Thursday, May 10, 2012

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግርና የአንድ አድርገን ዘገባዎች/ክፍል ሁለት/

click here to read in pdf
(በክፍል አንድ ጽሁፋችን የማኅበረ ቅዱሳን አፍ የሆነው አንድ አድርገን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ዙሪያ በጻፈው ጽሁፍ ላይ ያሉትን መሰረታዊ ችግሮች እና የማኅበሩን ድብቅ አጀንዳ በዝርዝር ገልጠን ለማሳየት ሞክረን ነበር፡፡ የዚህን ተከታይ ደግሞ ቀጥሎ እናቀርባለን፡፡
“የኢህአዴግ ትልቁ ችግሩ ከ1997 በኋላ ሰዎች ማህበር ሲፈጥሩ አይኑ ደም ይለብሳል ፤ ጥሩ እቅልፍ ላይ ካለም ይባንናል፤ ፍርሀት ጥሩ ነው ፍርሀቱ ደግሞ ጠርዙን ያለፈ ይመስለናል ፤ ሰው በሀይማኖት ስም ስለ ቤተክርስትያ ብሎ ማህበር ሲመሰርት በሌላ አይን መመልከት ጤነኝነት አይመስለንም ፤ እናንተ ፖለቲካችሁ ላይ ብትበረቱ እኛ ደግሞ እምነታችን ላይ እንበረታለን ፤ ከአባቶቻችን የተቀበልነውን እምነት እና ስርዓት ለልጆቻችንና ለልጆቻችሁ ለማውረስ እንሰራለን”                     
በሐመር፣ በስምአ ጽድቅና በስሙ በሚጠራው ድረገጹ ፖለቲካዊ አቋሙን በግልጽ ማንጸባረቅ የሚያስከፍለውን ዋጋ የተረዳው ማኅበረ ቅዱሳን፣ እንደፊኛ የተወጠረ ፖለቲካዊ ስሜቱን የሚያስተነፍሰው እንደአንድ አድርገን ባሉት ሙዓለ ሕፃናት ድረገጾቹ ላይ ነው። እነዚህ ድረገጾች የማቅን ፖለቲካዊ አቋም በማንጸባረቅ የታፈነ ስሜቱን የፈለገውን ያህል ተንፈስ ያደርጉለታል። ይሁን እንጂ በዚህ ስራቸው ስሜቱን ከማስተንፈስ ባሻገር በርካታ ማቅን ግምት ውስጥ የሚከቱና እጥፍ ድርብ ዋጋ የሚያስከፍሉ ወራዳ ተግባራትን በመፈጸም ላይ ናቸው። በተለይም አንድ አድርገን ለዚህ ፊትአውራሪ ነው።
መቼም የአንድ አድርገን አዘጋጆች ትልቅ ችግር በታሪክ፣ በፍልስፍና፣ በፓለቲካና በሃይማኖት ጉዳይ “ሊቅ” እንደሆኑ ማመናችሁ ነው። በእርግጥ ስውርም ቢሆኑ ፖለቲከኞች በመሆናችሁ ኢህአዴግን መተቸታችሁ ተገቢ ሊሆን ይችላል። በ“ሊቅነታችሁ” የኢህአዴግ ችግር ያላችሁትን ለማስረዳት ያነሳችሁት ነጥብና የሰጣችሁት ማብራሪያ ራሳችሁንም ትዝብት ላይ የሚጥል ሆኗል። ይኸውም ኢህአዴግ “ማህበራት ሲደራጁ አይኑ ደም ይለብሳል” ማለታችሁ ነው። አንድ አድርገኖች በታሪክም በኩል ሊቅ ነን ከማለት አልተመለሳችሁምና “ሊቅነታቸሁ” እንዴት እንዳላገዛችሁ እንጃ እንጂ እናንተ ራሳችሁ እኮ የተደራጃችሁት ከምርጫ 97 በፊት ነበር። ነገር ግን በእናንተ መደራጀት ምንም ደም የሚያስለብስ ምክንያት የለም። ባይሆን እናንተ ከምርጫ 97 በኋላ እንዳረገዘች ሴት ፖለቲካዊ ባህርያችሁ አልደበቅ ስላለ ልብ ከገዛችሁ ብዙ የምትማሩት ነገር ይኖራል። 

