Saturday, August 18, 2012

የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዜና ዕረፍት እና የቤተክህነቱ ሁኔታ

Click here to read in PDF: Abune pawlos3
(ሐሙስ ነሀሴ 12 2004 ዓ.ም. ዐውደ ምሕረት//www.awdemihret.blogspot.com // www.awdemihret.wordpress.com )የቅዱስነታቸው ዜና ዕረፍትየፈጠረው ድንጋጤ እንዳለ ሆኖ በዕረፍታቸው ቤተክርስቲያንዋ የገጠማትን ክፍተት ብጹአን አባቶች በለቅሶና በታላቅ ሀዘን እየገለጹ ይገኛሉ። በትናንትናው ዕለት በመንበረ ፓትርያርክ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የነበረው ስነ ስርዓትም ይህንኑ የሚጠቁም ነበር። በዕለቱ ብጹአን አባቶች ያደረጉት ንግግር የብዙዎችን ልብ የሰበረ እና አብዛኛዎቻችን ከምንሰማው ውጭ የሆነውን የቅዱስ አባታችንን ሰብዕና የገለጸ ሆኗል።  በተለይም ብጹእ አቡነ ማርቆስ ሐዘናቸውን የገለጹበት መንገድ አዳራሹን በለቅሶ እንዲሞላ አድርጎ ነበር።
እንደለመታደል ሆኖ ቅዱስነታቸው ፓትርያርክ በሆኑ ጊዜ የነበሩ ሚዲያዎች ከምንም ተነስተው ከፍተኛ ጥላቻቸውን ደርዝ ያለፉ የሀሰት ዘገባዎችን የሚያወጡበት ጊዜ ስለነበር ህዝቡም በጥላቻው መንፈስ የመወሰድ ሁኔታ እንደነበር ግልጽ ነበር። በየአጋጣሚው የሚከሰቱ አንዳንድ ሁኔታዎችም የቅዱስነታቸውን ስህተቶች እያጎሉ በነጻው ፕሬስ ይካሄድባቸው የነበረውን ዘመቻ ያጠናክሩት የነበረ እንደሆነ ይታወቃል።  በተለይም በ1980ዎቹና በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የቅዱስነታቸውን ስም ሳያነሱ የሚወጡ ጋዜጦችን ማንበብ ብርቅ ነበር። በወቅቱ እንደምናስታውሰው በተገኙበት የንግስ በዓል ሁሉ የሰዉን ልብ እያሸነፉ ሁለተኛ የእሳቸውን ስም በክፉ አልጠራም የሚለውን ህዝብ ቁጥር እየበዛ መጥቶ የነበረ መሆኑ እውነት ነው። በተለይም “…እባካችሁ ልጆቼ የእኔን ኃጢአት አትሸከሙ የእኔ ኃጢአት ለእኔ ተዉት ስለ እኔ ብዙ እያወራችሁ በእኔ ኃጢአት ለምን ትጠየቃላችሁ…” እያሉ ያደርጉት የነበረው ንግግር ሰዉን እውነታቸውን ነው እያስባለ ክፉ ከማውራት እንዲቆጠብ ረድተውት ነበር። 

