Saturday, May 12, 2012

የልደታው ምሽት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ

click here to read in PDF
  • አምስት ጳጳሳት ማንንም የማያስር ሴራ ሲሸርቡና ሲገምዱ አመሹ
 ረቡዕ ዕለት የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የሚጀመርበት ቀን ነበር። በዕለቱ ልደታ በመሆንዋ ጠዋቱን ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ሊቃነ ጳጳሳት በቤተክርስቲያን ስለዋሉ ከሰዓት በኋላም ሁሉም ላይ የድካም መንፈስ ይታይ ስለነበረ ስብሰባው በነጋታው እንዲካሄድ ተወሰነ። የዚያን ዕለት ማታ ግን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሌላ “ድብቅ” የሴራ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፤ - በአራት የማቅ ጉዳይ አስፈጻሚና ሲኖዶስ በጥባጭ ጳጳሳት እንዲሁም የእነርሱ መናጆ በሆኑ አንድ ጳጳስ አማካይነት።
ጊዜው መምሸት ሲጀምር ፊት ሦስቱ አቡነ ሳሙኤል፣ አቡነ ኤልያስ፣ አቡነ ዲዮስቆሮስ መናጆ ከሆኗቸው አቡነ ማቴዎስ ጋር የተራ መነኩሴ ቆብ አድርገውና አንታወቅም ብለው ወደ ግቢው ጨለማን ተገን አድርገው ገቡ። ተማሪዎቹ ሌላው ቢቀር አብረውት የሚኖሩት አቡነ ሳሙኤልን ምንም አይነት ልብስ ቢለብሱ መለየት ኣያቅተውምና እሳቸውን ሲያይ ሌሎቹስ ማናቸው ብሎ ትኩረት መስጠት ጀመረ። ከአቡነ ሳሙኤል ጋር ያሉት እነማን እንደሆኑም መለየት ቻለ።
አለወትሮአቸው በዚያ ሰዓት ያውም ቆባቸውን ቀይረው ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት በቦታው መገኘታቸው ግርታን የፈጠረበት ተማሪም ሁኔታቸውን በንቃት መከታተሉን ቀጠለ። ሁሉም አንድ በአንድ ወደአቡነ ጢሞቴዎስ ቢሮ ገቡ። አቡነ ጢሞቴዎስ ለወትሮው በቢሮዋቸው ብዙ የማያመሹ ሲሆን ያን ቀን ግን ከቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በፊት በአላማ ከሚመስሉዋቸው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ሊመክሩበት ያሰቡት ጉዳይ ስለነበራቸው በቢሮዋቸው ነበሩ።