ማቅ በምርጫ 97 የግል ጋዜጦች በቅንጅት እንቅስቃሴ ላይ ምን አይነት ሚና እንደነበረው ስለምታውቁ፣ እናንተም ከምርጫው በኋላ ሀሳባችሁን ለማስፈጸም አለማዊ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ከመጠቀም ጀምሮ ፈንድ አድርጎ “አዲስ ነገር” የተባለውን ጋዜጣ እስከ ማቋቋም ድረስ የዘለቀ ተሳትፎ እንደነበረው አይዘነጋም። ባለፈው ጊዜ እንኳን በሕያዋኑና በሞቱት የቤተክርስቲያን ልጆችና ሊቃውንት ላይ በሌለው ሥልጣንና መብት በድፍረት እርግማንና ውግዘት ሲያስተላልፍ በዋነኛነት የተጠቀመው አለማዊ መጽሔቶችንና ጋዜጦችን ነው። እንዲያውም በአንዳንድ መጽሔቶች ላይ አምደኛ ሆነው የሚጽፉት የስምአ ጽድቅ ጋዜጠኞችና በebs ቴሌቪዝን የሚተላለፈው የአኮቴት ፕሮግራም አዘጋጆች ናቸው። ይህ ባህርያችሁ ከምርጫ 97 በፊት የምናውቀው አይደለም።    
ከዚያ ወዲህ ደግሞ ፍርሀታችሁ ጠርዝ ስላለፈና እንቅልፍ ስላሳጣችሁ ገና ለገና እንፈርሳለን በሚል ፍርሀት ዋናውን ማኅበረ ቅዱሳን ወደ ጥቃቅን ቡድኖች በመበታተንና በራቸውን በከፈቱላችህ አንዳንድ አድባራት ውስጥ አስርጋችሁ በማስገባት በጽዋ ማህበር ስም መደራጀት ከጀመራችሁ እኮ ሁለት አመታት አስቆጠራችሁ። በቤተክርስቲያን ውስጥ ያወጃችሁት ሽምቅ ውጊያ መሆኑ ነው። ለመሆኑ እንፈርሳለን የሚል ፍርሀት ጤነኛ ስራ የሚሰራን ድርጅት ሊያሰጋው ይችላል? በፍጹም!!
“እናንተ ፖለቲካችሁ ላይ ብትበረቱ እኛ ደግሞ እምነታችን ላይ እንበረታለን”  ብላችኋል። ይህማ ቢሆን አንድ ነገር ነበር። ችግሩ እኮ ያለው እናንተ በሃይማኖቱ የላችሁበትም፤ በሀይማኖት ስም ግን የፖለቲካ ስራ ትሰራላችሁ፤ ሰው መግደላችሁ፣ ማሰቃየታችሁ፣ በሀሰት መወንጀላችሁ፣ አባቶችን ማሳቀቃችሁና አልፎም ፓትርያርክ አውርዳችሁ የራሳችሁን ፓትርያርክ ለመሾም እንቅስቃሴ ማድረጋችሁ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ፓለቲካ ውስጥ በመግባት መንግስትን ለማወክ መፈለጋችሁ ነው የእናንተ “ሃይማኖት”። አንዳንድ የዋህ አባላቶቻችሁ በቅንነት እንደሚያስቧችሁ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ብትሰጡ  እና መንፈሳዊ ለመምሰል እንኳን ከሴራ፣ ከአሳዳጅነትና ከክፋት ብትርቁ ጥሩ ይሆን ነበር። 
“ወሀቢዝም ምን ማለት እንደሆነ ካላወቃችሁት እኛ ልናስረዳችሁ ፍቃደኞች ነን ፤ እናንተ ጋር ካለው አመለካከት እኛ ጋር ያለው መረጃ የሚሻል ሊሆንም ይችላል ፤ ይህን አመለካት ከጥቂት ሰዎች በስተቀር እስከ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ድረስ ገብቷቸዋል ብዬ አላስብምታዲያ እነዚህን በምን ምግባራቸው እና ስራቸው ነው ከማህበረ ቅዱሳን ጋር ያመሳሰሏቸው? ማህበረ ቅዱሳን ክርስትያናዊ መንግስት ለማቋቋም የሚሰራ ተቋም አይደለም ፤ ባይሆን የእምነቱ ተከታዮች በክርስትና እንዲኖሩ የሚጥር ተቋም እንጂ፡፡”
በአንድ ወቅት አንድ ወዳጄ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኬሚካል ኢንጅነሪንግ ትምህርት በሚማርበት ጊዜ የመመረቂያ ጽሁፉን በሳሙና ፋብሪካ ላይ ይሰራ ነበር። እና እያጠናቀቀ ሳለ የ3ተኛ ክፍል ተማሪ የሆነ ታናሽ ወንድሙ “ምን እያደረክ ነው?” ይለዋል። እርሱም የሚሰራውን ጥናት ሲነግረው ልጁም “ኤጭ” አለው፤ “ኤጭ ስለሳሙና ከስር መሰረቱ አጠናለሁ ብለህ ሳሙና ፋብሪካ ድረስ ከምትሄድ እኔን አትጠቀኝም ነበር? ሳሙና ትልቁ ስራው አረፋ ማውጣት ነው። እሱን ከኔ የተሻለ ማን ያስረዳሃል? በከንቱ ደከምክ።” አለው።
