Thursday, June 14, 2012

እሪ… በይ ቤተ ክርስቲያን… እሪ እንበል ወገኔ…!!!

Click here to read in PDF
በ ከንፈ ገብርኤል
‹‹በኃይል ጩኽ፣ አትቆጥብ፣ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ…፡፡›› (ኢሳ 581)፡፡
የሚጮኹና ለመጮኽ ዕድል ያልተነፈጋቸው ሰዎች የታደሉ ወይም ዕድለኛ ይመስሉኛል፡፡ ቢያንስ ተናግረውና ጩኸው የልባቸውን አድርሰው እፎይ ለማለት ይችላሉና፡፡ በእርግጥ ሰሚ ጆሮ በሌለበት ቢጮኽ ድካም እንጂ ምን ትርፍ አለ? ብለው የሚከራከሩም ባይጠፉም፤ ቢሆንም… ቢሆንም መጮኽ ግን ደግ ነው እንላለን፡፡ በእርግጥ በዚህች አጭር ጹሑፍ በመጠኑ ለመዳሰስ የፈለግነው የጩኸት ዓይነት ከንቱ፣ ተራና ሰሚ ጆሮ የሌለው ሳይሆን ወደ ጸባዖት የሚደረግ ቅዱስ ጩኸት… አዎን… ቅጥሩን ለማፍረስ፣ ኢያሪኮን ለመናድ ብርቱ ኃይል ስላለው ልዩና ቅዱስ ጩኸት ጥቂት ነገሮችን ለማለት ነው፡፡
በአንጻሩ ደግሞ አሉ አንዳንዶች እንደ መረግ በከበደ ዝምታቸው ዓለምን የሚያደባልቅ፣ ጠላቶቻቸውን መውጫ መግቢያ የሚያሳጣ፣ ወደረኞቻቸውን የሚያስጨንቅና እረፍት የሚነሳን ጩኸትን የሚጮኹ፡፡ ዝምታቸው የፍርሃት ደመናን፣ የድንቁርናን ጨለማ የሚገፍ፣ የእውነትን ጠላት የሚያሳድድ… ስለ እነዚህ በታላቅ ዝምታቸው ብርቱውንና ኃይለኛውን ጩኽት ስለሚጮኹ ጀግኖች ሳስብ በአንድ ወቅት አሁን በሕይወት የሌለሉ አረጋሽ የተባሉ ገጣሚና ባለቅኔ የቋጠሩት ስንኝ ወደ አእምሮዬ መጣ፡-
እዬዬም… ጩኸት ነው፣
ዋይ ዋይም… ጩኸት ነው፣
እሪታም… ጩኸት ነው፡፡
ይሄ ሁሉ ሲጮኽ ዝም በል ይሉታል፣
ዝ-ም-ታ… ሲጮኽስ እንዴት ያደርጉታል?! 

 የራማው ጩኸት… የራሄል እንባ ከመቅደሱ አድማስ አድማሳትን ተሻግሮ፣ አየር አየራትን ሰንጥቆ ወደ ጸባዖት፣ ወደ ልዑሉ መንበር ወደ አርያም እየነጎደ፣ እየተረጨ ነው፡፡ አባሽ ያጡ እንባዎች፣ ሰሚ ያጡ ጩኸቶች ዛሬም ያለማቋረጥ በእግዚአብሔር በቅድስናው ስፍራ እንደ ጅረት ያለማቋረጥ እየፈሰሱ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጩኽቱን ተቀምቶ ታፍኖና ተረግጦ ያለው ወገናችን ደግሞ በዝምታው የውስጡን ብሶት የልቡን ጩኸት፣ እሪታ ወደ ጸባዖት ወደ አምላኩ እያሰማ ነው፡፡ በመጮኽም ሆነ በዝምታው የሰው ያለህ… የፍትህ ያለህ በሚል የተጮኽው ጩኸት፣ እሪታና ዋይታ በመቅደሱ አደባባይ ነግሶአል፣ በጎዳና ጩኸት፣ በየመንገዱ ማዕዘን፣ በፍርድ አደባባይ የብዙዎች ጩኸት ተበራክቷል፡፡
ለጩኸታችን፣ ለእሪታችንና ለዋይታችን… መፍትሔ አመላካች ናቸው ብለን ተሰፋ ያደረግናቸውና የተማጸንናቸው ቤተ ክርስቲያንና አባቶቻችን ጩኸታችን ሊጮኹልንና ጩኸታችንን ሊሰሙልንና ሊያሰሙልን ቀርቶ እርስ በርሳቸው በራሳቸው ጩኸት ውስጥ ላይደማመጡ ተውጠው የዘረኝነቱ፣ የጥላቻው፣ የመወጋገዙና የመፈራረዱ እኩይ ጩኸት በአባቶቻን መካከል ያለቅጥ ነግሶ እኛ ልጆቻቸው በእፍረት ተከድደናል፣ በእፍረት አቀርቅረናል፡፡
ቅዱሱን ጩኸት የሚያጯጩኹን፣ በፊታችን የተጋረጠውን የኢያሪኮን ቅጥር ይናድ ዘንድ በመንፈሳዊ ወኔና ጀግንነት ጀግነው የሚያጀግኑን ኢያሱዎች፣ በርቱ ልጆቻችን የሚሉን አባቶች ቁጥራቸው ቢመናመን አድራሻቸው ቢሰወርብን ‹‹እሪ በይ ቤተ ክርስቲያን፣ እሪ በል ወገኔ …!›› ለማለት ወደድን እንጂ እንዲሁ ደርሶ የመጮኽ አባዜ ተጣብቶን አይደለም እንጩኽ እሪ እንበል ማለታችን፡፡ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ምነው ዓይኔ የእንባ ጎርፍ ፈሳሽ ምንጭ በሆነ ነው ያለው ያ የኢየሩሳሌም ጥፋት፣ የእግዚአብሔር መቅደስ መደፈርና መቃጠል፣ የሀገሩ ውርደት የሕዝቡ ጉስቁልና የእግዚአብሔር ቅዱስ ከተማ መፍረስ፣ የሕዝቡ ምርኮና ፍልሰት ነፍሱ ድረስ ዘልቆ እረፍት የነሳው ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ፡፡
ዛሬም እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ኡ…ኡ…ኡ የሚያስብለን እሪ የሚያሰኝ የእንባን ምንጮችን ሁሉ የሚነድል ግፍና በደል በእግዚአብሔር ቤት በእጅጉ ተንሰራፍቷል፡፡ የግፍ፣ የመከራ፣ የድረሱልን ጥሪ፣ የሰው ያለህና የፍትሕ ያለህ… ጩኸት፣ ዋይታና እዬዬ በየአቅጣጫው በዝቶአል፡፡ ጩኸት፣ ዋይታና እዬዬ በፍርድ አደባባይ፣ ጩኸት በጎዳና፣ ጩኸት በቤት፣ ጩኸት በጓዳ፣ ጩኸት በድሆች መንደር፣ ጩኸት በቤተ ክርስቲያናችን፣ ጩኸት ዋይታና እዬዬ የተቀደሰ መቅደሱን አደባባይ የሐዘን ከል አልብሶታል፡፡
