Thursday, May 31, 2012

የጠላት ከፍታ


Click here to read in PDF            ከቤተ ጳውሎስ ብሎግ የተወሰደ
ጴጥሮስና ዮሐንስ በተሰጣቸው ጸጋ በተአምራት ወደ ላይ ሲወጡ ያየው ሲሞን መሠርይ እኔም እንደ እነርሱ ማድረግ እችላለሁ ብሎ በምትሐት ወደ ላይ ከፍ ሲል ጴጥሮስና ዮሐንስ ከታች ወደ ላይ ሲመጣ አዩት፡፡ ጴጥሮስም ችኩል ነውና እናማትብበት አለ፡፡ ዮሐንስ ግን “ከፍ ከፍ ይበል ለአወዳደቁ እንዲመች” አለው በማለት አንድ መምህር በልጅነቴ አጣፍጠው የነገሩኝን አልረሳውም፡፡

ሙሴ የሠራውን ተአምራት የሚመስል የፈርዖን ጠንቋዮች ሠርተዋል /ዘጸ. 7፡8-13/፡፡ የሙሴ ተአምራት ግን አሸንፏል፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ሥራ ፊት የሰይጣን ሥራ ስለማይቆም ነው፡፡ የበኣል ነቢያት በኣል ሆይ ስማን እያሉ ሲጣሩ ውለዋል፡፡ ለወትሮ የሚሰማቸው መንፈስ ዛሬ ግን ቀርቦ ምንም ሊያደርግ ያልቻለው የእግዚአብሔር ሰው ኤልያስ በዚያ ስለነበረ ነው /1ነገሥ. 18፡25-29/፡፡ መንፈሳዊውን ዓለም እየታከከ የሚኖር ጥገኛ መንፈስ አለ፡፡ ሰይጣን ራሱን ችሎ መቆም አይችልም፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔር ተግባር ትይዩ አስመሳይ ተአምራቶች በማድረግ አምልኮን መጋራት ይፈልጋል፡፡ ሰይጣን ካዱ ከሚል የነገሥታት አዋጅ ይልቅ እምነት በሚመስል ምዋርት ብዙ ውጤት እንደሚያገኝ ያውቀዋል፡፡

ብዙ ጊዜ የተቃዋሚዎቻችን ከፍታ ይረብሸናል፡፡ የጠላት ከፍታ ለመውደቅ መሆኑን ግን የሚያውቁ በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ በሥራችን ስኬታማ ካለመሆናችን ይልቅ የሚረብሸን የጠላቶቻችን ጊዜያዊ ድል ነው፡፡ ውጤታማ ነን ብለን የምንለካው በራእያችን መሳካት አይደለም፡፡ የጠላትን ሬሣ ካላየን ውጤታማ ነኝ ለማለት አንደፍርም፡፡ ጌታ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል ልኮናል እንጂ በተኩላዎች ሬሣ መካከል አልላከንም /ማቴ.10፡16/። ጠላትም አለ እኛም እንኖራለን። እግዚአብሔር ለእባቡ አሳብ እንጂ እግር አልሰጠውም። ጴጥሮስ የሆነው ማንነታችን ግን ቶሎ እርምጃ ለመውሰድ ይፈልጋል፡፡ በራሳቸው ሊጠፉ የነበሩ የጠላት ሰፈሮች በመነካካታቸው እንደገና ተቆስቁሰው እናያለን፡፡ ያለጊዜው የሆነ እርምጃ ለጠላት ህልውናን የሚጨምር ነው፡፡ ዮሐንስ የሆነው ማንነት ግን በትዕግሥት ሆኖ ከፍታው ለውድቀት መመቻቸት መሆኑን ያውቀዋል፡፡ ምክንያቱም ያለ እግዚአብሔር ከፍ ያሉ ይዋረዳሉና። ቃሉ፡- “ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ፤ … ለንጉሡም ኃይል ይሰጣል፤ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል” ይላል (1ሳሙ. 2÷10)፡፡

