Wednesday, August 22, 2012

ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስና ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ምን እንማራለን?


ምንጭ፡- አባ ሰላማ

በዚያን ጊዜም ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች አወሩለት።
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን?
እላችኋለሁ፥ አይደለም፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ።
ወይስ በሰሌሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፥ እላችኋለሁ፤
ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።
(ሉቃ. 13፥1-5)
2004 ዓ.ም. አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ታላላቅ ሰዎችን በሞት የተነጠቀችበት ዓመት ነው፡፡ የቤተክርስቲያናችንና የአገራችን መሪዎች ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዲህ በአንድነት በሞት የተጠሩበት አጋጣሚም ያለ አይመስለንም፡፡ የመሪዎቻችን በአንድ ሰሞን በሞት መጠራትና የነገሮቹ ግጥምጥሞሾች በኢትዮጵያውያን ላይ ልዩ ልዩ ስሜት ፈጥሯል፡፡ ሁለቱንም መሪዎች የሚጠሏቸው ብዙዎቹ ሳይቀሩ አዝነዋል፡፡ ሌሎቹ የሚጠሏቸው ደግሞ ጸሎታቸው እንደተሰማ ቆጥረው ደስ ብሏቸው ይሆናል፡፡ እንዲህ የምንለው አቡነ ጳውሎስ በሕይወት እያሉ በአቡነ ጳውሎስ ላይ ሲያሟርቱ የነበሩና የዘንድሮው በዓለ ሲመታቸው የመጨረሻቸው ነው ብለው የጻፉ ብሎጎች ስለነበሩ ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ታመው በሕክምና ላይ እያሉ ሞታቸውን ብቻ ሲያቀነቅኑ የነበሩ ሚዲያዎችም ስለነበሩ ነው፡፡


እልፍ ሲልም ለሁለቱም ሞት የእነርሱን ጸሎት በምክንያትነት የሚያቀርቡ ግብዞችም አልጠፉም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዋልድባ ገዳም መሬት ላይ ለስኳር ፕሮጀክት ቆርሰው ስለወሰዱ፣ አቡነ ጳውሎስም ዝም ስላሉና ስላላወገዙ የባሕታውያኑ ጸሎት ነው ለዚህ ያበቃቸው፤ በእስልምናው አካባቢ ደግሞ አክራሪ እስልምናን አስመልከተው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በፓርላማ ላይ ስለተናገሩ የእኛ ዱኣ ነው ለዚህ ያበቃቸው እየተባለ ሲወራም ሰምተናል፡፡ ይህ ሁሉ ግን የተሳሳተ ፍርድ ነው፡፡ ዛሬ ሕያው የሆነና የእለተ ሞቱን ተራ የሚጠብቅ ማቹ ሰው እንዲህ የሚል ከሆነ እጅግ ተሳስቷል፡፡  

እንዲህ ብለው የፈረዱ ሰዎች ስለራሳቸው የተሳሳተ ግምት ያላቸው፣ ራሳቸውን ጻድቅ ሌላውን ኃጢአተኛ አድርገው የሚመለከቱ ግብዞች እንደሆኑ የእግዚአብሔር ቃል ይመሰክርባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ስለገሊላ ሰዎች አሟሟት ለኢየሱስ ያወሩለት ሰዎች የተሰጣቸው ምላሽ እንዲህ የሚል ነበር፡፡ «እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን? እላችኋለሁ፥ አይደለም፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ። ወይስ በሰሌሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፥ እላችኋለሁ፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።»

እነዚህ የቤተ ክርስቲያናችንና የአገራችን መሪዎች ትናንት እንደእኛ በሕይወተ ስጋ የነበሩ፣ ለቤተ ክርስቲያናቸውና ለአገራቸው ብዙ ራእይና እቅድ የነበራቸው፣ እንደእኛ እንኖራለን ብለው የሚያስቡ፣ በአመራር ላይ ሳሉ ብርቱም ደካማም ጎን፣ የሚመሰገኑበትም የሚወቀሱበትም ነገር ያላቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን ከመካከላችን በሞት ተለይተዋል፡፡ እነርሱ ሞተው እኛ በሕይወት የቀረነው ግን እነርሱ ከእኛ የተለዩ ኃጢአተኞች ሆነው፣ እኛ ደግሞ ከእነርሱ የተሻልን ሆነን አይደለም፡፡ ይህን ድንገተኛ ጥሪ አስበን ንስሃ እንድንገባ ነው፡፡ አሊያ እኛም እንደእነርሱ መጠራታችን አይቀርም፡፡ ስለዚህ በእነርሱ ላይ መፍረድ ትተን ስለራሳችን ልናለቅስ ይገባል፡፡ በሞታቸው ተደስተን የእግዚአብሔርን ሳይሆን የራሳችንን የልብ መሻት ለመፈጸም የምናልም ካለንም እጅግ ተሳስተናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ቀድመውን ይህን ዓለም በተሰናበቱ ሰዎች ላይ እንዳንፈርድና እኛም ንስሓ እንድንገባ ይመክረናልና፡፡

