Friday, June 22, 2012

ትግሉ በሕዝብና በ"ማኅበረ ቅዱሳን" መካከል ነው፤ ቤተክርስቲያን ለአደጋ ተጋልጣለች ቢሆንም በመጨረሻው ሙሽራው እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ አሸናፊ ነው

Click here to read in PDF
ምንጭ፡-http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com

"ማኅበረ ቅዱሳን" "እውን የማኅበረ ቅዱሳንና ኦርቶዶክስ 'ተሐድሶ' ፍልሚያ ወይስ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሕልውና ጉዳይ"? በሚል ርዕስ  ደጀ ሠላም (deje selam) በተባለው ትዊተር ገጹ ላወጣው የማደናገሪያ ጽሑፍ የተሰጠ መልስ

ድሮ ልጆች ከሚያውቁት ሠፈር ርቀው እንዳይሄዱና እንዳይጠፉ ጭራቅ ይበላሃል፤ ጭራቅ ይበላሻል እየተባሉ በዐዋቂዎች ማስፈራሪያ ይደረግባቸው ነበር፡፡ ይህ ጭራቅ በሕይወት የሌለና በምናብ የተፈጠረ ሲሆን፣ ጥርሶቹ ሾል ሾል ያሉ፣ ሁለት ትልልቅ ዓይኖች ከፊት፣ ሁለት ትልልቅ ዐይኖች ደግሞ ከማጅራቱ /ጭንቅላቱ/ በኩል በድምሩ አራት ዐይኖች ያሉት ሲሆን አንገቱን ዞር ዞር ማድረግ ሳያስፈልገው በሁሉም አቅጣጫ ስለሚመለከት ማንም ሊያመልጠው አይችልም፡፡

ጭራቅ በቁመናው ሰው እየመሰለ ከሰው መካከል በተለይ ልጆችን እየመረጠ፣ ወስዶ በትልቅ ጋን ውስጥ እንዳለ በመክተት ከቀቀለ በኋላ ያለ ቢላዋ ሥጋቸውን የሚነጭ አውሬ ነው ይባል ነበር፡፡ ምንም እንኳን ጭራቅ በግዑዙ ዓለም የሌለና የፈጠራ መሆኑን ብናውቅም በአባቶችና በእናቶች በተደረገብን ጫና ሳቢያ ዛሬም ያለ የሚመስለን ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

አባቶችና እናቶች ልጆችን እንዲታዘዙ የሚያደርጉት በጭራቅ በማስፈራራት ነበር፡፡ እኛም ልጆች በጊዜው ጭራቅ መጥቶ እንዳይበላን የተሰጠንን ሥራ ባንወደውም ሠርተናል፡፡ ጀንበር ሳይጠልቅ ወደ ቤት ስብስብ ብለን እግራችንን ታጥበን፣ እራት በልተን ተኝተናል፡፡ አፋችን ክፉ ቃል እንዳያወጣ ገደብ ተደርጎበታል፡፡ ጭራቅ እንዳይበላን አባትና እናታችን ጉያ ውስጥ ውሽቅ ብለን፣ ፍርሃት እንደናጠን አድገናል፤ ኖረናል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም፣ የዘመኑ "ማኅበረ ቅዱሳን" ተሐድሶ መጣብህ፣ መጣብሽ ማስፈራሪያም ከድሮ እናትና አባታችን የጭራቅ ተረት ለይተን አናየውም፡፡ "ተሐድሶ" "ኦርቶዶክስ ተሐድሶ" "ፕሮቴስታንታዊ ተሀድሶ ኑፋቄ" "መናፍቅ" እንዲያው "ማኅበረ ቅዱሳን" የወጣው ስም ብዙ ነው፡፡ ታዲያ
ሁሉ ጩኸት እኔ የእግዚአብሔር ባሪያ አገልጋይ ርግብ፣ እንደ ስሜ ቅዱስ ነኝ ሌላው ቤተክርስቲያኔን ሊበላ የመጣ ጭራቅ ነው በማለት የሚደረግ የማደናገሪያ ዘመቻ ነው፡፡

