኑኤል ቤተክርስቲያን ሰንበት /ቤት መንፈሳዊ ዕውቀት የዘለለ ትምህርት ስላልሸመተ ከዚህ በላይ እንዲያስብ አይጠበቅበትም፡፡ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ለዲፕሎማ መርሀ ግብር ትምህርት አራት ዓመት ቢቆይም ትምህርቱ ዳገት ስለሆነበት ሳያጠናቅቅ መልቀቅ ግዴታ ሆኖበታል፡፡
ተስፋዬ ውሎው "የአራት ኪሎ ግሩፕ" ከሚባሉት ከእነ ዳንኤል ግርማ፣ ጳውሎስ /ሥላሴ፣ በላይ ወርቁ፣ መኮንን (የአዲሱ ሚካኤል // ኃላፊ) ከበደ አራጋው፣ ማንያዘዋልና ዘሪሁን ሙላቱ ጋር ስለሆነ፣ "ማኅበረ ቅዱሳን" የሚሰጠውን የቤት ሥራ ከመወጣት ውጪ ሕግና ሥነ ሥርዓትን ያከብራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋልና የዚሁ ግሩፕ አባል የሆነው "ማኅበረ ቅዱሳኑ" ሮቤል ማቲያስ በተክሊል ተጋብታ ከተለያየች ሌላ ሴት ጋር እንደገና በተክሊል መጋባቱም ተመዝግቦለታል፡፡ ከአቡነ መልከ ፄዴቅ እጅ ዲቁናን የተቀበለው የሀላባው ሮቤል ማቲያስ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተባርሮ ድንቅ "ማኅበረ ቅዱሳን" የአመፃ መሣሪያ በመሆኑም ጭምር ይታወቃል፡፡
እንደ እነ ተስፋዬ ሞሲሳ እና ሮቤል ማቲያስ የመሳሰሉ የሠራዊት አባላት የተሰገሰጉበት "ማኅበረ ቅዱሳን" ሌላውን አገልጋይ ያለ ውሎ አበል አይንቀሳቀስም ብለው እየተሳደቡ ራሳቸው በሺህ ብሮች የሚቆጠር ሀብት እየዘረፉ ቤተክርስቲያንን እያወኩ ናቸው፡፡ ዘሪሁን ሙላቱ ሀዋሳ ላይ ባደረገው ስብከቱ ከማርታ ጋር ስለ አልአዛር ታለቅስ የነበረችው ማርያም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ብሎ ሕዝቡን ውዥንብር ውስጥ መክተቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡  ዝንጀሮ የራሷን መላጣ መቀመጫ ሳታይ በሌላው ትስቃለች እንዲሉ፣ ቤተክርስቲያንን ከጉልላቷ እየነቀነቁ ሌላውን ሙሰኛ፣ ዘረኛ፣ መናፍቅ፣ ተሀድሶ እያሉ ዚፕ በሌለው አፋቸው ይሰድባሉ፤ ያዋርዳሉ፡፡
ባለንበት ዘመን ንቅዘት ዋነኛ የቤተክርስቲያናችን ችግር ሆኗል፡፡ ገንዘብና ነዋይ የብዙ አገልጋዮች መሰናከያ ሆኗል፡፡ ሙዳየ ምፅዋት እዚህም እዚያም ይገለበጣል፡፡ በየቦታው የተጀመሩ ሕንፃዎች ከአሥር ዓመታት በላይ ግንባታቸው እየተጓተተ የግለሰቦች ኪስ ማድለቢያ ሆነዋል፡፡ ኦዲት፣ ቁጥጥር የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡ ምዕመናን የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ግራ ተጋብተዋል፡፡ "ማኅበረ ቅዱሳን" ቡችሎች በስም ብቻ "ቅዱሳን" ልጆች ሆነው በግብር እንደ ዔሊ ልጆች እንደ አፍኒንና እንደ ፊንሐስ ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው መስዋዕት እጃቸው መያዝ የቻለውን ያህል እየቦጨቁ፣ በከበረው ቅዱስ ቁርባን በተክሊል ስም እየሸቀጡ ማመንዘርን ባህላቸው አድርገውታል፡፡
ቅን ወንጌላውያን አገልጋዮች ስለ ስሙ ተሰደዋል፤ በደላቸውን ስቃያቸውን የሚያይላቸው አባት አላገኙም፡፡ አባት የተባለው እርሱም ለመስዋዕቱ ከተዘጋጀው የድርሻውን እየወሰደ ከሰዳቢዎቹ ጋር አብሮ የሚደንስ ሆኗል፡፡ ዛሬ መንፈሳዊ ትምህርት ተምረው ዲግሪና ዲፕሎማው ያላቸው በውጭ ተወርውረው፣ ኢንጂነርና ባዮሎጂ ተምሬአለሁ ባዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤትን ለቅቆ በቤተክህነት ተመሽጓል፡፡ ወደ መቅደሱ ገብቶ፣ እምኩራቡ ላይ ወጥቶ ራሱን በሲኖዶሱ ቦታ አስቀምጦ ያወግዛል፣ ይራገማል፣ አፉ እንደ ተሳለ ሰይፍ ሆኗል፡፡
አቤቱ አባታችን ኃያል ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ
የቤተክርስቲያንህን አንድነትና ዕርቅ ከማይፈልጉ!
እንደ አክዓብ ሕዝብህን ከሚረግሙና ከሚያሳድዱ የእፉኝት ልጆች!
ሕዝብህንና ቤተክርስቲያንህን ጠብቅ!!!
አሜን!!!

1 comment:

  1. Very very good article. God Blesse you Awude mihret. Take them out that worobela maheber in
    our Church please?

    ReplyDelete