Wednesday, November 28, 2012

እናያለን ትላላችሁ እንጂ ዕውሮች ናችሁ!

Read in Pdf: Enayalen
በዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

ዕለታዊ፣ ሰሙናዊ: አልፎ አልፎም ወርሐዊና ዓመታዊ የዜጎች መውጫና መግቢያ የሚይዙ መነጋገሪያ አጀንዳዎችና ርእሰ ጉዳዮች ዛሬ ብቻ ሳይሆን በየትኛው ዘመን ያለ፣ የሚታይና የሚነሳ ነገር ነው። የዛሬ ሁለት ሺሕ ዓመት በእስራኤል ምድር ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ጥቂቶች የማይባሉ ጸጉር ያስነጨና ፊት ያስቧጨረ ወደ አንድ ጉዳይ ላምራችሁ።
"በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤  ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር ፈሪሳውያንም አይተው እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ እርሱ ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን? ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን? ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኰነናችሁም ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።"

"ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ" ይልና ነገር ያልበረደላቸው ፊሪሳውያንም ተከትለውት እንደገቡ ወይንም ደግሞ በሙክራቡ ውስጥም እንደጠበቁት አውስቶ ከቀደመ ስህተታቸውም ትምህርት ወስደውና ተምረው ራሳቸውን ለመልካም ነገር ከማዘጋጀት ይልቅ "እነሆም፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን? ብለው ጠየቁት እርሱ ግን ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥  ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው? እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል አላቸው ከዚያም በኋላ ሰውየውን እጅህን ዘርጋ አለው። ዘረጋትም፥ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች" ይህን ጊዜ "ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት" ይላል (የማቴዎስ ወንጌል 12፣1-14)
ፈሪሳውያን ማለት ደግሞ እነማን ናቸው? የሚል አንባቢ ስለማይታጣ የጽሑፉን ዋና መልዕክት በአግባቡ ከመረዳት አንጻርም ሊፈጠር ስለሚችለው ብዥታ ለማጥራት ያክል በማስቀደም ስለፈሪሳውያን በግርድፉ ጥቂት ልበል። ፈሪሳውያን ማለት ከአይሁድ የሃይማኖት ወገኞች አንዱ ክፍል ሲሆኑ ሰው የሚጸድቀው ሕግን በመጠበቅና በመፈጸም ነው በማለት አጥብቀው የሚያምኑና ወግ ሲያጠብቁ ምሕረት፣ ሕይወትንና ደህንነትን ያመለጣቸው፤ ቢከፈት ከአጥንት በቀር ሌላ የማይገኝበት ካማረና ከተዋበ መቃብር ጋር አመሳስሎ የሚገልጻቸው እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ አነጋገር ግብዞች ሰዎች ነበሩ። በተጨማሪ ፈሪሳውያን ማለት -
Ø ሥራቸው ሁሉ ግራ
Ø መንገዳቸው ሁሉ ሸፍጥ የሞላበት
Ø ለክፋት የማይተኙ ርህራሄ የሌላቸው አመጸኞች
Ø ወግ አጥባዊዎች
Ø የሚበጃቸው፣ የሚረባቸውና የሚሆናቸውን ለይተው የማያውቁ …
Ø ደግ ደጉን ከማሰብና ከማየት ይልቅም ሴረኝነትና ጥመት የሚቀናቸው
Ø ነፍስ ለመጣል የንጹሕ ሰው ደምም ለማፍሰስ ተማምለው የሚወጡ
Ø ከሳሶች
Ø መሰረት የሌለውና ያልበሰለ ነቀፋ ለመሰንዘር፣ መልካሙን ሁሉ ለማብጠልጠል ነፋስ "ሮጦ" የማይቀድማቸው
Ø የተናቁት በእምነታቸው ሲድኑ ከትዕቢታቸው የተነሳ የተኮነኑ ትምክህተኞችም ነበሩ ፈሪሳውያን ማለት።