እንዳለመታደል ሆኑ በሕትመትም ይሁን በኤሎክትሮኒክስ ሚዲያውም እሳቸውን በክፉ የሚያነሱ ሰዎች ቦታ በመያዛቸው አንድም የሰሩትን መልካም ነገር ከማውራት ይልቅ የሆነውንም ያልሆነውንም እያወሩ ቅዱስነታቸውን የማስጠላት ዘመቻ ተካሂዷል። አሁን እንኳ በእረፍታቸው ይሄ አካሔድ አለመቆሙ አሳዛኝ ከስተት ነው። በተለይም የማኅበረ ቅዱሳን ብሎግ የሆነችው ደጀ ሰላም እስከአሁን ደረስ በብጹአን አባቶች ከተደረጉት ንግግሮች አንዱንም መልካም ሰብዕናቸውን የሚያነሳ ነገር ሳትዘግብ ሞተው እንኳ አላሳርፍ በሚል ክፉ ዘገባ ተጠምዳ ትገኛለች። ስለስሳቸውም ሆነ ስለሚወዱዋቸው ሰዎች ጥላቻ አጠንክር ዘገባዋን ገፍታበታለች። ክፉ ያልሁኑ ነገሮችን ሁሉ ክፉ በማለት እና ያልሆነ ነገሮችን ተፈጸሙ በማለት የሰዎችን ስም በከንቱ በማንሳት ላይ ተጠምዳለች።
በሀዘን ላይ የማይነሱ እና የማይመስሉ ነገሮችን በማንሳት በወይዘሮ እጅጋየሁ እና ሌሎች የመንፈስ ልጆቻቸውን እያብጠለጠለች የጥላቻ ድግስዋን በየእለቱ እያቀረበችልን ትገኛለች። ጥላቻቸው ልክ በማጣቱ የሚጽፉትንም አስካለማወቅ ደርሰዋል። “አልሞቱም። አስከሬን ይመርመርኝ።” አሉ ብሎ መዘገብ  ምን ማለት ነው። የአስከሬን ሕያው አለው ወይ? የአስከሬን ምርመራ የሚደረገው ሰው ሲሞት አይደለምን? መልሱን ለደጀ ሰላም እንተወዋለን። በቅን ልብ ትተው ሊታለፉ የሚችሉ ነገሮችን ከቶውንም ያልተፈጠሩ ነገሮችን እያነሱ ሰውን መወንጀል ጥቅሙ ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። እንዲህ ያለው ዘገባ ካልተራገምረን አይንጋልን የሚል የቆየ ጸሎታቸውን የሚያሳኩበት መንገድ እንደሆንም ተገምቷል።
ቤተክርስታኒቱ ሀዘን ላይ ነች ያጣቸው ፓትርያርክ መሾም ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ለረጅም አመት የመሩዋትን አባት ነው።ያጣችው በእድሜዋ አይታው የማታውቀውን አለም አቀፍ ተቀባይነት ያስገኙላትን አባት ነው። ያጣችው መንፈሳዊ ኮሎጆችዋ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያደረጉ አባትን ነው። ያጣችው በቤተክህነት አካባቢ ያሉ ሰዎች ሁሉ እንደሚመስክሩት ከፍተኛ የይቅርታ ልብ ያላቸውን አባት ነው። ዜና ሆኖ ተዘግቦላቸው ባያውቅም በግላቸው በርካታ ድሆችን የሚረዱ አባትን ነው። ያጣችው የሁሉ አባት ነኝ እገሌን ከእገሌ የሚጠሉኝን ከሚወዱኝ ለይቼ ማስተናገድ አልችልም እያሉ ሁሉን በሚቀበል ሰፊ ልብ ያስተዳድሩዋት የነበረ አባትን ነው። ሀዘንዋን በቅጡ እንድትወጣ እድል የማይሰጡ ዘገባዎችን የጥላቻ ፕሮፓጋንዳዎችን ትተን ቢያንስ ነሐሴ 17 በቀኑ ስድስት ላይ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል እስከሚፈጸመው ቀብራቸው ድረስ መቆየቱ ጥሩ ነው።
አባቶቻችን ሙት መውቀስ ድንጋይ መንከስ የሚል አባባል አላቸው። ድንጋይ እየነከሱ ጥርስን ከማሰበር ነገሮችን አሁን እንኳ በማስተዋል መንገድ ብናያቸው ጥሩ ነው። ሰሞኑን በየዕለቱ ሳይሆን በየሰዐቱ ልንጽፍባቸው የምንችላቸውን ብዙ ነገሮች ታዝበናል። በእውነት የብጹአን አባቶችን የዋህነት የእበላ ባዮችን እና አጋጣሚው ለኔ ተመቸኝ ባዮችን ሩጫ ከፍተኛ የአሰራር ዝርክርክነት እና ሌሎችም ነገሮች በግልጽ የሚታዩ ናቸው። ብጹአን አባቶች የዘመኑ ተማርኩ ባይ ትውልድን ተንኮል መቋቋም ምን ያህል እንዳስቸገራቸው እና ሁሉም ካሁኑ በጥቁር ራሱ ከኋላ ሆኖ “ፓትርያርክ” የሚሆንበትን መንገድ እያመቻቸ መሆኑን መታዘቡ ያሳፍራል። ለሚደረስበት ነገር ካሁኑ መንገብገብ ምንድን ነው?ያሰኛል። በቤተክርስቲያኒቱ ይሄ ነው የሚባል ቦታ ሳይኖረው የማንያዘዋል ሁሉ በእጄ ወድቋል በሚል መንፈስ መንቀዠቀዥ ያስደንቃል። በነዚህ ጉዳዮች ጊዜው ሲሆን ብዙ የምንላቸው ነገሮች ይኖራሉ።  
