Monday, June 11, 2012

“በረከታችሁም” ሆነ “ውግዘታችሁ” ማንንም አያድንም አይገድልምም!

Click here to read in PDF
በትናንቱ ዕለት በምዕራቡ ዓለም የሰዓት አቆጣጠር ከለሊቱ 12: 00 (pm) ይሆናል (በሀገር ቤት የሰዓት አቆጣጠር ማለዳ መሆኑ ነው) ወደ አገር ቤት ስልክ መትቼ ነበር። የረጅም ዘመን ትውውቅና ወዳጅነት አለን ከትውውቅም ያለፈ የአባትነትና የልጅነት ያክል የጠበቀ ግኑኝነት ካለን አንድ የዕድሜ ባለፀጋ፣ የመጻህፍት አዋቂ፣ የሲኖዶስ አባልም የሆኑት አባት (ሊቀ- ጳጳስ) በስልክ ተገናኝተን “አውግተን” ነበር። ስልክ የመደወሌ ምክንያት ለሰላምታ ነው። መንፈስን የሚያሳርፍ መንፈሳዊ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላም “ጨዋታ ጨዋታን ያመጣዋል” እንደሚባለው አገልግሎትን በተመለከተ አንዳንድ ነገሮች ስናነሳ ያመራነው ወደ ቤተ-ክርስቲያናችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ነበር። አንስተን ከተነጋገርንባቸው ዓበይት ቁምነገሮች መካከል እጅግ የገረመኝና ያሳዘነኝ በመጨረሻው ዕለት በመጨረሻዋ ሰዓት በጥቂት የሲኖዶሱ አባላት ተከሰተ ሲሉ ዝቅ ባለ ድምጽና በስብራት ያወጉኝን በጥቂቱ ለንባብ በሚያመች መልኩ ላካፍላችሁ ወደድኩ።
በዋናነት እኚህ ሊቀ ጳጳስ “ተዉ! እንዲህ ያለ ስህተት መስራቱ አስፈላጊ አይደለም። እየሆነ ያለውም አግባብነት የለውም ደግሞም በታሪክ የሚያስጠይቅ ውርደት እየፈጸምን ነው ያለነው። … እዚህ የተሰባሰብን ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሁላችን ሴራው ሳይገባን ቀርቶም አይደለም ታድያ ግን ነገም በቀረን በእኛ ላይ መነሳታቸው የማይቀር ጥቂቶችን ለማሰደሰት ሲባል ስርዓተ ቤተ-ክርስቲያን ጥሰን የገዛ ልጆቻችንን እየገፋን ነው ያለነው … ።” በማለት ድምጻቸውን ካሰሙ ጥቂቶች መካከል አንዱ ናቸው። 
    
ቀደም ስል በመግቢያዬ እንደገለጽኩት በመሃከላችን ካለው እጅግ የጠበቀ ግኑኝነትና መቀራረብ የተነሳ በደረቁ ካነሳሁላቸው ጥያቄዎች መካከል ግንቦት 15/2012 ዓ.ም ሲኖዶሱ ያወጣውን የአቋም መግለጫ ቁ. 10 ላይ በሰፈረው “ውግዘቱን” በተመለከተ ያቀረብኩላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ነበር። “ …በመሰረቱ እናንተስ ብትሆኑ ከዚህ ቀደም ስታወግዙ ተወጋዦቹ ደግሞ ተመልሰው አውግዘውል ውግዘቱም እስከ አሁን እንደጸና ነው ታድያ እንዲህ ባለ ሁኔታ የማውገዝ ስልጣን አላችሁ ወይ? ስል ነበር ጥያቄን ያቀረብኩላቸው። ያገኘሁት መልስ “አይ አንተ ደግሞ … እስቲ ተው … ይህንሳ አታንሳው” በማለት ነበር ቁምነገራቸውን በውስጠ ወይራ ያስጨበጡኝ። እኔም ነገሩ ስለገባኝ ምን ለማለት ፈልገው ነው ለማለት አልደፈርኩም። ባይሆን ግን እዚህ ላይ ለአንባቢያንና ለአማኞች አንድ አንኳር ነጥብ ግልጽ ለማድረግ እወዳለሁ ይኸውም አውጋዡን ይመለከታል። እንደው ከዚህ ቀደም ስታወግዙ ተወጋዦቹ አካላትም በበኩላቸው ውግዘታችሁን ውድቅ በማድረግ ተመልሰው እንዳወገዧችሁ ውግዘቱም እስከ አሁን እንደጸና እናንተም ሆናችሁ ሌላውን የእምነቱ ተከታይ የሚያውቀው እውነት ነው ታድያ እንዲህ ባለ ሁኔታ የማውገዝ ስልጣን አላችሁ ወይ?