ቤተ መንግሥቱ መሪውን በክብር እየሸኘና ወደሚቀጥለው የሕይወት ምዕራፍ ለመሸጋገር እንደወሰነ እያደረገ ካለው መረዳት ይቻላል፡፡ ዛሬ መላው ሀገሪቱ ማለት ይቻላል በሐዘን ድባብ ተውጣ ነው የዋለችው፡፡ የመለስ ዜናዊ ሞት ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ ብዙዎችን መሪር ሐዘን ላይ ጥሏል፡፡ አስከሬናቸውን ለመቀበል በብዙ ሺህዎች የሚቆጠር ሕዝቡ የወጣው ቀን ላይ ነው፡፡ «እንወድሃለን እናከብርሃለን» «ሐዘናችን ትልቅ ነው» የሚሉና ሌሎችንም መፈክሮችና የመለስን ፎቶዎች ይዞ እስከ ምሽት ድረስ ሲጠባበቅ ቆይቷል፡፡ እስከ እኩለ ሌሊትም ድረስ በላዩ ላይ እየወረደ የነበረውን ዝናብ ከምንም ሳይቆጥር  ለመሪው ያለውን ፍቅርና አክብሮት በሀዘንና በልቅሶ ሲገልጽ አምሽቷል፡፡ 4 ሰዓት ሊሆን ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስከሬን የያዘው አውሮፕላን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሰ ሲሆን፣ የመንግስት ባለስልጣናትና የመለስ ቤተሰቦች በልቅሶና በዋይታ አስከሬኑን ተቀብለዋል፡፡ አስከሬኑም በከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የፖሊስ ማርሽ ታጅቦ ነው ወደ ቤተመንግስት ያመራው፡፡ ወጣቶች «ጀግና አይሞትም» እያሉ ሆታ እያሰሙ ለመለስ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር ሲገልጹ ነበር፡፡ የአቀባበል ሥርአቱ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የዘለቀ ሲሆን ከቦሌ እስከ ቤተመንግስት ድረስ በተዘጋጀው የአቀባበል ስርአት በየመንገዱ ዳር የተሰበሰበው በብዙ ሺህ የሚቆጠረው ሕዝብ ወንዱ ሴቱ ህጻን አዛውንቱ ጧፍ አብርቶ በጥልቅ ሀዘን፣ በልቅሶና በዋይታ ነበር የመሪውን አስከሬን የተቀበለው፡፡ በአጠቃላይ ሕዝቡ ለመለስ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያሳየበት ዕለት ነው ማለት ይቻላል፡፡

አሳሳቢው የቤተክህነቱ ጉዳይ ይመስላል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ላይ አድመው የነበሩትና በእርሳቸው ላይ የነበራቸው ተቃውሞ ያፋቀራቸው ጳጳሳት አሁን አንድ ይሆኑ ወይ? የሚለው አጠያያቂ ሆኗል፡፡ ሲኖዶሱን እየመራው ያለው የሥጋና የደም ሀሳብ እንጂ በስሙ የሚነገድበት መንፈስ ቅዱስ አለመሆኑ ግልጽ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ጥቂቶች ፍላጎታቸውን ለማሳካት በየጳጳሳቱ ቤት እየዞሩና የሎቢ ስራ ሲሰሩ አምሽተው በበነጋው  ሲኖዶሱ ይሰየምና ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ ለምሳሌ ቅዱስነታቸው እንዳረፉ ዐቃቤ መንበር ከቀብር ስነስርአቱ በኋላ ይሰየማል ሲል ነሐሴ 11 ወስኖ የነበረው ሲኖዶሱ፣ ነሐሴ 14 ቀን ቃሉን አጥፎ ዐቃቤ መንበር ሰይሜአለሁ ሲል መግለጫ ሰጠ፡፡ ቀጣዩ ምን ይሆን?

አባቶች ሆይ እባካችሁ ለቤተክርስቲያን አስቡ፤ ኃላፊነታችሁንም ተወጡ፡፡

ለማንኛውም አቡነ ጳውሎስና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ላይመለሱ ተለይተውናል፡፡ እኛም ነገ መከተላችን አይቀርም፡፡ ስለዚህ እኛም እንደምንሞት እናስብ፡፡ ስለራሳችንም ንስሓ እንግባ፡፡




1 comment: