Thursday, August 9, 2012

የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሕመምና ዙሪያ ገብ ሙግቶቹ

P M meles:click here to read in PDF
(ነሐሴ 3 2004 .. ዐውደ ምሕረት / www.awdemihret.blogspot.com/ www.awdemihret.wordpress.com) የጠቅላይ ሚኒስቴሩ  ህመም  ከአንድ ወር በላይ ከፍተኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ሰንብቷል፡፡  የሰሞኑ ወሬ ዕረፍት ላይ ናቸው ከሚለው ጥግ ተነስቶ ሞተዋል እስከሚለው ጥግ የዘለለ ነው፡፡ በብሎጎች እና በዌብ ሳይቶች ከሚተላለፉት አሉ ሞተዋል ወሬ በተጨማሪ በፌስ ቡክ የሚደረጉ ክርክሮችም የሰዉን ልብ ልክ እና የአስተሳሰብ ደረጃ ግምት ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው፡፡

በተደጋጋሚ እንዳስተዋልነው የዲያስፖራው እና የሀገር ቤቱ ነዋሪ ህዝብ አስተሳሰብ ምን ያህል እንደተራራቀ የሚያሳይ ክስተትም ሆኗል፡፡ የሀገር ቤቱ ህዝብ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ቢወድም ባይወድም በአብዛኛው የጠቅላይ ሚኒስቴሩን በዚህ ሁኔታ መሞት አይፈልግም፡፡ ዳያስፖራው ደግሞ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ከሚቃወመው ክፍል ዛሬውኑ ሞተው ቢያድሩ ደስታው ነው፡፡ ፌስ ቡክ ላይ ያለው ክርክር በግልጽ የሚያሳየን ይሄንን ነው፡፡ በፌስ ቡክ የግለሰብ ገጾችም ሆነ ቡድኖች ላይ ዲያስፖራው በአዶቤ የተቀባባ የሞተዋል ምስል ሲያሳየን የአገር ውስጡ ደግሞ ከኢንተርኔት ውስጥ የቆየ ፎቶግራፍ ፈልጎ ከአይሮፕላን ሲወርዱ ያሳየናል፡፡