ውግዘት እንደሚሰራ ከታመነበት አስቀድሞ የተወገዛችሁ ወጊድ ተብላችሁ የተለያችሁም እናንተው ራሳችሁ አይደላችሁም ወይ? ታድያውግዘት ይሰራል ብላችሁ የምታምኑ ከሆነ መጀመሪያውኑ ውግዘቱ እናንተው ራሳችሁን አቅም እንዳሳጣችሁ እንዴት ዘነጋችሁ? ማን ቢፈታችሁስ ነው ደግሞ ዛሬ ሌላውን ለማውገዝ የተነሳችሁ? እንግዲህ ያሰራችሁም እስኪፈታችሁ ድረስ በተፈቱ ላይ አንዳች ስልጣን የላችሁም! ከዚህ በተረፈ ደግሞ መንጫጫታችሁ ለአፍታ፣ መልሶ መላልሶ የሚደመጥ የወይን ጠጅ ዓይነቱ ሳይሆን እንደ መብረቅ ብልጭ ብሎ የሚጠፋውን የከረመም እንደሆነ ለጤና ጠንቅ የሆኑትን እንደ ዝንብ ያሉትን ነፍሳት የሚሰበስብ የወተት ዓይነት ዘፈን ነው የሚሆነው። ቀለል ባለ አማርኛ እንደ መሰሪው ማህበር “ማህበረ ቅዱሳን” ያለ ድብቅ ዓላማ ያለው በግርግር እንጀራውን የሚጋግር ከማስደሰት አልፎ የእናንተ “አውግዘናል” ማለት አንዳች የሚያመጣው ለውጥም ሆነ የሚፈይደው ፋይዳ የለውም።
እንደው ለመሆኑስእንዴት ነው አንድ ሰው÷
v ሊለካ የማይችል ፍቅር
v ሊሞት የማይችል ሕይወት
v ሊደመሰስ የማይችል ጽድቅ
v ሊረበሽ የማይችል ሰላም
v ሊታወክ የማይችል እረፍት
v ሊጠፋ የማይችል ደስታ
v ሊያሳዝን የማይችል ተስፋ
v ሊቀንስ የማይችል ክብር
v ሊጨልም የማይችል ብርሃን
v ሊደክም የማይችል ብርታት
v ሊረክስ የማይችል ቅድስና
v ሊያልቅ የማይችል በረከት
v ሊሻር የማይችል ጥበብ የሰጠንና የሆነልን ጥንት የነበረ ዛሬም ለዘላለምም ያው/ህያው የሆነውን የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ኢየሱስ ሰበከ መሰከረ ጻፈ ተናገረ ተብሎ ያለ አንዳች ጭብጥና ሙግት በጭፍንና በግርግር “ይወገዝ!” ተብሎ የሚወገዘው? በመሰረቱ ውግዘት የሚገባውም ሆነ የሚያስወግዝ ድርጊት ልብ ተብለዋል? እንግዲህ ይህን ያደረገ፣ የፈጸመና ያስፈጸመ፣ የተባበረ በተቀቡት ላይ እጁን ያኖረና የተማማለ ሁሉ ደም በእጁ ሰይፍም በቤቱ እንደሆነ ልብ ይበል።
አንድ መንፈሳዊ ስልጣን የሌለውና ለመንፈሳዊ ስልጣንም የማይገዛ ስመ መንፈሳዊ የመናፍስትና የሙታን ጠሪ ስብስብ አንድ መንፈሳዊ የወንጌል አገልጋይ የማውገዝም ሆነ የመለየት ስልጣን የለውም። አቅም ያንሰዋል! ኃይል ያለው ስራ ለመስራት በጥቂቱም ቢሆን ኃይል ይስፈልጋል። ይህ ማለት በሌላ አገላለጽ ሥጋ የሥጋን ስራ ከመስራት በዘለለ በመንፈሳዊ ዓለም ላይ አሁንም በድጋሜ እጽፈዋለሁ አንዳች ስልጣን የለውም። እንደውም የሚመከረው በሰላም ዲቃላዎቻችሁን እንድታሳድጉ ነው። ለማስመሰል በገፋችሁበት ቁጥር የከፋውን እውነት ሊመጣ እንደሚችልም ደግማችሁ ደጋግማችሁ አስቡበት።
ሌላ የደነቀኝ ነገር በጉባኤው መሃከል “ወደ ውግዘቱ ከመቸኮላችን በፊት መምህራኖቹ ተጠርተው ይምጡና ቃላቸውን አድምጠን ውሳኔያችን እናስተላልፍ” ሲሉ አንዳንድ የሲኖዶሱ አባላት ያሰሙትን ድምጽ በመቃወምተጎንብሰው ምድር እየዘበጡ ኡ! ኡ! ብለው የጮኹ “ሊቃነ ጳጳሳት” ነበሩ የሚል ነው። እዚህ ላይ የደነቀኝ ሌላ ሳይሆን እንደው እንደ ጅረት ውሃ ቃሉ ሲተረተር የባሳን ላሞች የሚያስደነብራቸው፣ የሚያንቀጠቅጣቸው፣ የሚያስጮሀቸውና የሚያንፈራግጣቸው ብሎም አራፋ የሚያስደፍቃቸው ነገር ስላልገባኝ ነው። ከቅዱሳት መጻህፍት መረዳት እንደሚቻለው ቃል ሲሰማ የሚጮኸው መንፈሳዊ ሰው በቆመበትም መቆምም ሆነ መቀመጥ የማይችለው አጋንንትና ሰራዊቱ እንደሆነ ነው የሚያስተምሩን። ታድያ “ተሳስተዋል” የተባሉ መምህራን መሳት አለመሳታቸውን ለማረጋገጥ ቃል ከአፋቸው እንስማ ሲባል ይህን ሁሉ ትእይንት የፈጠሩ ከማን ወገን ቢሆኑ ነው? እንግዲህ ለዚህ ነው ንጽህና ቢኖር ኖሮ አርባና ሃምሳ ሰው መሰባሰቡ ባላስፈለገ ነበር የምለው። ስህተት የተገኘበት ለቤተ-ክርስቲያንም ሆነ ለአማኞች መንፈሳዊ ጤናና አንድነት ጠንቅ ሆኖ የተገኘውን ለማውገዝና ከህብረቱም ለመለየት የአንድ ከነውር የራቀ መንፈሳዊ ሰው ቃል በቂ ነው። ምን ነው? ቢሉ ከቃሉ ጋር እግዚአብሔር ይቆማልና።ታድያ÷