የእስራኤል ልጆች የግብፅን ድንበር ለቀው ሊወጡ ጥቂት ሲቀራቸው የኤርትራ ባሕር ከፊት ለፊታቸው ተጋረጠባቸው፡፡ ከኋላ የፈርዖን ሠራዊት ከቀድሞ ይልቅ ባሪያ ሊያደርጋቸው እየገሰገሰ ይመጣል፡፡ እስራኤልም ለለመዱት መንግሥት መገዛት ሳይሻል አይቀርም፣ ከመሞት መሰንበት መልካም ነበር፣ ሙሴ ጉድ ሠራን ብለው ተጨነቁ፡፡ በዚህ ጊዜ ሙሴ፡- “አትፍሩ÷ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ÷ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል÷ እናንተም ዝም ትላላችሁ” /ዘጸ. 14፡13-14/።
ግብፃውያን ዛሬ የጦር ሠራዊት ሆነው ይታያሉ፤ እስራኤል ደግሞ ኮተት የተሸከሙ ስደተኞች ሆነው ይታያሉ፡፡ ግብፃውያን ዛሬ አሳዳጆች ሆነው ይታያሉ፤ እስራኤል ግን ንጉሥ አልባ መስለው ይታያሉ፡፡ ግብፃውያን ዛሬ አባራሪና መላሽ እንደገናም ከሳሽ መስለው ይታያሉ፤ እስራኤል ደግሞ መድረሻ ያጡ “ከእሾህ ቢሸሹ ጋሬጣ፣ ከእከክ ቢሸሹ ፈንጣጣ” የተባለው የደረሰባቸው ይመስላሉ፡፡ ግብፃውያን ዛሬ በብዙ የጦር ኃይል በደረጀ ሠራዊት ይታያሉ፤ እስራኤል ደግሞ በሴቶችና በሕፃናት እንባ ይንገላታሉ፡፡ ግብፃውያን ዛሬ ማራኪ፣ ካልሆነም ባሕር ጨማሪ ሆነው ይታያሉ፤ እስራኤላውያን ከፊት የቀይ ባሕር ከኋላ ሠራዊት ያጋጠማቸው ይመስላሉ፡፡ ይህ ዕይታ ግን የዛሬ ዕይታ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከሰዓታት በኋላ ይገለብጠዋል፡፡
ነገርን በመገልበጥ የታወቀው ጌታ የሚታየውን ሳይሆን የሚታመነውን አደረገ፡፡ ሠራዊት ያላቸው ሰጠሙ፣ እግረኞችና ስደተኞች ባሕሩን ረገጡ፡፡ ግብፅ በዙፋኗ የሚቀመጥ ንጉሥ፣ የሚጠብቃት ሠራዊት እስክታጣ ባዶ ሆነች፡፡ ይሞታሉ የተባሉ ተሻገሩ፣ ይገድላሉ የተባሉት መቃብራቸውም ታጣ፡፡
“እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተም ዝም ትላላችሁ” (ዘፀ. 14÷14)፡፡ እግዚአብሔር እንዲዋጋ መንገድ መልቀቅ፣ እርሱ እንዲናገር እኛ ዝም ማለት ያስፈልገናል፡፡ እኛ ስንዋጋ ደም እንቃባለን፣ እግዚአብሔር ሲዋጋ ቂም በቀል የለም፡፡ ዛሬም ሕዝቡን የማያስደፍረው ጌታ እንዲህ ይሠራል፡፡ የጠላት ልዕልናው፣ አደረጃጀቱ፣ የአሰላለፍ ብቃቱ፣ የደኅንነት መዋቅሩ፣ የጦር ዕዝ ችሎታው፣ የሠረገላው መትመም፣ የጥንካሬው ጉልበት፣ ኃይሌ ይህ ነው የሚልበት ሰልፍ፣ በአደባባይ የሚፎክርበት የጥይት አረሩ፣ ይዋጉልኛል የሚላቸው የተመረጡ ጎበዞች …. ለዘላለም አይታዩም፡፡ ሞት የታወጀባቸው ግን ይኖራሉ፡፡ ሕይወት በእግዚአብሔር እጅ ነው። የመኖር ፈቃድም ከላይ ነው።
የመርዶክዮስ ወንጀሉ ለሐማ አለመስገዱ ነበር፡፡ ለዚያ መንግሥት የዋለው ውለታ ሁሉ ተረስቶ የሚሰቀልበት እንጨት ተጠርቦ ነበር፡፡ መላው አይሁድ እንዲደመሰስ የሞት አዋጅ ወጥቶ አይሁዳውያን በያሉበት አንብተው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን ከፍ ከፍ ያለውን ሐማን አዋረደው፡፡ ለመርዶክዮስ በጠረበው እንጨት እንዲሰቀል አደረገው፡፡ የንጉሡንም የሞት አዋጅ በሕይወት አዋጅ የሚቀይሩ ፈጣን ፈረሶች ቀደሙ፡፡ አይሁዳውያን በሚሞቱባት ቀን ገዳዮቻቸውን ተበቀሉ፡፡ ዛሬ እንደ አስቴር የቤተ መንግሥት ድርጎኛ የሆኑ አይሁዳዊነታቸውን እንደ አስቴር የሸሸጉ በጸሎት ሆነው ሊገለጡ፣ ለምን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሞት ይፈረድበታል ሊሉ ይገባል። አሊያ እግዚአብሔር ሕዝቡን ያድናል እነርሱ ይጠፋሉ። መጽሐፈ አስቴር የተጻፈው ለእምነት እንጂ ለትረካ አይደለም፡፡ ቁመናውን አስረዝሞ፣ መስቀሉ ተተክሏል እያለ የሚፈነጥዘው፣ ንጉሡን አሳምኛለሁ፣ የመወሰኛው ምክር ቤት በእጄ ነው እያለ ፊርማ ይዞ የሚዞረው ሐማ ይሞታል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ግን ይድናል፡፡