ማኅበረ ቅዱሳን ለአላማው የሚጠቀምባቸውን ጳጳሳት አጀንዳ እያስጨበጠና እየከፋፈለ ሰሞኑን የተጠናከረ ዘመቻ ያደረገ ሲሆን፣ በዚህ መንገድም ተገቢውን ሥራ ሰርቼ ውሳኔዎች እኔ በምፈልገው በመንገድ ይፈጸማሉ ብሎ ያምናል። ለዚህም አስቀድሞ በፈጠረው ሴል መሰረት የስብሰባውን ሂደት በየቀኑ የሚገመግም ሲሆን፣ ከመስመር ወጡ ብሎ ባመነባቸው ነገሮችም የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ጉዳዩን በነጋታው እንደ አዲስ ያንቀሳቅሳል።
በዚህ ረገድ እነዚህ አምስት ሊቃነ ጳጳሳት ለአላማው ያሰለፋቸው እና በቀላሉም ነገሮችን ተረድተው ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ናቸው። እንደ ጎረምሳ ሸሚዝ ለብሰው ከዲያቆናት ጋር የሚደባደቡትና የአርባ ምንጭ ህዝብ ሲነሳባቸው በአምቡላንስ ተደብቀው ያመለጡት ሁከተኛው አቡነ ኤልያስ እና የትግራይ ሕዝብ እርስዎ ከሚመሩን መንበረ ጵጵስናው ባዶውን ቢቀመጥ እንመርጣለን ብሎ ያባረራቸው እንዲሁም በሌሎች የተረጋገጠ ማስረጃ ባላቸው ነገሮች የሚታሙት አቡነ ዲዮስቆሮስ የታዘዙትን ለመፈጸም የማያመነቱ ሲሆን፣ አቡነ ሣሙኤል ግን የማኅበሩ ደጋፊ ቢሆኑም ለማህበሩ አጀንዳ ወድረው የሚከራከሩት የራሳቸው ተያያዥ አጀንዳ ካላቸውና የግል ቂማቸውን የሚወጡበት እድል የተፈጠረ መስሎ ከታያቸው ብቻ ነው።
በዚያ ምሽት ታዲያ እነዚህን ሲጠሩ አቤት፣ ሲላኩ ወዴት የሚሉትን አባቶች ሰብስበው አቡነ ጢሞቴዎስ ቢሮ የተሰበሰቡትና የመከሩት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ሊቀ ጳጳስ ከሆኑበት የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፥ በኮሚሽኑ ስም የተከፈቱትን የተንቀሳቃሽና ቁጠባ ሒሳቦች እንዳያንቀሳቅሱ በመታገዳቸው ይህን ነገር እንዴት እናስቀለብሳለን በሚል አጀንዳ ላይ ነበር።
ቤተክርስቲያኒቱ  የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመቅረፍ በኩል የበኩሏን አስተዋፅኦ ለማድረግ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንን ታኅሣሥ 26 ቀን 1964 . ማቋቋምዋ ይታወቃል፡፡ ኮሚሽኑ በዐዋጅ ቁጥር 621/2001 እና ደንብ ቁጥር 168/2001 በሚደነግገው መሠረት በዳግም ምዝገባ ሰርቲፊኬት ቁጥር 1560 የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅት ኾኖ ተመዝግቧል፡፡
በዚህ ምዝገባ መሰረትም ቁጥጥር የሚደረግበት ከቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ከመንግስትም ጭምር ነው።  መንግስት በሚያደርገው ቁጥጥርና ክትትልም የኮሚሽኑ አሰራር አጥጋቢ ሆኖ ባለመገኘቱ በሊቀ ጳጳስ መመራቱ ቀርቶ በበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ ዐዋጅ ቁጥር 621/2009 መሠረት ማናቸውም የልማትና በጎ አድራጎት ማኅበር በቦርድ ብቻ የሚተዳደር ኾኖ አመራሩ በቦርድ ወይም በጠቅላላ ጉባኤ እንዲከናወን ስለሚያዝና ኮሚሽኑ 9 የቦርድ አባላት እና 20 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ቢኖሩትም አፈጻጸሙ አጥጋቢ ሆኖ ባለመገኘቱና ትክክለኛ የሆነ ተጠያቂነት ያለው አሰራር ባለመኖሩ ኮሚሽኑ ምንም አይነት ሊቀ ጳጳስ ሳያስፈልገው በቦርድ ብቻ እንዲተዳደር ወስኗል።