አንድ አድርገኖች የምትናገሩትን ብታስተውሉት ጥሩ ነበር። ኦርቶዶክሳዊነት ገና በቅጡ ሳይገባችሁ በሁሉም ሀይማኖት ጉዳይ ሊቅ ነን ባትሉ ምን ነበረበት? አሁን ይሄን ጉዳይ ባት    ጽፉት ምን ይቀርባችሁ ነበር? “ሊቅ” ነን ለማለት ሁሉን ነገር ማውራት የለባችሁም እኮ። እባካችሁ በመጀመሪያ የቤተክርስቲያን ትምህርት ምን እንደሆነ በቅጡ ለይታችሁ እወቁ፤ ከዚያ ስለሌላው መናገር ብትሞክሩ ያምርባችሁዋል። ገና ኦርቶዶክሳዊነት ምን መሆኑ እንዳልገባችሁ በአንድ ወቅት በድረ ገጻችሁ ፖስት ያደረጋችሁትና በአለቆቻችሁ ትዕዛዝ ያወረዳችሁት ጽሁፍ ይመሰክርባችሁዋል።  እንደ ህጻኑ ልጅ ውሃ ሲያገኘው ሳሙና አረፋ ይሆናል ከሚል የማይሻል ዕውቀት ይዛችሁ የተሻለ ስለምናውቅ እናስተምራችሁ? ማለታችሁ ያሳዝናል። 
ወሀቢያን በምን ምግባር ነው ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር የምታመሳስሉት ብላችሁ ጠይቃችኋል። እኛ እኮ እንዴት አሳነሱባችሁ? በሽፋን ስማችሁ ሳይሆን በግብር ስማችሁ እንዴት አልጠሯችሁም? አለን። አታውቁም እንዴ ስማችሁን? መንፈሳዊ ኮሌጆች አካባቢ አልቃይዳ፣ ወደ ደቡብ ታሊባን፣ ሀረር አካባቢና በዩኒቨርስቲዎች  አልሻባብ፣ ወደ ሰሜን በሊባኖሱ ሂዝቦላ ስም እኮ ነው የምትጠሩት። አላወቃችሁም? ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው የሚባለው እውነት ነው። ማህበረ ቅዱሳን እንዴት ከወሀቢያ ጋር ይመሳሳላል ለሚለው ጥያቄህ በቂ ምላሽ ለማግኘት ከፈለክ አውደምህረት ላይ የወጣውን ማህበረ ቅዱሳንና ሰለፊያ ማን የማን ግልባጭ ነው? የሚለውን ጽሑፍ ተመልከት።
“ባለፈው ጥምቀት ምን ሆነ መሰላችሁ ፤ ጊዮርጊስ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች የጥምቀትን በዓል ለማክበር ሲንቀሳቀሱ  ለመንገዶች ማስዋቢያ የገዙት ባንዲራ መሀሉ ላይ ኮከብ የሌለበት ነበር ፤ ይህ ባንዲራ በተሰቀለ በሰዓታት እድሜ ውስጥ የፌደራል ፖሊስ አባላት መጥተው አማርኛ መናገር የማይችሉ አባላት ፤ ‹‹ባንዲራው ላይ አንባሻ አድርጉበት ወይም አውርዱት አሏቸው››(ይህ አነጋገር ከአንደበታቸው የተሰማው እንጂ የኔ አይደለም) ፤ ወጣቶቹም ‹‹መሀሉ ላይ አንባሻ እድርገን ባንዲራውን አንሰቅልም ›› ፤ ብለው በማውረድ አረንጓዴውን ለብቻ ፤ ቢጫውን ለብቻ ፤ ቀዩን ለብቻ ፤ መሀል ላይ ነጭ ቀላቅለውበት በየስልክንጨቱ በመስቀል በዓሉን ሊያከብሩ ችለዋል ፤ ከ10 ዓመት በፊት የማከብራቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባንዲራ ጨርቅ ነው ብለው ሲናገሩ አጨብጭበው ሲያበቁ ፤ አሁን ደግሞ ስለ ባንዲራ ክብር ለኛ ሊነግሩን መጡ ፤ እናት ለልጇ አይነት ነገር …….  እነዚህ ወጣቶች ውስጣቸው የሌለውን ማድረግ አልፈለጉም ፤ እኛም በሀገራችን ላይ 1000 ዓይነት ሀይማኖት መንግስት ህገ መንግስቱን መከታ አድርጎ ቢፈቅድ ‹‹ሃይማኖት ብዙ ነው ፤ ጥምቀት አንዲት ናት›› አንልም ፤ ብለንም አናምንም አናስተምርም ፤ ህገ መንግስቱ በሰዎች አማካኝነት የተጻፈ ነው ፤ እኛ ምናምንበት ወንጌል ግን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈ ነው ፤ ስለዚህ ህገመንግስቱን የሚቃረኑ ነገሮች ቢኖሩ እንኳን እርሱን ከመስበክም ሆነ ከማመን ወደ ኋላ አንልም ፤ ደግሜ  ለማስረገጥ ‹‹አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤›› የማይዋጥ እውነት ፡፡”
