Wednesday, November 7, 2012

ዓይነ መርፌው የጠፋበት ሲኖዶስና ሴራዎቹ

Ayne merfe
በዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
እስራኤል በርካታ እግዚአብሔር የሚያስከፉ ከጠየቃቸው ጥያቄዎች መካከል ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ንጉሥ ስጠን በማለት ያቀረቡት ጥያቄ ተጠቃሽ ነው። ይህን የእስራኤል አሳብና ጥያቄም እግዚአብሔር ክፉኛ እንዳሳዘነና ለጥያቄአቸውም በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ አህያ ፍለጋ የወጣውን የቢንያማዊው የቂስ ልጅ ሳዖል ንጉሥ አድርጎ እንደሰጣቸው በቅድሳት መጻህፍት በስፋት ታትቶ እናገኘዋለን። ንጉሥ ሳኦል በዋናነት የሚታወቀው ምንም እንኳን በእግዚአብሔር ፈቃድ የተሾመ ንጉሥ ቢሆንም እግዚአብሔር በመታዘዝ ባለመጽናቱ እግዚአብሔር የናቀው ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ክፉ መንፈስ ያደረበትና መናፍስት ጥሪ ወደ ሆነች ሴት የሄደም ፍጻሜው ያላማረለት ታሪኩ ባነበብት ቁጥር ልብ  የሚሰብር ንጉሥ ነው። 
በእርግጥ የሲኖዶስ አመሰራረትና አነሳስ በተመለከተ በመጠኑም ቢሆን ከሐዋሪያት ሥራ መጽሐፍ ለመረዳት እንደሚቻለው ዓላማውና ግቡ የእግዚአብሔር ክብር ለመግለጥና እውነት የሆነችውን የጽድቅ መንግሥቱም በምድር ሁሉ  ላይ ለማስፋት እንደሆነ/እንደነበር ለመረዳት አያዳግትም። በሌላ መልኩ ያየነው እንደሆነም የአባቶች መሰባሰብና በህብረት መቀመጥ ጥቅሙ የሚያጠያይቅ አይሆንም።
ወደ ነባራዊው የራሳችን ጉዳይ የተመለስን እንደሆነ በአንፃሩ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ነው የምናገኘው። ሁላችን እንደምናውቀው ሲኖዶስ ተሰበሰበ በተባለ ቁጥር ለመስማት የምንጓጓው ዛሬስ በተራው ማን ይወገር ይሆን?፣ ማን ማንን ይዘልፍና ይዘነጥል ይሆን? የሚል ነው። እውነትም ስብሰባው በተጠናቀቀበት ቅጽበት ከወደ መገናኛ ብዙሐን በኩል የምንሰማውም "ለ … ያህል ቀናት ስብሰባውን ሲያካሂድ የሰነበተው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ስብሰባውን አጠናቀቀ። ስብሰባው በርካታ ትእይንቶች የታየበት ሲሆን አቡነ እገሌ አቡነ እገሌ … ሲሉ መዝለፋቸውን፣ …  የውስጥ አዋቂ ምንጮችቻችን በደረሱን ዘጋባ ለማወቅ ተችለዋል"  ጨምሮ ሌሎች በርካታ የማይሰማ አሳዛኝ ነገር የለም።

