Monday, May 21, 2012

ልሳነ ሌዋታን“ደጀ ሰላም” የማን ናት?

Click here to read in PDF
በዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

አንብበው ይፍረዱ!


ይህ የሚመለከቱት መረጃ “ደጀ ሰላም” በመባል የሚታወቀውን ድረ-ገጽ/ብሎግ ሲጀመር ማኅበሩ የራሱ እንደሆነ በይፋ በድህረ ገጹ የገለጸበት/ያስተዋወቀበት በእንግሊዝኛ የድረ-ገጹ የመጀመሪያ የጽሑፉ “ሊንክ” ነበር። በተለይ deje-selam.blogspot.com/…/Ethiopia-mahberekidusan-eotc-past.html- የሚለውን ጽፈው ለመጎልጎል የሞከሩ እንደሆነ “ጭራሽ ከስፍራው ተነቅለዋል” የሚል መልስ ነው የሚያገኙ ለምን? ማኅበሩ ስራዬ ብሎ ቅድስት ቤተ-ክርስቲያንን መዋጋትና ማፈርስ ብሎም ቅድስት ቤተ-ክርስቲያንና የአባቶችን ክብር በሚነካ መልኩ ከአንድ በኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ ያደገ ፍጡር በማይጠበቅ ልቅነትና ዋልጌነትን በእጅጉ አይለው በሚታዩበት ሁኔታ ማዋረድና ማንቋሸሽ እየተያያዛው ሲመጣ ጽሑፉን ከስፍራው በመንቀል የእኔ አይደለም እስከማለት ደርሰዋል። ቀደም ሲል ሌሎች የዜና ማእከላትና ድረ ገጾች ድረ ገጹን ዋቢ አድርገው ዘገባቸውን በሚያቀርቡበት ወቅት “ባለቤትነቱ ማህበረ ቅዱሳን የሆነውን ድረ ገጽ እንደዘገበው” እያሉ በዋቢነት ይጠቀሙበት የነበረውን ምክንያት ከዚህ የተነሳ ነበር። በዚህ ድረ ገጽ ስለ ቤተ-ክርስቲያን ያልተባለና ያልተነገረ እንዲሁም ያልተዋረደና ያልተዘለፈ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን የወንጌል አገልጋይ የለም።

ውድ አንባቢ! አሁን ብሎጉ የማን ነው? በሚለውን ነጥብ ላይ ከዚህ በላይ ብዙ ማለት እርስዎን ማሰላቸት ጊዜዎትንም ማባከን ነው የሚሆነው። ታድያ የቀረበውን መረጃ አንብቦ መረዳት የሚችል ሰው ሁሉ ድረ ገጹ የ“ማኅበረ ቅዱሳን” ለመሆኑ ይስተዋል የሚል እምነት የለኝም። ይህ ጽሑፍ ያስፈለገበትም ዋና ምክንያት አንዱ ሰሚም ሆነ ድረ ገጹን በዋቢነት የሚጠቀም ማንኛውም አካል ይህን እውነት አውቆ ይገባበት ዘንድ ለማሳሰብ ነው። እውነት ፈልገው ሲያበቁ እውነትን ከሚቀብሩ ደቂቀ ሌዋውያን ጋር እንደ መጎራበት ማለት ነው። ሌዋታን ማለት ቀንን የሚረግም ጠማማ የእባብ ዝርያ ነው።1954 እትምኢሳ.271, ኢዮብ 38 ይመልከቱ።

