Tuesday, July 24, 2012

በአቡነ ጳውሎስ ስም የኤች አይ ቪ ኤድስ እና ቲቪ በሽታ ማገገሚያ ማዕከል ሊገነባ ነው

Abun pawlos center: Click Here To Read In PDF
  • “እግዚአብሔር ያዘዘን የማይለወጠው የማይሻሻለው ቃል ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚል ነው።”                                                                                         ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ
  • ማዕከሉ  በሁለት መቶ ሚሊየን ብር ይገነባል።

(ሐምሌ 17 2004 ዓ.ም.፣ ዐውደ ምሕረት/www.awdemihret.blogspot.com)በትናንትናው ዕለት በሸራተን አዲስ የአቡነ ጳውሎስን 20ኛ አመት በዓለ ሲመት አስመልክቶ በራእይ ለትውልድ በጎ አድራጎት ድርጅት  በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የኤች አይ ቪ ኤድስ እና ቲቪ በሽታ ማገገሚያ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ። 

ራዕይ ለትውልድ ባዘጋጀው በዚህ የእራት ግብዣ ላይ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ሚኒስትሮች ሌሎች ባለስልጣናት የጠቅላይ ቤተክህነት ሰራተኞች ባለሀብቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ ሰዎች የተገኙ ሲሆን የእለቱ የክብር እንግዳ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ነበሩ። ቅዱስነታቸው በቦታው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከ10 ላይ በብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ታጅበው የደረሱ ሲሆን እርሳቸው የክብር ቦታቸውን እንደያዙ መርሐ ግብሩ በራዕይ ለትውልድ ፕሬዝዳንት ብሌን ገነነ ንግግር ተከፍቷል። ወጣት ብሌን በንግግሯ ስለራዕይ ለትውልድ መጠነኛ መግለጫ የሰጠች ሲሆን ድርጅቱ በሴቶችና በሕጻናት ላይ እንደሚሰራና እና እስካሁን ድረስም እያደረገ ባለው አስተዋጽኦ ደስተኛ መሆንዋን ገልጻ እንዲህ ያለውን ዝግጅት ያዘጋጁበት ምክንያት ለሀገራቸውን እና ለህዝባቸው መልካም ስራ ሰርተው ላለፉ ኢትዮጵያዊያን መታሰቢያ እንዲሆን ታስቦ መሆኑን ግልጻለች። 

