Monday, July 16, 2012

ሐረርና አዲሱ የዘረኝነት ምጧ

Harerena zeregenete :Click here to read in PDF
ወንድም ነኝ ከሐረር

(ሐምሌ 9 2004 ዓ.ም. ፣አውደ ምህረት/www.awdemihret.blogspot.com)በዘመናት ሀሉ መካከል ዘረኝነት ዘረኝነት ቋሚ የኢትዮጵያ ችግር ሆኖ ቀጥሏል። እንደ ንጉሱ አጎንብሱ በሚባልበት የፖለቲካው አለም ያለው ዘረኝነት ምንጩ የኔ ዘር ለምን ከስልጣን ወረደ የገሌ ዘር እንዶት አገር ይመራል ከነገስኩ ዘሬን ላንግስ ከሚሉ ስጋዊ ምክንያቶች የሚመነጭ ነው። ፖለቲካው ከስህተቱ እየተማረ ነገሮችን ማስተካከል የሚችልበት እድሉን ለመጠቀም አያመነታም። እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ዘረኝነት የትም እንደማያደርስ ሲረዳ ዘረኝነትን በታማኝነት ተክቶ ለፖለቲካው ሲስተም ታማኝ ኦከሆኑ ድረስ ከየትኛውም ብሔር የተገኘውን ሰው ይጠቀማል። ፖለቲካ ዘረኝነትን ቢያስብ ትክክል ነው ባይባልም አይደንቅም። ፖለቲካ የአለም ስርዓት ነው ዘረኝነትም አለማዊነት ነው።
ዘረኝነት አገሬ በሰማይ ነው ብላ ልታምን በሚገባት በቤተክርስቲያን ሲከሰት ግን ኃዘናችን ከፍ ይላል። ዛሬ ዛሬ ከተወሰኑ አገልጋዮች በቀር ከጳጳስ እስከ ዲያቆን ሀገሩ በሰማይ ሳይሆን ወይ በትግራይ ወይ በጎንደር አሊያም በጎጃም… ነው። የእግዚአብሔርን ሥራ በእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን በብሔራቸው መነጽርነት የሚመዝኑ አገልጋዮች ለቤተክርስቲያኒቱ ፈተና ሆነውባታል። የብሔራቸው ሰው በዙሪያቸው እስከተከማቸ ድረስ የትኛውንም የእግዚአብሔር ቃልና ሓሳብ ለመጋፋት ወደ ኋላ አይሉም። 

