Tuesday, July 10, 2012

በጽንፈኝነትና በአክራሪነት መንፈስ የሚራገቡ የአደባባይ ተረታ ተረቶች የታሪክ ሐቅን ሲገዳደሩ፡- በኢትዮጵያ ታሪክ «አልነጃሺ» የተባለ የሰለመ ንጉሥ ነበርን. . .??

                            (ከሪፖርተር ጋዜጣ የእሁድ ሐምሌ 1/2004ዓ.ም እትም ላይ የተወሰደ)
ጸሐፊው፡- ፍቅር ለይኩን፡፡ nejasi. click here to read in PDF
ከጥቂት ወራት በፊት የመንግሥታቸውን የሥራ ሂደት ሪፖርት ለማሰማትና ከምክር ቤት አባላት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በፓርላማ የተገኙት ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ መስመሩን እየሳተ እየሄደ ስላለውና አንዳንድ በሃይማኖት ሽፋን የአክራሪነትና የጽንፈኝነት እንቅስቃሴን ስለሚያራምዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ባስተላለፉት ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ በሚመስል ንግግራቸው፡- ‹‹እንዲህ ዓይነቱን በሃይማኖት ሽፋን እየተካሄደ ያለውን ማንኛውንም ዓይነት የሀገርን ሰላምና ጸጥታ የሚያደፈርስ የአክራሪነትንና የጽንፈኝነትን እንቅስቃሴ መንግሥት ችላ እንደማይለውና በንቃት በመከታተል እርምጃ እንደሚወስድም በግልጽ አስረድተው ነበር፡፡››
ጠቅላይ ሚ/ሩ አክለውም በሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ታሪካዊና ጥንታዊ የሆኑት ሁለቱ ሃይማኖቶች ክርስትና እና እስልምና ለረጅም ዘመናት በሀገራችን ተከባብረውና ተዋደው የኖሩና ይህ ልዩ የታሪክ እውነትም የተቀረው ዓለም እስከ አሁንም ድረስ የሚደነቅበትና በመልካም አርዓያነቱ የሚጠቅሰው መሆኑን አስታውሰው ይህን እውነታ የሚያስረግጥ አንድ ገጠመኛቸውን ለፓርላማው አባላት እንዲህ አቅርበው ነበር ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ፡-
በቅርቡ አሉ ጠቅላይ ሚ/ሩ አንድ ከወሎ ክ/ሀገር የገጠር ቀበሌ የመጣ ሰው/ወደጃቸው በዛ ቀበሌ ዝናብ በመጥፋቱ ምክንያት ድርቅ ስላጠቃቸው በቀበሌው ያሉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ ክርስቲያኖች ታቦታቸውን ነቅለው ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ መቁረጣቸውን የሰሙ የእስልምና እምነት ተከታዮችና የዕድሜ ባለጸጋ አባቶች ክርስቲያን ወገኖቻቸውን ይህ ታቦት የእናንተ ብቻ እኮ አይደለም የሁላችንም ነው፡፡ በዚህ ቦታ ለብዙ ዘመን ቆይቷል እናም እባካችሁ ከዚህ ቦታ አትንቀሉት እኛም አላህን እንለማመናለን እናንተም እግዜርን ተማጠኑ በማለት ክርስቲያኖቹ ታቦታቸውን ነቅለው እንዳይሄዱ እንዳገላገሉ ለፓርላማው አባላት ተናገረው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚ/ሩ በዚህ ንግግራቸው ሊያስተላልፉ የፈለጉት መልእክት ለብዙዎቻችን ግልጽ ይመስለኛል፡፡ በታሪካችን የቆየውና እንደ ምሳሌ የምንጠቀስበት በሃይማኖቶች መካከል ያለው መከባበርና መቻቻል በዚህ ዘመን በአንዳንድ በሃይማኖት ሽፋን ጽንፈኝነትና አክራሪነትን በሚያራምዱ ግለሰቦችና ቡድኖች እንዴት እየደበዘዘ፣ እየጠፋና መስመር እየለቀቀ እንዳለ ያሳሰቡበት መልእክት ይመስለኛል፡፡