ማን አለ እንደ እኛ በመከፋፈል በመለያየት እርስ በርስ በመወጋገዝ በመረጋገም በመጠላላት ዓለምን ጉድ ያሰኘ፡፡ የኢትዮጵያ ሲኖዶስ፣ የአሜሪካው ሲኖዶስ፣ የገለልተኛ… በዓይነ ቁራኛ የሚተያዩ በስድብና በእርግማን ሠይፍ የሚተራረዱና የሚተላለቁ የሚመስሉ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆኑ ማኅበራትና ቡድኖች ብዛት እና ዓይነት ለሚታዘብ ለጉድ ነው፡፡ እርስ በርሳችን በመነቃቀፍና በመለያየት ማን ይመስለናል?… ማንስ ያክለናል?…፤ በዚህ ሁሉ ውስጥ የነገ መድረሻችን ሲታሰብ ደግሞ ልብ በእጅጉ ይደክማል፣ መንፈስም ይዝላል፡፡ ነገ ደግሞ ምን ሊመጣ እንደሚችል ማን ያውቃል!!!!!
አባቶቻችን ለልጆቻቸው ፍቅርን፣ ምህረትንና ተስፋን ለተራበው ሕዝባቸው የሚያበረታና የሚያጽናና መልእክት ይዘውልን ለመምጣት ደክመዋል፤ እናም በራሳቸው ጉዳይ ተጠምደው የሌት ተቀን አሳባቸው የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ እንደ እግር እሳት የሚያንገበግባቸው የደመወዝ ጭማሪ፣ ሞዴል መኪና፣ ምርጥ ሕንጻ ስለመገንባትና የአውሮፓ ወይም የአሜሪካዊ ዜግነት የማግኘት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱም ይህን ምድራዊ አጀንዳ በመስማትና በመዳኘት በስሞታና በአሉባልታ ሲናጥና እንደ ሽንብራ ሲንገረገብ ሰንብቶ ያለአንዳች ዘላቂ መፍትሔ ይበተናል፡፡
በዚህ ሁሉ ሁከት፣ በዚህ ሁሉ ቀውስ መካከል ደግሞ ለንስሐ የሚያነቃን በፈረሰው ቅጥር በኩል በመቆም አቤቱ ለሕዝብ ራራ እያሉ በመጮኽ በመቅደሱ አደባባይ ተግተው ያተጉናል ያልናቸው አባቶቻችን ውሎ አዳራቸው ከቄሳር አደባባይ ሆኖብን ልባችን በእጅጉ አዝኗል፡፡ በዚህ ልባቸው የተከፋ፣ በአባቶቻቸው በእጅጉ ተስፋ የቆረጡና ያዘኑ፣ በቅዱስ መቅደሱ ክፋትና አመጻ በመንገሱ ኃዘናቸው ቅጥ ያጣ አንዳንድ ልጆቻቸውም በየብሎጉና በየድረ-ገጹ የአባቶቻቸውን በደልና እፍረት በአደባባይ በመገለጽ ላይ ናቸው፡፡
ልጆቿን ተመለሱ፣ ተመከሩ ብላ በፍቅር ለመቀበልና ለመገሰጽ አቅም፣ ጉልበትና ድፍረት ያጣች ቤተ ክርስቲያን ከገዛ ከአብራኳ ክፋዮች ጋር እየተቋሰለች፣ እየተዳማች፣ ገመናዋንና ኃጢአቷን በየአደባባዩ እየገለጠች ሌላ የውርደት ሌላ የእልቂት ታሪክ ለመጻፍ ደፋ ቀና እያለች ይመስላል፤ በበርካታ በተገፉ ልጆቿ ልብ ውስጥም የተሰወረው የበቀል ድማሚትም አንድ ቀን የፈነዳ ጊዜ ሊያደርሰው የሚችለውን ጥፋት ለሚያስብ ደግሞ ወዮልን ለእኛ የሚያሰኝ ነው፡፡ የልጆቿን ጩኸትና ዋይታ እና እሪታ ላለመስማት ‹‹የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ!›› ያለች እናት ቤተ ክርስቲያን ዛሬም በ21ኛው መቶ ክዘመን ማውገዝ ማስወገዝን፣ መውገር ማስወገርን፣ መለየትን ስራዬ ብላ የቀጠለች ይመስላል፡፡ ልጆቿ ነን የሚሉ ተቆርቋሪ መሳዮችም በሕይወት የሌሉና ለሀገራቸው ባለውለታ የሆኑ ሰዎች አስክሬናቸው እንኳን አርፎ እንዳይተኛ ይወገዙልን በሚል ስም ዝርዝራቸው ቀርቦ ውሳኔ ይሰጣቸው ዘንድ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