የኛ በምሳሌ አስረጂ!  “ድንቅ!” የሚያሰኝ ምክንያት በምሳሌ አስደግፈህ አቀረብክ ማለት ነው? ለመሆኑ ምን እንደጻፍክ ገብቶሃል? እስኪ ተመልሰህ አንብበው። ወጣቶቹ የፈለጉትን ባንዲራ ገዙ፤ የፈለገውን አይነት ይሁን ለምን ያ ሆነ አንልም። የፌደራል ፖሊሶቹ ስራ ግን ምኑ ላይ ነው የሚወቀሰው? ፖሊሶቹ አማርኛ ስላልቻሉ ኢትዮጵያዊነታቸው ያንሳል? የወጣቶቹ ስራ እንደ ክርስቲያን ትክክል ነው ሊያሰኝ የሚችል ምን መሰረት አለው? የእነርሱ ተቃውሞስ በኋላ ላይ ያነሳኸውን እርባና ቢስ ሀሳብ በሙሉኑት ለማብራራት በቂ ነውን?
ገና ሕጻናተ አእምሮ ናችሁ። አካሄዳችሁ ያልጠራና ጭፍን፣ የማህበሩን ሀሳብ እንደወረደ ከማብራራት ያለፈ አይደለም የምንላችሁ ለዚህ ነው። እዚህ ሀሳብ ውስጥ ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ማውጣት እንችላለን።
1.     ዘረኝነታችሁን
2.    መንግስትን የምትቃወሙት በፖለቲካ አቋም መሆኑን
3.    ግልጽ የሆነ ፖለቲካዊ አጀንዳ ያላችሁ መሆኑን ነው።
መንፈሳዊ ሰው አገሩ በሰማይ ነው። ታዛዥነቱ ደግሞ ለእግዚአብሔር ቃል ነው። ለእግዚአብሔር ሲል ለሰው ስርአት ሁሉ ሊገዛ ይገባዋል። እናንተ ግን እያደረጋችሁ ያላችሁት ከዚህ በተቃራኒ ነውና በስራችሁ ፖለቲከኞች እንጂ ሃይማኖተኞች እንዳልሆናችሁ አውቀናል። ስለ ፖሊሶቹ አማርኛ አለመቻል የጠቀሳችሁት ባንዲራውን ቀይሩ ያሉዋችሁ በአማርኛ መሆኑን በመግለጽ ነው፡፡ ስለዚህ ቁም ነገራችሁ የፖሊሶቹ ዘር ነው፡፡ አማርኛ አለመቻላቸው ስለ ባንዲራ ለመነጋገር መብት የሚነፍጋቸው አይደለም፡፡ በውስጣችሁ የተቀበረው የዘረኝነት መንፈስ ቱግ ብሎ ስለገነፈለ ግን አማርኛ አለመናገርን ኢትዮጵያዊ አለመሆን አድርጋችሁ ነው የቆጠራችሁት፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ነገሩ ትክክልም ይሁን አይሁን፣ የባንዲራ አዋጁ በሀገሪቱ ላይ የሚውለበለብ ባንዲራ የሕገ መንግስቱ አርማ እንዲኖርበት ያዛል፡፡ ፖሊስ ደግሞ ሕግን የማስፈጸም ግዴታ አለበት፡፡ ከዚህ ግዴታው ተነስቶ ጊዮርጊስ አካባቢ ያሉትን ወጣቶች ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ቦታ የሚውለበለበውን ባንዲራ አስመልክቶ አርማ የሌለበት ከሆነ አስተካክሉ ማለት የህግ ግዴታው ነው፡፡  እናንተ ግን ይህን እንደ ትልቅ ጥፋት የቆጠራችሁበት ምክንያት አስቂኝ ብቻም ሳይሆን የአእምሮአችሁ የማሰብ አቅም የት ድረስ እንደሆነ የሚያሳይም ነው። 