የቅዱስነታቸው ዜና ዕረፍት ከተሰማ በኋላ ቤተክርስቲያን ራስዋን በመንታ መንገድ ላይ አግኝታዋለች። ብጹአን አባቶች ቢያንስ በሚታይ ሁኔታ የወንበሩ ነገር ሳያሳስባቸው የአልፎ ሂያጁ እንደዚህ መንቀዥቀዝ ምንድን ነው? ያሰኛል። ቅዱስነታቸው ሳይቀበሩ ሁሉም የራሱን ፓትርያርክ መርጦ ጨርሷል። ሁሌም በራሱ መንገድ መሄድ የሚመርጠው ማንያዘዋል በሁሉ ነገር እንደ ልጅ የሚታዘዙት አቡነ ሳሙኤል እነዲሆኑለት ከአሁኑ ጠብ እርግፍ ማለት ጀምሯል። በየቀኑ ማታ ማታ ሁለቱም በስብሰባ እየተጠመዱ ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ልቡን ወደ አቡነ ሉቃስ አጋድሏል። በቅድመ ምዘናው መንግስት ሳያስቀይሙ ለማኅበሩ በመታዘዙ በኩል እሳቸው ይሻላሉ የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። ከዛ በፊት ግን የምርጫ ስነ ስርዓቱን ለመቆጣጠር እንዲመቸው በቀብር አስፈጻሚ ኮሜቴ በኩል አድርጎ ከዛም የአቃቤ መንበር ምርጫ ላይ እጁን በማስገባት አቃቤ መንበሩን ለመርዳት በሚልም የፓትርያርክ ምርጫ ላይ ሙሉ ሀላፊነቱን ለመውሰድ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሯሯጠ ይገኛል።
የማኅበሩ አመራሮች አይናቸውን በጨው አጥበው በማይመለከታቸው ጉዳዮች ላይ ሁሉ ከቤተክህነቱ የስራ ኃላፊዎች ጋር ስብሰባ መቀመጥ ጀምረዋል። ከቀብር ስርዓት አስፈጻሚ ኮሚቴ ጀምሮ ሁሉን ነገር ለመቆጣጠር አስበው ተንቀሳቅሰዋል። ማህበሩ ያሰበው ሰው ካልሆነ በቀር ሌላ ሰው ቢሾም አቧራውን በደንብ ለማጨስ እንዲመቸው የትንኮሳ ዘመቻዎችን ካሁኑ ጀምሯል። ስለዚህም ጉዳይ ወደፊት ብዙ የምንለው አለን።
አስከ ቀብር ስነ ስርዓቱ ድረስ በሲኖዶሱ ሰብሳቢነት እንዲቆዩ የተደረጉት አቡነ ፊሊጶስ የነገሩ ክብደት በግልጽ የገባቸው ይመስላሉ። ጭንቀታቸውን በግልጽ ከፊታቸው ላይ ማንበብ ይቻላል። መንፈስ ቅዱስ በፓትርያርኩ ምርጫ ላይ ድርሻ እንዳይኖረው የሚደረገው ስጋዊ እንቅስቃሴ የመንፈሳዊነት ዳርቻ የጠፋባት ቤተክርስቲያን አስመስሏታል። ምዕመናን እግዚአብሔር በሁሉ ነገር ጣልቃ እንዲገባ እና እርሱ ያለው ብቻ በቤተክርስቲያናችን ተፈጻሚ እንዲሆን ጊዜያቸውን ሁሉ ተጠቅመው በጸሎትና በምልጃ ከእግዚአብሔር ጋር ቢሆኑ መልካም ነው።
የቅዱስነታቸው ቀብር በመጪው ሐሙስ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ ይፈጸማል።
ኃዘኑ የመላው ኦርቶዶክሳዊ ሀዘን ነው። ልጅ አባቱን አባቴ የሚለው ከፍቅር እና ከጥላቻ በመለስ ነው። ምንም ይሁን ምን አቡነ ጳውሎስ አባታችን ሆነው 20 ዓመት መርተውናል። ኃዘንን መግለጽ የልጅነት ድርሻችን ነው። ከዛሬው ዕለት ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርክ በተዘጋጀው የክብር መዝገብ ምዕመናን ኃዘናቸውን በጽሁፍ መግለጽ እንደሚችሉ ታውቋል።
ረቡዕ ነሐሴ 16 ቀን አስከሬናቸው ከባልቻ ሆስፒታል ወደ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተወስዶ ጸሎተ ፍትሐት ይደርሳል።
ከጸሎተ ፍትሐቱም በኃላ መንግስት ባዘጋጀም ሰረገላ ወደ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ይወሰዳል።
ሐሙስ በ17 12 2004 ዓ.ም. በብጹአን አባቶች መሪነት ጸሎተ ቅዳሴው ይከናወናል።
ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ላይ የቅዱስነታቸው አስከሬን ወደ ውጭ ይወጣና ይፋዊ ስንብት ይካሄዳል
ከሽኝት ስነ ስርዓቱ ፍጻሜ በኃላ ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሐይማኖት ጎን አስከሬናቸው በክብር እንዲያርፍ ይደረጋል።