በዛሬው ጽሑፌ ይሄንኑ በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል ለረጅም ዘመናት የዘለቀውን የመከባበር ባሕል እያጠፉና ወደ ጽንፈኝነትና አክራሪነት እየመሩ ካሉት ምክንያቶች አንዱ በሃይማኖቶች መካከል ያለውንና የነበረውን ታሪክ ከማጣመምና አንዳንዴም ደግሞ ያለ በቂ መረጃ በአፈ ታሪክ የሚነገሩ ትውፊቶችና ተረቶችን በአማኞች መካከል የተጋነነ ስሜትና የተሳሳተ አቋም እየፈጠሩ በሃይማኖቶች መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነቶች ሲያሻክሩት እየታዘብን ነው፡፡ ከነዚህም መካከል በብዙዎች የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ እየተነገረና በሰፊው እየተጻፈለት ያለው የአክሱም ንጉስ «አልነጃሺ» እና አክሱማውያንም መስለማቸውንና ከዚህም የተነሳ አንዳንዶች አክሱም እንደ ክርስቲያን ሃይማኖት ማእከልነቷ ሁሉ ቅዱስ የሙስሊም ከተማ ናት እስከማለት የደረሱበትን ሌላ ድብቅና መሰሪ አጀንዳ ያነገበውን አቋማቸውን በአደባባይ ጭምር እየታዘብነው ነው፡፡
እናም እስቲ በዚህ በአክሱማውያን፣ በአልነጃሺ መስለምና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ በትምህርትና በሥራ አጋጣሚ በእጆቼ ከገቡ ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብት በማጣቀስ ጥቂት ነገሮችን ልበል፡፡
፳፻ ዓ.ም ወርኃ ክረምት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እያለሁ በእስልምና ሃይማኖትና በአክሱማውያን ሥርወ መንግሥት መካከል የነበረውን ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ግንኙነት ለማጥናትና ለማስተርስ ዲግሪ ማሟያ የሚሆነውን የመመርቂያ የጥናት ጹሑፍ ለማዘጋጀት ከአሜሪካ ሜኔሶታ ግዛት ከሚገኝ ዩኒቨርስቲ ከመጣ አንድ ጎልማሳ አሜሪካዊ ወዳጄ ጋር ወደ ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ አክሱም ከተማ ለመስክ የምርምር ጥናት አቅንተን ነበረ፡፡ በቆይታችንም በአዲግራት ከተማ ከሚገኘው የሙስሊሞች ቤተ-አምልኮ ከሆነው «አል ነጃሺ» መስጊድ ተገኝተን ነበር፡፡
በዚሁ ‹‹በአልነጃሺ›› መስጊድ ቆይታችንም በዛ ከሚገኙ በዕድሜ ባለጸጋ ከሆኑ የእምነቱ አባቶችና ሸህዎች ጋር ለጥቂት ሰዓታት እጅግ ደስ የሚያሰኝ ቆይታን አድርገን ነበር፡፡ እስካሁን ልረሳው ባልቻልኩት በልቤ ጽላት ውስጥ በማይደበዝዝ ቀለም በታተመ እጅግ በሚመስጥ ትሕትና፣ ጨዋነትና የኢትዮጵያዊነት እንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ነበር አቀባበል ያደረጉልን እነዚህ የሃይማኖቱ አባቶች፡፡
እነዚህ የዕድሜ ባለጸጋዎች የመጀመሪያዎቹ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች በነቢዩ ምክርና ትእዛዝ ወደ አክሱም ግዛት እንዴት እንደመጡና በአክሱም ስለተደረገላቸው አቀባበል፣ በዛም እስልምናን ለማሳፋፋት ስላደረጉት እንቅስቃሴና ይህም እንቅስቃሴያቸው በወቅቱ የአክሱምን ንጉሥ እንደ እነዚህ ሰዎች እምነት «አል ነጃሺን» ጭምር ሳይቀር የእስልምናን እምነት በገዛ ፈቃዱ እንዲቀበል እንዳደረጉትና በአክሱም ግዛት የሚኖሩ ሰዎችና አንዳንድ መነኮሳትም ጭምር ሳይቀሩ እስልምናን መቀበላቸውን፣ ስለ እስልምና ሃይማኖትና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነት ጭምር በአፈ ታሪክ ከአባቶቻቸው የተቀበሉትን ትውፊት ከቅዱስ ቁርዓንና እንዲሁም ከዐረቡ ምድር ታሪክ አዋቂዎች የታሪክ ሰነድና አፈ ታሪኮች በማጣቀስ ጭምር ያስረዱን በራስ መተማመን ፍጹም የተረጋጋ ስሜት ውስጥ ሆነው ነበር፡፡