ጽሁፉ ዝም ብሎ ባንዲራ ስለማውለበለብና አለማውለብለብ የሚያወራ ሳይሆን ፖለቲካው ምን ያህል ውስጣችሁ ስር እንደሰደደና መንግስትንም የምትቃወሙት በአቋም መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ በሃይማኖታዊ በኣል ላይ ይህን ፖለቲካዊ አጀንዳ ማንሳትና ግጭት ውስጥ መግባት ለምን አስፈለገ? እናንተ ሃሳባችሁ መንፈሳዊ ከሆነ ባንዲራው ላይ አርማ ኖረ አልኖረ ምን ያስደንቃችኋል? ባንዲራችን በተለያዩ ዘመናት የተለያየ መልክ ነበረው። ደግሞስ ወጣቶቹ ባንዲራ ላይ አርማ አለማድረጋቸው ፖለቲካዊ እንጂ ምን መንፈሳዊ አጀንዳ አለው? ስለዚህ በሃይማኖት ሽፋን ፖለቲካዊ አቋም የምታራምዱ ለመሆናችሁ ይህ በቂ ምስክር ነው፡፡
እንደ ክርስቲያን በጎም ይሁን ክፉ እናንተ ነፍስ ሁሉ ለበላይ ባለስልጣናት መገዛት እንዳለበት የሚያዘውን የእግዚአብሔር ቃል ቸል ብላችሁ ፖለቲካዊ አቋማችሁን “የማናምንበትን አናደርግም” ብላችሁ ስለገለጻችሁ ጥሩ ነገር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ለመንግስት የማይታዘዘው እግዚአብሔርን ተው ሌላውን አምልክ በሚል አምልኮውን የሚያውክ ነገር ሲታዘዝ ብቻ ነው። እንደ ደርጉ ጊዜ መጽሀፍ ቅዱስን ትተህ የማርክስን ካፒታል አንሳ የሚል ትዕዛዝ ሲመጣ እምቢ ብሎ በዚህ የሚመጣም ቅጣት ካለ መቀበል አለበት።
ባንዲራ አርማ ኖረበት አልኖረበት ያ የፖለቲከኞች ስራ ነው። ከአምልኮ ጋር የሚያገናኝ ምንም ነገር የለውም። ባንዲራ ላይ ያለውን አርማ መቃወምና ከፖሊሶች ጋር መተናነቅም ምንም አይነት  መንፈሳዊ ፍይዳ የለውም። በእንዲህ ያለ ተራ ምክንያት አጀንዳችሁ ከመንፈሳዊነት ይልቅ ፖለቲካዊ መሆኑን ከጊዮርጊስ አካባቢ ወጣቶች ጀርባ ሆናችሁ ስላሳወቃችሁን ጥሩ ነው። ከዚህ ሁሉ እኮ ከላይ የደረባችሁትን የሃይማኖት ካባ አውልቃችሁ በቀጥታ ወደ ምርጫ ቦርድ ሄዳችሁና የፓርቲ ስም ሰይማችሁ ብትመዘገቡና አንደኛችሁን በይፋ ብትታገሉ ጥሩ ነው፡፡ ለምን እንደ አበደ ውሻ እየተክለፈለፋችሁ ቤተክርስቲያናችንን ታምሳላችሁ? 
እስኪ ደግሞ ይሄኛውን ጽሁፍ እንመልከት።
ከ97 ዓ.ም በፊት ነገሮች ሁሉ መልካም ይመስሉ ነበር ፤ መንግስት ሌሎች ሲያደርጉ ተመልክቶ ፤ እኔም ለምን ይቅርብኝ በማለት ዲሞክራሲያው ምርጫ አደርጋለሁ ብሎ ተነሳ ፤ ጥሩ የሆነ ሂደት ያለው የፖለቲካ ቅስቀሳ በመላው ሀገሪቱ ተካሄደ ፤ መጨረሻ ግን ሁላችን እንደምናውቀው ውጤቱ መንግስት እንዳልጠበቀው ስለሆነ የምርጫውን አቅጣጫ የሚያስቀይር ስራ ተሰርቶ ፤ ኮሮጆ ተገልብጦ ፤ ብዙ ሰዎች ሞተው ሁሉም ነገር እንዳልሆነ ሆነ ፤ ከዚህ በኋላ መንግስት የሰራው ስራ ቢኖር ለመሸነፌ ምክንያት ምንድነው? ብሎ በመነሳት ከበታችኛው አመራር ጀምሮ እስከ ላይኛው ባለስልጣናት ድረስ ሂስና ግለ ሂስ ፤ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶችን ማውጣት ማውረድ ተያያዙት ፤ በርካቶች ላይ ግልጽ እርምጃ በመውሰድ ከመስመር አስወጧቸው ፤ በርካታ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለ97 ምርጫ መሸነፍ የራሳቸውን ሚና መጫወታቸው በስመጨረሻ ደረስንበት አሉ ፤ ለመያዶች ህጉ በሀገሪቱ ውስጥ የማያሰራቸው በማድረግ ከጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ አደረጓቸው ፤ በዚህ ማህበራትን የማክሰም ስራ በርካቶች የተመሰረቱበትን ፍቃድ በግልጽ ፍቃዳቸውን መለሱ ፤ በዚህ ጥናት ወቅት ‹‹ማህበረ ቅዱሳን›› ለመሸነፋችን አንዱ ምክንያት ነው የሚል የውስጥ አቋም ያዙ ፤ ይህን የምነግራችሁ ሂደቱን ስለማውቅ ነው ፤ በምን መስፈርት ሚዛን ላይ ‹‹ማህበረ ቅዱሳንን›› አስቀምጠውት ይህን ሊሉ እንደቻሉ አላውቅም ፤ የህልውና ጉዳይ ስለሆነም የፈለጉትን ቢሉ ተሳስታችኋል ማለት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ነበርን ፤ ማህበሩ የተቋቋመበት መንገድ ለማፍረስ ቢፈልጉ ቀላል እንደማይሆን ሌላ ጥያቄ እንደሚያስነሳ ስለተገነዘቡ በውስጥ እና በውጭ አካሄዱን መከታተል ተያያዙት ፤ አንድ ነገር ርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው ማህበሩ የሚያወጣቸው መጽሄቶች ፤ ጋዜጦች ፤ ሲዲዎች እና የድረ-ገጽ ጽሁፎች ከመንግስት ሰዎች አምልጦ አያውቅም(ተጠንቅቆ መስራ ግድ ነው) ፤ የፈለጉበት ቢሮ ቢገቡ ህትመቶቹን አያጧቸውም ፤ የሚጽፉቸው መንፈሳዊ ጽሁፎች ሁላ የሚታዩበት መነጽር ለየት ያለ ነው ፡፡
ይህ አንቀጽ ዝም ብሎ የተጻፈ አይደለም። ፓለቲካዊ አቋም ነው። “ሌሎች ሲያደርጉ ተመልክቶ ፤ እኔም ለምን ይቅርብኝ በማለት…ሁላችን እንደምናውቀው ውጤቱ መንግስት እንዳልጠበቀው ስለሆነ የምርጫውን አቅጣጫ የሚያስቀይር ስራ ተሰርቶ ፤ ኮሮጆ ተገልብጦ…ሁሉም ነገር እንዳልሆነ ሆነ።” የሚል ገለጻ አቋም እንጂ ሌላ ሊባል አይቻልም። እንዲህ ያለው ገለጻ የኔ ስራ ሀይማኖት ነው ከሚል ተቋም የሚጠበቅ ሳይሆን በነገሩ ላይ ያለኝ አቋም ይሄ ነው ከሚል ፖለቲካዊ ድርጅት የሚጠበቅ ነው። “ለምን ይቅርብን በማለት… ኮሮጆ ገልብጦ…” የሚሉት ቃላት ግልጽ የሆኑ ፓለቲካዊ አቋም ናቸው። በወቅቱ የሆነውን ነገር ሁሉም ያውቀዋል። እንዲህ ያለው ነገር በሀገራችን እንዳይደገም የሁላችንም ፍላጎትና ጸሎት ነው። በወቅቱ በነበረው ሁኔታ ከመንግስትም ይሁን ከተቃዋሚ እኔ ላይ ምንም ጥፋት የለብኝም የሚል ወገን ቢኖር እንደ መንፈሳዊ ሰው ነገሮችን ዞር ብሎ እንዲመለከት እንመክራለን። ከዚያ አልፈን ግን የፖለቲካው አካል ሆነን እንዲህና እንዲያ ብለን ፖለቲካዊ አቋም በመንፈሳዊ አገልግሎት ስም አንገልጽም። መንፈሳዊ ሰው ነገሩን ከሰዎች ይልቅ ወደ አምላኩ ወስዶ የዚህ ነገር ምስጢር ምንድር ነው? ብሎ ከአምላኩ ጋር ይነጋገራል እንጂ “ይህማ …  እንዲህ ነው” ብሎ ጥሪውና ስራው ባልሆነ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ አይዘባርቅም። ስለ እርቅ፣ ሰላምና ፍቅር ማበርከት ያለበት ድርሻ ካለ ያን ለመወጣት የበኩሉን መወጣት ግዴታው ነው። 

ችግሩ በቤተክርስቲያንም በዓለምም በተገኘው መንገድ ስልጣንን ለመቆጣጠር ስለምትፈልጉ ትንሽ ስትነኩ የታመቀው ፖለቲካዊ ማንነታችሁ ይገነፍልና ፈሶ የምሥጢር ቋታችሁን ያቆሽሽባችኋል። ብዙ ጊዜ ባታወሯቸው ምንም በማይቀርባችሁ ከተነሳችሁበት ፍሬ ነገር (ካላችሁ ማለት ነው) ጋር የማይስማማን ሀሳብ እያነሳችሁ ድብቁን ፖለቲካዊ ማንነታችሁን ሳታስቡት ትገልጻላችሁ።