3 comments:

  1. እግዚአብሄር ይስጣችሁ ዐውደ ምሕረቶች መልካሙን መናገር የከርስቲን ሰው ደንብ ነው። ማህበረ ቅዱሳን ግን የራሱን ያልሆነው ከስንበት ት/ቤት በአስራት መልክ የሰበሰበውን ገንዘብ ኦዲት አላስደረግም ያለው ነውጠኛ ክፉ ሰይጣን ነው። ነገር ግን የአቡነ ጳውሎስ ገንዘብ ልያሸሹ ነው እያለ ይጮሃል። ተመልከቱ ስግብግብ ቡድን ሰራው የይሁዳ ባህርይ ነው፡፤ ኣበቱ ይሁዳ ስለሆነ እርሱ ደግሞ ልጁ ነው ። ጌታውን አሳልፎ የሰጠው ለገንዘብ ብሎ ነው። ማቅ አደናግሮ የገንዘብ ችግሩን በዚህ አጋጣም ለመዝረፍ ፈልጎ እንደ ተራበ ጅብ ይጮሃል። ክፉ። እያንዳንዱ ሊቀ ጳጳስ ልብ ልሉ ይገባቸዋል።ማቅ ዘሬ ጉቦ እንድደግፉት ገንዘብ ብሰጣቸው ነገ የሰጠውን ብር ከነ ስርአል ቁጥሩ ለጋዘጣ ያቀርባቸዋል። ከፍ ያደረጋቸውን ያህል ይቀብራቸዋል መካር ካለ እነዚህ ጳጳሳት ይምከራቸው።በሌላ በኩል ዘረኝነቱ ስያሳይ ነው። እሳቸው የትግራ ተወላጅ ስለሆኑ በጥላቻ መንፈስ የቀብራቸው ስነ ስርዓቱ ለማበላሽ ብዙ እየሞከረ ነው። ነገር ግን ማቅ እራሳን የአማራ ተጠር አድርጎ ሌሎቹን ብሔረሰቦችን ከእግሩ በታች ለመግዛት ባዶ ህልም እያለመ ይገኛል።

    ReplyDelete
  2. ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የኢትዮጵያ ፓትሪያሊክ ከዚህ አለም በሞት በስጋ በመለየታቸው እጅግ በጣም አዝነናል። ሆኖም ግን እውነተኛ
    የጌታ ሐዋርያ ፣ የሐይማኖታችን አርበኛ፣ በትእግስት የሚገባውን ሩጫ ፈፅሞ ወደ ጌታው በመሄዱ ደግሞ ፍፁም ክርስቲያናዊ ደስታና ሃሴት
    ተሰምቶናል። ሰው የማያውቀውን የድል አክሊል የሚያውቀው አምላኩ እግዚአብሔር እንደሚያቀዳጀውም በምሥሉ ልብ እናምናለን።