ከወጣትዋ ንግግርም በኋላ ራዕይ ለትውልድ ያዘጋጀው የቅዱስነታቸውን ሕይወትና አገልግሎት የሚያስቃኝ የ25 ደቂቃ ዶክሜንተሪ መታየት የጀመረ ሲሆን ፊልሙ የቅዱስነታቸውን የልጅነት ታሪክ፣ በአሰር ቤት ያሳለፉትን ጊዜና የመታሰራቸውን ምክንያት፣ በትምህርት ላይ ስላሳለፉት ጊዜ፣ በፓትርያርክነት ዘመናቸው ስለሰሩት ስራ እና ስለተሸለሙት ሽልማቶች በአጭሩ የሚያሳይ ነበር። በተለይም በስደተኞች ጉዳይ ላይ ለሰጡት ትኩረትና ለሰሩት ስራ በኖርዌይ መንግስት የተሸለሙት የናንሰን ሽልማት ከአፍሪካ ቅዱስነታቸውን ጨምሮ 4ት ሰዎች ብቻ እንደተሸለሙት እና የኖርዌይ መንግስትም ለስራቸው ያለውን ከበሬታ ያሳየ መሆኑ ተገልጿል። የፊልሙ ቅንብር የተዋጣለት ሊባል የሚችል ቢሆንም 15 ደቂቃ እንደታየ ድምጹ አልሰማ በማለቱ ተቋርጦ በእለቱ የተገኙ እንግዶች ንግግር እንዲያደርጉ ተደርጓል።
በእለቱ የተገኙት የሃይማኖት መሪዎች ተራ በተራ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ቅድሚያውን የወሰዱት የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት መሪው ቄስ ደረጀ ድንበሩ ናቸው። በንግግራቸው “በ20ኛ ዓመት በዓልዎ ላይ ተገኝቼ የቤተክርስቲያንን ደስታ ሳቀርብ ደስታዬ ወሰን የለውም። በዓሉ የሁላችን ነው። የ20 ዓመት መልካም ግንኙነት አለን። ትላልቅ ሥራዎችን አብረን ሰርተናል። ቅዱስነትዎ አብያተ ክርስቲያናት አብረው እንዲሰሩ ያደረጉት ትግልና ጥረት የሚያኮራ ነው። በሰላም ጉዳዮችና በማህበራዊ አገልግሎት አብረን ሰርተናል። በተለይም በእርቅ ጉዳይ ሰፊና የሚያኮራ ስራ አብረን ሰርተናል። የሰራነው መልካም ቢሆንም ከፊት ደግሞ ታላቅ ስራ ይጠብቀናል።
ቅዱስነትዋ ይፍቀዱልኝ እና አንድ ጥያቆ ልጠይቅዋት እወዳለሁ ፈቃድዎ እንደሚሆንም ተስፋ አደርጋለሁ” ያሉት ቄስ ደረጀ ጥያቄያቸውን እንዲህ ሲሉ አቅርበዋል። “ከዚህ በኃላ ባሉት አመታት የሁላችን አባት ሆነው ከፊት ሆነው እየመሩን አብረን እንደንሰራ ለመጠየቅ እወዳለሁ” ብለዋል። በመቀጥልም “ይህቺን አንዲት አገር ኢትዮጵያን እንደ መንፈሳዊ አባት ማገልገል ከሁላችን ይጠበቃል። ስለዚህም በጸሎትና በመንፈሳዊ እንቅስቃሴ ከፊት ሆነው ይመሩናል ብለን እንጠብቃለን። እኛም አንድ ቀን በእድሜያችን ቆመን ቅዱስ አባታችን በህዝባችን በመካከላችን ለእኛም ይህን አደረጉ የምንልበት ዘመን ያድርግልን።” ሲሉ ንግግራቸውን አጠቃለዋል። በእስልምና ሃይማኖት ስምም ለረዥም ጊዜ የእስልምና ምክር ቤቱን የመሩት ሼክ አልያስ ሬድዋን ንግግር ያደረጉ ሲሆን “ቅዱስ አባታችን አብረን በሰራንባቸው ወቅት ጠንካራ ሰውነታቸውን አይቻለሁ። እንኳን ለዚህ አበቃዎት ለማለት እወዳለሁ።  በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት እና በ97 ምርጫ በነበሩ ችግሮች በጅማና በወሎ ችግሮች በነበሩበት ወቅት ከእንዲህ ያለ ሰው ጋር በብስለት መምራት ከሚችሉ ሰው ጋራ አብሮ በመስራት አገራችንን አንድ አድርገናል። ትልቁም ስራ የእሳቸው ነው። ምስክርነቴም ይህ ነው።