ü ለራስዋ ያልተፈወሰች ነፍስ ስለ ፈውስ:
ü ለራስዋ ያልዳነች ነፍስ ስለ መዳን
ü ለራስዋ ያልተቀደሰች ነፍስ ስለ ቅድስና
ü ለራስዋ ከባርነት ቀንበር ያልተላቀቅች ነፍስ ስለ ነጻነት
ü ለራስዋ ከእስራት ያልወጣች ነፍስ ስለ መፈታት፣ ፈውስ፣ መዳን፣ ቅድስናና፣ ነጻነት የሚጋደለውንናየቆመውን የወንጌል ባለ አደራፊት ለፊት መቆምም ሆነ መቀመጥ አይቻላትምና በሩቁ “አውገዘናል” መባሉ ምኑ ይደንቃል? እንግዲህ ጥጉ ይህን ታደርጉ ዘንድ ስልጣኑ ብቻ ሳይሆን የሞራል ብቃቱም እንደሌላችሁ ነው በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ የምወደው።
ለእናንተ መዳን በክርስቶስ ኢየሱስ ለሆነላችሁ ወንድሞች የጠራው ባሪያውን በማይተውና በማይረሳ ጌታ ደስ ይበላችሁ። እየሆነ ባለ ነገርም የማናችሁም ልብ አይውረድ ይልቁንስ እንዲህ ባለ ጊዜ የቆሬ ልጆች መዝሙር[1] ከአንደበታችሁ አይታጣ። መጽሐፍ ስለ ዳዊት “ዳዊት እጅግ ተጨነቀ ዳዊት ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን አበረታ” (1ኛ ሳሙ. 30: 6) እንዲል ወንድሞች ሆይ! ልባችሁ ኃይልን በሚሰጥ በእግዚአብሔር ይበርታ ደስም ይበላችሁ።
አሁንም ደግሜ ይህን እላለሁ። እናንተ በብዙ ወከባና እንግልት የምትገኙ ወገኖች ሆይ! በመከራችሁ ብዛት ደስታችሁን የሚበዛበት የሐሴት፣ በለቅሶ ፈንታም የደስታ እንባ የምታነቡበት ዕለት በደጅ ነው። ዕለቱ ምን ይመስላል? ስትሉ የጠየቃችሁኝም እንደሆነ በዚያን ዘመን በይግባኝ ሳይሆን (የተላለፈብኝ ውሳኔ እኔ ቀርቤ ሳልጠየቅ ነው፣ ይህን ያደረገም እገሌ ነው) ተብሎ ተሟግተህም በመርታት ሳይሆን በፍለጋ ያለ አንተ ይህን ሕዝብ ይሰበስብ፣ ያስተምር፣ ይመራና ይመግብ ዘንድ የሚቻለው ማንም የለም፤ የእግዚአብሔር እጅ  መንፈሱም ከአንተ ጋር ናትና እባክህ ወደ እኛ ተመለስ በእኛ ላይም ሁሉ አለቃ መሪም ሁነን እባክህ” ተብለህ በፊታቸው ተሻግረህ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ታገለግላለህ(መሳ. 11÷1- 11)።
ይብላኝ የንጹሐን ህይወት ለማበላሸት፣ ደም ለማፍሰስና ነፍስ ለመግደል ራሳችሁን የሾማችሁና የተሾሟችሁ ቅጥረኞች እንጅ መጽሐፍ መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፥ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።”  እንዲል ጳውሎስ አለን ሲል በታላቅ ደስታ በሙላትና በድፍረት የሚተርከው አዳኝ፣ ከስሞችም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ኢየሱስ ታዳጊህ ነው። ነውረኞች “ይወገዙ” ቢባል በአመንዝራነታቸው፣ በሌብነታቸውና በብልሹ ስነ - ምግባራቸው ግርፋት/ቅጣት የሚገባቸው ማፈርም የሚገባቸው ብዙዎች አሉና ስለ ስሙ መገፋታችሁን ክብራችሁ ስለሆነ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ። እንዲህ ባለ ደስታም የሚገኘውን ሐዘን የሌለበት በረከትና ድል በማጣጣም በኩል ብዙዎቻችን ምስክር ነን።