መቼም ማውገዝ ማስወገዝ፣ መውገርና ማስወገር ለእኛ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ታሪካችን አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል ለመጥቀስ በቅርብ የታሪካችን ዘመን እንኳን በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በሃይማኖት ሰበብ ውግዘትና ውግረት ስለደረሰባቸው ወገኖቹ 20ኛው ክ/ዘመን የሀገራችን ጥቂት ምሁራን መካከል ቁንጮ የሆነው ወጣቱ ምሁር፣ ጸሐፊ፣ የኢኮኖሚ ተንታኝ የሆነው ፖለቲካል ኢኮኖሚስቱና የታሪክ ተመራማሪው ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ‹‹የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ሥራዎች›› በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሐፋቸው ላይ ገብረ ሕይወት በሀገሩ ያጋጠመውን ጉድ እንዲህ ሲል ትዝብቱን በአግራሞትና በትልቅ ቁጭት ውስጥ ሆኖ ይገልጻል፡-
. . . አንድ ልበ ብሩህ ያበሻ ሰው መሬት ትዞራለች ብሎ ቢያስተምር አሁን በቅርቡ በሀረርጌ በዳኛ ተይዞ አልነበረምን… አሁን በ19ኛው መቶ ዓመታት ከክርስቶስ ልደት በኋላ አልፈን ሃያኛውን መቶ ዓመት ስንጀምር አንድ ሰው የተዋህዶን ሃይማኖት ቢነቅፍ ካዲስ አበባ ገበያ ላይ በድንጋይ አልተወገረምን እስከዛሬስ ድረስሳ ወደ ሩቅ ሀገር ተሰደው ወደ አበሻችን ከሚመጡት ፈረንጆች ጥቂት ጥበብ ተምረው ያገራቸውን መንግሥት ሊጠቅሙ የሚፈልጉ ወንድሞቻችን ጵሮተስታንት፣ ካቶሊክም፣ መናፍቃን የሌላ መንግሥት ሰላዮች እየተባሉ ሲራቡ ሲከሰሱም እናይ የለምን የእንዚያም መከረኞች ስም ስንት ብለን እንቁጠር . . . ፡፡
አሰገራሚው ነገር እንደ ገና ከመቶ ዓመትም በኋላ እነዚሁ ሰዎች መጽሐፋቸው መወገዝ እነርሱም መለየት አለባቸው በሚል ስም ዝርዝራቸው ተጠቅሶ ውግዘት እንዲተላለፍባቸው አቤት የሚል ማኅበር በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን መከሰቱ ሌላ እንቆቅልሽ ሌላ ግርምትን የሚፈጥር ነገር ሆኖብናል፡፡ ይህን የጀመረውን የማውገዝና የማስወገዝ ዘመቻ ዓላማውንም ለማሳካት ይኽው ማኅበር ላይ ታች  እያለ በመሯሯጥ ላይ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ትጥራንና እንነጋገር በእውቀትም ሆነ ያለ እውቀት ያጠፋነውም ስህተት ከተገኘብንና ከአባቶቻችን ትምህርት የተለየ ነገር ካስተማርን እንመከር እንገሰጽ በሚሉበት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማውገዝንና መለየት ምን የሚሉት አካሄድ እንደሆነም ግራ የሚያጋባ ነው፡፡
በመሠረቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮና ስርዓት ውጭ የሚሄዱ ሰዎችም ሆኑ ማኅበራት ካሉ ልቅ መለቀቅ አለባቸው የሚል ጭፍን አቋም የለንም፤ ግን ማውገዝና መለየት የመጨረሻ እንጂ የመጀመሪያ አማራጭ ሊሆን አይገባውም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዲህ አልተነገረንም፣ አልተጻፈምም፡፡ የዘመናችን ጩኸትና እሪታ መሆን ያለበት አንገብጋቢው ጉዳያችንስ የትኛው ነው፣ ሌሎችን ስለማወግዝና ስለመለያየት ነው እንዴ… ስንት እሪ የሚያሰኘን ክፋትና አመጻ በእግዚአብሔር ቅዱስ መቅደስ በነገሰበትና ጆሮን ጭው የሚያደርግ ጉድ በሚሰማባት ቤት እንዴት ዝኆኑን ውጠን ትንኟን ለማጥራት እንዲህ ወደር የሌለው በሚመስል ግብዝነትና ፈሪሳዊነት ውስጥ ተዘፍቀን ራሳችንና ሕዝባችን እናታልላለን፡፡
መጮህ… ኡ…ኡ…ኡ…! ዋይ… ዋይ… ዋይ…! እሪ… እሪ…እሪ…! ማለት ካለብን ፍቅርን ስለማጣታችን፣ ስለመለያየታችን፣ ቅንና በጎ ኅሊና ስለማጣታችን፣ እስከ አንገታችን ስለተዘፈቅንበት የዘረኝነት የጥላቻና የመለያየት አባዜ እንጂ፣ መጮኽ ካለብን በቀቢጸ ተስፋ ተውጠው በጫትና በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ተጠምደው ለቤተሰባቸውና ለሀገራቸው ሸክም ስለሆኑ፣ ስደትን ተስፋ አድረገው በእግር፣ በባሕር፣ በበረሃ እየተጓዙ የሞት ሲሳይ እየሆኑ ስላሉት በሺህ ስለሚቆጠሩ ወጣት ስደተኛ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን እንጂ፣ መጮኽ እሪ ማለት ካለብን ፍርድን ፍትህን ስለተነፈጉ በኃጢአት ባርነት ቀንበር ስር ስለሚማቅቁ ሕዝቦች እንጂ… ኡ ኡ ኡ ማለት ካለብን ለአባቶቻችን ፍቅር፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት፣ ለሀገር ሰላም፣ ለወገን ብልጽግና፣ ለገዢዎችና ለመንግሥታት ከአርያም የሆነ ማስተዋልና ጥበብ እንዲሆንላቸው መጮኽ አለብን እንጂ እንዴት በከንቱ ጩኸት በባዶ እሪታ ጉልበታችንን እንፈጃለን፣ ኃይላችንን እናባክናለን፡፡
ቅዱሱን ጩኸት ከመጮኽና ከመማለድ የሚበልጠው ጩኸት የሚበልጠው እሪታስ … የቱ ይሆን የተወደዳችሁ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እኛ ግን በስተመጨረሻ አንድ ነገር ለማለት እንወዳለን ቅዱሱን ጩኸት በአንድነት ለመጮኽ አንድከም፣ እንዛል… እግዚአብሔር የሕዝቡን ጩኸት የሚያደምጥ ቅዱስ፣ የተፈራ፣ በምድር ላይ ፍርድን፣ ፍትህንና ምሕረትን የሚያደርግ፣ እጅግም የሚራራ አምላክ ነውና!!!
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ያስብ!