አውሮፓ በተለያየ ጊዜ አብረን ሄደናል በተለይም ጀርመን በሄድን ጊዜ የኢትዮጵያን ተምሳሌትነት ሲያስረዱ ኦርቶዶክሱን ብቻ ሳይሆን መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወክለው ሁሉም ተቻችሎ ኗሪነቱን አና በአንድ ድንኳን አዳሪነቱን በጥሩ ሁኔታ ገልጠዋል።” በማለት ንግግራቸውን አጠናቀዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ብርሃነ ኢየሱስም “ የሃይማኖት አባቶች ቅዱስነታቸው ለሰላም ያደረጉትን አስተዋጽኦ ተናግረዋል እኔም እደግመዋለሁ። ቅዱስነታቸው ለሰላም ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ለኢትዮጵያ በሃይማኖቶች መካከል ተከባብሮ ተቻችሎ ስለመኖር ያደረጉት ታላቅ አስተዋጽኦ ትልቅ ብቻ አይደለም በኢትዮጵያም ብቻ የተወሰነ አይደለም። በመላው ዓለም ቅዱስነታቸው ኢትዮጵያን የመቻቻል እና የመፈቃቀድ አርአያ መሆንዋን ነግረው አሳምነዋል።” ካሉ በኃላ እዚህ ላላችሁ የውጭ አገር ሰዎችም ምን እያልኩ እንደሆነ በእንግሊዝኛ ልነግራቸው እፈልጋለሁ በማለት “ his holiness abune pawlos patriarch of Ethiopia is celebrating 20 years as great Religious leader of Ethiopia. It is 20 years but before that he suffered a lot especially under the last regime where he had to undergo 7 years in prison. I think that is a greatest university he attended on earth….” በማለት የእስር ቤት ቆይታቸው ከሁሉ የላቀ ትምህርት ቤት መሆኑን ከገለጹ በኋላ ወደ አማርና ቋንቋ ተመልሰው “…ወደፊትም ይህንን ስራዎትን በመቀጠል የሰላም አባት እንዲያደርጎት እግዚአብሔርን እለምናለሁ።” ብለዋል።
የፕሮግራሙ አዘጋጅ ራዕይ ለትውልድ ከ1000 ሺህ በላይ ሴት ተማሪዎችን በወር 200 ብር በመስጠት እያስተማረ ያለ ሲሆን የህይወት ልምድ ባለቸው ትላልቅ ሰዎችም ያስመክራቸዋል። የራዕዩ ባለቤት ተብሎ የተገለጠው ወጣት አቶ ያሬድ ግርማ ጉልበት ያለው እና ጠቃሚ ንግግር ያደረገ ሲሆን የምሽቱ ወሳኝ አላማና የፕሮግራሙን መዘጋጀት ምክንያት ሲያብራራ “ይህ ምሽት የምንከባበርበት ምሽት ነው። እኔ ዲያቆን አይደለሁም ቄስ አይደለሁም እንዲሁ ብቻ በሀገሬ አንድ አስተዋጽኦ ማድረግ የምፈልግ ሰው ነኝ። በአውነት ነው የምለው እኚህን አባት በማግኘቴ እንደ እኔ የታደለ ሰው የለም። እንዳለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያዊያን የማክበር ባህል የለንም። ትንሽ ጥፋት ካየን የማዋረድ እና የማንቋሸሽ ባህል ነው ያለን። እናመሰግናለን ማለትን ባህላችን ልናደርገው ይገባል። ራዕይ ለለትውልድ ከአንድም ፈረንጅ ብር ሳይቀበል ኢትዮጵያዊያን ብቻ ስፖንሰር የሚያድርጉት 1000 ሺህ ሴቶችን እንረዳለን። ባለሀብቶች ፎቅ መስራታችሁ ጥሩ ነው። ግን ሰው መስራት ከዛ ይበልጣል። ሰው ላይም ኢንቨስት አድርጉ፡፡” ካለ በኋላ የእለቱ ዋና ጉዳይ ወደ ሆነው ርዕስ በማምራት 200,000,000.00 ሚሊዩን ብር የሚያስወጣ ፕሮጀክት አስተዋውቋል። ፕሮጀክቱ በአቡነ ጳውሎስ ስም የሚጠራ ሆኖ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቲቪ በሽታ ማገገሚያ ማዕከል እንደሚሆንም ጠቅሟል። ቅዱስነታቸው የሁሉም ኢትዮጵያዊ አባት ናቸው። ይህንን ፕሮጀክት ለቅዱስነታቸው 20ኛ ዓመት በዓለ ሲመት እንደ ስጦታ እናበረክትላቸዋለን። ይህም ባለታሪኮቻችንን በህይወት እያሉ የምናከብርበት መንገድ ነው። በቅዱስነታቸው ስም ይሰየም እንጂ የሚታከሙበት የኢትዮጵያ ድሆች ናቸው። ከጎናችን ላሉት ለትላልቅ ሰዎቻችን ተገቢውን ክብር እንስጥ።” ሲል የፕሮጀክቱን አላማ አስረድቷል።