ከዚህ ቀደም ብሎ አባ ሳሙኤል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በነበሩበት ወቅት የሀገረ ስብከቱን ካዝና አራቁተውና ብዙዎችን ደም እንባ አስለቅሰው በፈጸሙት ግፍ ንስሃ በመግባትና በመጸጸት ፈንታ፣ ያለ ስራ ለወራት ተቀምጠው በብዙ ደጅ ጥናት የልማት ኮሚሽን ሊቀጳጳስ ከሆኑ በሀላ እንደተለመደው ዝርፊያውን በማጧጧፋቸው ከፓትርያርኩ ጋር ሌላ ግጭት ውስጥ ገብተዋል። ቅዱስ ፓትርያርኩም የኮሚሽኑን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሳሙኤልን ከፈራሚነት ያገዱ ሲሆን ይህም ውሳኔ ተዳፍኖ የነበረውን የቅዱስ ፓትርያርኩንና የአቡነ ሳሙኤልን አለመግባባት አድሷል። እንደሚታወሰው ለሚሌኒየሙ ዝግጅት “ሸብረብ” በማለት በአዘጋጅ ኮሚቴ ውስጥ ዋና አስተባባሪ መሆናቸው በውስጣቸው የተሳሳተ ሥዕል ፈጥሮላቸውና አላማ ከማቅ ጋር አወዳጅቷቸው ገና በተሾሙ በ2 ዓመታቸው “የሚሌኒየሙ ምርጥ አባት እኔ ነኝ” ሲሉ ለራሳቸው ተናገሩ። የማቅ ሰዎችም የልባቸውን አንብበው “ይደልዎ ይደልዎ” ሲሉ አሟሟቋቸው። “ፓትርያርኩ አርጅተዋል፣ እርሳቸውን ሊተኩ የሚችሉ አባት እርስዎ ነዎት፤ እኛም ቀኝ እጃችንን ሰጥተንዎታል።” በሚል ክፉኛ ስሜታቸውን ሲኮረኩሩላቸው፣ ነገሮችን በዚያው ፍጥነት ማሮጥ የያዙት አባ ሳሙኤል፣ ነውረኛ ምስጢራቸውን ማቅ እንደሚጠብቅላቸው፣ ፓትርያርክ ሲሆኑም የቤተክርስቲያኒቱን አጠቃላይ መዋቅር በማቅ እጅ ውስጥ እንደሚያስገቡ ቃል ኪዳን ተገባብተው ነበር። ነገሮችን በዘዴ መያዝ የማይሆንላቸውና በአንድ ጊዜ ካገኙት ጋር መላተም ስራቸው የሆነው አባ ሳሙኤል ከምስጢር ጠባቂያቸው ከዘሪሁን ሙላቱ ጋር “ለሚሌኒየሙ ከተመደበውና ከዘረፍከው ገንዘብ አካፍለኝ” በሚል ሲጣሉ፣ ማቅ ጠብቄ አቆየዋለሁ ያለውንና ብዙ ዋጋ ያወጣልኛል ያለውን ምስጢራቸውን አደባባይ ላይ አሰጣው። ያን ተከትሎም ከፓትርያርክነት ቅዠታቸው ሲባንኑ ራሳቸውን ከስራ ውጪ ሆነው አገኙት።
በብዙ ልመና የልማት ኮሚሽን ሊቀጳጳስ ሆነው ከተመደቡ በኋላ፣ የተለያዩ ሴራዎችን ሲሸርቡ የነበሩትና እንዳይፈርሙ የታገዱት አባ ሳሙኤል፣ ይህ አጀንዳ በሲኖዶሱ ለውይይት በሚቀርብበት ጊዜ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ ተወካዮች ተገኝተው “ከሕግ በላይ መሆን የሚችል የለም፤ የሚለወጥ ነገርም የለም፤ እድል ሰጥተናችሁ የነበረ ቢሆንም አልተጠቀማችሁበትም፤ ስለዚህ እንደማንኛውም በጎ አድራጎት ድርጅት በተቀመጠው አሰራር መሠረት የመቀጠል ግዴታ አለባችሁ” የሚሉትን አሰራር ያስረዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ አሰራሩን ለመቀየር እና ልማትና ክርስቲያናዊ ኮሚሽንን በልዩ ሁኔታ ለማየት እስካልፈቀደ ድረስም ኮሚሽኑ በሊቀ ጳጳስ የሚመራበት ሁኔታ እንደማይኖር ታውቋል። ስለዚህም በጉዳዩ ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ተወያየበትምም አልተወያየበትምም የልማትና ክርስቲያናዊ መምሪያው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ ፈቃድ የሰጠው አጀንሲ በወሰነው መሰረት ነገሩ ተፈጻሚ መሆኑ የማይቀር እና የኮሚሽኑን አሰራር መከታተልና የአካሄዱን ትክክለኛነት መወሰን ከሲኖዶሱ ቁጥጥር ውጭ መሆኑ ተነግሯል። ምናልባት ግን አባ ሳሙኤል የለመዱትንና በተደጋጋሚ የተለያዩ ሰዎችን መብት የተጋፉበትን ከወንጀል የማምለጫ መንገድ እዚህ ላይ ሳይጠቀሙ እንደማይቀር ይገመታል። እርሱም “ጉዳዩ ሃይማኖታዊ ነውና በቤተክህነት ነው መታየት ያለበት እንጂ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ መመልከት የለበትም” ይላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

No comments:

Post a Comment