ከዛም ባሻገር ከመጀመሪያዎቹ ወደ አክሱም ከመጡት የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል የነቢዩ ሙሐመድ ልጅ የሆነቸው ሩቂያ፣ ባለቤቷ በኋላም ሦስተኛ ከሊፋ የሆነው ኡስማን አቡበከር፣ ጃፋር አቡጣሊብና የሌሎችንም የመጀመሪያዎቹ ስደተኞች በአክሱም በሰላም መቆየታቸውንና ከእነዚህም ስደተኞች መካከል አሥራ አምስት የሚሆኑት በዚሁ በአል-ነጃሺ መስጊድ ቅጥር መቀበራቸውን የሚያረጋግጥ መካነ መቃብራቸውንም በእነዚህ የእምነቱ አባቶችና ዕድሜ ባለጸጎች ልብን ከሚመስጥ ትረካቸው ጋር ለመጎብኘት ችለን ነበር፡፡ እነዚህ የእምነቱ አባቶች በገለጻቸው መጨረሻም በነቢዩ መሐመድም ሆነ ከእርሱ በኋላ በተነሡ የእስልምና ታላላቅ አባቶች ዘንድ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በሙስሊም ሃይማኖት አማኞችና በዐረቡ ዓለም ያላቸውን ታላቅ ተቀባይነት፣ መፈራትና ክብር የነገሩን ታላቅ በሆነ ሀበሻዊ ኩራትና ደስታ ውስጥ ሆነው ነው፡፡
‹‹በአልነጃሺ›› ለሰዓታት ባደረግነው ቆይታችን ይህ አሜሪካዊ ተመራማሪ ለመመረቂያ ጽሑፉና ለምርምር ጥናቱ የሚጠቅሙትን መረጃዎች በድምፅ በምስልና በጽሑፍ ከከተበ በኋላ በሰጡን ሰፊ መረጃዎችና ትንታኔዎች ላይ ሞቅ ያለ ውይይትና ክርክር እያደረግን ወደ ጥንታዊቷ አክሱም ከተማ ተመለስን፡፡ ጉዞአችን እጅግ አስደሳችና ውጤታማ በመሆኑ በወቅቱ የተሰማን ስሜት እጅግ ልዩ ነበር፡፡ እስቲ የጉዞአችንን ማስታወሻ ትረካ በዚሁ ልግታውና እነዚህ የእስልምና ሃይማኖት አባቶችም ሆኑ በዘመናችን በኢትዮጵያውን ሙስሊም ወገኖቻችን ዘንድ ስለሚራገበው የአልነጃሺና አክሱማውያን መስለም ጉዳይ አንዳንድ ጥያቄዎችን በማንሳት ወደ ጽሑፌ ዋና ጭብጥ ላምራ፡-
ለመሆኑ አክሱማውያን/ኢትዮጵያውያን ከእስልምና ሃይማኖት ጋር የነበራቸው ታሪካዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ግንኙነት አንዳንዶች እንደሚሉት የአክሱምን ንጉሥና አክሱማውያን ከክርስትና ወደ እስልምና እስኪያፈልስ ድረስ ጉልበት ነበረውን? ስለ ‹‹አልነጃሺ›› እና ስለ አክሱማውያን መስለም የሚተረከው ታሪክስ ምን ያህል እውነት ነው? የታሪክ ድርሳናትና መዛግብት እንዲሁም በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ምሁራንስ ምን ይላሉ፣ ምንስ ጻፉ…፡፡ 
በእርግጥስ በኢትዮጵያውያኑ፣ በምዕራባውያኑና በዐረብ ሀገራት የታሪክ ተማራማሪዎች፣ ሊቃውንትና ጸሐፍት የታሪክ ድርሳናት ዘንድ በእርግጥ የአክሱም ንጉሥና አክሱማውያን ስለመስለማቸው ነው የሚነግሩን ወይስ በተቃራኒው፡፡ በእኛስ ዘመን «ኢትዮጵያ ክርስቲያናዊ ደሴት» የሚለው የቆየው ብሂል በአንዳንድ ሙስሊም ወገኖቻችን ዘንድ ለምን ቅር ከማሰኘት አልፎ ከቃላት ውርጅብኝ ወደ ቁጣና ወደ ግጭት እና ጥቃት ለመሻገር እንዲበቃ ያደረገው የዘመናችን ጽንፈኞችና አክራሪዎች «የአልነጃሺ ሰልሟል» እና «አክሱም የመጀመሪያዋ የእስልምና ከተማ ናት» መፈክርና ተጨባጭ ማስረጃ የሌለው ትረካ ከሃይማኖቱ ባለፈ ግብ ያደረገውና የተቀመመበት ታሪካዊና ፖለቲካዊ መነሻ ዳራው ከየት ነው የተመዘዘው? በአንዳንድ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከመካ፣ ከመዲናና ከሶሪያዋ ደማስቆ ቀጥሎ አክሱም አራተኛዋ የእስልምና ቅዱስ ከተማ ተደርጋ መጠቀሷስ ውስጠ-መልእክቱ ምንድን ነው?