እንደ ኢሳት ያለ ኃላፊነት የማይሰማው እና ከሟርት የዘለለ ዜና እና ከመቃወም ያለፈ ፖለቲካ የማያውቅ የዜና ድርጅትም ተአማኒነት ለማግኘት ሲል በውሸት ኃላፊነት የሚሰማውን ድርጅት ጠቅሶ ኃላፊነት የሌለው ዜና ያሰማናል፡፡ ሁልጊዜም የሚደንቀን ነገር በአውሮፓና በአሜሪካ ያሉ የዲሞክራሲ ተሟጋች ነን የሚሉ ዌብ ሳይቶች፣ ሬድዮ እና ቴልቪዝን ጣቢያዎች ጉዳይ ነው፡፡ ለእነርሱ ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግስት ፀረ ዲሞክራት መሆኑን መንገር ነው፡፡ በአንጻሩ ግን እነርሱም አስተሳሰባቸውን የሚቃወም ጽሁፍ እና አስተያየት በሬዲዮ ጣቢያቸውም ሆነ በድረ ገጾቻቸው እንዳይስተናገድ በማድረግ ዲሞክራሲን እያፈኑ መሆኑን አይገነዘቡም፡፡ ኢቲቪን በውሸታምነት እና በገዢው ፖርቲ አገልጋይነት እየኮነኑ እነርሱ ግን ከኢቲቪ የባሰ ውሸት ሲያወሩና ለግል የፖለቲካ አስተሳሰባቸው ባሪያዎች ሆነው ኃላፊነት የጎደለው ዜናና ሪፖርት ማቅረባቸውን እንደ ስህተት አይቆጥሩትም፡፡ የሚተችና የሚወቅሳቸውንም ባላቸው ኃይል ሁሉ ያሳድዳሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ህመም እንደዜጋ ያሳስበናል፡፡ ከድጋፍና ከተቃውሞ በመለስም እግዚአብሔር አምላክ ፍጹም ፈውስን እንዲሰጣቸው እንጸልያለን፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ የሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ረሀብ ባለባት ሀገር የጠቅላሚኒስቴሩ ሞት ችግሮችን ቢያብስ እንጂ መፍትሔ እንደማይሆን ከልብ እናምናለን፡፡ ህዝባችን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ወደ ከፋ የሰቆቃ ህይወት እንዲገባ አንፈልግም፡፡ ስለ ዲሞክራሲ እንሟገታለን የሚሉ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ከስሜት በዘለለ መንገድ ነገሩን እንዲያዩት እንመክራለን፡፡ የመሪ ሞት እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሰላምዋ በቀላሉ ሊደፈርስ በሚችል ሀገር ቀርቶ እንደ አሜሪካም ባለ ሰው ሳይሆን የአስተዳደር ስርዓቱ ሀገር በሚመራበትም ሀገርም ቢሆን ጭንቅ ነው፡፡
የዲሞክራሲ ልምምዳቸው እና ታሪካቸው እዚህ ግባ የማይባሉ በርካታ አገሮች የመሪዎቻቸው ሞት ችግርን ሲያባብስ እንጂ ሲቀንስ አላየንም፡፡ በብዙ ሀገሮችም እልልታው ወደ ዋይታ ድግሱ ወደ ተዝካር በፍጥነት የተቀየረበትን ሁኔታ አስተውለናል፡፡  እንደ ኢትዮጵያ ላላ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ላሉዋት ሀገር የሃይል ሚዛኑ የተሸራረፈበት ግጭት የሚያስከትለው ጦስ ቀላል አይደለም፡፡
አሜሪካ ውስጥ የሰላም አየር እየተነፈሱ ኢትዮጵያ ውስጥ አቧራው እንዲጨስ መናፈቅ የጤነኛ አስተሳሰብ ውጤት አይደለም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ አቧራው ቢጨስ የሚታፈኑ ወገኖች እንዳሉን ማሰብ ጥሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን የሚወዳቸውም የሚጠላቸውም የኅብረተሰብ ክፍል ሆነ እሳቸውን ከስልጣን ለማውረድ ከነዘርፈ ብዙ ችግሮቹም ቢሆን ሰላማዊ ትግልን የመረጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል ደንግጠዋል፡፡ አዝነዋል፡፡ አብዛኛው ሰውም ሞታቸውን አይመኝም፡፡ ሞታቸውን የማይመኝ የህብረተሰብ ክፍል ሁሉ ግን የሚወዳቸው ነው ማለት አይደለም፡፡ በሰው ሁሉ ልብ ውስጥ አንዳንድ ጊዜ የሚገለጡ ፍቅርና ጥላቻን ተሻግረው የሚሄዱ ስሜቶች አሉ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካው እያደገ ወደ አንደኛ ደረጃ ክፍል ደርሷል፡፡ በዲሚክራሲ ባህር ውስጥ እየዋኘ ባለው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ጭንቅላት ውስጥ ግን ፖለቲካ ገና ሕጻናት መዋያ ውስጥ ናት፡፡ ይሔ መገለጫ የገዢው ፓርቲ ደጋፊውንም ተቃዋሚውንም ያጠቃልላል፡፡ ለሀገራችን ትልቅ ውድቀት የሚሆነው የዲያስፖራው ፖለቲከኛ አሁን ካለው አስተሳሰቡ ጋር ስልጣን ላይ የወጣ እንደሆነ ነው፡፡ ዲሞክራሲን ጥላቻ ዲሞክራሲን ዘረኝነት ዲሞክረሲን እኔ ብቻ በሚል አስተሳሰብ የተረጎሙ የገዢው ፓርቲ ደጋፊም ይሁን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በፈቃዳቸው ከገቡበት የኅጻናት መዋያ ፖለቲካ ነጻ የሚወጡበትን ቀን እንናፍቃለን፡፡