    እኛም ክርስቲያኖች ከብፁእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፤ ፈተናንና መከራን በትእግስት ማሳለፍን ተምረናል። እግዚአብሔር አምላካችን ከቅዱስነታቸው ረድኤትና በረከት ያካፍለን እንላለን፣ አሜን፣ አሜን፣ አሜን።

    ReplyDelete
  3. ደጀ ብርሃን እግዚአብሔር የእያንዳንዳችን ልብና ኩላሊት የሚመረምር ታላቅ አምላክ ስላለን፡ የማንም ደንቆሮ እየተነሳ በሐጢያት በገማ
    አፉ እናንተንም ሆነ ቅዱስነታቸውን እንዲሁም ሌሎችን እውነተኛ ክርስቲያኖችን ያዋረደና የተሳደበ ቢመስለው አትደነቁ። ምክንያቱም
    ማቅና ጀሌዎቹ እንደሆነ የዲያቢሎስ እስረኞች ናቸው። ክርስቶስ ከቤሊያር ጋር ምን ግንኙነት አለው \ ልትጠፋ ያለች ከተማ ፣ ነጋሪት
    ቢጎሰም አትሰማ አይደል የሚባለው። ሚሊዮን የማቅ ጡንቻ ራስ ሁሉ ተጨፍልቆ ቢሠራ እንኩአን አንድ የቅዱስነታቸውን ጭንቅላት ወይም ክርስትና ህይወት ሊሆን አይችልም። ማቅ በብፁእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ለእኩይ አላማው የተመቼው መስሎት
    ለጊዜው ጮቤ ቢረግጥም፣ እግዚእብሔር ግን ከላይ እንዳልኩአችሁ ሁሉን አዋቂ ስለሆነ አይሳሳትም። ማቅ ግን ምን አይምሮ አለውና ፣ ምንስ ያውቃልና ዝም ብሎ ይዝለል ተውት፣ እንደ ይሁዳ ጌታውን በ30 ብር ሸጦ ለጊዜው እንደዘለለው፤ በሁአላ ግን ንፁህ ሰው አሳልፎ መስጠቱ ሲታወቀው፤አለቃው ዲያቢሎስ ራሱን አንቆ እንዲገድል አድርጎታል። አሁንም ማቅ ሐይማኖት የለሽና የቤተክርስቲያናችን ካንሰር ስለሆነ
    ተውት ይፈራገጥ መጨረሻው የታወቀ ነው። ከኛ የሚጠበቀው መምህራችን ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን መሆን ነው\ እንደቅዱስነታቸው\ ማቅ ደግሞ ያው ጠላት እንዳስተማረው ካዋጣው ይቀጥል። ፈራጁና እውነተኛ ዳኛ ግን ጌታችን ነውና በዚህ እንታመናለን። አሜን።

    በተረፈ ግን ቅዱስነታቸው በጣም በጣም እግዚአብሔር የሚወዳቸው ታላቅ ሐዋርያ በመሆናቸው ለጠላት ንክሻና ለውርጋጡ ማቅ መሳለቂያ
    ሳያደርጋቸው እግዚአብሔር አባታችንን እንኩአን ነፍሳቸውን ወደ እርሱ ወሰዳቸው እንላለን። ነገር ግን ለእኛ ለልጆቻቸውና ለወዳጅ ዘመድ
    በፓትሪያሊካችን በአቡነ ጳውሎስ በስጋ መለየት የተሰማንን ሐዘን ለመግለፅ እንወዳለን። በመጨረሻም በአገራችን አባባል እንደሚባለው
    ሰው ካልሞተ ወይም ካልሄደ አይመሰገንም እንደሚባለው ቅዱስነታቸውን እኛ ባናመሰግናቸውም በመልካም ሥራቸው ዓለም ሲያስመሰግናቸው
    ይኖራል፣ ታሪክም አይረሳቸውም። ጌታ እግዚአብሔር ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ሰውን በመልካም ሥራው ማመስገንን ያስተምረን። ሁልጊዜ
    መርገምንና ስለ ሰው ክፉውን ብቻ ማውራቱን ደግሞ ከኛ ያስወግድልን። ወስበሐት ለእግዚአብሔር አሜን ።


    ReplyDelete