ከዚህ ሁሉ የታሪክ ሽሚያ ወይም ዝርፊያና ሃይማኖትን ማስፋፋት ዘመቻ ባሻገር በሀገራችን በሁለቱ ሃይማኖቶች ዘንድ በአንጻሩም ቢሆን ለዘመናት የቆየው ተከባብሮና ተዋዶ እስከ ጋብቻ መጣመር ድረስ የዘለቀውና ለተቀረው ዓለም ሁሉ ምሳሌ እስከመሆን የዘለቀው በሰላም የመኖር ባሕል በእኛ ዘመን በተዛባ ታሪክና በጓዳው ውስጥ ተረት ተረት/አፈ ታሪክ እየተነዳ ባለ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት መንፈስ እንዴት እንዲህ ያለው አደጋ ሊጋረጥበትና እንዲህ ዓይነቱ አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ ቻለ? ከዚሁ ሁሉ ሁነቶች ጀርባና ስለ ‹‹አል ነጃሺ›› አክሱምና አክሱማውያን ከእስልምና ሃይማኖት ጋር የነበራቸውስ ግንኙነት ምን ድረስ ነው በሚሉት ጉዳዮች ላይ የታሪክ መዛግብትና ሰነዶች ምን ይላሉ የሚለውን ከታሪክ ድርሳናት እውነት አንጻር በጣም በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በዓለማችን ተወዳዳሪና አቻ ካልተገኘለት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጀምሮ በእስልምና ሃይማኖት መጽሐፍ ቅዱስ ቁርዓን፣ ዓለማችን አሁን ለደረሰችበት ስልጣኔና ዕድገት ትልቁን ድርሻ በሚወስዱት በግሪካውያኑ ታላላቅ የጥበብ፣ የፍልስፍና እና የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ስሟ ተደጋግሞ በአድናቆት የተጠቀሰ በመካከለኛው ክፍለ ዘመንም ለአውሮፓውያን አሳሾችና ተጓዦች የልብ ትርታ ሆና የቆየችና «የቅዱስ ዮሐንስ ክርስቲያን ሀገር» በመባል ትልቅ ስምና ዝናን ያተረፈች ሀገር መሆኗን በርካታ አሳሾችና የታሪክ ድርሳናት የመሰከሩላት ናት፡፡
ከዚህም ባሻገር በጥበብ ፍቅር ዕረፍት ለነሣትና አቅሏን ለሳተችው በቅዱስ ወንጌል በጌታችን በኢየሱስ አንደበት ‹‹የጥበብን ሀሰሳ ረጅም ጉዞዋ›› በአድናቆት የተተረከላት የንግሥተ ሳባ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ይህች ንግሥታችንም በሩቅ ሆና በሰሎሞን የጥበብ ዝና መንፈስዋ ሸፍቶባት ይህን ታላቅ ጥበብ በጆሮዋ ሰምታ በዓይኗ ዓይታ ለማረጋገጥ ከምድር ዳርቻ እስከ ዛሬ ድረስም ሆነ ወደፊትም አንድ ሴት ለአንድ ወንድ ልሰጠው ከምትችለው ስጦታ ወደር ያልተገኘለትና እንደ ሁለቱ እንግሊዛውያን የታሪክ ምሁራንና ጸሐፍት ኖርማን ፐርን እና ቨርኖን ባርሎው Quest for Sheba በተባለው መጽሐፋቸው በአድናቆት እንደገለጹት፡-
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ሀገራችን በነበራት የኢኮኖሚ አቅም ሲሰላ ከሃያ አምስት ሚሊዮን ፓውንድ በላይ የሚገመት ስጦታን ይዛ፣ (የብራችን የመግዛት አቅም ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆለ ባለበት በዚህ በእኛ ዘመን የንግሥተ ሳባ የስጦታ መጠን በብር ሲመነዘርና ይዛ የተጓዘችውን ይህን የስጦታ መጠን ስናነጻጽረው ዛሬ በድህነት ቀንበር ሥር ወድቀን በቀን ሦስቴ እንኳን እንደ ነገሩ በልቶ ለማደር  የመጽዋቾችን በር ነጋ አልነጋም ብለን ደጅ ለመጥናት ለተገደደን ኢትዮጵያውያን ወይ ነዶ… እንዲህ ካለው የታሪክ ሰገነት ተሸንቀጥረን ነው ለዚህ የበቃነው አያሰኝም ትላለችሁ?!) በሺህ ግመሎችና የጋማ ከብቶች የተጫኑ ውድ የሆኑ የከበሩ ማዕድናትን አስጭና የተጓዘች የጥበብ ምርኮኛ ንግሥት የሳባ ሀገር ኢትዮጵያ የዓለማችን የእግዚአብሔር ምሥጢር ምድር እንደሆነች በብዙዎች የተጻፈላትና የሚደመሙባት ሀገር ናት፡፡ ይህች እናት ሀገራችን  ኢትዮጵያ ገና ብዙ የአርኪዮሎጂና የታሪክ ምርምር ጥናት የሚያስፈልጋት ባለ ብዙ ምሥጢርና ባለ ብዙ ኅብር ባለ ታሪክ ምድር ናት፡፡
ሀገረ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬም ድረስ ዓለም ምሥጢርና እንቆቅልሽ የሆነበት የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚገኘው በእኔ ምድር ነው ኢትዮጵያውያንም የዚህ ታላቅ የእግዚአብሔር ምሥጢር ጠባቂና ባለአደራ ናቸው የምትል ብቸኛዋ የዓለማችን ሀገር ናት፡፡ ከዚህም የተነሣ የብዙዎችን ጎብኚዎች አሳሾችና ታሪክ ተመራማሪዎች ቀልብ የሳበች ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡ በአንድ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የሽያጭ ጣራን ለመቆናጠጥ የበቃው በእንግሊዛዊው ግራሃም ሀንኩክ የተጻፈው The Sign and the Seal የተባለው መጽሐፍ ኢትዮጵያን ከጥንት ጀምሮ በመንፈሳዊ ኩራት ስለሚናገሩለት ስለእዚሁ ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት ሀሰሳ/ፍለጋ የተጻፈ ክርስቲያኑን ዓለም በሰፊው ያነጋገረ መጽሐፍ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ሌላው አስገራሚው ገጠመኝ ደግሞ ኢትዮጵያ ከዓለማችን ሀገራት በተለየ መልኩ በመካከለኛው ምሥራቅ ለተገኙት ለሦስቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች ለአይሁድ፣ ለክርስትና እና እስልምና ቀዳሚ ማዕከል መሆኗ ነው፡፡ ይህን እውነት የመካከለኛው ምሥራቅና የዐረብ ሀገራት እውቅ የታሪክ ተመራማሪ፣ የእስልምና ሃይማኖት ምሁር፣ የእስራኤልና የዐረቡ ዓለም/የፍልስጤም ግጭት ታሪክ ተንታኝና በአንድ ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ መምህሬ የነበሩት በአንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ Department of History and Heritage Management ባልደረባ የነበሩት ፕሮፌሰር ሁሴን አሕመድ Aksum in Muslim Historical Traditions በሚል ጥናታዊ ጹሑፋቸው አክሱምን ሁለቱን የመካከለኛው ምሥራቅ ሃይማኖቶች በሰላም ያስተናገደች ከተማ መሆኗን ሲገልጹ፡-
Aksum possesses the unique distinction of being at once the cradle of both Christianity and Islam in Ethiopia, and perhaps represents perhaps the earliest example of a geographical setting favorable for a peaceful encounter and harmonious coexistence between two great monotheistic religions: Christianity and Islam.
በተጨማሪም ፕሮፌሰር ሁሴን አሕመድ al-Tiraz al-Manqush fi Mahasin al-Habush (The Colored Brocade on the Good Qualities of the Ethiopian) በሚል ርእስ መሐመድ አብዱል ባኪ አል ቡከሃሪ አል ማቅዚ (በዚህ የዐረቢኛ ስም የአማርኛ ትርጉም ላይ ሰህተት አድርጌ ከሆነ አስቀድሜ አንባቢያንን ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡) እ.ኤ.አ በ1583 ዓ.ም የጻፉትን ታሪካዊ ሰነድ ዋቢ አድርገው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በነቢዩ መሐመድና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ያላቸውን ተወዳጅነት እና ክብርም እንዲህ ገልጸውታል፡-
«Who brings an Ethiopian man or woman into his house brings the blessings of God there.»