ምንፍቅና በማንኛውም ሃይማኖትና ቤተእምነት ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ማንም ዋስትና ሊሰጥ አይችልም፡፡ አንድ ሰው ተኝቶ በተነሳና ባዛጋ ቁጥር ምን እንደሚያስብ አይታወቅም፡፡
የየሃይማኖቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን /ስክሪፕቸርስ/ አንብቦ በተረዳው መጠን ሊያምን ወይም ደግሞ ከሃይማኖቱ ሊያፈነግጥ ይችላል፡፡ ይህ ዓይነቱን ምንፍቅና የሰውዬውን  ምንነት ካረጋገጡ በኋላ ሥርዓት ባለው መንገድ ወደ ቀደመው እምነቱ እንዲመለስ አለዚያም ተወግዞ እንዲለይ ይደረጋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እየሆነ ያለው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በመዋቅር ያልተደራጀ፣ ሰዎቹ በግል እነማን እንደሆኑ የማይታወቁ፣ ሥርዓት ባለው መንገድ አስተምህሯቸውን እንኳን መፈተሽ ያልተቻለ፣ በምድር ላይ የሌለ "ተሐድሶ" የሚባል ቡድን አለ ሲባል የምንሰማው "ማኅበረ ቅዱሳን" ነው፡፡ይህ የጭራቅ ምስል የተሠራለት የተሐድሶ ቡድን "ማኅበረ ቅዱሳን" ንጹሐንን ማደናገሪያና ለራሱም ዕድሜ ማራዘሚያ ሆኖለታል፡፡

የአባላትህን ዝርዝር አሳውቅ፣ የሀብትህን ምንጭ ግለጽ፣ ንብረትህን አስቆጥር፣ ሌላም ሌላም ትዕዛዝ ሲወጣበት እንዳልሰማ ሆኖ ይህ "የተሐድሶዎች ጩኸት ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችን ልትፈርስ ነው" እያለ ከሁሉም ቀድሞ በመጮኽ አርዕስት ያስቀይራል፡፡ በቅርቡ "እውን የማኅበረ ቅዱሳንና ኦርቶዶክስ 'ተሐድሶ' ፍልሚያ ወይስ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሕልውና ጉዳይ"? በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባም በተመሳሳይ ሁኔታ ሲቀባጥር ይታያል፡፡

ለዚህ ማደናገሪያ ጽሑፉ የግል ኢሜሎችን ዋቢ አድርጎ ያቀረበው 'ማኅበረ ቅዱሳን' ". . . ተሐድሶ ሚሲዮናውያኑ ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ አውጀው የነበረውን ጦርነት በውክልና የሚዋጋ ወኪል እንጂ በራሱ የቆመ ወይም ኢትዮጵያዊ መሠረት ያለው ቡድን አይደለም፡፡ የሚታዘዘውም፣ የሚመራውም፣ አይዞህ ባዮቹም እነዚሁ ምስጢረ ብርቱዎቹ ሚሲዮናውያን ናቸው. . . " በማለት እንድንጃጃልለት ነግሮናል፡፡

"... ተሐድሶ . . . በራሱ የቆመ ወይም ኢትዮጵያዊ መሠረት ያለው ቡድን አይደለም" ብሎ "ማኅበረ ቅዱሳን" ካመነ፣ ይህ ሁሉ ጋጋታና ጫጫታ፣ ክስና ትርምስ ለምን አስፈለገ ብለን ልንጠይቀው እንገደዳለን፡፡

"ማኅበረ ቅዱሳን" ተሐድሶ ተብሎ ሊፈረጅ የሚችል ግለሰብ ወይም ተቋም፣ ማኅበር እንደሌለ ልቦናው አበጥሮ አንጠርጥሮ ያውቀዋል፡፡ ግን ይህን ሁሉ ዓመት ሲዘላብድበት የነበረውን ውሸት ትንሽ ነፍስ እንዲዘራ ለማድረግ ሚሲዮናውያንን እዚህ ጉዳይ ውስጥ አምጥቶ ደንቅሯል፡፡ ሚሲዮናውያን ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋት ከዐፄ ሱስንዮስ ጊዜ ጀምሮ የጦር መሣሪያና ስጦታ በማቅረብ ጭምር ጥረት ሲያደርጉ እንደነበረ ቢታወቅም ለዛሬዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የውስጥ ችግርና ሁከት ተጠያቂ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

የዛሬው የቤተክርስቲያናችን ሁከትና ዝቅጠት ዋናው ምክንያት "ማኅበረ ቅዱሳን" ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ካህናትን፣ ምዕመናንንና ራሷ ቤተክርስቲያንን ተክቼ እኔ ልምራ፣ እኔ የፈቀድኩት ብቻ ይፈጸም የማለት "በሁሉ ገባሽ" አባዜው እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

የሲኖዶሱ ለሁለት መከፈል አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም ዛሬ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ለደረሰው የሞራል ድቀትና ዝቅጠት "ማኅበረ ቅዱሳን" አልታዘዝ ባይነት፣ ሥርዓት አልበኝነት፣ ጋጠ ወጥነት፣ ከፍተኛውን አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ ለብዙ መቶ ዓመታት ታፍራና ተከብራ የኖረችው ቤተክርስቲያን ትላንት ከሃያ ዓመት ወዲህ በተፈለፈለ የአንበጣ መንጋ ተወርራ ስቃይዋን በማየት ላይ ትገኛለች፡፡

ዛሬ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ተንቆ፣ ቤተእግዚአብሔር ተደፍሮ ቅዳሴ በጨኸትና በግርግር የሚስተጓጎልበት፣ ካህናትና ምዕመናን በስለትና በድንጋይ የሚቀጠቀጡበት፣ ገንዘብና ንዋየ ቅድሳት ለጉቦና ለቅጥረኛ ተደባዳቢዎች ድርጎ የሚውሉበት፣ ሊቃነጳጳሳቱ ክብራቸው ተገፎ የሚብጠለጠሉበት፣ አገልጋዮች ካህናት ከሀገር ወደ ሀገር የሚሰደዱበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ "ማኅበረ ቅዱሳን" ለቤተክርስቲያናችን ያተረፈው ይሄንን ነው፡፡ "ማኅበረ ቅዱሳን" ከመመሥረቱ በፊት "መመሥረት የለበትም" ብለው ሲሟገቱ የነበሩ ብፁዓን አባቶች ምን ያህል ትክክል እንደነበሩ ዛሬ ሁሉም ይረዳዋል፡፡

አዲስ አድማስ፣ ፍትሕ፣ አዲስ ነገር እና ሌሎችም የግል ፕሬሶች "ማኅበረ ቅዱሳን" አባላትና አመራሮች የሚንቀሳቀሱ መሆኑን ስናስተውል፣ ማኅበሩ በሃይማኖት ካባ ተወሽቆ ፖለቲካዊ አጀንዳ እንደሚያራምድና የመንግሥትንና የቤተክርስቲያንን ሥልጣን ለመቆናጠጥ ምን ያህል ጥማት እንዳለው እንረዳለን፡፡

"ማኅበረ ቅዱሳን" በሕልሙ አግዝፎ ከሳለው ተሐድሶ ጋር የምታገል ነኝ ቢልም እውነታው ግን ትግሉ "ማኅበረ ቅዱሳን" (በአንድ ወገን) እና በሕዝብና በቤተክርስቲያን( በሌላ ወገን) ነው፡፡ ኑፋቄን ወይም ተሐድሶን በጋራ የምንታገለው ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ "ማኅበረ ቅዱሳን" ይህንን ትግል እኔ ነኝ የምመራው ሊል የሚችልበት ሕጋዊም ሆነ ሞራላዊ ውክልና የለውም፡፡ በተለይም ከመሬት ተነስቶ በአገልጋዮች ላይ የሚለጠፍ "ተሐድሶ"ነት ስድብ እንዲቆም መግለጫ እስከማውጣት ተደርሷል፡፡

ቤተክርስቲያን ይህንን አስመልክቶ "ሕግን፣ ሥርዓትንና ቀኖናን ሳይከተል እየተካሄደ የሚገኘው 'ተሐድሶ' እወጃ የቤተክርስቲያንን ቀኖና ያልተከተለ በመሆኑ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግበት" በሚል ሐምሌ 25 ቀን 2003 . በቁጥር ልጽ/598/1604/03 ባወጣችው መግለጫም፣ ማንም በማንም ላይ የተሐድሶነት ታፔላ እንዳይለጥፍ ብርቱ ማስጠንቀቂያ አስተላልፋለች፡፡

ይሁን እንጂ ራሱን ከቤተክርስቲያን በላይ ያስቀመጠው "ማኅበረ ቅዱሳን" ይህንን ለመቀበል ዝግጁ አይደለም፡፡ ዛሬም ከዚህ አንደበቱ አልተቆጠበም፡፡ በመላው አህጉረ ስብከቶች መበጥበጡን አላቆመም፡፡  ሀዋሳ፣ ሐረር፣ ክብረ መንግሥት፣ ነጌሌ ቦረና፣ ሽሬ፣ መቀሌ፣ ዲላ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ በአዲስ አበባም ልደታ ማርያም፣ እስጢፋኖስ፣ ቅዱስ ዮሴፍ፣ ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም፣ ምስካየ ሕዙናን መድኃኔ ዓለም፣ ተክለሃይማኖት፣ ቅድስት ማርያምና ሌሎችንም ሀገረ ስብከቶችንና አጥቢያ ቤተክርስቲያናትን ሲያምስ ከርሞ አሁን ደግሞ ተረኛው ግቢ ገብርኤል ሆኗል፡፡

ሕዝብና ቤተክርስቲያን  ኃላፊነታቸውን በምሥር ወጥ በለወጡ በአንዳንድ አፍቃሬ "ማቅ" ሊቃነጳጳሳት ጀርባ ታዝሎ የሚያውካቸውን ይህንን "ማኅበረ ቅዱሳን" የተባለ ማፊያ ቡድንን አደብ ለማስገዛት በከፍተኛ ተጋደሎ ላይ ናቸው፡፡ አንዳንድ አጥቢያዎች መዋቅራቸውን "ማኅበረ ቅዱሳን" የማጥራት ሥራ ሠርተዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የግንቦት ርክበ ካህናት ጉባዔውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ተራ ቁጥር 5 ላይም የሚከተለው ውሳኔ ተቀምጧል፡፡ "የተሰጠውን ደንብና የአሠራር መዋቅሩን ከወቅቱ ሁኔታ ጋር እንደገና መርምሮ ማሻሻል በማስፈለጉ ከብፁዓን አባቶች ከሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና ከሕግ ዐዋቂዎች በተውጣጣ ኮሚቴ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ጉባዔው ወስኗል፡፡ ደንቡ ተሻሽሎ እስከሚፀድቅ ማኅበሩ ተጠሪነቱ ለብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ አመራር በመቀበል እየሠራ እንዲቆይ ጉባዔው መመሪያ ሰጥቷል"፡፡ ውሳኔው ይህ ሆኖ ሳለ "ማኅበረ ቅዱሳን" በመምሪያ ደረጃ ራሱን ችሎ እንዲደራጅ ተወሰነ ተብሎ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሲነዛ ተከርሟል፡፡