ዳዊት ይህን በሕይወቱ ተለማምዶ ነበር፡- “ኀጥእን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት፡፡ ብመለስ ግን አጣሁት፤ ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም” ብሏል (መዝ. 36÷35-36)፡፡ የሊባኖስ ዝግባ በቁመቱ የታወቀ ነው፡፡ ቆሞም ሆነ ወድቆ ዓይን ይሞላል፡፡ ዳዊት ግን አጣሁት ነው የሚለው፡፡ ሄዶ መመለስ ቅጽበታዊ ነው፡፡ ያ ከፍ ከፍ ያለው ግን ለማለቅ ቸኰለ፡፡ መታሰቢያውም ተደመሰሰ፡፡ መቃብሩ እንኳ አልተገኘም፡፡ ስለዚህ የጠላት ልምላሜ በዓለም ሁሉ ሞልቻለሁ ከሩቅ እታያለሁ የሚለው ፉከራው ለዘላለም ያከትማል፡፡ ሰይፉም ይደንዛል፣ ሠራዊቱም ይበተናል። የእግዚአብሔር ቁጣ ግን በዐመጸኞች ላይ ለዘላለም ይኖራል።
ፈሪሳውያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ገድለውታል፡፡ የአሸናፊነት ድግስ ደግሰዋል፣ ወይን ተራጭተዋል፡፡ ቀጥሎ ደቀ መዛሙርቱን እናጠራለን ብለዋል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሸነፈ የመሰለው ለሦስት ቀን ነው፡፡ ፊሪሳውያን ለሦስት ቀን ጀግና ተባሉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለዘላለም የይሁዳ አንበሳ ተብሎ ይኖራል፡፡ የጠላት ድል ጊዜያዊ ነው፡፡ ፈሪሳውያን ከመንግሥቱ ተአማኒነት አለን፣ ሠራዊት ይታዘዝልናል፣ ወደ ሮም ብንሄድ ተቀባይነት አለን፣ እኛ ያወገዝነው ውጉዝ፣ እኛ የፈረድንበት ሙት ነው አሉ፡፡ ነገር ግን እነርሱና ምድራቸው ተደመሰሱ፡፡ ከ7ዐ ዓ.ም እስከ 1948 ዓ.ም ፈረሱ፡፡
 ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ የበለጠ ሥልጣን ተቀብሎ ወደ ደማስቆ ሲሄድ በመብረቅ ብርሃን ወደቀ፡፡ ለጠላው ኢየሱስ ተማረከ፡፡ ዛሬም ብዙ አሳዳጆች የበለጠ እንዲሠሩ ሥልጣን ሲጨመርላቸው እናያለን፡፡ ማሳደድ ብቻ ሳይሆን ማሰርም በእጃችሁ ነው ተብለው ሠራዊተ ክርስቶስን ለማጥፋት በሥልጣን ይወጣሉ። የእውነተኞች ነፍስ በእጃችሁ ነው የከሰሳችሁት ይግባኝ የለውም ተብለው ሲቀቡ እናያለን። “የወረት ውሻ ስሟ ወለተ ጴጥሮስ ነው” እንዲሉ፡፡ ወረቱ ሲያልቅ ወለተ ጴጥሮስ ወለተ ሰይጣን ትሆናለች። ለዘመናት የማይስማሙት ጲላጦስና ሄሮድስ በኢየሱስ ሞት ተስማሙ። የዓርብ ፍቅር ከትንሣኤው በኋላ ያልቃል። የዓርብ እድርተኞች፣ መስቀል አሸካሚዎች የንስሐ ጊዜአቸው ዛሬ ነው። የኔሮን አቅም ያላቆመውን ወንጌል የጎበዝ አለቆች አያቆሙትም።
ጳውሎስ ወደ ወንጌል ከመጣ በኋላ ብዙ ተንገላታ፡፡ ዛሬ ጳውሎስን ያሳደዱትን አናውቃቸውም፣ ጳውሎስን ግን  እናውቀዋለን፡፡ አሳዳጆች፣ ገራፊዎች ለዘላለም አይታወቁም፡፡ የተሰደዱትን ግን እንደታወሱ ይኖራሉ፡፡ ድል ያለው መግፋት በመቻል ሳይሆን የድሉን ጌታ በመያዝ ነው፡፡ እኒያ መምህር ያሉትን አስታውሰን እንዝጋ፡- “ከፍ ከፍ ይበል፣ ላወዳደቁ እንዲመች!

4 comments:

  1. correct!!! so if you know this wongel, don't accuse mk. you see mk did not accuse any body except publicizing the 'tequlas' who highly want to convert the church in to protestant-devil based religion. now, start to read bible so that you will start to refrain from baseless attacking mk ( which is against the bible.)

    ReplyDelete
    Replies
    1. i agree on its correctness. but if you read it correctly u truly understand what is says. and no one is attacking mk with out a base. come to awasa or harer we will show you plenty of evidence about mks devilish work.

      Delete
  2. this is good. every body has to read it.

    ReplyDelete
  3. Grium Megelet new "Bete Pawlos" ahunem tsegawin yabzalih?

    Yebetechristian Amelak simu Kef Kef yebel!

    Amen!

    ReplyDelete