መንግስት በ14 ዓመት ውስጥ በሀገሪቱ ላይ ሊሰራ ያልቻለውን ስራ ማህበሩ በጥቂት ጊዜያት መስራት ችሎ መታየቱ ለእነርሱ ጥሩ አጋጣሚ አልነበረም ፤መንግስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች(ቅንጅት ነፍስ ይማር) ‹‹ማህበረ ቅዱሳን›› የዘረጋውን ኔትወርክ ለአላማቸው ማስፈጸሚያ ተጠቅመውበታል የሚል አቋም ነበረው ፤ ይህ ግን የፖለቲከኞቹ  የተሳሳተ ግምት እንጂ እውነታው የመንግስት አቅም ማነስና ህዝብን ያለማድመጥ መሰረታዊ ችግር ነበር  ፤ በጊዜው በየመድረኩ ያጨበጨበ ሁላ ደጋፊ መስሏው ነበር ፤ 

“ድሀ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ ኖሮ…” አለ ያገሬ ሰው። ጭራሽ ከመንግስት የተሻለ ስራ ሰርተናል ብላችሁ ታምናላችሁ? ለራሳችሁ የምትሰጡትን ግምት መርምሩት። ደግሞ ሲወራ የሚያሳፍርና የማያሳፍርን ነገር የሚያስገምትንና የማያስገምትን ነገር ለይታችሁ እወቁ። ዝም ብሎ ባልተሳካ አማርኛ ሆድ ውስጥ ያለው ሁሉ አይዘረገፍም።
ሰውየው ህጻን ልጅ አለው። ከቤት ከመውጣቱ በፊት ልጁ “አባዬ አውሮፕላን ግዛልኝ” ይለዋል። አባትዬውም የአውሮፕላን ስሙ ገና አስደንግጦት “አይ ልጄ አሁን አውሮፕላን ለመግዛት የሚችል ገንዘብ የለንም፡፡ ወደፊት ሀብታም ስንሆን እገዛልሀለሁ” አለው። ልጁም እርሱ በፈለገው አውሮፕላንና በሀብት መካካል ያለው ርቀት ታይቶት ነው መሰል አዝኖ ተቀመጠ። ረፈድ ሲል አባትየው አየር ለመቀበል ወደ ከተማ ሲወጣ መንገዱ ሁሉ በሚሸጥ አውሮፕላን ተሞልቶ ያያል። እንዴ ይሄ ነገር እንዴት እንደዚህ በዛ ብሎ በመገረም ወደ አንዱ ሻጭ ጠጋ ብሎ ዋጋውን ቢጠይቅ፣ ዋጋው ከጠበቀው በታች ርካሽ ሆኖ ያገኘዋል። ከዚያም “አይ ልጄን በማይረባ ነገር አሳዘንኩት” ብሎ አውሮፕላኑን ገዝቶ ወዲያወኑ ወደ ቤቱ ይመለሳል። ልክ በር ከፍቶ ሲገባ ህፃን ልጁ አውሮፕላኑን ሲያይ “አባዬ አባዬ ሀብታም ሆንን አይደል” እያለ በደስታ መዝለል ጀመረ። 
የአንድ አድርገን ህፃናተ አእምሮ ጸሀፊዎች ከዚህ ልጅ የተሻለ አስተሳሰብ የላቸውም። ማህበሩ እንደኢሰፓ ተደራጅቶ ሰዎችን በማሰቃየት “እምንልህን ካልሆንክ ተሃድሶ ነህ እንልሀለን” እያለ በማስፈራራት በየአመቱ ከቤተክርስቲያን የሚያባርራቸውን ሰዎች ብዛት እየቆጠሩና “በገልባጭ መኪና ተቀብሎ በሻይ ማንኪያ የሚሠጠውን ስጦታ” እያዩ አቤት ማህበሩ የሰራው ስራ!! ይህ ስራ እንኳን በማህበር በመንግስትስ ሊሰራ ይችላል? አይችልም እያሉ በጓዳ ከመመፃደቅ አልፈው እንዲህ ሲያድጥ አደባባይ ላይ ማስጣት ጀምረዋል። አቅማችሁን አለማወቃችሁና ለራሳችሁ የምትሰጡት ግምት ምን ያህል እንደሆነ ይሄ ገለፃችሁ ያሳያል። ዳንኤል ክብረት ከማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሀፊ ከሙሉጌታ ጋር የተጣለ ጊዜ መናገር ጥሩ ነው አሁንም ይናገር በሆድ ያለ ምን እንደሆነ ይታወቃልና ብሎ ነበር። እኛም “ተናዳችሁም አዝናችሁም ተደስታችሁም ተቆጥታችሁም ብቻ ተናገሩ ምን እያሰባችሁ እንዳለ እናውቃለን” እንላችኋለን።
ለማንኛውም በምርጫ 97 ጊዜ ማህበረ ቅዱሳን የነበረውን ሚና ለማወቅ ቀረብ ብሎ የወቅቱ የሐመር መጽሄት አዘጋጆች የነበሩትን “ጋዜጠኞቹን” መርሻንና አሉላን መጠየቅ ነው። መቸም ጋዜጠኝነት የማያስገባው ቦታ የለ አይደል? ለመሆኑ መርሻ ከሀገር የመጣው ለምን ይሆን? ኧረ ተዉ እናንተ ልጆች እየቆሰቆሳችሁ ሁሉን አታስወሩን?