"ማኅበረ ቅዱሳን" ላይ መግለጫ ሲወጣ ይህ የመጀመሪያው አይደለም የመስከረም 12/2002 . የሠላም ጉባዔም የሚያወሳው "ማኅበረ ቅዱሳን" በቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅርና የመንግሥት ፖለቲካ ውስጥ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆም ነው፡፡ ልዩ ልዩ ሀገረ ስብከቶችና አጥቢያ ቤተክርስቲያናትም እንደራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ልዩ ልዩ ማስጠንቀቂያዎችን ጽፈዋል፡፡

"ማኅበረ ቅዱሳን" እንደድሮው በበግ ለምድ ተለብጦ ማወናበድ አይቻለውም፡፡ ሕዝብ፣ ቤተክርስቲያንና መንግሥት ነቅተውበታል፡፡ ተጠያቂነት የሌለው ሕቡዕ አደረጃጀቱ፣ ግልጽነት የጎደለው የሀገር ውስጥና የሀገር ውጭ የገንዘብ ዝውውሩ፣ ኦዲት የማያውቀው ደመ ነፍስ በጀት አጠቃቀሙና ስውር ሃይማኖት ለበስ ፖለቲካዊ አካሄዱ የትም አያደርሱትም፡፡

አንዳንድ የዋሃን "ማኅበረ ቅዱሳን" ተከታዮችና ምኑንም የማያውቁ ምዕመናን "ማኅበረ ቅዱሳን" ከኪስ በሚዋጣ ገንዘብ ንዋየ ቅድሳትን እየገዛ በዱር በገደሉ ተጉዞ ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት ድጋፍና ዕርዳታ የሚያደርግ ቅን ማኅበር አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ሲጀመር እንዲህ ነበር፤ ዛሬ ግን እውነታው ግን ይህ አይደለም፡፡ በገጠር አብያተ ቤተክርስቲያናት ስም በገንዘብና በዓይነት ዕርዳታ ይሰበሰባል፡፡ በተቃጠሉ ሕንፃ ቤተክርስቲያናት እንዲሁም እንደዝቋላ ገዳም ባሉ ገዳማት ድንገተኛ አደጋ በሚነሳበት ጊዜ በአንድ ጄሪካን ውሃ እስከ 40 ብር ድጋፍ እየተጠየቀ ሕዝብ ይገፈፋል፡፡ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያናቱ ሱቆችንና ልዩ ልዩ የንግድ ድርጅቶችን ከፍቶ ለመንግሥትና ለቤተክርስቲያን ተገቢውን ገቢ ሳያስገባ ይቦጠቡጣል፡፡ ዕርዳታና ገቢው ለታለመለት ዓላማ አይውልም፡፡ ጭራሹኑ በተቃራኒው ለሕቡዕ እንቅስቃሴው ማስፈጸሚያ ከበጀት አርዕስት ውጪ ይረጫል፡፡ ከቤተክርስቲያን ሥርዓት አፈንግጠው የማኅበሩን ዓላማ ለሚደግፉ ሊቃነ ጳጳሳትና ካህናት ቋሚና ተደራቢ ደመወዝ ይከፈላል፡፡ ዛሬ "ማኅበረ ቅዱሳን" አመራሮችና ተራ አባላት መካከል ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ልዩነት ይታያል፡፡ "ማኅበሩ" ሲመሠረት የነበረው መንፈሳዊ ገጽታ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ ሰይጣናዊ አስተሳሰብና ዓለማዊ አመለካከት ተጠናውቶታል፡፡

ሁኔታው ተባብሶ የቤተክርስቲያን ሥርዓት በአግባቡ እንዳይከናወን እስከመፈታተን ደርሷል፡፡ "ማኅበረ ቅዱሳን" በጥባጭነት የተነሳ ታቦታትን ከመንበራቸው አንስቶ ለማንገስ አልተቻለም፡፡ ሥርዓተ ቁርባንንና ቅዳሴን በአግባቡ መምራት አልተቻለም፡፡ ቤተክርስቲያን የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎችን ዕገዛ እስከመጠየቅና የአብያተ ቤተክርስቲያናት ቅጥር ግቢም የተኩስ ድምፅ የሚሰማባቸው እስከመሆን ደርሰዋል፡፡