በሀገራችንም ሆነ በዐረብ ታሪክ ጸሐፊዎችና የእስልምና እምነት ሊቃውንቶች ዘንድ የተጻፉት የታሪክ ድርሳናት አክሱማውያን የነቢዩ መሐመድን ተከታዮችን በሞቀ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዳስተናገዷቸውና በአክሱም ግዛት በነጻነት የመኖር መብት እንደተሰጣቸው በግልጽ ያስረዳሉ፡፡ በአክሱማውያን ግዛት እነዚህ በእምነታቸው ምክንያት የተሰደዱ ሰዎች በሰላም መስተናገዳቸውና በነጻነት መንቀሳቀስ መቻላቸው ቁጭትና እልህ ውስጥ የከተታቸው የመካ ሹማምንት በብዙ ስጦታና አጀብ ወደ አክሱም በላኳቸው መልእክተኞቻቸው እነዚህ በስደት ወደ ግዛትህ የገቡ ሰዎች የእኛንም ሆነ የአንተን እምነት የማይከተሉ ከሃዲያንና አረመኔዎች ናቸውና አሳልፈህ እንድትሰጠን አደራ ጭምር የታከለበት መልእክት በዘመኑ ወደነበረው የአክሱም ንጉሥ ልከው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
አክሱማዊው ንጉሥ ግን እነዚህን ሰዎች አስቀርቦ ስለተሰደዱበትና አሁን ደግሞ በገዢዎቻቸው በጥብቅ ስለሚፈለጉበትና ስለተከሰሱበት እምነታቸው ከጠየቃቸው በኋላ ወደ መካ ሹማምንት በላከው መልእክት እነዚህ ሰዎች ምንም ክፉ ነገር አላገኘሁባቸውምና አሳልፌ ልሰጥህ አልችልም በሚል መልእክተኞቹም ያመጡትን ስጦታና መደለያ ይዛችሁ በሰላም ወደመጣችሁበት ወደ ሀገራችሁ መሄድ ትችላላችሁ በማለት ቁርጣቸውን ነግሮ እንዳሰናበታቸው በተለያዩ የዐረብ ሀገራት ታሪክ ጸሐፍት ሰነዶች ውስጥ በግልጽ ተጠቅሷል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንድ የዐረብ ጸሐፊዎችና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሰለመው የአክሱም ንጉሥ «አልነጃሺ» ለነቢዩ መሐመድ ተከታዮች ባደረገው ውለታና እንክብካቤ የተነሣ ከነቢዩ ጋር ልዩ የሆነ ወዳጅነት መሥርተው እንደነበርና ይህ መልካም የሆነ ግንኙነታቸውም አድጎ ይኸው የአክሱም ንጉሥ ነቢዩ መሐመድን ለመጎብኘት ሲጓዝ በመንገድ ላይ ማረፉንና በወቅቱም በዚህ መጥፎ አጋጣሚ ልባቸው የተነካ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሐዘናቸውን የገለጹበት የሙሾ ግጥም እስከ አሁንም ድረስ በትውፊት ደረጃ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዘንድም እንደሚታወስ ፕ/ር ሁሴን በጥናታቸው እንዲህ ገልጸውታል፡-
ወዳንቱ ሲመጣ ወዳንቱ ሲሸሽ፣
ትግሬ ላይ የቀረው «አሕመድ አል ነጋሽ/አልነጃሺ፡፡»
አልነጃሺ ከነቢዩ መሐመድ ጋር የወዳጅነት የደብዳቤ ልውውጥ ማድረጋቸውንና እስከ አሁንም ድረስ ብዙዎችን እያከራከረ ስላለውና የአክሱም ንጉሥ ሰልሟል የሚለው አገላለጽና በአክሱማውያን ንጉሥና በነቢዩ መሐመድ መካከል ተደርገዋል የተባሉት የወዳጅነት የደብዳቤ ልውውጦችም ከአፈ ታሪክ በዘለለ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ የሌላቸውና እንዲሁም የአክሱም ንጉሥ ስለ መስለሙ የሚነገሩ አፈ ታሪኮችና በአንዳንድ ጸሐፍት ዘንድ በዋቢነት የሚቀርቡ ደብዳቤዎችም ሆኑ ክርክሮች በቂ የሆኑ ታሪካዊ መረጃዎች የሌላቸው መሆኑን ፕሮፌሰር ሁሴን አሕመድ በጥናታቸው ሲያብራሩም፡-