የዘረኝነት ጉዳይ ፈፅሞ ሊታይባት በማይገባት ቅድስት ቤ/ክ ጓዙን ጠቅልሎ ከገባም ሰነባብቷል፡፡ ዘረኝነቱን እያስፋፉት ያሉት ደግሞ ካህናት መሆናቸው እድሜውን በቤ/ክ እንዲያራዝም ረድቶታል፡፡ ቤ/ክንንም እያስተዳደሩ ወይም እያገለገሉት ያሉትም ደግሞ እነዚሁ ዘረኞች ናቸው፡፡
ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ደግሞ አሁን አሁን በሐረር እየሆነ ያለው ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ሰሞን አቡነ ሳሙኤል ቅዱስ ፓትርያርኩን እንደዚያ ያስቸገሩዋቸው ሰዓት “እንዴት ሲደረግ” በማለት በአቡነ ሳሙኤል ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ያሰሙ እንደነበር እናስታሳለን፡፡ አሁን በግንቦቱ ሲኖዶስ ደግሞ አቡነ አብርሃም ፊታውራሪ ሆነው ተተኩ፡፡ እነኚሁ ካህናት አሁን ደግሞ አሰላለፋቸውን ከልሰው “አቡነ አብርሃም ወይም ሞት” እያሉ ይገኛሉ፡፡ በዘር የአባ አብርሃም የሀገር ልጆች የሆኑ እነዚህ ካህናት “አባ ጳውሎስ አልኮስኩሰው ያበላሹትን ጀግናው አባ አብርሃም አስተካከሉት” ሲሉ መደመጣቸው ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል፡፡
መቼ ይህ ብቻ፡፡ በአቡነ ያሬድ ጊዜ “ወንጌል ታጠፈ” ብለው ምዕመናንን ሲቀሰቅሱና ከጀርባ ሆነው ሲያስተባብሩ እንዳልነበር አሁን በወንጌል አገልግሎት ዙሪያ ምንም ችግር እንደሌለ እና ችግር እንዳለ በማስመሰል ቅስቀሳ ለማድረግ የሚፈልጉት ግን የመናፍቃኑ የውስጥ አርበኛ ሆነው በመስራት ላይ ያሉ ካህናት ናቸውና አትስሟቸው ሲሉ አይናቸውን በጨው ታጥበው ሊነግሩን ሲሞክሩ የምንላቸው ነገር ቢኖር እኛስ ታዘብናችሁ ነው፡፡
ሌላው የሚገርመው ጉዳይ በዐውደ ምህረቱም አገልግሎት የስብከትና የዝማሬ ለውጥ አድርገው ስናይ “እነዚህ ሰዎች የሚያገለግሉት አቡነ አብርሃምን ነው ወይስ እግዚአብሔርን? ምን ነክቶአቸዋለዋል?” እንድንል አድርጎናል፡፡ ከሰሞኑን አቡነ አብርሃም ዝማሬን አስመልክቶ የኪዳነ ምህረት ዕለት ባደረጉት ንግግር “የእኛ ያልሆነውን ከራሳችን ጋር መቀላቀል አይሆንም ወይ ንስሃ ገብቶ መመለስ ነው እንጂ” በማለት ያራመዱትን አቋም ሰምቶ እንዳልሰማ ከመሆን ባለፈ “የዝማሬ ጉዳይ ዋና ጉዳይ አይደለም” ሲሉ በድፍረት ሲናገሩ ስንሰማ ለእኛስ የዝማሬ ጉዳይ ዋና ጉዳይ ነው፤ የምንዘምረው ለሞተልን ጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ለእርሳቸው አይደለም እኛ ግን ታዘብናችሁ፡፡
እነኚህ ሰዎች አቡነ አብርሃም ስብሰባ ጠርተው ከተገኙ በስብሰባው የመገኘት ዋና አላማቸው ከስብሰባው ለሚገኘው የመጨረሻ ውጤት ማማር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ ሳይሆን የአባ አብርሃም አቋም በስብሰባው ላይ ምንም ይሁን ምን አቋማቸውን መደገፍ አንዲሁም የሚቃወም ካለ ደግሞ በፍጥነት መልሶ በመቋወም እሱም ሆነ ሌላ ለመቃወም ያሰበ ካለ እንዳይናገር በማሸማቀቅ ለሀገራቸው ልጅ ጥበቃ ማድረግ ነው፡፡ ሰሞኑንም እየተነሳ ባለው ተቃውሞ ከአባ አብርሃም የበለጠ የታመሙት እነሱ ናቸው፡፡ አባ አብርሃም ሰባኪያኑን መውቀስ ሲጀምሩ ቀበል አድረገው ይጨርሱታል “እንዳው ይሁን ብለን ነው እንጂ ሰባኪ ነን ብለው የሚመጡት እንኳን ሊያስተመሩ ውዳሴ ማርያም እንኳን በቅጡ የማይደግሙ ናቸው” በማለት መድረክ ተገኘ ብለው አብረው ሲያወግዙ ስብሰባው ያበቃና ይበተናል፡፡ ሰባክያኑ ዘማርያኑ ካልመጡልን እንዳላሉ፣ አብረው እንዳልቀደሱ፣ ማህሌቱን አብረው እንዳላደመቁት ዛሬ ደግሞ በመቅደሱ አገልግሎት ፈፅሞ እንደማይሳተፉና መሳተፍ እንደማይችሉ ሲነገር ስንሰማ ምን እንላለን ፤ትርፉ ትዝብት ነው፡፡
እንግዲህ ምን እየተኮነ ነው? እርግጥ አቡነ አብርሃምን መደገፍ አያስፈልግም እየተባለ አይደለም፡፡ መደገፍማ ያስፈልጋል፡፡ መደገፍ ያለብን ግን የማቅ አገልጋይነታቸውን እንዲገፉበት ሳይሆን የእግዚአብሔርን አደራ በታማኝነት እንዲወጡ፤ መልካም የሆነውን እነዲያዘወትሩትና ስህተት የሆነውን ከመናገርም ሆነ ከመተግበር እነዲታረሙም ጭምር ነው፡፡ እርሳቸው በተክለ ሃይማኖት ቤ/ክ አገልጋዮቹን ምዕመናን ፊት እንደተናገሩት ባይሆንም ወዳጅ ነኝ ባይ ለብቻቸውም ቢሆን የማያዋጣውን አያዋጣም ብሎ መናገሩና መመካከሩ ግን ለሁሉም ጠቃሚ ነው እንላለን፡፡
ካህን ዘረኛ ሊሆን አይገባውም፡፡ እርሱ የክርስቶስ አገልጋይ ነውና፡፡ ክርስቶስ በደም እንጂ በዘር ቤ/ክንን አልመሰረተም፡፡ አዎን!“አዕይንተ እግዚአብሔር ካህናት” ዘረኞች ሊሆኑ አይገባም፡፡ ይህ ሲባል ግን ሁሉም ዘረኞች ናቸው እየተባለ አይደለም ይልቁንም ዘረኛ ያልሆኑና “ሁሉን በክርስቶስ አውቃለሁ” የሚለውን የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን መልዕክት የአገልግሎታቸው መርህ ያደረጉት እንዳሉ ሊዘነጋ የሚቻል አይደለም፤ እነርሱን ቁጥራቸውን እንደ አሸዋ ያብዛልን፡፡ ዘረኝነትን የምታራምዱቱ ግን ዘረኝነት ካድሬ ቢያስብል እንጂ ካህን አያስብልምና የዘረኝነቱን ካባ አውልቃችሁ “ክርስቶስን ልበሱት”፡፡ አለበለዚያ ትዝብት ነው ትርፉ፡፡
አዎን እኛ እንታዘባችኋለን ቤተክርስቲያን ትታዘባችሁዋለች ምዕመኑ ይታዘባችኋል ከሁሉ በላይ የዘርን ካባ አውልቃችሁ አገራችሁ በሰማይ ነው የሚለውን ቃል የሕይታችሁ መርህ እንድታደርጉ ያዘዛችሁ ጌታ ያዝንባችኋል። አቡነ አብርሃም ዛሬ አሉ ነገ ይሄዳሉ። የሀረር ህዝብ ግን ሁሌም ከእናንተ ጋር ነው። ለዘራችሁ ብላችሁ እውነትን አትግፉ። የማትገዳደሩትን ታግላችሁ የማታሸንፉትን የእግዚአብሔር እውነት ለዘራችሁ ስትሉ ለመሰዋት አትሞክሩ። ዘር ከልጓም እንደሚስብ ብናውቅም በእግዚአብሔር ቤት ላይ እና በእግዚአብሔር ቃል ላይ ግን አይሰራም። በሰማዩ መንግስትም አመድ አፋሽ ያድርጋችኋል።  
                                   
 ይቆየን!

No comments:

Post a Comment