     እንግዲህ እነዚህ ሰዎች ናቸው ኢየሱስን በዕለተ ሰንበት ለምጻምን ታነጻ ዘንድ: የዕውሩንም ዓይን ታበራ ዘንድ እንዴት ብትደፍር ነው? የለም! የለም!  ጎበዝ እንደው ይህማ "እንገት ቆርጠህ ጸጉርን እንደ ማስተካከል" ነው ሲሉ አምጸው ሕዝብን ሲቀሰቅሱበትና ሲያሳሙጽበት የምናገኛቸው:: በዚህም አልረኩም /አልተመለሱም ነገሩን ሲያስቡት የዚህ “ሰው” (የኢየሱስ) መልካምነት፣ ደግነት፣ ቸርነትና ባለጠግነት እንዲህ ባለ መልኩ የቀጠለ እንደሆነ “ነገ የእኛ ነገር …” ሲሉ ገቢያቸው ክፉኛ ሲያሽቆለቁልና ኪሳቸው ሲራቆት እየታያቸው "በማን ላይ ቆመሽ እግዜርን ታሚያለሽ "በማለትም ይገድሉት ዘንድ ተመካከሩበት:: ለበለጠ ዝርዝር መረጃ ዮሐ. 11፣47- 57 ያንብቡ::
ፈሪሳውያን የሰው ልጅ መዳን፣ መፈወስ፣ ከእስራትና ከበሽታ ነጻ ወጥቶና ተላቆ በነፃነት ንጹሕ አየር ሲተነፍስ በአጠቃላይ የሰው ደስታ ከማየት ይልቅ የሰው ልጅ በስቃይ: የነፍስ እረፍት ከማጣት የተነሳም ሲናጥናበ ኃጢአት ባርነትም ሲማቅቅ፣  ሲጮህ እያዩ ሰንበት ግን በሰንበትነትዋ ተጠብቃና ተከብራከ ማየት በላይ የሚያስደስታቸው ነገር የለም:: ከሰው ልጅ ይልቅ ሳምንታዊው ሰንበት የሳምንቱ ሰባተኛው ቀን በልጦባቸው ለምን ጋኔን ያደረበት ነጻ ወጣ፣ ለምን ዕውር ያያል፣ ለምን የዲዳ ጆሮዎቹ ተከፈቱ፣ ለምንስ ለምጻም ከለምጹ ነጻ? ሲሉ በውናቸው ቀርቶ በህልማቸው ያደርጉት ዘንድ የማይቻላቸው መልካም ሥራ ሲቃወሙና አቧራውን ሲያስጨሱት ከቅድሳት መጻህፍት የምናነበው። ከዚህ የፈሪሳውያን አጉልና ጭንጋፍ እውቀት የተማርኩት ቁም ነገር ቢኖር ግን ሰው እግዚአብሔር ዓይኑን ካልከፈተና ልቡም ካላበራለት በስተቀር ሰው ሲባል እንደው የሚሰራውን የማያውቅ ምስኪን ፍጥረት መሆኑን ነው
አንድ ጊዜ መቃወም ስለጀምሩ ብቻ ሁሉ ጊዜ መቃወም እንዳለባቸው አድርገው ራሳቸው ያሳመኑ ፈሪሳውያን ትልቁ ስህተታቸው ይህ ነበር። ነገሩ እማኮ ሲውል ሲያድር ሕመሙ አድጎባቸው የተጸናወታቸው በሽታ ለራሳቸው ተመልሶ ሲበላቸውና ሲያስቸግራቸው ነገር ሁሉ ተቀላቅሎባቸውም አንዱን ከሌላውን መለየት አቅቶአቸው ሁሉን በአልማሚት ሲቃወሙ የምናገኛቸው። በመጨረሻም ኢየሱስ በእጃቸው የያዙትን፣ ተሸክመውትም የሚዘሩትን መጽሐፍ ቃል ጠቅሶ እናውቃለን ሲሉ ስለሚናገሩት ነገር እንኳን ሳይቀር ይቅር ለሌላ ሊተርፉ ለራሳቸውም  ቢሆን ምንም ዓይነት ግንዛቤ እንደሌላቸውና በባዶ ራሳቸውን የሞሉ በትዕቢት የተወጠሩ አላዋቂዎች ለመሆናቸው "አላነበባችሁምን?”  ሲል ሲጠይቃቸው የሚገቡበት አጥተው ሲሽቆጠቆጡ የምንመለከታቸው። ዛሬም እርማቸው ያልቆረጡ: ዘገምተኞች: የሰው ደስታ ደም ለሚያስቀምጣቸው ደቂቀ ፈሪሳውያን እአምሮ ያላቸው እንደሆነ ከስህተታቸው ታርመው እንዲመለሱ እንቢ ለሚል ደንዳና ልብ ደግሞ ያለ እውቀት ምክርን ለሚያጨልሙ ጨለምተኞች ሁሉ ቃለ-ወልደ እግዚአብሔር የሚሰራ ህያው ቃል ነውና ለፍርድ ዛሬም ሕያው ነው::
(ስለ ጥንቱ ነው) ሰንበትን ማክበር፣ ሰንበትን መጠበቅ፣ መንካበካብ፣ ማወደስ፣ መቀደስና ከዚህም አልፎ ስለ ሰንበት እሪ ማለትና ስለ ሰንበት አለሁ ማለት፣ መቆምና መከራከር ጥሩ ነው! ጥጉ ግን እፍ ብሎ እስትንፋስን የዘራበት የሰው ልጅ መዳን፣ መንጻት፣ ከመንፏቀቅ መረማመድ መቻል፣ ከእስራት መፈታት፣ ከዘወትር ሕጻንነት ወደ ማደግ መምጣት፣ መለወጥ፣ መጠቀም፣ አልፍ ማለትና ዕረፍትን ማግኘት ደግሞ ሰንበትን ከመጠበቅ፣ ከነገር ሁሉም የሚበልጥ ከሁሉም በላይ ምነው። ስለ ሰንበት ተብሎ ደቀ-መዛሙርት የሚራብበት፣ ዳዊት በረሃብ አለንጋ የሚገረፍበት፣ ልጅ እጁ ሰልቦ ለቤተሰቡና ለሀገሩ ሸክም የሚሆንበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም!! ለዚህም ነው ኢየሱስ ፈሪሳውያንን በእውነቱ ነገር እንዲህ ሽንጣችሁን ገትራችሁ በአደባባይ ስትከራከሩ ያዬ ሰው እኮ እውነት ይመስለው ይሆናል እውቀት ያላችሁም ትመስሉትም ይሆናል እውነቱ ግን ሲል - እናያለን ትላላችሁ እንጂ ዕውሮች ናችሁ! በማለት የሚገስጻቸው (የዮሐንስ ወንጌል 9)::

ያልተጻፈ አልጻፍኩም!
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
United States of America

1 comment: