Tuesday, May 15, 2012

የቅዱስ ሲኖዶስ የዛሬ ከሰዓት ውሎ

Click here to read in PDF
  • የዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ ጉዳይ ወደ ኮሚቴ ተላለፈ
ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬ ከሰዓት ውሎው የዜና ቤተክርስቲያናት ጋዜጣን ጉዳይ እንዴት እንዝጋው በሚል የተነጋገረ ሲሆን የአቡነ ሉቃስ የአቡነ ዲዮስቆሮስ የአቡነ አብርሀምና የአቡነ ሳሙኤል የይወገዙልን ፉከራ ገደብ አጥቶ እንደነበር ተነግሮዋል። በአንድ ወቅት አንድ ብጹዕ አባት ማኅበረ ቅዱሳንን የሚደግፍ የጀርባ ቁስል ያለበት ብቻ ነው ብለው እንደተናገሩት የጀርባ ቁስላቸውን እንዲያኩላቸው በማሰብ የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊ የሆኑት እነዚህ ጳጳሳት በምሳው እረፍት ከማህበሩ ሰዎች በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት የይወገዙልን  ጥያቄውን አጠንክረው አቅርበዋል።
 በዚህ ሰበር አጀንዳ የተሰላቹት ቅዱሳን አባቶች ወይ ተጠርተው ይጠየቁ አሊያም ደግሞ አንድ ውሳኔ ይደረግ ብለው በጠየቁት መሰረት ቅዱስነታቸው የብጹአን አባቶች ፍላጉት ይሄ ከሆኑ አዘጋጆቹ ይግቡ ብለው ነበር። ነገር ግን አራት ሊቃነ ጳጳሳት እነርሱ ከገቡ እኛ አንቀመጥም ብለው ብድግ ስላሉ ይግቡ የሚለው ትዕዛዝ እንደገና ሊታጠፍ ችሏል።

በዚህ ሁኔታ ድምጻቸው ሳይሰማ ሀሳባቸው ሳይደመጥ ማውገዝ ተገቢ አለመሆኑ በመነገሩ ሶስት ሊቃነ ጳጳሳት እና አራት የሕግ ሰዎችና ምሁራን ያሉበት ኮሚቴ የተመረጠ ሲሆን ከሚቴውም ጽሁፉ  እንደሚያስወግዝና እንደማያስወግዝ ይወስናል ተብሏል። ሰባቱ የኮሚቴ አባላትም  ፡- ብፁዕ አቡነ ያሬድ ፣ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ዶ/ር ተክለ ሃይማኖት አንተነህ፣አቶ በፍርዱ መሠረት፣ አቶ ፊልጶስ ዓይናለም እና ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ፣ ናቸው፡፡
ከሶስት ቀን ውሎ በኃላም ሲኖዶሱ በነገው ዕለት በሌላ አጀንዳ ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።

የጋዜጣው ጽሁፍ ያስወግዛልን?
የዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ ዘገባ በተጨባጭ ምክንያት፣ ማስረጃና የቤተ ክርስቲያን የሕግ መጽሀፍ ድጋፍ የተጻፈ እንደመሆኑ አዘጋጆቹን ሊያስወግዝ የሚችል ምንም ምክንያት የለም። እንዲያውም እነርሱ የሚወገዙ ከሆነ ሀሳባቸውን ለማጠናከር የጠቀሱዋቸው መጽሐፍት ማለትም አራቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሕግጋት ምንጮች እነሱም ፡-
1.      ፍትሕ መንፈሳዊ
2.     ዲድስቅልያ
3.     ቀሌምንጦስ
4.     መጽሐፈ ሲኖዶስ አብረው ሊወገዙ ይገባል።
ለምሳሌ ስለ ሢመተ ጵጵስና በጻፉት አንቀጽ ላይ፥ ለጳጳሳት ሹመት የህዝብ ተሳትፎ ያስፈልጋል ሲሉ ያነሱት ሀሳብን ያብራሩት እንዲሁ የሁሉ ተሳትፎ የዘመናዊነት መገለጫ ነው ብለው ሳይሆን የዲድስቂልያን መጽሀፍ ስለሚደግፋቸው ነው። ማስረጃውም ይኼ ነው።
“አንድ ኤጲስ ቆጶስ ሲሾም በሚሾምባቸው ሕዝቦችና በሊቀ ጳጳሳቱም ፈቃድ ይሁን” (ድስ.36)፡፡
“ኤጲስ ቆጶስ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ በሕዝብ ምርጫ ይሾም፡፡ (ፍ.መ.5፡91)”

ይህ ማስረጃ ዲዲስቅልያ መጽሀፍ ላይ ከሌለ  ሊጠየቁበት ይገባል። መጽሐፉ ላይ ካለ ግን በየትኛው መጽሐፍ ድጋፍ ሊያወግዙዋቸው ይችላሉ?
የሀብትና የውርስን ጉዳይ በተመለከተ ፍትህ መንፈሳዊ ለጻፉት ጽሁፍ ዋና ማስረጃ ነው።
ከሊቀ ጳጳሳትና ከመነኮሳት ጋር በተያያዘ ከሆነ የሀብትና የውርስ ጉዳይ በቀጥታ የሚገናኘው ከሙስና ጋር ነው፡፡ ምክንያቱም ፍትሕ መንፈሳዊ፡-
“መነኮሳት ምድራውያን መላእክት፣ ሰማያውያን ሰዎች፣ የሐዋርያት ምሳሌዎች ናቸው፡፡”
“ኤጲስ ቆጶስ ለራሱ ጥሪት (ሀብት ንብረት) አያብጅ፣ የላመ የጣመ ለመቅመስ ታዘዙኝ ለማለትም አይድከም፣ ጊዜ ሳይወስኑ መገዛት ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡” (ፍ.መ.4፣77) ይላልና፡

ይህንን የፍትህ መንፈሳዊ መጽሀፍ ድንጋጌ አንቀበልም የሚል ጳጳስ እስከሌለ ድረስ በምን አይነት የስነ ምግባር ሕግ ነው የጋዜጣውን አዘጋጆችን ሊያወግዙ የሚችሉት? ባይሆን ምናልባት ይህን ሕግ ለመጀመሪያ ጊዜም ከሆነ ያነበቡት ንስሐ ገብተው ሀብታቸውን ለቤተክርስቲያን ሰጥተው “…ጊዜ ሳይወስኑ መገዛት ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡” የሚለውን ቃል አክብሮ መቀመጥ ነው እንጂ የምን ይወገዙ ነው? ፍርዱን ለአስተዋይ እንተወዋለን።
ሀብትና ውርስን በተመለከተ ሕገ ደንቡ ይሻሻል ሲሉም ያቀረቡት ትንታኔ ይኼን የመሰለ ነው።

በአንጻሩ በ1991 ዓ.ም በወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 45 ቊጥር 1 ላይ “አንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ከዚህ ዓለም በሞት በሚለይበት ጊዜ የግል የሆነ ገንዘብ ቢኖረው ይረዳቸው ለነበሩ ዕጓለ ማውታና ለችግረኞች ይሰጣል (ኢብጥሊስ 39)” የሚል እስከ አሁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያልነበረ ሕግ አውጥቷል፡፡ ይህ አንቀጽ መሠረታዊውን የምንኲስና ሥርዓት የሚያፋልስ ከመሆኑም በላይ የቤተ ክርስቲያንዋ ጥንተ መሠረት የሚያናጋ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ የነበራቸውን ተአማኒነት የሚሸረሽር፣ ንጽሕናቸውንና ቅድስናቸው ጥያቄ ውስጥ የሚጨምር ነው፡፡

ይህን የተሳሳተ አመለካከት ለማለት የሚደፍር ማንነት ይኖራልን? አባቶቻችን ይሔንንስ ውሸትና ቅንነት የጎደለው አስተያየት ለማለት ትደፍሩ ይሆን?

አሁን ሁሉም ብፁዓን አባቶች በጠቅላይ ቤተ ክህነት ከተሠራላቸው የተሟላ ማረፊያ በተጨማሪ ከደረጃውን ክብራቸው ጋር የሚመጣጠን በቂ ወርሃዊ ደመወዝ፣ ነጻ ሕክምናና ነጻ ምግብ ያገኛሉ፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን እየተዳደረች ያለችው ቅዱሳን አባቶች ሠርተው በተውዋቸው ሕንጻዎች፣ ብፁዓን ምእመናን ከልጆቻቸው በፊት ቤተ ክርስቲያኖቻቸውን አስቀድመው ለቤተ ክርስቲያን አውርሰዋቸው ከሄዱ ሕንጻዎች ከሚገኘው ኪራይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ዓለማውያን የመንግሥት ባለሥልጣናት ቀሪ ሀብት ንብረታቸውን እያስመዘገቡ ባሉበት ወቅት ብፁዓን አባቶች በቤተ ክርስቲያን ስም ያገኙት ሀብትና ንብረት ለቤተሰብ ማውረስ ምን ይሉታል?

እነዚህ ጋዜጣው ላይ የተጻፉ ጹሁፎች በምን መመዘኛ እንዳስቆጡ? እንዳነጋገሩና የ3 ቀን ጊዜ እንደወሰዱ ለሁላችንም ግራ የሚያጋባ ነገር ሆኗል። አስተዋይነት ቢኖር ኖሮ ገና ከጅምሩ ለስብከተ ወንጌልና ሐዋራዊ ተልዕኮ መምሪያ እና ለመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ጉዳዩን አስተላልፎ እነርሱ በሚዛናዊነት እንዲመረምሩት እና ውሳኔውን ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲያሳውቁ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ የተሻለ እና 3 ቀን ሙሉ እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ ለክብር በመቆርቆር ከማሳለፍ ያድን ነበር።  
ኮሚቴው ጥናቱን አጠናቆ እነዚህ ወገኖች መባረር አሊያም ቅጣት ይገባቸዋል ካለ ከላይ የተዘረዘትን የቤተክርስቲያን የስርዓት መጽሓፍት አብረው ለማውገዝ ሙሉ ዝግጁነት ያስፈልጋቸዋል እንላለን።
 

1 comment:

  1. hi hilegeworgis!i kill u. i started u familly!!!!!

    ReplyDelete