የድረ ገጽ ልዩ መታወቂያዎች

አንድ፥ ይህ ድረ ገጽ ገና ሲጀምር ራሱን ለማስታወቅ ያደረገው ጥረት ልብ ላለው እጅግ የሚያሳዝን ነው። ድረ ገጹ ራሱን ለማስተዋወቅ ከተጠቀመባቸው ስልቶቹ መከከል ሳይከሰስና ስሙ ሳይጠራ ሰለ ራሱ በራሱ እንደበት ክስ መስርቶ ለዳኝነት መጮኹ ነበር። የሀገሬ ሰው የአይጥ ምስክርዋ ድንቢጥ እንዲል በአንዳንድ ሚዛናዊነት በሚጎድልባቸው ሀገር ውስጥ የሚታተሙ የግል ጋዜጦችም ጭምር ከበሮ አስመትተዋል። ከዚህም የተነሳ ፍጹም መሰረት የሌላቸው ዜናዎቹና ዘገባዎችሁ የአንባቢያን ልብ ለመክፈል ችለዋል።
ሁለት፥ በዚህ ድረ ገጽ የሚሰራው ዜናም ሆነ የሚያቀርቡት ዘገባዎች የቤተ-ክርስቲያን ችግር ለመቅረፍና መፍትሔ ለማምጣት ሳይሆኑ ሆን  ተብሎ ወደ ከፋ ሁከትና ብጥብጥን የሚጋብዙ፣ ነገሮች አቅጣጫቻውን ስተው ሌላ ችግር እስኪ ፈጥሩ ደረስ የመለጠጥና የማጋነን ባሕርይ የተጸናወታቸው ያልተጻፈውን የቅጥፈት “ጸጋ” ባለ ቤቶችም ናቸው።

ሦስተኛ፥ የድረ ገጹ አዘጋጆችሁም ሆነ ደጋፊዎች የተገለጠ ማንነት ፍጹም በዘገባዎቻቸው የክርስትና ሥነ-ምግባር የማይታይባቸው፣ በዜናዎቻቸውም ኃላፊነትነትንና ተጠያቂነትን የማይሰማቸው፣ በአቀራረባቸው ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌላቸው፣ እግዚአብሔር ያየናል ማለት ያልተቻላቸውም ናቸው። የጠሉት ሲቆርጡና ሲፈልጡ ለዓላማቸው መጠቀሚያ ጥሩ መሣሪያ የሆነ ሁሉ ደግሞ የሌለውን በመስጠትና በመለጠፍ በእውነት ላይ የሚያምጹና የጽድቅን መንገድ የሚያጨልሙ ናቸው። 

ድረ ገጽ አዘጋጆች የተጸናወታቸው አራት የውሽት ዓይነት/ልክፍቶች እንደሚከተለው ይመስላል

1ኛ. አሉባልተኞች ናቸው፥ አንድ ሰው አሉባልተኛ ነው ከተባለ በጥሬ ትርጉሙ አስመሳይ፣ ከሀዲ፣ የተናገረውን የማይደግም፣ አሉ ባይ ማለት ነው። ይኸውም በአንዱ ፊት ሌላ ተናግሮ ሲያበቃ ምራቁ ሳይደርቅ ደግሞ በሌላው ወገን ሰልፍ መሀከል ተገኝቶ የመጀመሪያውን ቃሉን ሽምጥጥ በማድረግ ጎራውን ለመምሰል በአዲስ መልክ ራሱን የሚገልጥ ሌላ የሚምስ የሚተነፍስ ማለት ነው። “ደጀ ሰላም” በመባል የሚታወቀው ድረ ገጽ አዘጋጆች ደግሞ በእንዲህ ዓይነቱ የአዋጊ ስልት “በእሳት” የተጠመቁ ነበልባሎች ናቸው። ርዕስ አስጩኸው ሲያበቁ ውስጡ ደግሞ ባዶ ቃላቶች ሰንገው የዋኁን ማህበረሰብ በማደናገር ረገድ ቁርጥ ነፍሰ ግዳዩ አባታቸው ዲያብሎስ! ይህ ብቻ አይደልም ይህ ማህበር የሚዘውራቸው ጋዜጦችና መጽሔቶች አጉል ተቆርቋሪነትን ሲያንጸባርቁ በዚህ ድረ ገጽ ደግሞ ቀንድ አውጥቶ ቤተ-ክርስቲያን መውጋትና ማፍረስ ነው የተያያዘው። በግርግር ተጠቃሚ ሌባ ነውና። ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ አሉባልተኞች የማይገባውን የሚናገሩ ለፍላፊዎችና በነገር ገቢዎች እንደሆኑ በ1ኛ ጢሞ 5፥13 በመግለጽ ማንም ከዚህ ዓይነቱ ልክፍት/በሽታ መራቅ እንደሚገባም አበክሮ ይመክራል።