የጽሑፉ  ዓላማ አንድም የማይባልበት ግልጽና ቀጥተኛ ነው:: ይኸውም በተለይ ከቀድሞ ቅዱስ ፓትሪያሪክ አባ ጳውሎስ ሞት በኋላ ስራዎቹ መያዣ መጨበጫ የታጣበት ኮከቡ የጠፋበት የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ በተለይ ተተኪው ፓትሪያርክ በማስመልከት ለሚያስተላልፈው ውሳኔ ጉዳዩ ደግመህ ደጋግመህ ማሰብ የሚያስፈልግበት ጉዳይ ሆኖ ሳይሆን ቢሳናቸውም  እንኳ ለሚሰሩት የግብር ይውጣ ስራ ዋጋ እንደሚከፍሉበትና የቤተ እምነቱ ተከታዮችም በቤተ ክርስቲያን አከባቢ ማን ምን እያደረገና እየተደረገ እንዳለ ቀጥተኛ  ማለትም ትርፍ እገኝበታለሁ በሌለበት ከማኛቸውም ፖለቲካዊ መተሻሸት የራቀ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት ተጻፈ::
በጽሑፉ መግቢያ እንደተጠቀሰ ንጉስ ሳዖል የእግዚአብሔር መንፈስ በተለየው ጊዜ  ወደ መናፍስ ጠሪ እንደሄደ ሁሉ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ሲኖዶስም ክፉኛ እያደናገረ ቀጥተኛና ግልጽ የሆነ ሚና እተጫወተ ስለሚገኘው ሰላቢ ድርጅት ማንነት በግርድፉ በማውሳት ሐተታዬን እጀምራለሁ። "ማኅበረ ቅዱሳን"- የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን አስተዳደራዊ መዋቅሮችንና አስራሮችን ጠብቆ ሰነዶች በማጭበርበርና ከፍተኛ የቤተ- ክርስቲያኒቱ ባለ ሥልጣኖችን በማደናገር ለ18 ዓመታት በቤተ ክርስቲያን ስም የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎች በመመልመል ዓቅሙን ያፈረጠመና አሁንም በቤተ ክርስቲያን ስም ከማንኛውም መንግሥታዊ ቀረጦች ነጻ የሆኑ በመላ አገሪቱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የተለያዩ የገቢ ምንጭዎችና የንግድ ማዕከላት በመክፈት ጥላ እየዘረጋ፣ የካዝና ቁልፍ እይሰበረ፣ ንብረትነታቸው የ/ኦ/ተ/ቤ/ያን የሆኑትን ንዋየ ቅድሳትን እየሸጠ ከሚያግበሰብሰው ሀብት በተጨማሪ መንፈሳዊ ካባ ለብሶ ቤተ- ክርስቲያንን በማወክ፣ ምእመናን በማበጣበጥና አገልጋዮችን በማፈናቀል ረገድም ቀዳሚና ተከታይ የሌለው ድርጅት ለመሆኑ የአደባባይ ሚስጢር እየሆነ መጥተዋል።
ይህ ማኅበር ቀደም ሲል እንደሚታወቀው ከጥቂት ... አነፍናፊዎች ግብረ አበረቹ በመሆን መዋቹ ፓትሪያሪክ አባ ጳውሎስ ለማዳከም ከዘረጋቸው ወጥመዶች መካከል የተለያዩ አቅመ ቢስ ሊቃነ ጳጳሳት ድጅ በመጽናት በሽንገላ ቃል "ቀጣይ ፓትሪያሪክ እርስዎ ኖት!” እያለ እንደ እነ አባ ጢሞቴዎስ ቦ ጥሪት ዘአልቦ እውቀት እንዲሁም ሳይገባቸው አንዳችም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓተ ጵጵስና ሲመት መመዘኛ የማያሟሉ ምንም ዓይነት የሥነ መለኮት ትምህርትም ሆነ መረዳት የሌላቸው፣ ሌላው ቢቀር እንደ አንድ ተራ ምእመን እንኳን በዕለተ ሰንበት የሁለትና ሦስት ሰዓት ቅዳሴ ለማስቀደስ የማይተጉ ለልዩ ጥቅም ምልዓተ ጉባኤ ሳያምንባቸው የተሾሙትን እንደ እነ አባ ሳሙኤልና አባ አብርሃም የመሳሰሉትን ከሴት ጭን የማይታጡ የዲቃላዎች አባትና አባዎራዎች እየሰበሰበ ሲኖዶስ ሲያውክና ሲያተረማምስ የመጣውን ዛሬም በተመሳሳይ ግለሰቦች ትክሻ ላይ ወጥቶ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን በታሪክ ጉልህ የሆነ ስህተትና ነውር ትፈጽም ዘንድ ሌት ተቀን ተግቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ከሞላ ጎደል ማኅበሩ ባዘረጋው ወጥመድ ተሰነካክለው በነውር መዝገቡ ውስጥ የሰፈሩ ማኅበሩ "ይህን ያድርጉልኝ፣ ይህን ይሻሩልኝ፣ እገሌን ያውግዝሉኝ፣ እገሌን ይሹምልኝ" በማለት "ማኅበረ ቅድሳን" ከሚያቀርብላቸው ጥያቄ ውጭ ፍንክች የማይሉ ለማኅበሩ ቃል ከመታዘዝ ውጭም ሌላ ምንም ዓይነት አማራጭ የሌላቸው የማኅበሩ የቁም እርስረኞች ብዛት ያላቸው ግለሰቦች በአባልነት የሚገኙበት የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ የዕለት ዕለት እንቅስቃሴውና ስራዎቹ በተጨባጭ መንፈሳዊ ወሳኔዎች ለመሆናቸው በአደባባይ አፍ አውጥተህ ለመናገርና ብዕር መዘህም ለመፃፍ እማይቻልበት አሳፋሪ ደረጃ መደረሱ መደበቅ እስከማይቻልበት ደረጃ ተደርሰዋል።  
በእውነቱ ነገር ምራቃቸው የዋጡና ቀደምቶቹ የዕድሜ ባለጸጋ አባቶች ዓይኖቻቸውን አፍጥጠው ከማየት ውጭ የመናገር ዕድሉ ተነፍጎአቸው ዕድሉ አግኝተው የተናገሩ እንደሆነም ተሰሚነት አጥተው አንገታቸውን ሲደፉና ሲያቀረቅሩ አፍላዎቹ ደግሞ እግዚአብሔር ያያል ማለት ቀርቶ ፈሪሐ እግዚአብሔር ርቆባቸው እንዳሻቸው በማን አለብኝነት ሲወጡና ሲወርዱ፣ ሲፈልጡና ሲቆርጡ፣ የወደዱትንም ሲያደርጉና ሲደነፉ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትም እየተላለፉ እርስ በርሱ የሚጣረስ ውሳኔዎችን ሲያሳልፉና በገዛ ወንድምህ ላይ እጅህን ለማስረዘም ለአመጻ ሽንጣቸውን ገትረው ሲሞግቱ ከመስማትና  ከማየት በላይ የከፋ የልብ ሐዘን የለም።
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጉዞ ሁሉም ነገር መልካም ነበር ማለት አይደለም። በተለያዩ ዘመናት የተነሱ የሃይማኖት መሪዎች ወቅቱ በሚያመጣቸው እክሎች እየተጠላለፉ ከፍተኛ የሆነ ስህተት ሰርተው አልፈዋል እንዳው የአንዳንዶች ስህተትማ ጦሱ ዛሬም ድረስ የአማኞችን ልብ እንደከፈለና ቀጣይነቱ በማያጠራጥር መልኩ አሁንም ጎልቶ የሚታይ ያለም ነው።  ወጣም ወረደ በአሁን ሰዓት በሀገር ቤት የሚገኘውን ሲኖዶስ ራሱን የቅዱሳን ማህበር ሲል በሚጠራ ነፈሰ ገዳይ ድርጅት እየተዘወረ እየሄደበት ያለው መንገድና በግልጽ እየተከተለው የሚገኘውን አሰራር ዕርቅና ሰላም አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን:
·        መንፈሳዊነት ከቤተ ክርስቲያንና ከክርስቲያኖች ህይወት መንግሎ የሚያወጣ:
·        የቤተ-ክርስቲያን ታሪክ የሚያደበዝዝ:
·        ሥነ መለኮታዊ እውነታ የሚያፋልስ:
·        መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የሌለውና:
·        የአበው ፈለግ ያልተከተለ በአንፃሩ ሥጋ ሥጋ የሚሸትና የአውሬ አራት የሚያደርግ ሥራ እየሰራ ለመሆኑ መታወቅ አለበት ለማለት እወዳለሁ። እንዲህ ያለ ዓይኑ ያፈጠጠ መንፈሳዊ ኪሳራ ምንጩ ደግሞ ሌላ ማንም ሳይሆን መጻህፍትንና የእግዚአብሔር ሃይል ካለማወቅ ተከትሎ የሚመጣውን ድንቁር የሚያስከትለው ድፍረትና ንቀት ያሰከረው ራሱን የቅዱሳን ማኅበር ሲል የሚጠራ መራሄ ሲዖል "የማኅበረ ቅዱሳን" ምክር ለመሆኑ አንድና ሁለት የሌለው እውነት ነው
ባለፈው ጽሑፌ ለማስነበብ እንደመኮርኩት የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ማኅበሩ በነደፈለት እቅድ መስረት እየሄደ  ለመሆኑ በሲኖዶስ ስም እየተላለፉ ያሉትን ውሳኔዎች ብቻ በመመልከት ሁኔታዎቹን መገምገምና መረዳት ይቻላል። በተለይ በሦስቱ ጣምራ ጠላቶች፣ ቱባ ቱባ ባለሀብቶችና ነፍሰ ገዳዮች በአባ ሳሙኤል፣ አባ አብርሃምና አባ ሕዝቅኤል የሚመራውን ቡድን ፓትሪያሪክ መርቆሪዎስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ የሚለውን አስተሳሰብ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለውና መደራደርያ አጀንዳ ሆኖ መቅረብም እንደሌለበት በመመጎት ላይ ሲሆኑ ከዚህም አልፈው እጅግ ክት ብለው በመሳቅ "ፓትሪያሪክ መርቆሪዎስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ" የሚለውን አስተሳሰብ ከተረትና ምኞች የዘለለ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም ሲሉ መሳለቃቸውን ጭምር ለማወቅ ተችለዋል(እነዚህ ሦስት የሲኖዶስ አባላት በዋናነት "ማኅበረ ቅዱሳን" ሲኖዶስ ለማበጣበጥና የጋራ  አቋምም እንዳይኖረውና ይዞም እንዳይወጣ ዓላማውን ለማስፈጸም እየተጠቀመባቸው የሚገኙ ግለሰቦች ናቸው)
ይህ "በማኅበረ ቅዱሳን" የበላይ አመራርነትና ቀጭን ትዕዛዝ እየተነዳ “የማኅበረ ቅዱሳን” የጥፋት፣ የልዩነትና የሁከት ተልዕኮ አነግቦ በትጋት እየፈጸመና እያስፈጸመ የሚገኘው ቡድን በሲኖዶስ ስም በነደፈው ዕቅድ መሰረት ቀጣይ ስራው መቀመጫቸው  አሜሪካ ባደረጉ በእርቀ ሰላሙ ጉባኤ ውስጥ ከፈተኛ የሆነ ድርሻ ያላቸው ሃይለ ሥላሴ እንዲሁም አንዱአለም የተባሉ (ነዋሪነታቸው ኦሪገን) ግለሰቦች አስተባባሪነት የሚመጡት  አራት አባላት የሚገኙበት በአቡነ ገሪማ የሚመራውን ቡድን ወደ አሜሪካ በመላክ በተለይ ልዑካኑ ፓትሪያሪክ መርቆሪዎስ ላይ በማተኮር በውጭ የሚገኙትን ሊቃነ ጳጳሳትንና አገልጋዮችን ልብ በመክፈል ድርሻውን ተወጥተው ሲያበቁ ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ ደግሞ አቃቤ መንበሩ ብጹዕ አቡነ ናትናኤል ወደ አሜሪካ በመላክ ቀደምት ልዑካን በጠረጉት መንገድ መሰረት ፓትሪያሪክ መርቆሪዎስ ይዘው ወደ ሀገር ቤት መግባት የሚለውን ነው።