ሕዝብ በሠላምና በጸጥታ የማምለክ መብት አለው፤ ቤተክርስቲያን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሥርዓቷን የመምራት መብት አላት፣ መንግሥትም በጸደቀው ሕገ መንግሥት መሠረት ሀገርን የመምራትና የማስተዳደር መብት አለው፡፡ ይህንን ሥርዓት የሚያፋልስ እንቅስቃሴ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ "ማኅበረ ቅዱሳን" ገና ለገና 'ተሐድሶ' ብሎ ይሰድበናል፣ 'ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ' ይለናል ብለን እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም፡፡

የሕክምናው፣ የምሕንድስናው፣ የግብርናው፣ የሕጉ፣ የከርሰ ምድሩ፣ የመልክዓ ምድሩ፣ የቋንቋው ወዘተ ዲግሪዎች ለቤተክርስቲያን መለኮታዊ አገልግሎት ምንም ረብ የላቸውም፡፡ ቤተክርስቲያንን ለማገልገልና ሌላውን ተሀድሶ ብሎ ለመፈረጅ ሥነ መለኮታዊ ዕውቀት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ፣ ዐወቅን፣ ዐወቅን የሚሉት "ማኅበረ ቅዱሳን" አባላትን አርፋችሁ ተቀመጡ፣ በቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ ጣልቃ አትግቡብን እንላቸዋለን፡፡ በበጎ ፈቃደኛነት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ሕጋዊ አደረጃጀትና ግልጽነት ያለው አሠራር ይኑራችሁ፤ ካለበለዚያ ቤተክርስቲያናችን የወንበዴዎች፣ የማፊያዎች መሸሸጊያ አይደለችም፤ ጥፉ እንላቸዋለን፡፡

በግል መንግሥትን መቃወም ትችላላችሁ፡፡ እንደ ፓርቲ ተደራጅታችሁ ከተመዘገባችሁ በኋላ ሀገርን ለመምራትም መወዳደር ትችላላችሁ፡፡ ከዚህ ውጪ በዋልድባ ገዳም ስም የሕዝብን ስሜት በመቀስቀስ፣ ቤተክርስቲያን ጉያ በመሸሸግ ፖለቲካችሁን ማራመድ አትችሉም ቤተክርስቲያንን ለቀቅ አድርጉ እንላቸዋለን፡፡

ከዚህ አንፃር ትግሉ የሕልውና ጉዳይ የሚሆነው "ማኅበረ ቅዱሳን" እንጂ ለቤተክርስቲያን አይደለም፡፡ ቤተክርስቲያንማ ጥንትም ነበረች፤ ዛሬም አለች፤ ነገም ትኖራለች፡፡ "ማኅበረ ቅዱሳን" የያዘውን ሀገርንና ቤተክርስቲያንን የማፈራረስ ሰይጣናዊ ዓላማ ሰባት ጊዜ ጮሆ እስከሚለቅ ሕዝብና ቤተክርስቲያን እስከመጨረሻው ይታገሉታል፡፡

1 comment:

  1. አዲስ አድማስ፣ ፍትሕ፣ አዲስ ነገር እና ሌሎችም የግል ፕሬሶች በ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባላትና አመራሮች የሚንቀሳቀሱ መሆኑን ስናስተውል፣ ማኅበሩ በሃይማኖት ካባ ተወሽቆ ፖለቲካዊ አጀንዳ እንደሚያራምድና የመንግሥትንና የቤተክርስቲያንን ሥልጣን ለመቆናጠጥ ምን ያህል ጥማት እንዳለው እንረዳለን፡፡BESAKKKKKKKKKKK

    ReplyDelete