የሃይማኖት ጉዳይ ዋንኛ አጀንዳና የአክሱማውያን መለያ በሆነበት ሁኔታ የአክሱም ንጉሥና አክሱማውያን ሰልመው ቢሆን ኖሮ እንዴት ያን ሊገልጹ የሚችሉ በአርኪዮሎጂ ቁፋሮም ሆነ በሌሎች የታሪክ ድርሳናት የተቀመጡ ይህን እውነት ሊያረጋግጡና ፍንጭ ሊሰጡ የሚችሉ ጥቂት እንኳን መረጃዎች እንዴት ሊገኙ እንዳልቻሉ በመጠየቅ… አሳባቸውን ሲያጠናክሩም በቅድመ ክርስትና ዘመን የግሪክን አማልክት ሲያመልኩ የነበሩ አክሱማውያን ክርስትናን በተቀበሉ ማግስት በወርቅ ሳንቲሞቻቸው ላይ የክርስትና ሃይማኖት መቀበላቸውን በግልጽ በሚያረጋግጥ መልኩ በሳንቲሞቻቸው ላይ የነበሩትን ምልክቶች በመስቀል ቅርጽ መተካታቸውንና አክሱማውያን በዘመኑ ከነበሩት ነገሥታት ጋር ባደርጓቸው የደብዳቤ ልውውጦችም ሆነ በዐውደ ግንባር ስለተጎናጸፉት ድሎቻቸው ወደ ክርስትና ሃይማኖት መግባታቸውን የሚያረጋግጡ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በግልጽ መጠቀሳቸውን በአክሱምና በአዶሊስ አካባቢ በሚገኙ በአርኪዮሎጂ ቁፋሮና የታሪክ ምርምር የተገኙ የድንጋይ ላይ ጹሑፎች በግልጽ እንደሚያስረዱና በትክክልም የአክሱም ንጉሥ «አልነጃሺ» ወደ እስልምና ገብቶ ቢሆን ኖር ተመሳሳይ የሆኑ እንዴት እንዲህ ዓይነት ቢያንስ እንኳን ጥቂት መረጃዎች ሳይገኙ ቀሩ በማለት በአግራሞት ይጠይቃሉ…፡፡
በሂብሪው ዩኒቨርስቲ የመካከለኛው ምሥራቅ እውቅ የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሐጋይ ኤልሪችም Ethiopia and the Middle East በሚለው መጽሐፋቸው የፕሮፌሰር ሁሴን አሕመድን አሳብ እንደሚጋሩ በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡ ምናልባትም ይላሉ እነዚህ የመካከለኛው ምሥራቅና የዐረብ ሀገራት ታሪክ ከፍተኛ ተመራማሪዎችና እንዲሁም የእስልምና ሃይማኖት ከአክሱምና አክሱማውያን ጋር ስለነበረው ታሪካዊ ግንኙነት ሰፋ ያለ ጥናት ያደረጉት ሁለቱ ምሁራን፡-
በዘመኑ የነበሩ አንዳንድ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እምነቱን ለማስፋፋትና ብዙዎችን ወደ እምነቱ ለመሳብ ሲሉ በጊዜው እጅግ ገናና እና ታላቅ ስልጣኔ የነበረውንና በግዛቱም በሰላም የተቀበላቸውን የአክሱምን ንጉሥ እስልምናን እንደተቀበለ አድርጎ ወሬ መስፋፋቱ በአረቢያን ምድር ሃይማኖቱ ሰፊ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ሲሉ የመጀመሪያዎቹ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የተፈጠረ መላና ዘዴ ሊሆን እንደሚችል እነዚሁ ምሁራን ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
በእነዚህ ምሁራን የምርምር ሥራዎች፣ የታሪክ ጥናቶችና በኢትዮጵያና በእስልምና ሃይማኖት ግንኙነት ዙሪያ በተጻፉ የታሪክ መዛግብቶች ላይ በመመርኮዝ አጠር ባለ መልኩ ዳሰሳ ያደረግንባቸው ታሪካዊ ሰነዶችም ሆኑ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሱት የታሪክ ምሁራንና የመካከለኛው ምሥራቅ ሃይማኖቶች ታሪክ አጥኚዎች ኢትዮጵያዊው ምሁር ፕሮፌሰር ሁሴን አሕመድና አይሁዳዊው ፕሮፌሰር ሐጋይ ኤልሪች የአክሱም ንጉሥም ሆነ አክሱማውያን ስለ መስለማቸው የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ሰነድም ሆነ ማረጋገጭ እንደሌለ ነው በጥናታቸው ግልጽ ያደረጉት፡፡ ታዲያ ታሪካዊው እውነታው ይህ ከሆነ በዘመናችን የሌለ ታሪክን በመፍጠርና ታሪክን በመበረዝና ተጋነው የሚነገሩት አክሱማውያንና እስልምናን በተመለከተ የሚነገሩ አፈ-ታሪኮች ትክክለኛ ምንጫቸው ከየት ነው፣ ድብቅ አጀንዳና ዓላማቸውስ ምን ሊሆን ይችላል ብለን በአጽንኦት ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡
እንዴትስ በእነዚህ ሁለት እምነቶች መካከል ለብዙዎች ምሳሌ እስኪሆን ድረስ የቆየውን አብሮ በሰላም ተከባብሮና ተዋዶ የመኖር ባሕል በሌለ ታሪክና ተጨባጭነት በሌለው ተረት ተረት ለመናድስ ለምን አስፈለገ? እንዴትስ እንዲህ በግብታዊነትና በማን አለብኝነት አንዳንድ ጽንፈኝነትና አክራሪነትን የሚያራምዱ ሰዎች በእንዲህ ዓይነቱ ታሪክን የመበረዝና የማጣመም ዘመቻ ውስጥ ለመግባት ደፈሩ?