ንግግሩን ተደጋጋሚ ጭብጨባ እያቋረጠው የቀጠለው ያሬድ ቅዱስነታቸውንም “እጅግ እናከብርዎታለን እንወዶታለን። ለሀገሪቱ ባደረጉት አስተዋጽዖ የሚከበሩት ዛሬ አይደለም። እግዚአብሔር ቀን ይሰጥዎታል።” ብሏቸዋል። ስለ አቡነ ጳውሎስ ስራዎችም ሲናገር “እሳቸውን ያሰሩዋቸውን ሰዎች ከእስር አስፈትተዋል። ኤች አይ ቪን በተመለከተ እድሜና ፕሮቶኮልን ተሻግረው ብዙ ስራ ሰርተዋል። ለስደተኞች ተገቢውን አስተዋጽዖ አድርገዋል ስለዚህም አክብሮት ይገባቸዋል” ብሏል።
እግረ መንገዱን መከባበርን በተመለከተ በስራ አጋጣሚ ሄዶ ያያቸውን አንዳንድ አገሮች በማንሳት ለታላላቅ ሰዎቻቸው የሚያደርጉትን ነገር አስታውሶ “እኛስ ለምንድን ነው? ዩንቨርሲቲዎቻችንን በታላላቅ ሰዎቻችን ስም የማንሰይመው? እኛ ያላከበርነውን ታሪክ ማን ሊያከብርልን ነው? ዩንቨርሲቲን በከተማ ስም መሰየም ያለው ታሪካዊ ፋይዳ ምንድን ነው? ለምንድን ነው የአዲስ አበባውን ኤርፖርት በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ስም የማንሰይመው? ለምንድንስ ነው ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ቤተመንግስታቸውን ሰጥተው ያቋቋሙት ዩንቨርሲቲ በስማቸው ተመልሶ የማይሰየመው? ታላላቆቹን የማያደንቅ ሀገር ለመገንባት አንፈልግም። ታላላቅ ሰዎቻችንን ካላከበርን አገራችንን ማሳደግ አንችልም። ስለዚህ ክብር ለሚገባቸው ሁሉ ክብርን እንስጥ። የዛሬው የራት ግብዣም አላማ ይሄ ነው።” ሲል ቤቱ በደመቀ ጭብጨባ ተቀብሎታል። እንዲህ ያለውን ሀሳብ ስላነሳም ከፊውዳሉ ማኅበረሰብ ጋር እንዳይደመር በመስጋት ስለራሱ የተወሰነ ነገር ያወራው ያሬድ “እንዲህ በማለቴ የፊውዳል ርዝራዥ እንዳታደርጉኝ የአንድ 10 አለቃ ልጅ ነኝ።” ሲል ተናግሯል።
በመቀጠልም “በቅዱስነታቸው ስም ማዕከል የምንገነባው የቤተክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ ስለሆኑ አይደለም። ለኢትዮጵያ መልካም ስራ ስለሰሩ ነው። ማዕከሉ የሚገነባው ለኢትዮጵያዊያን ድሆች ነው። እኚህ ሰው የእኛ አባት ናቸው የቤተክርስቲያኒቱ አባት ናቸው ብለን ነው ይህን ፕሮጀክት ልንገነባ ያለነው። ከተሰማን ከፍተኛ ደስታም የተነሳ ቅዱስነታቸውን የራዕይ ለተውልድ የክብር ፕሬዚደንት አድርገናቸዋል። ይህን ያደረግነው ለእሳቸው ጥቅም አይደለም ለእኛ ጥቅም ነው። ዛሬ የምንሾማቸው ዝቅ ብለው የኢትዮጵያን ህዝብ እንዲያገለግሉ ነው።…ባገኘነው አጋጣሚ ትልልቅ ሰዎችን ማክበር ብንለምድ ጥሩ ነው።” በማለት ንግግሩን አጠናቋል።
ከዚህ በኃላ የተቋረጠው ፊልም ቀጥሎ ታይቷል።
በፊልሙ ውስጥ  ያሰሩዋቸው ያንገላቱዋቸውን የደርግ ባለስልጣነት ለምን ለማስፈታት እንደፈለጉ ተጠይቀው ቅዱስነታቸው ሲመልሱ “እግዚአብሔር ያዘዘን የማይለወጠው የማይሻሻለው ቃል ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚል ነው።” ብለው የሰጡት መልስ በስፍራው የነበረውን በርካታ ህዝብ ልብ የገዛ ነበር። ፊልሙ እንዳለቀ የዕለቱ የክብር እንግዳ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ንግግር እንዲያደርጉ ተጋብዘው ንግግር አድርገዋል።