ወንድሞች ሆይ!
v ወንጌል የተጠማ:
v የሰው ክብር የሚያውቅ:
v የምስራች የሚያወሩትን መልካም እግሮችን እንደ ዓይኑ ብሌን የሚንከባከብ:
v ከዚህ ሁሉ ተጋድሎአችሁም በኋላ ዘርተህ የሚበቅልበት የሚታረስ ልብ አሳልፎ እስኪሰጣችሁ፤በአንጻሩ ደግሞ ያስጨነቃችሁ፣ ያሳደዳችሁ፣ የገፋችሁና የተሳለቀባችሁም ጠላት ዓይኑ እያየ ጆሮውኑም እየሰማ በከበረ ስፍራ ላይ ከፍ ከፍ እስኪያደርጋችሁ ድረስ የእግዚአብሔርን የትድግናን ቀን ሳትናወጹ በጽናት ባስቀመጣችሁ ቦታ ላይ ጸንታችሁ በመጠበቅ መልካም ውጊያን ከመዋጋት እጃችሁን አትጠፉ።

v በክርስቶስኢየሱስየተስፋቃልጸንታችሁመቆምይቻላችሁዘንድምዘወትር ስለእናንተ በእግዚአብሔር ፊት እተጋለሁ።የ ምናምነውና የተከተልነው እግዚአብሔር ጻድቅ አምላክ ነው!

v በጽድቅናበእውነትለሚያገለግሉትምእንደእግዚአብሔርያለታማኝአምላክየለምውለታውም የሙት ባሪያውን አጥንት ቆጥሮ ትውልድን በበረከት የሚሞላ አምላክ ነው።
እግዚአብሔር ያዳናቸው ከጠላቶች እጅ የታደጋቸው ይናገሩ!
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
United States of America
June 10, 2012


[1]“አምላካችን መጠጊያችን ሃይላችን ባገኘን በታላቅ መከራ ረዳታችን ነው ስለዚህም ምድር ብትናወጥ ውኖች ቢናወጡ ተራሮች ቢናወጡ አህዛብ ቢናወጡ የእግዚ አብሔር ማደሪያ ግን እግዚ አብሔር በመካከሏ ነውና አትናወጥም እግዚአብሔር ፈጥኖ ይረዳታል።” መዝ (46) 1-7

3 comments:

  1. Yetewegezutema bewenet mewegez yeneberebachew nachew. Be Kirstos megelet sim menfekinan yemizeru ketemeseretew meseret lela lememesret temesaslew sitataru yeneberu! Teneqtoal ahun zim belo kemenchachat beneseha ketaserachehubet lemefetat tematsenu alebelezia endetaserachu....

    ReplyDelete
  2. አሁን በደንብ ተናዘዝክ

    ReplyDelete
  3. «የሰንበት ት/ቤቶች ማ/ መምሪያ በጠራው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባዔ የአቋም መግለጫ፤ የማቅን ደስታ የገፈፈ ነው»

    http://dejebirhan.blogspot.it/2012/06/blog-post_10.html

    ReplyDelete