እንዴትስ ከአክሱማውያን በኋላ በሺህ ዘመናት የጊዜ ርዝማኔ የምንገኝ ትውልዶች እንደ አክሱማውያን አባቶቻችን የሌሎችን አሳብ፣ እምነትና ፍልስፍና ለማከበር ያልቻልንበትንና ልዩነቶቻችንን በኃይልና በጉልበት ለመፍታት በተጠንቀቅ የቆምንበት የታሪክ ዝቅጠት ውስጥ ልንገኝ እንደቻልን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል… ‹‹ሀገር የጋራ ነው ሃይማኖት ግን የግል/የልብ ምስጢር ነው›› የሚለው የቆየውና ዘመናትን የተሻገረው ብሂላችን የሚነግረን ተግባራዊው እውነታ ምን እንደሆነ ቆም ብለን ልናስተውል የሚገባን ጊዜ ላይ ያለን ይመስለኛል…፡፡
በዓለማችን በሚገኙ አብዛኛው ሃይማኖቶች ዘንድ ያሉ አስተምህሮዎች ከሰዎች ሁሉ ጋር በሰላም እና በፍቅር ተከባብረንና ተስማምተን እንድንኖር የሚሰብኩና የሚያተጉን ትምህርቶችና ትዕዛዛቶች የሚያስተላልፉ ሆነው ሳሉ በምን ምክንያት በሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ተከባብሮና ተቻችሎ የቆዩ የክርስትና የእስልምና ሃይማኖቶች በመካከላቸው ጠብና ግጭት ይፈጠር ዘንድ ሌት ተቀን እየተጉ ያሉ ጽንፈኝነትንና አክራሪነትን የሚሰብኩ ግለሰቦችና ቡድኖች ወዴየት እየደሄዱ እንደሆነ ቆም ብለው እንዲያስቡ ልንነግራቸውና ከክፉ የጥፋት መንገዳቸው ይመለሱ ዘንድ ተው ልንላቸው ጊዜው አሁንም የረፈደ አይመስለኝም፡፡
ታሪክን በማጣመምና በመበረዝ እውነትን መሸፍን፣ ማደብዘዝና ማጥፋት አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት ታሪክ ‹‹አልነጃሺ የተባለ የሰለመ ንጉሥ አልነበረም፣ አክሱማውያን የሰለሙበትም ሆነ አክሱምም የእስልምና ቅዱስ ከተማ የተባለችበትም ሆነ የምትባልበት ዘመንም ሆነ ምንም ዓይነት ተጨባጭ የሆነ ታሪካዊ ማስረጃ የለም፤ በብዙዎች ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ዘንድ ስለ ‹‹አልነጃሺ›› የሚነገረውም ታሪክ መሠረት የለሽ፣ ከባዶ ቅዠትና የጓዳ ውስጥ የፈጠራ ተረት ተረት ከመሆን ያለፈ አንድምታ እንደሌለው ከታሪክ እውቀት ሐቅ/እውነት አንጻር ለመግለጽ እንገደዳለን፡፡
ባልተደረገና ባልነበረ ታሪክ ሌሎችን በማደናገር፣ በማሳሳትና በማነሳሳት በሃይማኖት ሽፋን ድብቅ የሆነ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም ሰይፍን የታጠቁና ለመላው የሙስሊም ዓለም የፍቅር ባለውለታና ባለዕዳ ለሆኑባት በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንና በክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ አንዳንድ በአክራሪነትና በጽንፈኝነት መንፈስ ሰይፋቸውን ከሰገባቸው የመዘዙ ሙስሊም ወገኖቻችንን፡- ‹‹የወንጌል ቃል ‹‹ሰይፍን የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ!›› ይላልና ከዚህ የጥፋት መንገዳቸው ይመለሱና ለበቀል የተመዘዘ ሰይፋቸውን ወደ አፎቱ ይመልሱት ዘንድ አስረግጠን ልንነግራቸው እንወዳለን!!
ሰላም! ሻሎም!


4 comments:

  1. for the first time in the history of Awdemihiret,a good reading in the favor of Tewahedo,

    ReplyDelete
    Replies
    1. Awdemihret is always favor Tewahedo but not mk. mk is not tewahedo it is an association who try to rule out the church in its died vision.
      don't associate mk and tewahedo. tewahedo is our church.

      Delete
  2. Really no alnejashi king who becomes Muslim in Ethiopian history. what is the advantage of advertizing false history for this country as well as for our Muslim brothers? do Islam accepts writing false history? any one from true Muslim who can answer for me please?

    ReplyDelete