8 comments:

  1. Bezih Blog Lemejemeriya gize Kemola godel Tiru neger tenebebe.

    ReplyDelete
  2. ኡ…ኡ…ኡ…! ዋይ… ዋይ… ዋይ…! እሪ… እሪ…እሪ…! have you started what is inevitable! sorry!sorry!sorry!
    but make sure that your cry will be endless unless and otherwise you confess and bow infront of God at His temple,Tewahedo!
    i am so sorry to hear your cry from the deep hell.

    ReplyDelete
  3. ህሊና ላለው ሰው ድንቅ ጽሁፍ ነው። ማስተዋላቸው የተሰወረባቸውን እግዚአብሔር ይግለጽላቸው።

    ReplyDelete
  4. ከ አሁን በሗላ የሚዘናጋ የለም ወንድሜ እንኳን ሁሉ ነገር ተለየ እንጂ

    ReplyDelete
  5. Thank's to God to read the first time spritual message from this blog,still not perfect but way better than before. please keep doing instead of posting about maq they are always fighing with any one if doing against mother church, by the way don't forget they are also human being b/c of that we are not expect 100% perfection from them.
    God bless you

    ReplyDelete
    Replies
    1. የእናንተ እንባ የአዞ እንባ ነው። አስመሳዮች ናችሁ። ይሁዳ እኮ ጌታውን የሸጠው በሐዋርያት መካከል ሆኖ ነው። እናንተም ቤተክርስቲያንን እየሸጣችሁ ያላችሁት ቤተክርስቲያን ጉያ ውስጥ ሆናችሁ ነው።ይህ የአካሄድ ለውጥ(ስልት) መቀየራችሁ ነው? ለቤተክርስቲያን አሳቢ መስላችሁ መቅረባችሁ ነው? እስስት ቀለሙን ይቀይራል እንጂ እስስትነቱን አይቀይርም።ተሀድሶም አካሄዱን ይቀይራል እንጂ ተሀድሶነቱን አይተውም።ቤተክርስቲያንን ግን የሲኦል ደጆች አይችሉአትም።

      Delete
  6. ክንፈ ገብርኤል ዕድሜዎን ያርዝምልን! በእውነት ድንቅ መልእክት ነው ያስነበቡን ምናለ እንደእነዚህ ዓይነቶቹን የቤተ ክርስቲያናችንን እንቁዎች እየፈለጋችሁ ቁም ነገር ብታስነብቡን እንዴት በነጋ ጠባ እርግማን፣ ስድብን፣ ዘለፋን፣ ውግዘትና የሰዎችን ገመና ስንሰማ ስናነብ ጆሮአችን ይመግላል፣ ዓይናችን ይፈዛል፣ ነፍሳችን ትቆስላለች፣ መንፈሳችንስ ይዝላል… እረ ባካችሁ እርስ በርስ መሰዳደቡና መጠላላቱ ምን ይጠቅመናል ለምን መስማት የማንፈልገውን እያሰነበባችሁን ልባችንን ታቆስሉታላችሁ፡፡
    እኛ የፍቅርን፣ የምሕረትን፣ የይቅርታን አዋጅን/ስብከት ነው እንጂ የተጠማነው የሰው ገመና ለማንበብማ የሀገራችን ጋዜጦችና መጽሔቶች አሉልን አይደል እንዴ! ዛሬ በእውነት ጥሩ ነፍስን የሚያሳርፍ ድንቅ መልእክት ነው ያስነበባችሁን አውደ ምሕረቶች እንደ ስማችሁ የምሕረትንና የይቅርታን ስብከትን እንዲህ ብታቃምሱን እንመርቃችኋለን፡፡ በእውነት ነው የምላችሁ ጹሑፉን እያነበብኩ ጩኽ… ጩኽ… እሪ በል… እሪ በል ነው ያሰኘኝ… በቤተ ክርስቲያናችን፣ በአባቶቻችንና በአገልጋዮቻችን የምንሰማው ጉድ ጩኸት… ዋይታና… እሪታ ሲያንሰው ነው፡፡ ‹‹ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይራዳም›› ይላሉና አበው በተረታቸው እስቲ እኔም ወደ እልፍኜ ልግባና በሬን ዘግቼ ኡ…ኡ…ኡ… እሪ… እሪ… እሪ… ዋይ… ዋይ… ዋይ … ልበል ጎረቤት ቢቀር የአካሌ ክፋይ ሚስቴና ልጆቼ ቢያግዙኝ… እናም የሰሙኝ ሁሉ ይራዱኝ ዘንድና ቅዱሱን ጩኸት በአንድነት እንጮኸ ዘንድ… ኦ! የአባቶቻችን አምላክ ስማን እባክህ

    ዘርዓያቆብ ዘሀገረ ኢየሩሳሌም ጽዮን ሰማያዊት!

    ReplyDelete
  7. Your writing capability is admirable, but you missed the truth?

    ReplyDelete