ንግግር አላበዛም አጠር አድርጌ ሀሳቤን እቋጫለሁ በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ቅዱስነታቸው ለሀገርና ለህዝብ በሚያስፈልጉ ነገሮች ሁሉ ህዝባቸውን እያገለገሉ ነው ያሉት። ስላደረጉት ነገር በመንገስት እና በራሴም ስም አመሰግናቸዋለሁ። 20 ዓመት በማንኛውም ኃላፊነት ላይ ሆኖ ማገልግለ ከባድ መሆኑን እናውቃለን። ኃላፊነት በባህሪው ሰፊ እና ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው። አባታችን በውስጣቸው ካለው መንፈሳዊ ኃላፊነት አንጻር ያደረጉት አስተዋጽኦ ታላቅ ነው። ከእሳቸው ጋር ለመስራት መንግስት ሁሌም ዝግጁ ነው።” ብለዋል።
በመቀጠልም በወቅቱ በሀገራችን ያለውን የሃይማኖት አክራሪነት ችግር በማንሳት የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ በፊት የነበረውን የፍቅር እና የመቻቻል ኑሮ እንዲቀጥልበት እና የአክራሪነት መንፈስን እንዲቃወም ጥሪ አድርገው ንግግራቸውን ፈጽመዋል።
በመቀጠል ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጰውሎስ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙ ሲሆን እሳቸውም “እኔ ለመናገር የምጋበዝበት ጊዜ አልነበረም። የተነገረውን ሁሉ መሸከም ያቅታል። ሁላችሁም የተናገራችሁት ከአቅሜ በላይ ነው።  ሀገራችን ከጥንት ጀምሮ ሃይማኖተኛ የሆነች ሀገር፣ በማስተዋል የምትራመድ ህዝቡም የህሊና ዳኝነት ያለው ነው። ሁላችንንም እግዚአብሔርን ስለምንፈራ በየስርዓታችን በየባህላችን መልካም መቀባበል አለን። ይህንን እግዚአብሔር የሰጠን ሰፊ እድል አድርጌ ነው የምወስደው። በስሜ ለተቋቋመው ድርጅትም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሩን አቶ ቴዎድሮስን የበላይ ጠባቂ እና ተቆጣጣሪ አድርጌ ሾሜያቸዋለሁ። ለሁላችሁም እግዚአብሔር ይስጣችሁ።” በማለት ንግግራቸውን አጠናቀዋል።
በስተመጨረሻም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሩ አቶ ቴዎድሮስ ንግግር እንዲያደርጉ ተጋብዘው ንግግር አድርገዋል። ንግግራቸውንም ሲጀምሩም “በእናንተ እና በእራት መካከል ስለቆምኩ ብዙ መናገር አልፈልግም” በማለት በስፍራው የነበረውን ሰው ፈገግ አሰኝተዋል። በመቀጠልም “ሁለት ነገር እላለሁ
የመጀመሪያው እድሉን ስላገኘሁ ደስ ተሰኝቻለሁ እንዲሁም ለቅዱስነታቸው እንኳን ደስ አሎት እላለሁ
ሁለተኛው ደግሞ ዛሬ ከእናንተ ጋር ስለዚህ ራዕይ ሰምቻለሁ። ዛሬውኑም ከቅዱስ አባታችን ሀላፊነት ተሰጥቶኛል። እምቢ ለማለት ስላማልችል የተቻለኝን ያህል ለማድረግ ቃል እገባለሁ።” ብለዋል።
የኤች አይቪ ኤድስ ተቪ በሽታ ማገገሚያ ማዕከልን ዲዛይን ያደረጉት አርክቴክት አቶ በእግዚአብሔር አለበል ያለምንን ክፍያ የሰሩት ስራ እጅግ የሚያስመሰግናቸው ነው። መተባበር እና መደጋገፍ ካለም በቀላሉ ብዙ ነገር ማድረግ እንደሚቻልም ያሳየ ስራ ነው።
ዝግጅቱን ያዘጋጀው ራዕይ ለትውልድም ተገቢ ምስጋና ይገባዋል። ከሁሉም በላይ ግን አቶ ያሬድ ግርማ ስለመከባበር የተናገረው ንግግር ትልቅ ትኩረት የሚገባው ነው።


መከባበር ለመንፈሳዊ ሞራል እድገት መከባበር የስነምግባር እሴቶችን ለመጠበቅ መከባበር ለባለታሪኮቻችንን ተገቢ ክብር ለመስጠት እጀግ አስፈላጊ ነገር ነው። በኦሪት ዘሌዋውያም ም 19፥32 ላይ “በሽበታሙ ፊት ተነሣ፥ ሽማግሌውንም አክብር፥ አምላክህንም ፍራ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” የሚል አምላካዊ ቃል አለ። ከላይ ለሆነው ሰማያዊ ሀሳብ ከምድር የሆነ መታዘዝ ያስፈልጋል።
 ራዕይ ለትውልድ የተባለው ድርጅት የሚሰራውን ስራ በተመለከተ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ባይኖረንም በወገኖች መካከል መከባበርን ለመፍጠር የሚያደርገው እንቅስቃሴ ግን አስደስቶናል።  ሌላው ቢቀር እንኳ እግዚአብሔር አምላክ በእድሜ የሚያስተምራቸው ነገር አለና ለዕድሜ ባለጸጋዎቻችን እና በታሪክ አጋጣሚ የሚታይ የስራና የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ የታደሙ አባቶቻችንን ልናከብራቸው ይገባል። ሊታወሱ የሚገባቸውን አባቶች አትርሱ የምትከፍቷቸውን አዳዲስ ዩንቨርሲቲዎች  እና ተቋማት በታላላቅ ሰዎቻችን ስም ሰይሙ። ታሪክ ምንም ብንገፋው ተፍቆ መውደቅ አይችልም። ጥቃቅኑን ስህተት እየነቀስን የባለታሪኮቻችንን ስም ከማጉደፍ ይልቅ የሚገባቸውን ቦታ ሰጥተን እናክብራቸው። የሰማዩና የምድሩ ጌታ ህያዉ ንጉስ ኢየሱስ ክርስቶስም ያዘዘን እንዲህ ብሎ ነው። “ትእዛዙን ታውቃለህ፥ …አባትህንና እናትህን አክብር” ቅዱስ ጳውሎስም ይህንኑ ቃል ሲያስረግጥ እንዲህ በሚል የፍቅር ድምጽ ታግዞ ነው። “መልካምም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት።”




 


  

8 comments:

  1. ለእውነትኛ ተዋህዶ ልጆች እንኳን ደስ ያላች!!!
    ደስ የምል በጎ ስራ ነው። በምድራችን ላይ ማንም ፍጹም የለም።ፍጹም አንድ ሰማያዊ እግዚአብሔር ነው። ብፁዕነታቸው ያደረጉት እውነተኛ ሥራ በራሱ እራሱን ይገልጻል።እኛንም ደስ አሰኝቶናል።እሳቸውንም እንኳን ደስ አላቸው።መላው እውነተኛውንም የተዋህዶ ሕዝቦች እንኳን ደስ ያላችሁ፡፤ባለ ራዕዎችን ለሀገር ለወገን ለሀይማኖት የሚጠቅም ስራ ሰርቶ ማለፍ እጅ ደስ ያሰኛል። አባትን ማክበር ያስመሰግናል ያስመርቃል በእግዚአብሔርም ፍትም ሰዎች የማያዩትን ዋጋ በሰማይ ያሰጣል;፡ሰማያዊ አባታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በስጋ ተገልጦ በመጣበት ዘመንም ሰዎች ስራቸው ክፉ ስለነበረ አልወደዱትን ነበር። መዳን የፈለጉት ሁሉ ግን ይወዱትና ይከተሉት ነበር። መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ምዕራፍ 2 ቁ 23 ታላቁ ነቢይና አባት ኤልሳዕ የሰደቡትን ሰዎችና ልጆች በእግዚአብሔር ስም ረገማቸው፦ በመንገድም ሲወጣ ብላቴኖች ከከተማይቱ ወጥተው። አንተ መላጣ፥ ውጣ፤ አንተ መላጣ፥ ውጣ ብለው አፌዙበት። ዘወርም ብሎ አያቸው፥ በእግዚአብሔርም ስም ረገማቸው፤ ከዱርም ሁለት ድቦች ወጥተው ከብላቴኖች አርባ ሁለቱን ሰባበሩአቸ።የአለም ምኞት እና የፖለትካ ህይወት ያሰከራቸው ማቅና ተከታዮቹ ብሰዱዋቸውም እግዚአብሔር ከፍ ካደረገ ሰው አያወርደውም ይልቁ ስለ እራስ ሐጢአት በንስሐ በፍቅር እግዚአብሔር ወደ ደጅ መመላልስ ይጥቅማል።ሰዎች ብጠሉን እግዝአብሔር ከወደድ ለምን እንታገላለን? ፍርዱን እግዚአብሔር ይሰጥ የለምን? ወይንስ የምናመልከው አምላክ ሀይል የለውም ብለን ነው በጡቻችን የምንመካው። ሁሉ ያልፋል የእግዚአብሔር ቃል ግን ለዘለዓለም ይኖራል። እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ብጹዕነታቸውን ለዚህ ክብር አበቃቸው።እግዚአብሔር ይህችን ጥንታዊት ሀይማኖትና ሀገር ይባርካት፡ ይጠብቃት አሜን። ከአሜሪካ ምድር

    ReplyDelete
  2. የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ዝም ብሎ ማየት ከሁሉ ይበልጣል። አንዱ የጠላውን ለሌላው እንድወደው ያደርጋል። ሥራው ታላቅ ነው። ስሙ ለዘለዓለም ይመስገን። ሰዎች ለምን ሰዎችን ይጠላሉ ብባል የራሱ ክፉ ስራው ለራሱ ስለማታወቀው ነው አሉ ይባላል።