ድምጻችን ታፍኖ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብታችን ተነፍጎ ነው ከሀገር የወጣነው የሚሉ ጋዜጠኞችም እነርሱም በተራቸው ሳያፍሩ ሳይፈሩና ሳይሰቀቁ ከእነሱ በተቃራኒ የሆነ አስተሳሰብ በራዲዮ ጣቢያቸው እና በድረ ገጻቸው እንዳይወጣ ሲያፍኑ ተሰደድንለት የሚሉትን የሰውን መብት እየተጋፉ መሆኑን አያስተውሉም፡፡
በአሜሪካ ያለ መንፈሳዊነት ስሩ እግዚዘብሔርን ማምለክ መሆኑ እየቀረ መጥቷል፡፡ አሜሪካ ውስጥ መንፈሳዊያን ሰዎች ሳይቀሩ እግዚአብሔርን የሚፈልጉት የፖለቲካ ሀሳባቸውን እንዲያስፈጽምላቸው መሆኑን መታዘቡ ያሳዝነናል፡፡ ይህንን እውነት ለመረዳት በቤተክርስቲያን የእግዚብሔርን ሀሳብ እንጂ የፖለቲከኞችን ሀሳብ አናስተናግድም የሚሉ አባቶች የሚደርስባቸውን እንግልት መታዘብ በቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ገዢው ፖርቲ እያስገደደን እንዲህ እና እንዲያ እናደርግ ነበር ትሉን የነበራችሁት የፖለቲካ ሰዎች እና የሀይማኖት መሪዎች ያንኑ ሀሳብ በግልባጩ ማስተናገድ መጀመራችሁ በማን ተጽእኖ እንደሆነ ሊገባን አልቻለም፡፡ ከእናንተ የምንፈልገው ኢትዮጵያ ውስጥ መጥታችሁ ስልጣን ብትይዙ በምን አይነት ዲሞክራሲያዊ ሕይወት እንደምታኖሩን በትንሹ እድላችሁ እንድታሳዩን ነው፡፡ በትንሹ ማኅበረሰባችሁ በትንሽዋ የሬዲዩ ጣቢያችሁ በትንሽዋ ድረ ገጻችሁ በትንሽዋ አጋጣሚያችሁ አሳዩን፡፡ ያኔ እናንተ ሳትጠይቁ እኛው ለትልቅ ስልጣን ተስፋ እንጥልባችኋለን፡፡ በርግጥ አቅማችን ከተስፋ ላይዘል ይችል ይሆናል፡፡ ተስፋ መደረግ መቻልም ግን ትልቅ እድል ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ሞት መመኘት ከኢትዮጵያዊ ስነ ምግባር አንጻር ቢታይ ተገቢ አይደለም፡፡ በሀገራችን “አልጋ በያዘው ላይ በትር አትምዘዝ” የሚባል አባባል አለ፡፡ አልጋ የሁሉም እጣ ነው ተብሎ ስለሚታመን ቀላሉን ያርግለት ነው የሚባለው፡፡ አገር ለሚመራ ሰው ደግሞ ቀላሉን መመኘት ጥቅሙ ለራስ ነው፡፡ አለመረጋጋት የሚያስከፍለው ዋጋ ተመኑ አይታወቅም ይልቁንም የሚታይ ጉልህ ተተኪ በሌለበት ሃገር ጎልተው የሚታዩ ችግሮች አይከሰቱም ማለት አይቻልም፡፡ ይሙት ይሙት ያልንም ስልጣን እንይዛለን ማለት አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ አለ የምንለውም ስቃይ ለማብቃቱ ዋስትና አይደለም፡፡
ዲያስፖራው ተስፋ ሆኖም ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ ያመጣል ተብሎም ቢያንስ በሀገር ውስጥ አይታሰብም፡፡ ሀገር ቤት ያለው ዘረኝነት አስመረረኝ ብለው አገር ጥለው የወጡ ሰዎች ከተወሰነ ጊዜ በኃላ የላቀ ዘረኛ ሆነው ነው ያገኘናቸው፡፡ እውነት ለመናገር ኢትዮጵያዊው ዳያስፖራ ላይ የሚታየው የዘረኝነት መንፈስ 10 በመቶው እንኳ ሀገር ቤት የለም፡፡ ሀገር ቤት ከፖለቲከኛው ውጭ ዘሩ የሚጨንቀው ብዙ ህዝብ የለም፡፡ የጎረቤቱን ዘር አጣርቶ ቤት የሚገዛም ሰው ፈጽሞ የለም፡፡ በየቀኑ ዘሩ ምን እንደሆነ የሚያስታውሰው ምግብ ቤት ካፌ ወይም ደግሞ ቤተክርስቲያን የለውም፡፡ ዲያስፖራው ያለበትን ሁኔታ ግን ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡  
ማኅበረ ቅዱሳን በአንድ አድርገን ብሎጉ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የታመሙት ዋልድባን ስለነኩ ነው ሊለን ሞክሯል፡፡ በደጀ ሰላምም በግልባጩ ይሔን ነግሮናል፡፡ በግንባር የምናውቃቸው የማኅበሩ የቅርብ ሰዎችም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የታመሙት ማኅበረ ቅዱሳንን ስለነቀፉ ነው እያሉን ነው፡፡ ወሀቢያዎችም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የታመመሙት በሙስሊሙ ጉዳይ ስለገቡ ነው ይሉናል፡፡ በኛ ጸሎት ታመሙ የሚሉት የማኅበረ ቅዱሳን እና ወሀቢያ በሁሉ ነገር መመሳሰል ያስደንቃል!! ሁሉም ስሜቱን የጸሎት መልስ ማድረጉ ይገርማል፡፡  
በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ዙሪያ የሚነሱ ሙግቶች መኖራቸው መጥፎ አይደለም፡፡ ጥያቄው የሚሆነው ለሙግቱ የምናነሳቸው ነጥቦች ይዘት ላይ ነው፡፡ ሰው ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን እንከን የለሽ ናቸው ብሎ እንዲያምን አንፈልግም፡፡ ከእንከን የነጻ ሰው የለምና፡፡ ስራቸው እና አስተሳሰባቸው ችግር ያለበት ነው ብለን የምናምን ከሆነ የተሻለ ሥራ ለመስራት እድል ባናገኝ እንኳ በተሻለ አስተሳሰብ ግን እሳቸውን ለመቃመም መሞከርን ግን የሚከለክለን ነገር የለም፡፡ ቢያንስ የውጮቹን ሰዎች የሚከለክላችሁ ነገር የለም፡፡ በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ የምናነሳው ሀሳብ ግን ግምት ውስጥ እንደሚከተን ማስተዋል ይገባል፡፡ ይልቁንም መንፈሳዊያን ሰዎች ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ በሰው ብቻ ሳይሆን ሁሉን በሚችል የሰማይ አምላክ ሚዛን ተሰፍሮ መቅለል ይኖራልና ማስተዋሉ ተገቢ ነው፡፡
ስልጣን ርስት ስላይደለ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ስልጣን በሌላ ሰው መተካት እንዳለበት እናምናለን፡፡ ይህ ግን በሞት ሳይሆን በሕይወት እያሉ ቢሆን ለሀገር መረጋጋት ጠቃሚ ነው፡፡ ለእሳቸውም ቢሆን እግዚአብሔር አምላክ ለንስሐ የሚሆንን ጊዜ እንዲሠጣቸው እንጸልያለን፡፡ ከዕድሜው ሶስት አራተኛውን በፖለቲካ ውስጥ ላሳለፈ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ከልብ ሊያወራቸው የሚገቡ ብዙ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ ያ ሰው ቢሰማውም ባይሰማውም ያን እድሜ እንዲያገኝ መጸለይ ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው፡፡ ሁሉ እንዲድኑ እንጂ አንዳች እንኳ እንዲጠፋ የማይወድ እግዚአብሔርን የሚያስድተውም እውነት ይህ ነው፡፡

5 comments:

  1. Thanks Lord God. Amen

    ReplyDelete
  2. Awde-Mhret!
    You are real "Awed-Mhret"!
    Your analysis of the Diaspora's thinking is correct. Both the "pro and anti" government
    blindly support/oppose the government. This is not healthy at all. How nice it would if the
    Diaspora can just reflect the Reality.

    About prime minister meles' health- Well, we should pray for him to recover form his illness; that is all what we can do for him, now!

    Again, I love Awde-Mhret's posts, please keep it up. Thank you so much for providing correct current events!

    ReplyDelete
  3. It seems better than any of your previous posts. I pray for the peace of the country and peaceful transfer of power. I pray for Meles so that he will get Mercy from God before he get departed.

    ReplyDelete
  4. I Love Awdw Mihret posts all the time. God Bless you many many years.
    This is the true Christiyanity way of people. Go for it teach them who
    plays game with Christiyanity like mk. woro bela mahber.

    Tebareku
    Adnakiyachu

    ReplyDelete