በሲኖዶስ ስም "በማኅበረ ቅዱሳን" አርቃቂነትና አቅራቢት ተግባር ላይ እየዋለ ያለ አጀንዳ መሰረት ለመረዳት እንደተቻለ በዋናነት የዕቅዱ ሰላባ ከሆኑት መካከል አንዱ ማኅበሩ ለዘመናት ጥርሱ የነከሰባቸው ብጹእ አቡነ መልከ ጼዲቅ የሚኝበት ሲሆን እኚህ አባት በተመለከተ የአጀንዳው ግብ ነጥሎ የመምታትና የመለየት ሲሆን የተቀሩት አዳዲስ ተሻሚዎች ደግሞ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ድጋሜ ከስልጣነ ክህነታቸው ተወግዘው እንዲሻሩ የሚል ይገኝበታል
ሌላው ዕርቀ ሰላሙ እውን እንዳይሆን እንደ አንድ ትልቅ ዕንቅፋት ተደርጎ ባልዋለበት ያለ ኃጢአያቱ ዜና እየተሰራበትና የጥላሸት እየተቀባ የሚገኘውን መንግሥት መወንጀል አግባብነት የሌለውና ፈጽሞ ኃላፊነት የጎደለበት ስራ ለመሆኑ በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ። በተጨማሪም እንዲህ ያሉ ዘገባዎችና ሐተታዎች እንዲሁ በስህተት የሚሰሩ ሳይሆኑ ሆነ ተብለው በስሌት የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጉዳይ ለግል የፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያ ለማድረግ በግርግሩም ትርፍ ለማግበስበስ ታልመው እየተሰራጩ የሚገኙ ተራ መሰረተ ቢስ ክሶችና አሉባላዎች ለመሆናቸው በማከል ለመግለጽ እወዳለሁ።
ዕርቁ እውን ላይሆን እና ላይከናውን በእርግጠኝነት እየስራ የሚገኘውን የድርድሩ ፍጻሜ የባሰ ሁከትና መለያየትን መሆኑን ከወዲሁ እያሟረተ ከሚገኘው ማኅበር ከወዲሁ ሌላውን ተጠያቄ ባያደርግ ነበር የሚገርመው። ስለ ሆነም በአንድም በሌላም ዕርቁ በሰላም እንዳይከናወን ሀገር ቤት በሚገኘው ሲኖዶስ የሰለጠነው የኢ.ህ.ዴ.ግ መንግሥት ሳይሆን በክፍፍሉ በዋናነት ተጠቃሚ የሆነውን "ማኅበረ ቅዱሳን" ለመሆኑ በማያሻማ አነጋገርና አገላለጽ ግልጽ ለማድረግ እፈልጋለሁ። በድጋሜ የወሬው ፈጣሪውም ሆነ መለከት ነፊው ስራውን የሚያውቅ የሐሰት ምስክርነት በመስጠት የታወቀና ያስመሰከረ ራሱ "ማኅበረ ቅዱሳን" መሆኑን ለይቶ ማወቁ በራሱ ሰላም ወዳዶች ምእመናን የእግዚአብሔር አገልጋዮች ዕንቅፋትን ለማስወገድና ለመጥረግ በምናደርገው ትጋት አስፈላጊነቱ/ጠቃሚነቱ አያጠያይቅም።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
United States of America

1 comment:

  1. ዲያቆን ሙሉጌታ የምታቀርባቸው ጽሑፎች ቀጥተኛና መድሎ የሌለባቸው ስለሆኑ
    ተመስጋኝ ነህ ቀጥል!

    ReplyDelete