    ReplyDelete
  3. ለትውልድ ምሳሌ የሚሆን ነገር እንዲህ መሥራት ስምን ያስጠራልይባል የለ?ለእኒህ ቅዱስ አባታችን ሲያንሳቸው ነው ብዬ ነው የምለው በዘመነ ፕትርክናቸው በተለይ የሥላሴ አማኞችን ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጋር በመሆን ማሰባሰባቸውና ፈቃደኛ መሆናቸው ታሪካዊና አነጋጋሪ ሆኖአል::አስገራሚም ነው::ትናንትና ድንጋይ ሲወራወሩ የነበሩት ክፍሎች ማለት ነው በአንድ ጠረጲዛ ዙሪያ ሆነው ተቀምጠው አብረው እንጀራ እንዲቆርሱ ማድረግ እንዲጨባበጡ ማድረግ የጎሪጥ መታየታቸው በቅቶ ለሀገር ልማት እንዲሰሩ ማበረታታት የእርሳቸውም አስተዋጽኦ አለበት::ይህን ያናደደውና ነገር እየፈለገ የሚቆሰቍሰው አጥፊ ተልእኮ ያለው ክፍ ቢኖርም ቤተክርስቲያኒቱ እስከአሁን በጽናት እየተፋለመችው ይገኛል::እኒህ ቅዱስ አባት ለሰላም ታችችሎ በፍቅር መኖር ተግባብቶ መነጋገር መፍትሔ እንደሚያመጣ ደጋግመው በመናገር በየመድረኩ ምክር ሲሰጡ ተመልክተናል::ሰምተናል::አባት እንዲህ ነው የክፉ ሰዎችን ታሪክ እየዘከርን እንደምናወጣ የመልካም ሰዎችንም ማውጣት በስማቸው በሕይወት እያሉ ይህን የመሰለ ነገር ማሳየት ባላቸው እድሜ ላይ የሞራል ድጋፍ አድርጎ እንደሚጨምርላቸው አምላክ የጀመሩትን እንደሚያስጨርሳቸው አንጠራጠርም::እናንተም ታሪክ ነው የሰራችሁትና በርቱ መልካም ጅምርን አጉልቶ ማሳየት ደግ ነው<ክብር ለሚገባቸው ክብርን ስጡ ይል የለምን?የሚገባውን መስጠት በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ነው::ከሚገባውም አናልፍም ለአምላክ የሚሰጠውንም አንሰጥም::ገና እኛ ሀገር ግን ብዙ እንዲህ ዓይነት ነገር በተከይ በሕይወት እያሉ ስላልተለመደ ይበርታበት!
    ኒቆዲሞስ

    ReplyDelete
  4. አባዬ ገና ስምዎት አለምን ይዞራል እድሜ ይስጥዎት!!

    ReplyDelete
  5. wow, Great job. congratulation Ethiopian orthodox church.
    Good bless our country.We proud in our peoples

    ReplyDelete
  6. አስተዋይ አእምሮ ላሌው ሰው ከማየትና ከመስማት ትምህርት ይገኛል። የእኝህን ታላቅ የቤተ ክርስቲያናችን አባት እግዚአብሔር በስማቸው እያደረገው ያለው ነገር ያስገርማል ያስደንቃል።ክፉ ሰዎች ስም ስያጠፉ አምላክ ደግሞ መልካም የሚያደርጉትን ህዝቦች ያስነሳል።ድንቅ ነው ስራው። እስራኤላዊያን ክፉ ስራ ስሰሩ መልካም ሰዎቸን እያስነሳ ይመልሳቸው ነበር ። ከእስራኤላዊያን ታርክ ብዙ ቁም ነገሮቸን መማር አንችላለን።
    ወገኖቼ እስክ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ? ማህበረ ቅዱሳን አንድን ፓትርያርክ ለመስደብ ስልጣንና መብት ማን ሰጠው? ሕጌ ቤተ ክርስቲኛችን ለማደስ ማቅ በውኑ ሥልጣን አለውን? ያለንበት ትውልድ በቀላሉ የሚታለል አይደልም። ብዙ አስተዋይ አርቆ አሰብ ሰዎችን አሉ። እንድው ዝም ብሎ የእግዚአብሔር ተአምራዊ ሥራው ማየት ከሁሉ ይበልጣል። እግዚአብሔር አምላካችን ስሙ ለዘልዓልም ይመስግን

    ReplyDelete
  7. እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል ይባል የለ ለዘራፊው ማ ቅ ያልተመቹት የዘመናችን ሐዋርያ ቅዱስ ፓትርያሪክ አባ ጳዉሎስ በጠንካራ አመራራቸው ስለሚታዎቁ አላማ ባላቸው ክርሰቲያኖች ዘንድ ተወዳጅነታቸው ይቀጥላል።

    ReplyDelete