የአቦይ ስብሀት አነጋገር ሲገርመን ፤ ባለፈው ሳምንት ደግሞ አቶ መለስ ኦርቶዶክሳዊ  አክራሪ የሚል ትርጉም ያለው ነገር መናገራቸው በጣም አስገርሞናልም ፤ እና ንግግራቸውን ተቃውመን ሰዎች ሰምተው እንዲቃወሙ በር ከፍተናል ፤ ስለዚህ መንግስት ለማህሩ ጥሩ ነገር የለውም ፤ ቢኖረውም ባይኖረውም እና ምንም መስሎ አይታንም ፤ ቤተክርስትያን ላይ የሚደረገውን ጥሩ ያልሆነ የማይጠቅምና የፖለቲካ ትርፍን መሰረት ያደረገን ነገር  ከመቃወም ግን ወደ ኋላ አንልም፡፡
አይ ሞኞ ምንም ባይመስልህማ መሽቶ እስኪነጋ በአንድ ዜማ ያውም በአበባዬ አትዘፍንም ነበር። ሰሞኑን ያውም በበዓለ ሃምሳው የያዛችሁት ጾምና ጸሎት (እዚህ ጋ አንባቢ የቤተክርስቲያን ስርዓት መፍረሱን ልብ ይበል) ምንም ስላልመሰላችሁ ይሆን? አንተም ልብህ እስኪተረተር ድረስ ደጋግመህ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በመቃወም የጻፍከው ምንም ስላልመሰለህ ነው? መልሱን ለራስህ እንደ በሰለ ሰው ለማውራት (ለማውራት ያልኩት የአጻጻፍ ስልትህ ከጹሁፍ ይልቅ ወሬ ስለሚመስል ነው) ሞክር።
በአጠቃላይ አንድ አድርገን በጭፍን የማህበሩ ፍቅር የተያዙ “ጸሀፊዎች” ማህበሩ አይሳሳትም የሚል እምነት ባላቸው “ተራ ካድሬዎች” ስሜትና እውነት በተቀላቀለባቸው፣ ፍቅርና እምነት በተምታታባቸው፣ ያወቋትን ትንሽ እውቀት እንደ ዋሻ አበጅተው እስዋ ውስጥ በሚደበቁ፣ በምንጽፈው ነገር እንመዘን ይሆን? ብለው በማያስቡ ህጻናተ አእምሮ የሆኑ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የምትዘጋጅ ብሎግ ናት። ማኅበሩን እንጠቅማለን ብለው በርካታ ምሥጢሮችንና ድብቅ አጀንዳዎችን ሳይገባቸውና ሳይገባቸው በደም ፍላት በቁጭትና በስሜት የሚንቀሳቀሱ ልጆች ምን ያህል አደጋ እንደሚሆኑ ያልተገነዘቡት የማቅ አባላት አካሄድ
እግዚአብሔር ሲጣላ አይመታም በበትር
እያደናገረ ይነሳሀል ምክር
የሚባለውን አባባል ያስታውሰናል።

2 comments:

  1. እወነትም የምሕረት አደባባይ ስለ ማቅ ብዙ ግንዛቤ አገኘን ተባረኩ።

    ReplyDelete
  2. yewushet diskur meche neewu ergmanachun yemtabekut enante endehon kegna wegen silalonachu aymeleketachum it is not your concern

    ReplyDelete