2ኛ ቀዳዳዎች ናቸው፥ ይህ የውሸት ዓይነት ከሌሎቹ ይልቅ እጅግ የከፋ ነው። ቀዳዳ አይቋጥርም፣ ቀዳዳ ዕቃም ሆነ ምሥጢርን የማይጠብቅ ሰው ልብ አይጣልበትም። በቀዳዳ ዕቃ ነገርዎን ለማስቀመጥ ቢሞክሩ ለመቅለጥ ወስነዋል ማለት ነው። ይህ ዓይነቱ ባህሪ ወደ ድረ ገጹ አዘጋጆች ያመጠነው እንደሆነ በእጅጉ ተክነውበታል ማለቴ ሲያንሳቸው ነው። የድረ ገጹ አዘጋጆች ምንም ለቤተ-ክርስቲያን የቆምን ነን ከማለት ባይመለሱም ዘጋባዎቻቸው ሁሉ ግን የቤተ-ክርስቲያን አንድነትና የምእመናን ሰላም የሚያውኩና የሚነሱ ለመሆናቸው አሁን አሁን ደጀ ሰላም ስሙ በተነሳ ቁጥር እንደ እሬት እየከነከናቸው የመጡትን የደጋፊዎችሁ ምስክርነት ብቻ መስማት በቂ ነው። 

3ኛ ሸንጋዮች ናቸው፥ ይህ ማለት ቀለል ባለ አማርኛ በጥርሱ እየሳቀ በልቡ የሚራገም ማለት ነው። ጠቢቡ “ሽንገላን የምትናገር ከንፈር ጥፋት ታደርጋለች” እንዲል ከሸንጋዮች አንደበት ጥፋትን የሚጋብዝ ውዥንብርን የሚፈጥር እንጂ የምስራችን/መልካም ዜና አይሰማም። ሰበር ዜና ብሎ ታላላቆችን ሲዘልፍና ሲዘነጥል እንጂ “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ” አይልም። ሸንጋዮች በፊታችን መልካም መልካሙን አውርተውልን ሲያበቁ ዘወር ያልን እንደሆነ ደግሞ እግራችንን ተከትለው የሚቦጫጭቁን ናቸው። ደረ-ገጹም (ደጀ ሰላም) ሆነ ዋናው ማኅበሩ (“ማኅበረ-ቅዱሳን”) በዚህ ልክፍት ቀዳሚና ተከታይ የላቸውም። ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአጸደ ስጋ በህይወት ሳሉ ያለ ስማቸውን ስም እየሰጡ ያላሳረፍዋቸው ከሞቱ በኃላ የአዞ እንባ እያነቡ አጽማቸውን አፈርና ድንጋይ ለመነስነስና ለመወርወር ማንም አይቀድማቸውም ይህ ደግሞ እግዚአብሔር እጅግ ይጸየፈዋል።

4ኛ አጋናዮች ናቸው፥ አንድ ነገር እንዳለ እውነት በእውነቱ ማስፈር ማስቀመጥ አይሆንላቸውም። ያገኝዋትን ትንሽም እውነት ካላሰፍዋት፣ ካለጠጥዋትና እስክትበጠስ ድረስ ካልወጠርዋት ስራ የሰሩ ዜና የዘገቡም አይመስላቸውም። ታድያ ይህ ነውር የማያውቅ ወገን የተፋውን ትፋት ነው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያንን በተመልከተ “ደጀ ሰላም” እንደዘገበችው እየተባለ የተሳሳተ መረጃ ለሕዝብ ጆሮ እየደረሰ ያለው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

United States of America

No comments:

Post a Comment