Thursday, August 23, 2012

የቅዱስነታቸው ቀብር በደማቅ ሁኔታ ተፈጸመ


በ76 ዓመታቸው ያረፉት የብጹዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የአለም የአብያተክርስትያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፤ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ፤ የዓለም ሰላም አምባሳደር ስርዓተ ቀብር ዛሬ ነሐሴ 17 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡30 ላይ በደማቅ ሁኔታ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

የቅዱስነታቸው ስርዓተ ቀብር ላይ ቁጥሩ እጅግ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ የተገኘ ሲሆን ጊዚያዊ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የእህት አብያተ ክርስቲያናት አባቶች የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ ፤ የህዝብ ተወካች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አባ ዱላ ገመዳ ፤ ምክትል አፈጉባዬ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ፤ አምባሳደሮች፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበትና በአክሱም ካሕናት እምቢልታ የታጀበ የቀብር ስነ ስርዓት ተደርጎላቸዋል። 

አቡነ ገሪማ የህይወት ታሪካቸውን ያነበቡ ሲሆን የእህት አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች እና የመንግስት ባለስልጣናትም ንግግር አድርገዋል። ሥነ ስርዓቱ በፖሊስ ማርሽና የሰንበት ተማሪዎችም ዝማሬ የታጀበ ነበረ።
በትናንትና ዕለት የጀመረው እጅግ ደማቅ የነበረው ስነስርዓትም በዛሬው ዕለት ፍጻሜውን አግኝቷል። ትናንትና ከቅዳሴ በኋላ የቅዱስነታቸው አስከሬን በሰረገላ ሆኖ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል በርካታ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት የእህት አባተ ክርስታናት ተወካዮች፤ የመንግስት ባለስልጣናት ፤ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ፤ በሊቃውንተ ቤተክርስትያን በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ፤ በአዲስ አበባ ፖሊስ ሰራዊት ባንድ ፤ በምዕመናንና በምዕመናት በክብር ታጅቦ በደመቀ ስነስርዓት የተካሄደውን የሽኝት ስነስርዓት ተመልካችን እጅግ አስደሳች ነበረ።
ከምሽቱ 2፡00 ጀምሮ እስከ ንጋቱ ድረስ ለሊቱን በሙሉ ጸሎተ ማህሌት ሲከናወን አድሯል ። ንጋት 12፡30 ላይ አስከሬኑ ባለፈበት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል በብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና አኅት አብያተክርስትያን ተወካዮች ባሉበት ስርዓተ ቅዳሴው ተከናውኗል ፤ ጸሎቱ እንዳበቀ የቅዱስነታቸው አስከሬን በክብር ታጅቦ ወደ አውደ ምህረት ወጥቷል በተዘጋጀለት ቦታ ላይ ለሰዓታት አርፏል፡፡
ይህን ተከትሎም ስነስርዓቱ የጀመረ ሲሆን የደመቀ የሚለው ቃል ሊገልጸው ከሚችለው በላይ ባማረ ሁኔታ የቀብሩ ስነስርዓት ተፈጽሟል።

1 comment:

  1. WONGEL FROM DALLAS, TEXASAugust 24, 2012 at 2:38 AM

    we miss you our pope paul. We remeber you for ever .

    ReplyDelete